Saturday, 25 February 2023 12:03

ስንዴ በኮንትሮባንድ እየተሸጠ ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(7 votes)

  - የአንድ ኩንታል ስንዴ ዋጋ ሰባት ሺ ብር ደርሷል
        - በስንዴ ዋጋ መናር ሳቢያ ዳቦ ቤቶች ስራቸውን እያቆሙ ነው
        - አርሶ አደሩ አንድ ኩንታል ስንዴ በ3200 ብር ለመንግስት እንዲያስረክብ ይገደዳል
            
        መንግስት የስንዴ ምርትን ወደ ውጪ አገር መላክ መጀመሩን ተከትሎ፣ የስንዴ ዋጋ በከፍተኛ መጠን እየናረ ሲሆን በአዲስ አበባ የአንድ ኩንታል ስንዴ ዋጋ 7ሺ ብር መድረሱ ታውቋል።
የስንዴ ዋጋ ንረቱ የተፈጠረው መንግስት የስንዴ ምርትን ወደ ውጪ አገር መላክ መጀመሩን ይፋ ካደረገ በኋላ ሲሆን፤ ይህም በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ የዳቦ መጋገሪያ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ጫናን መፍጠሩ ተነግሯል። የዋጋ ንረቱ ከአቅማችን በላይ ነው ያሉት የዳቦ መጋገሪያ ድርጅቶች ባለንብረቶች፤ ሥራውን ለማቆም መገደዳቸውን ይገልጻሉ።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አውቶቡስ መናኸሪያ አካባቢ የሚገኘው የነሂማ ዳቦ መጋገሪያ ባለቤት አቶ ከድር ሙክታር እንደሚሉት፤ በስንዴ ምርት አቅርቦት እጦት ሳቢያ የዳቦ መጋገር ስራቸው ለቀናት የተስተጓጎለ ሲሆን ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የዳቦ መጋገሪያ ድርጅታቸውን ለመዝጋት እንደሚገደዱ ተናግረዋል።
“በህገወጥ መንገድ በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች የሚሸጠውን ዱቄት በሰባትና ስምንት ሺ ብር እየገዛን ዳቦ ጋግረን ለመሸጥ ስለማንችል፣ ያለን አማራጭ ስራችንን ማቆም ብቻ ነው” ብለዋል።
እንደ አቶ ከድር ሁሉ የስንዴ ዋጋ ንረቱ በርካታ የዳቦ መጋገሪያ ድርጅቶችን ስራ ያስተጓጎለ ሲሆን በሂደቱም ድርጅታቸው እንዲዘጋ የሚያስገድዳቸው መሆኑን ይናገራሉ።  በስንዴ ዋጋ መናር ሳቢያ የተፈጠረው የዳቦ ምርት እጥረት በምግብ ሸቀጦች ዋጋ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ተጠቁሟል።
መንግስት በዚህ አመት ለውጪ ገበያ ከሚቀርበው ስንዴ 150 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ ይህ የመንግስት ዕቅድ ገና ከጅምሩ የአገር ውስጥ ገበያውን ማናጋት ጀምሯል ተብሏል።
መንግስት የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ስንዴ አብቃይ በሆኑ ክልሎች ያሉ አርሶ አደሮች፣ ለውጪ ገበያ የሚቀርብን ስንዴ በአነስተኛ  ዋጋ ለመንግስት አንዲያቀርቡ የሚያስገድድ አዲስ መመሪያ አውጥቷል። በዚህ የመንግስት አዲሱ መመሪያ መሰረትም፤ አርሶአደሩ አንዱን ኩንታል ስንዴ በ3200 ብር ሂሳብ ለህብረት ስራ ማህበራት እንዲያስረክብ ታዝዟል። ይህ ሁኔታ ያልተዋጠላቸው አርሶአደሮች በተጠቀሰው ዋጋ መሸጥ አያዋጣንም በማለት ምርቱን ለመሸሸግና ለኮንትሮባንድ ነጋዴዎች  ለመሸጥ መገደዳቸውን ለማወቅ ተችሏል። የስንዴ ምርትን ሸሽገው የተገኙ አሊያም በህገወጥ መንገድ ከቦታ ወደ ቦታ ሲያዘዋውሩ የተገኙ አርሶአደሮችም ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውና ምርቱም እንደሚወረስ አዲሱ መመሪያ ያመለክታል።
ስንዴ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ለማህበረሰቡ የሚሸጠው የስንዴ ምርት በኩንታል ከ4ሺ እስከ 5ሺ ብር የሚደርስ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ኩንታል ስንዴ ከ7ሺ እስከ 7ሺ አምስት መቶ ብር  እየተሸጠ ይገኛል። ይህም የሆነው ገበያው ከስንዴ አምራች አካባቢዎች እየራቀ በሄደ ቁጥር የኬላ ክፍያውም እየጨመረ ስለሚሄድ እንደሆነ ነጋዴዎች ይናገራሉ።
መንግስት ወደ ውጪ ለመላክ ካቀደው የስንዴ ምርት ውስጥ 3.1 ሚሊዮን ኩንታል ድርሻው የኦሮሚያ ክልል ሲሆን፤ ክልሉ የተጣለበትን  ኮታ ለማሟላት አርሶ አደሮች የስንዴ ምርታቸውን በርካሽ ዋጋ እንዲሸጡለት እያግባባ ነው ተብሏል።
ክልሉ ኮታውን ለማሟላት ስንዴ አብቃይ ለሆኑ ዞኖች ኮታ አከፋፍሎ፣ ዞኖች በወረዳዎች አማካኝነት የተመደበባቸውን የስንዴ ኮታ እንዲሰበስቡ የማድረጉን ተግባር እንደተያያዙት ታውቋል። አርሶ አደሮቹ ባለፉት አመታት አንድ ኩንታል ማዳበሪያ በ1500 ብር ሂሳብ እየገዙ፣ የሚያመርቱትን ስንዴ ኩንታሉን በ4ሺ ብር ሲሸጡ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ አሁን የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዋጋ ወደ 4500 ብር ባሻቀበበት ወቅት ያመረቱትን የስንዴ ምርት በ3200 ብር ሽጡ መባላቸው ፈጽሞ ተገቢነት የለውም ሲሉ መቃወማቸውን  ምንጮች ጠቁመዋል።
በተፈጠረው የዋጋ ውዝግብ ሳቢያ በአካባቢዎቹ ስንዴን እንደ ልብ ለገበያ አቅርቦ መሸጥ እንዳልተቻለና በርካታ አርሶ አደሮችም የስንዴ ምርትን በቤታቸው ሸሽገዋል በሚል ምክንያት የቤት ለቤት ፍተሻ እየተደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት በስንዴ ዋጋ ላይ እየታየ ያለው ከፍተኛ ጭማሪ እየቀጠለ እንደሚሄድ ግምታቸውን የገለጹት ምንጮች፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የታየው የዋጋ ጭማሪ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር እስከ 2000 ብር ጭማሪ ማሳየቱንም ጠቁመዋል።


Read 2654 times