Saturday, 25 February 2023 12:17

ነገረ መለኮት ከሌላ ማዕዘን...

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(1 Vote)

     [‹The I of man is The God of the scripture›]

        “ማመን ግን ሕልው የመሆኔ ማረጋገጫ ነው፤ ከመላው ሥነ-ተፈጥሮ ጋር የምገናኝበት የምዋዋልበት ቃልኪዳን.... ከሁለንታ ጋር የምተማመንበት፣ ሰው የመሆን መለኮትን የማምሰል ጸጋ (virtue)፣ በጎነት...”
         

         እኔ እንደ በርትራንድ ረስል ‹‹ሐይማኖት የፍርሃት ውጤት ነው›› አልልም፡፡ ይልቁንስ ምንነቱን እና ከየትነቱን የማያውቁት በቅጡ ያልተደመጠ፣ ምላሽ ያልተሰጠው የልጅነት ናፍቆት ወደ ማመን እንደሚመራን አስባለሁ። በእርግጥ የሕይወት፣ የአምልኮ ነገር ሲጀመር አደራረጉ እንደ ጅልነት እንደ ሞኝነት መሆን አለበት፡፡ አጀማመሩ ልክ ከፏፏቴ እንደ ማውጋት፣ ለጨቅላ እንደ ማንጎራጎር፤ ምናልባት ለነፋስ እንደ ማፏጨት ስሜት የማይሰጥ ከሚመስል መዳዳት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ነገር ግን መሰረታዊው ሰው የመሆን ቅጥም የተሰራው በዚህ የገርነት ቅኝት መሆን አለበት። ሰው የፍጥረት የበላይ (superior) የመሆኑን ቀቢጽ የሚሰብኩት ከራሱ መካከል ተከስተው ሙሉ በሙሉ ከተፈጥሮ ቅኝት እስኪነጥሉት ድረስ የንጽህና ልጅ ነበር፡፡
ለምሳሌ የላቲን አሜሪካ ቅዱስ ሕዝቦች ኮጊዎች (Kogi) የክርስቶስን አዳኝነት፣ የነብዩ መሐመድን መልዕተኝነትን ለመስማት ለአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመታት የቅኝ ገዥዎችን መምጣት መጠበቅ ነበረባቸው። ነገር ግን ሰው መሆን አልጠፋባቸውም፡፡ እንኳን ለመሰላቸው ለመላው ግዑዝ ለሆነው ስነፍጥረት ሁሉ ይራራሉ፡፡ ለሺህ ዘመናት አማኞች ነበሩ፡፡ ለዚያውም የተፈጥሮን ሥሪት የተከሉ... ዛሬም ድረስ የጥንታዊ አያቶቻቸውን የአምልኮና አስተሳሰብ ዘይቤዎችን እያስቀጠሉ፣ ዘመናዊውን የሰው ልጅ ሽሽት በኮሎምቢያ አይደፈሬ የተራራ ሰንሰለቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ለተፈጥሮ ካላቸው ጥንቁቅነት የተነሳ መንገድ ስንኳ ለመስራት አንዲትም ድንጋይ ከቦታዋ አያፈናቅሉም፤ አንዲትም ሀረግ አይነቅሉም፡፡ ሁሉንም ነገር የሚከውኑት የተፈጥሮን የልብ ምት በተከተለ መልኩ ነው። ሰሚ ባያገኙም ቅሉ ‹ስህተተኛው ታናሽ ወንድማችን› ለሚሉት ዘመናዊው የሰው ልጅ፣ ተፈጥሮን ስለመጠበቅ አስፈላጊነት በተከታታይ መልዕክቶችን ይልካሉ፡፡
የንጽህና ልጅ በነበረ ጊዜ ሰው ጨካኝ በሚመስለው ነገር ግን ፍትህና ርትዕ ሚዛኑ በሆነው ስሙር የተፈጥሮ ሰሌዳ ላይ ጊዜያዊያነቱን፣ አላፊ ጠፊነቱን በጸጥታ የተቀበለ ስኩን ፍጥረት ነበር... ተፈጥሮን ለመግዛት ለመግራት በበላይነት ስሜት ከመቅረቡ በፊት የሰው ልጅ እንደ ትል፣ እንደ እንጉዳይ፣ እንደ አመዳይ፣ እንደ አበባ፣ እንደ ማንም፣ እንደ ሁሉም ነበር፡፡  ተፈጥሮን ለመግዛት ለመግራት በበላይነት ስሜት ከመቋመጥ ይልቅ ተፈጥሮን መልበስ፣ መዋረስ ሰው የመሆን ደመነፍስን ያሰለጥናል፡፡ ሲጀመር የሰው ልጅ  የመሆነን ነገረ ውል ለመካን ሙዝን ልጦ የመብላት ጥበብ ማወቅ ብቻ ይበቃዋል፡፡ ሲፈጠርም ጀምሮ ስሪቱ የተፈጥሮ ነው፡፡ ለአደን፣ ለለቀማ፣ ለአባሮሽ፣ ለድብብቆሽ፣ እስከ እልፍ ከተዘረጋው ሰፊ የዓለም ሰሌዳ ላይ እንደ ዶሮ ለዕለት የምትበቃውን ‹ጥሬ› ብቻ እንዲለቅም የተተወ... በእርግጥም ያኔ የሰው ልጅ ደመነፍስ እንደ መላዕክት፣ እንደ መለኮቱ ጉልህ ‹እኔነቱ› በስግብግብ ምሪት ያልደበዘዘ ገር (simplistic) ነበር፡፡
በዘመን ሂደት ቀስ በቀስ የሰው ልጅ ሰው መሆንን ረስቶ አውሬነትን ተለማመደ፡፡ ሰው የመሆን ውሉ ሲደናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ሰሎሞንስ ስንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ እንደነሱ አልለበሰም›› የተባለላቸው የሜዳ አበቦች ግን አበባ መሆን እንግዳ አልሆነባቸውም። አበባ ለመሆን ብዙ ምርምር፣ ላቦራቶሪ አላስፈለጋቸውም፡፡ የጽጌ ጌጥነታቸውን ለመቀዳጀት የንጽህና ልጆች መሆን ብቻ ይበቃቸዋል፡፡
የሰውን ልጅ ግን እናውቅልሃለን በሚሉ በራሱ በሰው ልጆች የመላው ፍጥረት የበላይ መሆኑን እየተጋተ ልጅነቱን ካደ፡፡ ‹በሚያምነው› ፊት ምንምን፣ ጊዜንም ቢሆን የማይፈራ የነበረውን ፍጥረት በሂደት ድንጉጥ አደረጉት። ድንጋጤው ጭካኔን ወለደ፡፡ ለራሱ ለመላው ስነፍጥረት ሁሉ ጭካኔን የሚነዛ አረመኔ ሆነ፡፡ ከጊዜና ከቦታ ጽንፍ፣ ከራስ መዳዳት በላይ አልፎ ማሰብ የማይችል ድኩማን... ጊዜ ግን ሊታሰር፣ ከማንም ፊት ላይ የልጅነት ወዝን ከእንባ ጋራ እንዳያጥብ ሊከላከሉት የማይቻል ቢመስልም፣ ሁሉንም የሚያገረጣ፣ የሚያረግፍ፣ የሚያነጣው አድራጊ ፈጣሪው ይህ ጊዜ ስንኳ ውስን ሆነው ካልቀረቡት አቅመቢስ መሆኑ እሙን ነው፡፡ መለኮታዊነትን የሚሹ ሁሉ ይሄንን የጊዜ የቦታ እና የፍጥረት ውስንነት መሻገር ይኖርባቸዋል። ምናልባት ከንግግር፣ ከእውነትና ውሸት፣ ከብርሃንና ጥላ፣ ከጊዜ፣ ከጽድቅና ኩነኔ... ጭምር... ለምሳሌ እኔ ከሚያልፈው ከሆነው ከሚሆነው ሁሉ ነገር የምቀድም እና የምዘልቅ (enduring) ነኝ፡፡
መለኮቱ ግን እንደ ጻድቅ መነኩሴ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ አርበኛ፣ እንደ ነፍሰ ገዳይ፣ እንደ ቀማኛ፣ እንደ ጦረኛም እንደ ሁሉም እንጂ... ይህ አባባል ‹እግዚያብሔር ፍቅር ብቻ እንደሆነ› እየተነገረው ላደገ አዕምሮ ሊረዱት የሚያስቸግር ምናልባት ንፍቅ (heresy) የሚፈጥር ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን በቅዱሱ መጽሐፍ ሳይቀር በርካታ የሚባሉ አንቀፆች ላይ መለኮቱ የሰውን ልጅ አንዳንዴም መላውን ሥነ-ፍጥረት በሙሉ ለማውደም ሲዝት እናነባለን። በቅዱሱ የምኅረት ቃል መካከል ‹እንደ ሌባ በአሳቻ ሰዓት እመጣብሃለሁ› የሚል ቃል ተሰንቅሯል። ፍቅሩም እኛ የምንረዳው የእጮኛ፣ የወላጅ፣ የጓደኛ አይደለም፡፡ ፍቅሩ ከጭካኔ ጋር የተዋሃደ ነው፡፡ ፍቅሩም ጭካኔውም የመለኮት እንጂ የሰው ልጅ አይደለምና በሰውኛ ዘይቤ ሊረዱት ያስቸግራል፡፡ ዘወትር መዓቱን የሚዘረጋው ከምኅረቱ ጋር ነውና ይህ ሁሉ መልካምነቱን ከቶውንም አይሸራርፈውም፡፡ ቁምነገሩ መለኮቱ የቁጣ ገጹን በሚያሳየን ጊዜ እንዴት ራሳችንን አቅበን እንተርፋለን የሚለው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ጋር የምትያያዝ አንዲት የምስራቅ ታሪክ አንብቤያለሁ፡፡
ነገሩ የሆነው በአስራሦስተኛው መቶ ክፍለ-ዘመን በያኔዋ ኢራን ነው፡፡ በእስልምና ‹ሚስቲካል› አስተምህሮ ልቡ የማለለው ተማሪ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲዘዋወር ድንገት እባብ ተመለከተ፡፡ ምንም ሳያመነታ ተንደርድሮ ጨበጠው፡፡ ወዲያውኑ በእባቡ ተነድፎ እጁ ያለቅጥ አብጦ ውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ ሆነ፡፡ ተማሪዎቹ በሙሉ ከበቡት። የሚያስተምሩትም ሼይክ ተጠርተው መጡ፡፡ መምህሩ ሁሉንም ተማሪ ካባረሩ በኋላ ጠየቁ...
‹‹ልጄ ሆይ፤ ይህንን ስለምን አደረክ?››
‹‹መምህር ሆይ፤ እርስዎ አይደሉምን በሆነው ሁሉ ነገር ውስጥ ከመለኮቱ ውጭ አንዳችም ነገር የለም፡፡ ሁሉ ነገር መለኮቱ ነው ብለው ያስተማሩኝ፡፡ እና እባቡን በምመለከትበት ጊዜ በአእምሮዬ ውስጥ የነበረው መለኮቱ ብቻ ነበር። ስይዘውም መለኮቱን እያሰብኩ ነበር፡፡››
‹‹ነገር ግን ...›› አሉ መምህሩ
‹‹ነገር ግን መለኮቱ እንዲህ በሚያስፈራ መልኩ ራሱን በሚገልጥበት ጊዜ መደበቂያ መፈለግ ነው ያለብህ እኮ... ለወደፊቱም ይሄንኑ ካላደረክ የሚገጥምህ ተመሳሳዩ መሆኑን እወቅ...››      
እርግጥ ነው መለኮቱ በነዲድ በነበልባሉ፣ በመካት በመገርጣ፣ በእባብ በሁሉም ነገር ውስጥ አለ፡፡ ከአልቦው ጥልቅ በነፍስ መነካት እስኪነካን እኛ ሁላችንም የራሳችን ሕልውና አልነበረንም። ነገር ግን ይሄን ሕልውና በመረዳት፣ በመገለጥ እንጂ እንዲያው በጀብደኝነት ብትጠጋው ለራስህ ይብስብሃል፡፡ ነፍስ ግን ታውቀዋለች። ዘወትር በስውር ሕብሯንም የምታጠቅሰው ከዚህ አልፋ ቀለም ነው፡፡ ‹ቲክ ናት ሃን› የተሰኘ የቤትናም የኃይማኖት መምህር ሕልውና (the Divine - The oneness - I am that I am) ከዚህም በላይ የተሳሰረ መሆኑን በምሳሌ ሲያስረዳ፤ ‹‹እጃችን ላይ ባለች በቁራጭ ወረቀት ውስጥ ደመናውን በሕልውና ማየት እስኪቻለን ድረስ የምልዓተ ዓለሙ ቀመር አይገባንም፡፡›› ይላል። ምክንያቱም ደመናው ከሌለ ዝናቡ ሊኖር አይችልም፤ ዝናቡ ከሌለ ዛፉስ ከየት ይመጣል? ከየትም! ዛፉ ከሌለ ደግሞ ቁራጯ ወረቀትም ልትገኝ አትችልም፡፡ ይሄም ትስስር ቲክ ናት ሃን ‹inter-being› ይለዋል። እናስ ቁራጯ ወረቀት ደመናውን ብትቃወም ራሷን እንደተቃወመች አይደለምን?
ነገር ግን ጠብታዋ ምልዓት የሚሆንላትን ውቅያኖሱን መዋረስ እንጂ መዋጥ ይቻላታልን? ጠብታዋ አንዴ ወደ ውቅያኖሱ ጥልቅ ከተጠጋች፣ ከውቅያኖሱ ጠብታዎች እንደ ሁሉም ነችና ከየትኛዋም ጠብታ የምትሻል ልትሆን አይቻላትም፡፡ ‹ማንም ከራሱ የሚልቅ መሆን አልተፈቀደለትም፡፡ ማንም ማንንም መቀደስ መባረክ አይችልም፡፡ ለምሳሌ ሰው ውኃን መቀደስ መጸበል ይችላል? አይችልም! ሰው በንቃት መመላለስና ውኃም ሆነ ማንኛውም ነገር  በጥንተ ተፈጥሮው ቅዱስ መሆኑን መቀበል ብቻ ይበቃዋል፡፡› ለጠብታዋ አንዴ ከተዋሃደችው በኋላ ውቅያኖሱ ‹እኔዋ› እንጂ ‹እኛዋ› ሊሆን አይችልም። ደግሞስ ሌሎችን ‹እኛ› ከማለት ይልቅ ‹ሌሎችን› እኔ በማለት ውስጥ የበለጠ ርህራሔ ይታይ የለምን? አንተን ‹እኔ› ከማለት እና ‹አንተ እና እኔ - እኛ› ከማለት በእውኑ የቱ ነው ለነፍስ የቀረበ? የቱስ ነው ልባዊ?
እናም የእኔ ዕጣፋንታ ከዛፉ ከሳር ከቅጠሉ ከወፍ ከትላትሉ የተነጠለ አይደለም፡፡ ቅዱስ ቁርዓን ‹ማንኛዋንም ንጹህ ነፍስ የገደለ መላውን የሰውን ልጅ እንደገደለ፣ ማንኛዋንም ንጹህ ነፍስ ያተረፈ መላውን የሰው ልጅ እንዳተረፈ ይቆጠራል›› ይላል፡፡ በእርግጥም ማንኛውም ሰው የሚገድል፣ የሚጠላ፣ የሚቀማ፣ የሚያሳድድ፣ የሚያሳምጽ ሰው ራሱን እንደገደለ፣ እንዳራቆተ፣ እንደቀማ... ይቆጠራል፡፡ ይህ የኅሊና ህግ ለመላው ሕይወታዊም (sentient being) ይሁን ግዑዝ ሥነ ተፈጥሮ ጋር የምንገናኝበት፣ የምንዳኝበት ወርቃማ መርህ ነው፡፡ ሁላችንም ለሁላችም ኃላፊነት አለብን፡፡ ምክንያቱም ዣን ፖል ሳርትር እንዳለው፤ ‹‹የአንድ ሰው ነጠላ ድርጊት በመላው የሰው ልጅ ፊት የምትመዘን በውጤቱም በትልቁ ሰብዓዊነትን የምታኮስስ ወይም የምታጎላ ናትና፡፡››
በ1930ዎቹ እና 40ዎቹ በያኔዋ የዘር መድሎ የናኘባት አሜሪካ በኒውዮርክ  ኮራ ብሎ የሚራመድ፣ ሳይሳቀቅ ነጮች የሚበዙባቸው ሲኒማዎችን ከፊት ተቀምጦ የሚታደም አብዱላህ (Abdullah)  የተሰኘ ‹መልኩ እንደምጣድ ቂጥ የጠቆረ› የተባለለት ኢትዮጵያዊ ወልይ (mystic) ነበር አሉ፡፡ እንደ ጆሴፍ ሙራይ፣ ኔቪል ጎዳርድ እና ቻርለስ ፊልሞሬ የተሰኙ ታላላቅ ጸሐፍትና ጠቢባን ‹መምህራችን› ሲሉ ረቂቅነቱን ደጋግመው መስክረዋል፡፡ ከእነዚህ የኢትዮጵያዊው ጠቢብ አብዱላህ ደቀመዛሙርት አንዱ ባርባዶሳዊ ወልይ ኔቪል ጎዳርድ (Neville Goddard) በ1972 እ.ኤ.አ ከማለፉ አስቀድሞ ባደረገው የመጨረሻ ንግግሩ፤ ‹The I of man is The God of the scripture›› ብሏል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአንጻሩ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3፣13 ላይ ‹‹ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፡፡›› ይላል፡፡ እንደገናም የዮሐንስ ወንጌል 14፡20 ላይ እንዲህ ይላል። ‹‹እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ፣  እናንተም በእኔ እኔም በእናንተ እንዳለሁ ያን ጊዜ ታውቃላችሁ፡፡››
በዚህ አረዳድ ለሰው ልጅ ሁሉ ወዳጁ ቢሆንም ከራሱ በላይ ግን ጠላት የለበትም፡፡ ለእኔስ ከእኔ ወዲያ ወደረኛዬ ማን ነው? መለኮቱ ሲፈልግ እኔን በእኔ ላይ ያስነሳል፡፡ አንድ እኔ ሁሉንም ነኝ። በማየው፣ በማላየው፣ በሆነው በሚሆነው ሁሉ ውስጥ አለሁ፤ የነበረው ያልነበረው፣ የሚታሰብ የማይታሰበው ሁሉ ይመለከተኛል፡፡ ይህ እኔነት ብዙዎች በግርድፉ እንደሚረዱት ጭፍን ስግብግብ ምሪት(ego) አይደለም፡፡ ይልቁንስ ማንነት (self) ነው፡፡ ይህ ማንነት (እኔነት) የመሰረታዊውን መለኮታዊ የሕልውና ስር በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈ (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕ 1፡27) ሲፈጠር ጀምሮ ሰው የተባለ አዳም መለኮቱን መሰለ፡፡ ቃየንም አባቱን ተከተለ... አዳምም በአንድ ጊዜ አባትም ልጅም መሆን ቻለ፡፡ እኔም ለአባቴ ልጁ ሆንኩ፤ ለልጄ አባቱ ነኝ፡፡ እኔ ማን ነኝ? ልጅም አባትም... አዳም ነኝ፡፡ በአባቴ ልጅነት፣ በልጄ አባትነት የታደልኩ የነበርኩ የምኖር እኔ እኔ ነኝ። ( I am that I am)›  ምናልባት ያ እኔ የማምነው መለኮቱ ራሱ ነው፡፡ ይሄ እኔ ሲገራ ግዕዙ ‹አነ› የሚለው፣ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ‹እኔ እኔ ነኝ፡፡ - I am that I am› የሚለውን ሀቲት የሚስተካከል ነገር ይሆናል...› የእኔ እኔነት ግን ንጹህ ሰው የመሆን መጠራት እንጂ የመሲኃዊነት አይደለም፡፡ የእኔ ኅሊናዊ፣ ምናባዊና ሰብዓዊ እኔነት የመለኮት ቅኝት ነው። በንጹህ መዳዳቴ መለኮቱን የመሆን ሳይሆን የማከል ስንኩል አቅም ተሰጥቶኛልና። ነገር ግን ይሄን በማንም ሰው ውስጥ ያለ ንጹህ ‹እኔነት› እና የመለኮት አንድነት እንደወደረኝነት የሚረዱ ሰዎች ተሳስተው እንዳያሳስቱን እሰጋለሁ፡፡
ነገር ግን ጊዜስ ስንኳ ከዚህ ከዓይነተኛው ‹እኔነት› ውጭ ሲያስቡት ኦናና ትርጉም-የለሽ አይደለምን? ያለ ዓይነተኛው ‹እኔ› ምንም ነገር፣ የሆነን ነገር መሆን አይቻለውም፡፡ ዓይነተኛው እኔ (The divine - The _ I am that I am) የሕይወት ውል ነው፡፡ ይሄ እውነት ግን የሚኖሩት፣ ‹የሚገነዘቡት› (being endlessly aware) እንጂ የሚያመሰጥሩት አይደለም። ‹ማንም የምልዓተ ዓለሙን የምልዓት እርግብግቢት ክንውን በመቅኖቢስ ቃላት ጥርቅም ሊያመሰጥረው አይችልም፡፡ ጥቂቷን ነገር ብቻ መግለጽ ይችል ይሆናል... ‹‹ያለእና የሚኖር እኔ ነኝ›› (I am that I am) ብሎ ማለት ከጥቂቶቹ ጥቂቱ ቢሆን ነው፡፡ ቅዱሳቱ መጻሕፍት ከጥቂቶቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይህ የምልዓት ክንውን ግን የማይታወቅ፣ የማይነገር ነው፤ ውበት ነው፤ እግዜሩ ራሱ ነው፡፡ እኔም የዚህ የምልዓት ክንውን አካል ነኝ፡፡ ለምልዓት ክንውኑ ፍንጣቂ ውበት ነኝ፡፡ መለኮቱን የመሆን ሳይሆን፣ መለኮቱን የመምሰል ስንኩል አቅም (potentiality) የተቸረኝ የእግዜሩ መልክ ነኝ።" (ከባዶ ላይ መዝገን ገጽ 44) ‹‹እግዜርን ማየት ስትሻ ምኩራብና መቅደስ መኳተኑን ተውና መስታውት ፊት ቅረብ፡፡ ያኔ እግዚአብሔርን በዓይንህ በብሌኑ ትመለከተዋለህ፡፡ እሱ በልብህ መሻት የሆንከውን ይሆንልሃል፡፡›› (ገጽ 137)
እግዚአብሔርን እንደ አምባገነን ገዥ የምንረዳው ከሆነ የዚህን ሀሳብ መሰረታዊ ጭብጥ እንዳንስት ስጋት አለኝ፡፡ እግዚአብሔር ማንንም አይመስልም። ምልክት፣ ውክልና መገለጫ የለውም፡፡ በቀላሉ ዝም ነው፡፡ በልማድ፣ በቃላት፣ በቀኖናም በምንም ነገር የማይታሰር... ሁለት ነገሮች ብቻ ሊመስሉት ይችላሉ። አንደኛው ራሱ ዝም ነው፡፡ ሁለተኛው ለጊዜው ይቆየን... ዝሙ ግን ረቂቅ ጸሎት ነው... አርምሞ (meditation) የነፍስን ጩኸቶች ሁሉ አስክኖ ወደ የላቀ መንፈሳዊ መደነቅ የሚጋብዝ ተዓምር ነው፡፡ ያለ ቃላት፣ ያለ ተቃውሞ፣ ያለ ማጉረምረም፣ ያለ ክስ፣ ያለ ቅሬታ... በጽሞና የሚከናወን ረቂቅ ተግባቦት ነው፡፡
ጀርመናዊው ክርስቲናዊ ‹ሚስቲክ› ሜይስተር ኤክሃርት ‹‹Nothing in all creation is so like God as silence.›› ያለው ለዚህ ይሆን? ሆኖም ይሄን ጽሁፍ ጨምሮ በቃላት የሚነገር ማንኛውም ነገር ህጸጽ አያጣውም፡፡ ማመን ግን ሕልው የመሆኔ ማረጋገጫ ነው፤ ከመላው ሥነ-ተፈጥሮ ጋር የምገናኝበት የምዋዋልበት ቃልኪዳን.... ከሁለንታ ጋር የምተማመንበት፣ ሰው የመሆን መለኮትን የማምሰል ጸጋ (virtue)፣ በጎነት...



Read 1531 times