Saturday, 11 February 2023 20:24

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ ኮሚቴ ለጠ/ሚ ዐቢይ ጥሪ አቀረበ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ኮሚቴው በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍና መከራ በአስቸኳይ ይቁም ሲል ጠይቋል።
     - በሚሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ህዝብ በመንግስት ላይ ያለው እምነት እየተሸረሸረ መሆኑን ኮሚቴው አመልክቷል። - ችግሩ በአፋጣኝ   ካልተፈታ አገሪቷ በታሪኳ አጋጥሟት የማያውቅ ቀውስ ውስጥ ትገባለች ብሏል።
              
          በአሜሪካ የኢትዮጵያውያ ጉዳይ ኮሚቴ (ኢፓክ) ከዓለም አብያተክርስቲያናት፣ ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ካውንስል፣ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ካውንስል፣ ከምስራቅና ኦረየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እና ከበርካታ ታዋቂ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበራትና ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች ጋር በመሆን በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በአስቸኳይ እንዲያስቆሙና አገሪቱን ከቁልቁለት ጉዞ እንዲመልሱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተፈጠረው ቀውስ መነሻ ምክንያቶቹ በህገ-ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያፈነገጡት ቡድኖች መሆናቸው በግልጽ እየታወቀ የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ሃይሎች የበርካታ ንፁሃንን ህይወት ሲቀጥፉ ቤተክርስቲያኒቱ ክብሯ ሲዋረድና ከባድ ውድመት ሲደርስባት መንግሰት ሁኔታውን በዝምታ መመልከቱ በእጅጉ አስገርሞናል ያለው ኮሚቴው ይህም መንግስት የዜጎቹን ደህንነት መጠበቅ ሃላፊነቱን በአግባቡ አለመወጣቱን አመላካች ነው ብለዋል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና ዲያስፖራው በመንግስት ላይ ያለው እምነት በፍጥነት እየተሸረሸረ ሄዷል ያለው ኮሚቴው መንግስት ቀውሱን ለመፍታት ያለው ፍላጎት አነስተኛ መሆኑ ቀውሱን እራሱ አውቆ የፈጠረውና የሚደግፈው ነው ብሎ ለማመን የሚያስገድድ ሁኔታ ላይ እንዲደረስ ማድረጉን አመልክቷል።
በአገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስ እና የህግ ጥሰት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ካውንስል ለፌደራል መንግስትና ለተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ለመገናኛ ብዙሃን አካላት ያስተላፈውን መልዕክት በመደገፍ ተቋማቱ ሃላፊነት የሞላበትንና ህጋዊ አካሄድ በተከተለ መንገድ መፍትሄ ለመሻት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት በቤተክርስቲኗ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍና በደል አጥብቆ እንደሚቃወም የገለጸው ኮሚቴው በቅዱስ ሲኖዶሱ የተመደቡ የሃይማኖት መሪዋችን ማሰር መደብደብና ማጉላላት፣ ወደሀገረ ስብከታቸው እንዳይገቡ መከልከል፣  ምዕመናንን በጭካኔ መግደል፣ ያፈነገጡትንና በቅዱስ ሲኖዶሱ የተወገዙትን ሊቃነጳጳሳት በመደገፍ ህግ በመጣስ የአብያተክርስቲናትን በር እየሰበሩ ማስገባት፣ የቤተክርስቲኒቱን ክብር ማጉደፍና ሀብትና ንብረቷን የማዘረፍ ወንጀል አጥብቀን እንቃወማለን ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህገ-መንግስቱና ለሀገሪቱ ህግ የበላይ ጠባቂ መሆናቸውን በመገንዘብ ሃላፊነት ተሰምቷቸው አቅጣጫቸውን እንዲያስተካክሉና አገሪቱን ከከፋ መቅሰፍት እንዲያድኑ ጥሪ ያቀረበው ኮሚቴው ችግሩ በቶሎ ካልተፈታና እየተባባሰ ከሄደ ሀገሪቷ ከዚህ ቀደም በታሪኳ ካጋጠሟት ሁሉ የከፋ ቀውስ እንደሚያጋጥማትና መውጫ የማይገኝለት አዙሪት ውስጥ እንደምትገባ አበክሮ አሳስቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱ በድንገት ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ለማዳን የሚያስችል ትክክለኛና ቆራጥ አመራር እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።

Read 3087 times