Saturday, 27 October 2012 11:00

“ፍኖተ ሕይወት” እና ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(3 votes)

በዩኒቨርስቲ ወተት በቧንቧ ይቀርብ ነበር …
ንጉሱ ተማሪና ትምህርት ያበረታታሉ …
የሥራና የሕይወት ታሪካቸውን የያዘው “ፍኖተ ሕይወት”ን ጨምሮ 14 ያህል ወጥና የትርጉም መፃሕፍትን ሰንደው ለአንባቢያን አቅርበዋል፡ የሕይወት ጉዟቸውን የያዘውን መጽሐፍ ለማዘጋጀት ምክንያት የሆናቸው ብዙ ሰዎች “በሕይወት የሉም” ብለው ያስቡ በነበረበት ወቅት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ በመጋበዛቸው ነበር፡፡ ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም በ“ፍኖተ ሕይወት” መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ስለዚህ ገጠመኝ ሲናገሩ “ከሕብረተሰቡ ነጠል ብዬ እኖር ስለነበር አንዳንድ ሰዎች በአገር ውስጥ እንደሌለሁ፤ ሌሎች ደግሞ ገና ድሮ ሞቼ የተቀበርሁ እንደሚመስላቸው እሰማ ነበር፡፡

ስለሆነም የዶክተር ፈቃደን ግብዣ ተቀብዬ ለተማሪዎቹ አጭር ንግግር አደረግሁላቸው፤ በሕይወት መኖሬን ለማረጋገጥ ያህል!” ተጋባዡ ልምዳቸውን አቅርበው ሲያጠናቅቁ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ “ኦቶባዮግራፊህን ለምን አትጽፍም?” የሚል ጥያቄ ለደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም ያቀርባሉ፡፡ ባለ ታሪኩ ከዚያ በፊት የተዘጋጁበት ጉዳይ ባይሆንም ጥያቄው በነገሩ እንዲያስቡበት ገፋፋቸው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ “የሕይወት ታሪክዎን ለመፃፍ አስቤያለሁ” አላቸው፡፡ ሐሳቡ ጥቅም እንዳለው ሲረዱ ታሪካቸውን ራሳቸው መፃፍ ጀመሩ፡፡ 
ለማጠናቀቅ የአራት ዓመት ጊዜን የወሰደው “ፍኖተ ሕይወት” መጽሐፍ በ2000 ዓ.ም ታትሞ ለአንባቢያን ቀረበ፡፡ እንኳን ፃፉት የሚያስብል ብዙ ታሪክና መረጃዎችን ይዟል፡፡
ወተት በቧንቧ አቅራቢው ዩኒቨርሲቲ
ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም ከ1949-1952 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በቆዩባቸው ዓመታት ከሚያስታውሷቸው ታሪኮች መሐል ግቢው ውስጥ ትምህርታቸውን ከሚከታተሉት 400 ተማሪዎች ውስጥ የሴቶቹ ቁጥር 30 እንደነበር፤ ተማሪዎቹ ይለብሱት በነበረው ዩኒፎርም ምክንያት ሕብረተሰቡ ልዩ አክብሮት ይሰጣቸው እንደነበር፤ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ ምቾት ከመጨነቁ የተነሳ “ወተት እንደውሃ ከበርሜል ጋር ከተያያዘ ቧንቧ እየተቀዳ እንጠጣ እንደነበር አስታውሳለሁ” ይላሉ፡፡
ሆሊውድና ሴባስቶፖል
ከጥቂት ዓመታት በፊት በብሔራዊ ሙዚየም በተዘጋጀ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን የሻምበል አበበ ቢቂላ የእግር አሻራ የሚያሳይ ምስል የአትሌቱን ታሪክና ሥራ በሚያስቃኘው አውደ ርዕይ ማየቴን አስታውሳለሁ፡፡ ታዋቂ ሰዎችን መዘከሪያ እንዲህ ዓይነት ባህል በፈረንጆች ዘንድ በስፋት የተለመደ መሆኑን “ፍኖተ ሕይወት” ያቀረባቸው ታሪኮች አሉ፡፡ አንደኛው ገጠመኝ በፓሪስ (ዛንሶ) ያዩት ነው፡፡
ፈረንሳዮች ለቪክቶር ሁጎ ያላቸውን አክብሮት ለመግለጽ በሥሙ ቤተ መዘክር አቋቁመውለታል፡፡ ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም ቤተመዘክሩን ሲጎበኙ የቪክቶር ሁጎን እጅ የሚወክል የተቀረፀ ምስል ማየታቸውንና የሙዚየሙ አስጎብኝም “ሌ ሚዜራብል”ን የፃፈው እጅ ነው ብሎ በአድናቆት ነገረኝ ይላሉ፡፡ ፈረንጆች ለታዋቂ ሰዎቻቸው ያላቸው አክብሮት ከፍተኛ እንደሆነ የተመለከቱበት ሌላው ቦታ ሎስ አንጀለስ ነው፡፡ ስለዚህ ገጠመኛቸው ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም ምስክርነታቸውን ሲሰጡ፡-
“የሎስ አንጀለስ ዋና መታወቂያው ይኸው ሆሊውድና የፊልም ተዋናዮቹ መኖሪያ የሆነው ቤቨርሊ ሂልስ ናቸው፡፡
አሜሪካኖች የፊልም አርቲስቶቻቸውን ከማድነቅም አልፈው ያመልኳቸዋል ቢባል ከእውነት የራቀ አይደለም፡፡ አርቲስቶች ከመደነቃቸውና ከመመለካቸው የተነሳ በጣም ዝነኛ የሆኑት የእጅና የእግር ቅርጻቸው ሆሊውድ ውስጥ ከዋናው አውራ ጎዳና ግራና ቀኝ ባሉ የእግር መንገዶች (ፔቭመንትስ) ላይ በሲሚንቶ ተቀርጸው ስማቸው ተጽፎበት ይታያል፡፡”
የ“ፍኖተ ሕይወት” ደራሲ በፈረንሳይና በሎስ አንጀለስ ያዩት አክብሮት መግለጫ ተግባር በአገራችንም በሻምበል አበበ ቢቂላ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን እንደታየው ሁሉ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ግቢ ውስጥ በሚገኘው ሴባስቶፖል ሲኒማ ቤት መግቢያ በር ላይ የታዋቂ ኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች የእጅ መዳፍ አሻራ በሲሚንቶ ላይ በማተም ሥማቸውን ጭምር በማኖር የነጮቹ ባህል በአገራችንም እንዲለመድ ሙከራ ተደርጓል፡፡
የአፄ ኃይለሥላሴ ሐውልት በለንደን
ፈረንጆች ለታዋቂና ታሪካዊ ሰዎች ያላቸውን አክብሮትና አድናቆት ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ፣ ሃይማኖት … ሳይለዩ የሚገልጹ ስልጡኖች ናቸው የሚያስብላቸው ሌላው ገጠመኝ የለንደን ነው፡፡
ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም የለንደን ማዳም ቱሶ ቤተመዘክርን ሲጎበኙ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች ሐውልት በሰም ተቀርፆ ማየታቸውንና ከሐውልቶቹ መሐል የአፄ ኃይለሥላሴ፣ የገማል አብደል ናስር እና የዝነኛው እግር ኳስ ተጫዋች የፔሌም እንደሚገኝበት ይመሰክራሉ፡፡
አገር በመክዳት ቀዳሚው ማነው?
“ፍኖተ ሕይወት” መጽሐፍ “ስነ ጽሑፋዊ አሻራ” በሚል ክፍል ባቀረበው ጽሑፍ ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም የሥነ ጽሑፍ ሰው እንዲሆኑ በአገር ውስጥ በጐ ተጽእኖ አሳድሮብኛል የሚሉት ደራሲ እንደሌለ ይገልፁና ለሥራዎቻቸው የተለየ አድናቆት አለኝ በሚል ከአገር ውስጥም ከውጭም የተለያዩ ደራሲያንና ሥራዎቻቸውን ያስቃኛሉ፡፡ በዚህ ክፍል ሥራና ታሪካቸው ከቀረቡላቸው ኢትዮጵያዊያን ደራሲያን አንዱ አፈወርቅ ገብረየሱስ ናቸው፡፡
ከአፄ ምኒልክ የቅርብ ሰዎች አንዱ የነበሩት አፈወርቅ ገብረየሱስ ባልታወቀ ምክንያት ከእቴጌ ጣይቱ ጋር እየተቃቃሩ በመሄዳቸውና ችግሩም በመክረሩ እንደገና ለትምህርት ወደ አውሮፓ እንዲሄዱ ንጉሱ ወሰኑ፡፡
“እቴጌ ጣይቱ በሕይወት እስካሉ ድረስ ወደ ኢትዮጵያ አልመለስም” ያሉት አፈወርቅ ገብረየሱስ፤ የአውሮፓ ጉዟቸው በወቅቱ ከስደት ጋር ተቆጥሯል፡፡
ከአፈወርቅ ጋር ቅጣው ዛማኔልና ጉግሣ ዳርጌ የተባሉ ወጣቶችም አብረው ነበር ለትምህርት ወደ አውሮፓ የተላኩት፡፡
ሦስቱ ወጣቶች በተላኩበት (ስዊዘርላንድ) ብዙም ሳይቆዩ ወደ ጣሊያን በመሄድ ከአገር በመኮብለል “ፈር ቀዳጅ” ሆነዋል፡ከአገር በመኮብለል ሦስቱን ወጣቶች የሚቀድም ይኖር ይሆን?
አባ ማርሴና የማርክ አሰጣጣቸው
በእንጦጦ ጋራ ስር ይገኝ የነበረው ላዛሪስት ሚሲዮን ት/ቤት ውስጥ ከነበሩት መምህራን አንዱ ናቸው - አባ ማርሴ፡፡
መምህሩ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በተለየ እንዲታወቁ የሚያደርጓቸው ብዙ ነገሮች ነበሩዋቸው፡፡ አማርኛና ግዕዝን አጣርተው ያውቃሉ፡፡
ተማሪ ምንም ያህል ጐበዝ ቢሆን ከ10 ከተፈተነው ፈተና ከ8 በላይ ማግኘት የለበትም ብለው ያምናሉ፡፡ 9 ከ10 ሊያገኝ የሚችለው የተማሪዎቹ መምህር ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ከ10ሩ 10 ሊያገኝ የሚችለው ደግሞ እግዚአብሔር ነው ይሉ እንደነበር በላዛሪስት ሚሲዮን አምስት ዓመታት ትምህርታቸውን የተከታተሉት ሣህለሥላሴ ያስታውሳሉ፡፡
ደራሲው ስለ እግዚአብሔር
ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በቆዩባቸው ዓመታት ያነበቧቸው መፃሕፍት ማንነታቸውን በመቅረጽ ረገድ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አድርገውልኛል ይላሉ፡፡
ካነበቧቸው መፃሕፍት ያገኙትን ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ የተቀበሉት እንዳለ ሁሉ፣ በተቃራኒው ያላመኑበትን ለምን እንዳልተቀበሉ የራሳቸውን መረዳት በማሳያነት በማቅረብ ውድቅ ያደርጋሉ፡፡
በፍልስፍናው ዓለምና በየመፃሕፍቱ ለሚነሳው የእግዚአብሔር “አለ” እና “የለም” ክርክር የደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ መረዳት ይህንን ይመስላል
“አንድ ሰው የሕፃን ተምሳሌት የሆነን አሻንጉሊት ይሠራል እንበል፡፡ ምን እንደሰራ አሳምሮ ያውቃል፡፡
አሻንጉሊቱ ግን የሠራውን ሰው ባህሪ ቀርቶ ማን እንደሰራው እንኳ አያውቅም፡፡
ሰውም እንዲሁ ፈጣሪ እንዳለው ግንዛቤ ቢኖረውም እንኳ (ሰው ራሱን አልፈጠረምና) የእግዚአብሔርን ምንነት፤ የእግዚአብሔርን ባህሪ ተመራምሮ ሊደርስበት በቂ አእምሮ የለውም ባይ ነኝ” ይላሉ፡፡
“ባለውለታዎቼ ብዙ ናቸው”
ወላጆቼ፣ ተወልጄ ያደግሁበት መንደር፣ ዕውቀት ለመሸመት የቆየሁባቸው ትምህርት ቤቶችና መምህራን፣ በተግባር የኖርኩት ኑሮ፣ ከመፃሕፍት ያገኘሁት ዕውቀት ድምር ውጤት ነኝ የሚሉት ተርጓሚና ደራሲ ሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም የራሳቸውን የሕይወትና የሥራ ታሪክ መነሻ አድርገው ከ1930 ዓ.ም ጀምሮ ያዩና ያለፉበትን በመጽሐፍ ጠርዘው አቅርበዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ዕድገት ስለለፉ የተለያዩ አገር ዜጐች፤ ዘመናዊ ትምህርታችን ዛሬ የሚገኝበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የተለያየ አስተዋጽኦ ስላደረጉ ፈረንጆች፤ አፄ ኃይለሥላሴ ተማሪና ትምህርትን ለማበረታታት ያደርጓቸው ስለነበሩ ጥረቶች፤ ስለ ጉራጌ ሕዝብ ታሪክና ባህል ምንነት፤ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አለመቅረቡ ስላስከተለው ጉዳት፤ በ1983 ዓ.ም ደርግን አሸንፈው አዲስ አበባ የገቡት ኢህአዴጐች ምን ይመስሉ እንደነበር…ብዙ ብዙ ታሪክ ያስቃኛል መጽሐፉ፡፡ በመጨረሻ ፀሐፊውና መጽሐፉ እንዲፃፍ ያነሳሱት ግለሰቦች በዚህ አጋጣሚ ቢመሰገኑ ተገቢ ይሆናል፡፡

Read 4084 times