Saturday, 04 February 2023 18:24

በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 2ሺ 145 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተፈጽመዋል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የሀገር  ህልውናና  ሉዐላዊነትን በሚያስጠብቁ የፀጥታና የደህንነት   ተቋማት  ላይ ያነጣጠሩ 2,145 የሳይበር ጥቃቶችና  ሙከራዎች መደረጋቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) አስታወቀ። በግማሽ  የበጀት ዓመቱ ውስጥ በተቋማቱ ላይ ከተቃጡት የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ፤ 41 በመቶው “እጅግ በጣም ከፍተኛ” የሆነ ጉዳት የማድረስ አቅም እንደነበራቸውም  ተገልጿል።
 የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ኤጀንሲ (ኢንሳ) የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ   ዋና ዳይሬክተሩ  አቶ ሰለሞን ሶካ  እንደተናገሩት፤ የሳይበር ጥቃቶቹ  ኢላማ  ያደረጉት  የፀጥታና  ደህንነት ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣    በባንኮችና ፋይናንስ ተቋማት ፣ የተለያዩ  ቁልፍ የመንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የህክምናና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ነበር።
ዳይሬክተሩ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 2,145 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ገልፀው፤  በመንግስትና በግል ተቋማት ላይ ከተሞከሩት ከእነዚህ የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ 91.5 በመቶውን ማክሸፍ መቻሉን ተናግረዋል። የተሞከሩ ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ የመሰረተ-ልማቶችን ማቋረጥ፤  ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተወሰኑ ጊዜያት በማስተጓጎል ስራዎች እንዳይሰሩ በማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ገቢ የማስተጓጎል፤ የዳታዎች መሰረቅና መጥፋት፤ የግንኙነትን መንገዶችን በመጥለፍና የክፍያን መንገድ በመጠቀም ገንዘብን በማጭበርበርና በመውሰድ  ከፍተኛ ጉዳት ይደርስ ነበር ብለዋል- ዋና ዳይሬክተሩ  በመግለጫቸው፡፡
በሃገሪቱ ባለፉት ስድስት ወራት ስለተከሰቱ የጥቃት አይነቶች እና ኢላማዎች ማብራሪያ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በነዚህ ወራት በስፋት ከተሞከሩት የሳይበር ጥቃት አይነቶች መካከል የድረገጽ ጥቃት፤ ማልዌር፤ የመሰረተ ልማት ቅኝት (Scan)፤ የመሰረተ ልማት ማቋረጥ (DDOS)፤ የሰርጎ መግባት ሙከራ እንደየቅደም ተከተላቸዉ ከፍተኛ የጥቃት ሙከራ እንደተደረገባቸው  ገልጸዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም. የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ብዛት 3,036  እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ዘንድሮ በተመሳሳይ ወቅት የተፈጸሙ ጥቃቶች ከአምናው ጋር ሲነጻጸሩ በ29.3 በመቶ ያነሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።  የጥቃት ሙከራዎች ቁጥር መቀነሱ በመልካም ሊታይ የሚችል ቢሆንም፤ የተሰነዘሩት ጥቃቶች  በአገሪቱ ላይ ግዙፍ የሆነ ጉዳት  የማምጣት አዝማሚያ ያላቸው መሆናቸውን የገለጹት  አቶ ሰለሞን   ጥቃቶቹ ኢላማ ያደረጓቸው፤ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የሀገር ሀብትና ህልውና ወይም ሉዐላዊነት የሚያስጠብቁ ተቋማት ላይ መሆኑ  የጉዳቱን መጠን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።
በዚህ ዓመት የተደረጉትን ጥቃቶችና የጥቃት ሙከራዎች ከቀደምቶቹ የተለየ የሚያደርገው ጥቃቶች በሀገሪቱ  ዋና ዋና የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤  ሀገሪቱ  በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት  ውስጥ በነበረችባቸው ጊዜያት   በልዩ ልዩ   ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች  ተወጥራ በነበረችበት ጊዜ እንኳ እነዚህ ተቋማት በዚህ መጠን ኢላማ  አልተደረጉም  ነበር  ብለዋል።
በተጨማሪም አስተዳደሩ የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሀገር ወስጥ ለማስገባት ፈቃድ ከተጠየቀባቸው 2,158 የተለያዩ አይነት ቴክኖሎጂዎች 297 የሚሆኑት የደህንነት ስጋት የሚያስከትሉና አደገኛ ተብለው የተለዩ ቴክኖሎጂዎች በመሆናቸው ወደ ሀገር እንዳይገቡ መደረጉንም  ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
በሀገሪቱ የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት ላይ የተቃጡት ሙከራዎችን “ውስብስብ” ሲሉ የገለጿቸው አቶ ሰለሞን፤ ጥቃቶቹ “ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ” ፍላጎቶችን ያነገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የሳይበር ጥቃት አድራሾች የጸጥታ እና የደህንነት ተቋማትን ኢላማ ያደረጉት፤ “ከፍተኛ ትርፍ” ስለሚያስገኝላቸው እንደሆነ የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።  
ባለፈው መንፈቅ ዓመት፤ ከጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት ባሻገር ቁልፍ የመንግስት ተቋማት፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የግል ተቋማት እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይበር ጥቃት ሙከራ እንደተደረገባቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። በስድስቱ ወራት ውስጥ ከተሰነዘሩት የጥቃት ሙከራዎች ውስጥ 41 በመቶው፤ የክብደት ደረጃቸው “እጅግ በጣም ከፍተኛ” እንደሆነ ተነግሯል። በግማሽ ዓመቱ የተደረጉት የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች 15 ቢሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ እንደነበሩም ተገልጿል።

Read 1505 times