Saturday, 04 February 2023 20:29

የሚሰራውን ጠንቅቆ የሚያውቀው ጀግና!

Written by  ትግስቱ
Rate this item
(1 Vote)

አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ የሩጫ ጫማውን ከሰቀለ ወዲህ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ቢዝነሱ ማዞሩ ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ በሆቴልና ሪዞርት ዘርፍ የራሱን “ሃይሌ” ብራንድ ፈጥሮ በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ የሃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ስምንተኛ ቅርንጫፍ የሆነው ሃይሌ ግራንድ ሆቴል አዲስ አበባ ከሳምንት በፊት መደበኛ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አመራሩ በይፋ አብስሯል፡፡ የሃይሌ ሆቴልና ሪዞርትስ ቁጥርን ለማሳደግና 20 ለማድረስም እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡   
በቅርቡ የአዳማውን ሃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ጎብኝቼው ነበር፡፡ የህንፃው ውበት ልዩ ነው። የተንጣለሉ የመሰብሰቢያ አዳራሾች አሉት። ማራኪ ሬስቶራንቶችና ባሮችን የያዘ ነው፡፡ ውብ አረንጓዴ መናፈሻዎች ያሉት ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ምግቦች ዝግጅቱ እንከን የለሽ ነው፡፡ እኔን ከሁሉም የማረከኝ ግን መስተንግዶው ነው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጣቸው በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡
ለሦስት ቀናት በነበረኝ ቆይታ ግሩም መስተንግዶ አግኝቻለሁ- በልባዊ ፈገግታ የታጀበ፡፡ ከውጭው በር ጀምሮ በፍተሻው ሥፍራ፣ በእንግዳ መቀበያ ዴስኩ፤ በምግብና መጠጥ መስተንግዶ ሁሉ… ቤተሰባዊ መስተንግዶ ነው የሚሰጡት፡፡ ከጥበቃ ባለሙያዎች እስከ ሃላፊዎች ድረስ ለእንግዶቻቸው ደስታና እርካታ የሚጨነቁና የሚጠበቡ ናቸው፡፡
በአገራችን የሚከፈቱ ባለ 4 እና 5 ኮከብ ሆቴሎች በአብዛኛው ውብና ማራኪ ናቸው- በህንፃ ዲዛይን፡፡ ብዙዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ የመኝታ ክፍሎች ያሏቸው ናቸው፡፡ በርካታ ባርና ሬስቶራንቶች እንዲሁም የተንጣለሉ አዳራሾች አሏቸው - ለዓይን የሚማርኩ። የሚበዙቱ ምርጥ የመዋኛ ገንዳ፣ ሳውና ባዝ፣ ጂም ወዘተ… አሟልተው የያዙ ናቸው። ችግራቸው በአብዛኛው መስተንግዶ ላይ ነው - የእንግዳ አያያዝ፡፡ ይህን ችግር በተለያዩ ጊዜያት በርካታ አገራችንን የጎበኙ የውጭ አገራት ቱሪስቶች አንስተውታል፡፡ እኛም የአገሩ ባለቤቶች ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ ለረዥም ጊዜያት ግን ችግሩ እንዳለ ከማውራት ባለፈ መፍትሄ ላይ ብዙም የተጋን አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ በርካታ ዓለማቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች የመከፈታቸውን ያህል ብቁ ትምህርትና ስልጠና የሚሰጡ የሆቴል መስተንግዶና አመራር ማሰልጠኛ ተቋማት አልተከፈቱም፡፡
ብዙዎቹ በአገራችን ባለሀብቶች የሚከፈቱ ሆቴሎች ለመስተንግዶ ባለሙያዎች ሥልጠና እምብዛም ትኩረት የሚሰጡ አይመስሉም። ለምሳሌ እንደ ሂልተን ሆቴል ዓይነቶቹ ዓለማቀፍ ሆቴሎች በየጊዜው ሥልጠና የሚሰጥ የሥልጠና ዲፓርትመንት አላቸው፡፡ ለአጫጭር ሥልጠናም ሠራተኞቻቸውን ወደ ውጭ አገራት ይልካሉ፡፡
በአዳማው የሃይሌ ሪዞርትና ሆቴል ያስተዋልኩት ልባዊ መስተንግዶና ፕሮፌሽናል የእንግዳ አቀባበል ድንገት ወይም በአጋጣሚ የተከሰተ አይደለም፡፡ ከመነሻውም ሆቴልና ሪዞርት ላይ አተኩሮ መሥራት የጀመረው አትሌት ሃይሌ፤ በሆቴል አገልግሎት አሰጣጥ በተለይም በመስተንግዶ ዘርፍ ያለውን ክፍተት በጊዜ ሳይገነዘብ አልቀረም፡፡ ለዚህም ነው የራሱን ሃይሌ የሆቴል ማኔጅመንት ኮሌጅ ያቋቋመው፡፡
በየቀኑ ሩብ ሚሊዮን ቅጂዎችን ከሚሸጠው ታዋቂው የኬንያ ጋዜጣ “ዴይሊ ኔሽን” ጋር በቅርቡ ቃለ ምልልስ ያደረገው አትሌት ሃይሌ፤ ማንኛውም አዲስ ሰራተኛ በሆቴሉ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በሃይሌ የሆቴል ማኔጅመንት ተቋም ገብቶ ለአራት ወራት ሥልጠና እንደሚወስድ ተናግሯል፡፡ ለረዥም ዓመታት በሀይሌ ሆቴልና ሪዞርትስ በአነስተኛ የሥራ ዘርፎች ውስጥ በማለፍ ለሃላፊነት ደረጃ የበቁ ሰራተኞችም አዳዲስ ቅርንጫፎች ሲከፈቱ በአመራርነት እንደሚመደቡ ሃይሌ ለጋዜጣው ጠቁሟል፡፡
የሆቴልና መስተንግዶ ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ፉክክር የተሞላ መሆኑን የሚናገረው አትሌት ሃይሌ፤  ለደንበኞቻችን ምቹና ተስማሚ አገልግሎት መስጠት ካልቻልን ከእጃችን ያመልጡናል ይላል፡፡ ይሄ ደግሞ ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች በተለየ ትላልቅ ሆቴሎች እንደአሸን እየፈሉ ባሉባት አዲስ አበባ የበለጠ እውነት ይመስላል፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ብቻ ሳትሆን የበርካታ ዓለማቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ ደረጃቸውን የጠበቁና የተሟላ መስተንግዶ የሚሰጡ ሆቴሎችን ትፈልጋለች፡፡
 ሆቴል የከፈተውን ባለሃብት ሁሉ የሆቴል ማኔጅመንት ማሰልጠኛ ተቋም እንዲከፍት መመኘት የዋህነት ነው፡፡ ሁሉም የሆቴል ባለቤቶች ግን ሠራተኞቻቸው በቂ የሙያ ሥልጠና ማግኘታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው - በዘርፉ ተፎካካሪ ሆነው ለመቀጠል፡፡
በአገራችን የሆቴል መስተንግዶና አመራር ዘርፍ ውስጥ ያለውን ክፍተት ተረድቶ የማሰልጠኛ ተቋም የከፈተው አትሌት ሃይሌ፤ የራሱን ሰራተኞች ከማሰልጠን ባሻገር እንደ ማንኛውም የማሰልጠኛ ተቋም ለሌሎችም በሩን ክፍት ቢያደርግ ለአገር ያለው ፋይዳ የላቀ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ እግር መንገዱንም በሆቴል ሥራ መሰማራት ለሚፈልጉ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ኢንቨስተሮች የማማከር አገልግሎትም መስጠት ቢችል አገር ብዙ ትጠቀማለች፡፡
በአንድ ወቅት አትሌት ሃይሌ ሃውልት እንዲቆምለት ይፈልግ እንደሆነ ተጠይቆ ሲመልስ፤ ራሱ በስራዎቹ የራሱን ሃውልት እያቆመ መሆኑን ተናግሮ ነበር፡፡ አሁንም እያደረገ ያለው ይኼንኑ ነው- በሥራዎቹ ሃውልቱን እያቆመ ነው- አሻራው እያኖረ! አትሌት ሃይሌ በሩጫው ለዓለም ያሳየውን ጀግንነት በቢዝነሱም ደግሞታል፡፡ ዕፁብ ድንቅ ተግባር ነው፡፡   

Read 1734 times