Saturday, 04 February 2023 20:03

ታዳጊው ሥራ ፈጣሪ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“--ቬስትልን ከገዛ በኋላ እስከ ሩቅ ምስራቅ ድረስ በመሄድ በወቅቱ የነበረውን የገበያ ፉክክር አጥንቷል፡፡ ሲመለስም በአንድ ዓመት ውስጥ የቴሌቪዥን ምርት አቅሙን ከ360 ሺ ወደ 600 ሺ ለማሳደግ ወሰነ - የውጭ ገበያውን አቅም ለማስፋፋት  በማቀድ፡፡--”



           አህመት ዞርሉ ከቱርክ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጋር የተዋወቀው ገና በ15 ዓመቱ ነበር፡፡ በትውልድ ቀዬው በአቅራቢያው የሚገኘው ት/ቤት በ20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንደነበር የሚያስታውሰው ዞርሉ፤ በርቀቱ ሰበብ ትምህርት አቋርጦ ወደ ሙሉ ሰዓት ሥራ እንደገባ ይናገራል፡፡
በልጃቸው ሥራ ፈጣሪነት እምነት ያደረባቸው አባቱ፣ በወቅቱ የራሷ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ወዳልነበራት ትራብዞን የተሰኘች የቱርክ ግዛት ላኩት - ንግድ እንዲጀምር፡፡
ሱቅ ተከራይቼ በትውልድ አካባቢዬ የሚመረቱ ጨርቃጨርቆችን እሸጥ ነበር የሚለው ዞርሉ፤ እስከ 1961 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ድረስ ጥሩ እንደነገደ ይናገራል፡፡
የፖለቲካው አለመረጋጋት የፈጠረው የንግድ መቀዛቀዝ በወቅቱ ከነበረው ሃይለኛ የገበያ ፉክክር ጋር ተዳምሮ ታዳጊው ነጋዴ ከቢዝነስ ሊያስወጣው ምንም አልቀረውም ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ ጠቀም ያለ ትርፍ አግኝቶ ስለነበር በቢዝነሱ መቀጠል ቻለ፡፡
“አዲስ ሱቅ ኢስታንቡል ውስጥ በመክፈት አዳዲስ ምርቶችን መሸጥ ጀመርኩ፡፡ በርካታ አንሶላዎችን በመግዛት የተለያዩ ዲዛይኖች እያሳተምኩ በቱርክ የመጀመሪያውን ባለ ህትመት አንሶላ ለገበያ ማቅረብ ጀመርኩ። የአንሶላዎቹ ገበያ ሲደራልን ወደ ጠረጴዛ ልብሶች ሽያጭ ገባን፤ በሱም ቀናን፡፡ በ1973 ዓ.ም የራሳችንን የመጀመሪያ የሽመና ፋብሪካ ከፈትን፡፡”  
ፋብሪካው ከፍተኛ ስኬት እንዳስመዘገበ የሚያስታውሰው ታዳጊው፤ በ1970ዎቹ ዓመታት በስኬት ለመቀጠል ወደ አዳዲስ ዘርፎች መግባት እንደሚያስፈልግ መገንዘቡን ይናገራል፡፡
“ማምረትና ችርቻሮ ሽያጭ በቂ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ፤ አዳዲስ ብራንዶች ያስፈልጉን ነበር። እናም በ1975 ዓ.ም የራሳችንን “ታች” የተሰኘ የአገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ምርት ፈጠርኩ ሲል ያስረዳል፡፡ “ታች” በአገር ውስጥ ገበያ የመሪነቱን ሥፍራ ሲይዝና ትልቁ ጨርቃጨርቅ ላኪ ኩባንያ እየሆነ ሲመጣ የቱርክ የፖለቲካ ችግሮች እንደገና ቢዝነሱን አወኩት፡፡ በወቅቱ የበለጠ መስፋፋት እንፈልግ ነበር የሚለው ዞርሉ፤ ሆኖም በፖለቲካው ምስቅልቅልና ሁከት የተነሳ እንቅስቃሴያችንን ገታን ይላል፡፡
ከ1980 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት በኋላ የፖለቲካ አየሩ ተረጋግቶ ሰዎች እንደገና ኢንቨስት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ይሄን ጊዜ ነው “ኮርቴክስ” የተባለ የመጋረጃ አምራች ኩባንያ የገዙት፡፡ ኩባንያውን በማስፋፋትም በስድስት ዓመት ውስጥ በወቅቱ በዓለም ላይ ከነበሩ ትላልቅ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች አንዱ እንዲሆን አስችለውታል፡፡
የገበያ ተንታኞች እንደምንከስር ይናገሩ ነበር፤ እኛ ግን ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት እንዳለ እናውቅ ነበር ይላል- ዞርሉ፡፡
“በ1980 ዓ.ም አስተማማኝ የፖሊስተር ጨርቅ ያስፈልገን ነበር ፤ ስለዚህም የራሳችንን ፋብሪካ ተከልን፡፡ በሌሎች ላይ ከመተማመን የራሳችንን ማምረት ተመራጭ ነበር” ብሏል፡፡
በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዞርሉ አቅሙን  በአራት  እጥፍ ማሳደግ የቻለ ሲሆን በመላው ዓለም ትልቁ የፖሊስተር አምራች ለመሆን በቅቷል፡፡ ሆኖም የቱርክ የአገር ውስጥ ገበያ እየተጣበበ ከመሄዱም በተጨማሪ የዓለም የጨርቃጨርቅ ገበያ ተለዋዋጭ ስለነበር ዞርሉ ቢዝነሱን በተለያዩ ዘርፎች ማስፋፋት ነበረበት፡፡
“በ1992 ዓ.ም በጨርቃጨርቅ ብቻ የምንፈልግበት ደረጃ ላይ እንደደረስን ተገነዘብን እናም አዲስ ዘርፍ ማፈላለግ ጀመርኩ” ይላል- የቱርኩ ኢንቨስተር፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አምራች ኩባንያ የሆነው ቬስትል በኪሳራ ሊሸጥ መሆኑን የሰማው ዞርሉ፤ ኩባንያውን እንዴት እንደገዛው ሲናገር፡-
“ቬስትልን በደንብ ተመለከትኩትና የገንዘብ እጥረት እንዳለበት ተገነዘብኩ፡፡ ፋብሪካው ዘመናዊና በደንብ የተደራጀ ሲሆን ከአገር ውስጥ ብቃቱ በተጨማሪ በዓመት ከውጭ ገበያ 100 ሚ. ዶላር የማስገባት አቅም አለው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በክልሉ ቲቪ የሚያመርት ሌላ ፋብሪካ የለም” ብሏል፡፡
ቬስትልን ከገዛ በኋላ እስከ ሩቅ ምስራቅ ድረስ በመሄድ በወቅቱ የነበረውን የገበያ ፉክክር አጥንቷል፡፡ ሲመለስም በአንድ ዓመት ውስጥ የቴሌቪዥን ምርት አቅሙን ከ360 ሺ ወደ 600 ሺ ለማሳደግ ወሰነ - የውጭ ገበያውን አቅም ለማስፋፋት  በማቀድ፡፡
ቬስትል  103 ለሚደርሱ የዓለም አገራት የቲቪ ምርቶችን መላክ ችሏል- በዓመት 17 ሚ. ቲቪዎች፤ 12 ሚ. ዲጂታል መሳሪያዎች (ዲቪዲ፣ ሳተላይት መቀበያ እና ተያያዥ መሳሪያዎች) ይልክ ነበር፡፡
ቢዝነሱ የዚህን ያህል ቢጧጧፍም ዞርሉ ስለስኬቱ ብዙም አያወራም፡፡ ሲጠየቅም ገበያውን የማንበብ ችሎታና ጠንክሮ የመስራት ውጤት ነው ሲል ይመልሳል፡፡
“ገበያውን ማንበብ ሁሉም ነገር ማለት ነው፡፡ በ60ዎቹና 70ዎቹ ቱርክ የገበያውን ፍላጎት የሚያሟላ በቂ የጨርቃጨርቅ ምርት አልነበራትም፡፡  ያንን ፍላጎት አሟላንና ከገበያው ጋር አደግን፡፡ በኤሌክትሮኒክሱም ተመሳሳይ ነው፡፡ የገበያው አዋቂዎች ትከስራላችሁ ብለውን ነበር፡፡ በጥናታችን መሰረት ብዙ ፍላጎት እንደነበር ተገነዘብን፡፡ አልተሳሳትንም አድገናል” ይላል፡፡
በተመሳሳይ እሳቤ ነው ዞርሉ ወደ ተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የገባው - የገበያውን ፍላጎት በማሟላት አብሮ ለማደግ፡፡ በዚህም መሰረት በባንክ በፋይናንሽያል አገልግሎትና ኢነርጂ ዘርፎች ተሰማርቶ በስኬት እየገሰገሰ ይገኛል፡፡
በቅርብ ዓመታት 20 የቱርክ ትላልቅ ባንኮች ለኪሳራ መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡ ዞርሉ በ1996 ዓ.ም ከመንግስት ይዞታ ላይ የገዛው ዴኒዝ ባንክ ከተፎካካሪዎቹ የሚፈለገውን ዋስትና ለደንበኞች በመስጠቱ ስኬታማ ሊሆን በቅቷል፡፡ በአገሪቱ ሰባተኛው ትልቁ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ቡድን የሆነው የዞርሉ ተቋም፤ 200 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውም ጥሩ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡
ቱርክ ነዳጅ ባይኖራትም ወጣቶችና በደንብ የሰለጠኑ የሥራ አመራሮች አሉን የሚለው ዞርሉ፤ በኢነርጂ ክንፉም አስደናቂ ዕድገት እያስመዘገበ ነው - በአውሮፓ 98ኛው ፈጣን ዕድገት እያሳየ ያለ ኩባንያ ተብሎለታል፡፡
የዞርሉ የቢዝነስ ቡድን ወደ ኤሌክትሪክና ሃይል ማመንጨት ሥራ የገባው በቱርክ  ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የራሳቸውን የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያመነጩ  ዘርፉ ወደ ግል ይዞታ ከተቀየረ በኋላ ነው፡፡ ዞርሉ ግን  ለራሱ ፋብሪካ ሃይል በማመንጨት ብቻ አልተወሰነም፡፡ በቱርክ የመጀመሪያው የኤሌክትሪከ ሃይል አምራች ለመሆን በቅቷል፡፡ ከታዳጊነት እስከ ጎልማሳነት በስኬት መዝለቅ ይሏል ይሄ ነው፡፡
(“ታላላቅ ህልሞች” ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ)

Read 1301 times