Saturday, 04 February 2023 18:22

ግብርን በቴሌ ብር ለመክፈል የሚያስችል ስምምነት ተደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከትላንት በስቲያ ጥር 25 በኢትዮ ቴሌኮም እና በገቢዎች ሚኒስቴር መካከል የግብር ክፍያዎችን በቴሌብር  ለመሰብሰብ የሚያስችል ስምምነት ተደረገ፡፡
በዚህም ስምምነት፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ደንበኞች የተለያዩ የግብር ክፍያዎችን በቴሌብር የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ተጠቅመው በኦንላይን አገልግሎት ክፍያቸውን እንዲፈፀሙ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡
ይህ የአጋርነት ስምምነት በዋናነት ለገቢዎች ሚኒስቴር የገቢ ግብርን እና የግል ሰራተኞች የጡረታ መዋጮ ፤እንዲሁም የፌዴራል ታክስ ክፍያዎችን ለመሰብሰብና ለማሳለጥ ጉልህ ሚና ያለው ሲሆን፤ ከዚህም ባሻገር በየጊዜው እያደገ የመጣውን የግብር ከፋዮች የክፍያ አማራጭ ፍላጎት ቀላልና አስተማማኝ በማድረግ፣ የቴሌብር ተጠቃሚዎች ከግል ወይም ከድርጅት የቴሌብር አካውንታቸው በቴሌብር የሞባይል መተግበሪያ ወይም በአጭር ቁጥር *127# በመጠቀም የግብር ክፍያቸውን ባሉበት ሆነው በቀላሉ ለመክፈል የሚያስችላቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በቴሌብር ግብይት የሚፈፅሙ ነጋዴዎች ከሚፈፅሟቸው ግብይቶች ከሰበሰቡት ገንዘብ ላይ ለግብር ክፍያ በቀጥታ መክፈል የሚችሉበት ሁኔታም ተመቻችቶላቸዋል ተብሏል፡፡
አገልግሎቱን ለማግኘት የሚኒስቴር መ/ቤቱ ደንበኞች ወደ www.mor.gov.et  በመግባትና የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አገልግሎት የሚለውን በመምረጥ፣ አስፈላጊውን ሂደት ሲጨርሱ፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር የሚሰጣቸውን የሰነድ ቁጥር በመጠቀም በቀላሉ ክፍያቸውን  በቴሌብር አፕሊኬሽን መፈፀም እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል፤ ኢትዮ ቴሌኮም የክላውድ፣ የሙዚቃ ስትሪሚንግ እና የቴሌድራይቭ የሞባይል መረጃ ቋት አገልግሎቶችን ባለፈው ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም ከአጋሮች ጋር ስምምነት በመፈፀም በይፋ አስጀምሯል፡፡
በዕለቱ ይፋ ከተደረጉት አገልግሎቶች መካከል ከቨድሊ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ጋር የተፈፀመው ስምምነት አንዱ ሲሆን በዚህ አገልግሎት ደንበኞች በሞባይል ስልኮቻቸው የሚገኙ እንደ ፎቶ፣ ቪዲዮና የመሳሰሉ ከፍ ያለ መጠን ያላቸውን ፋይሎች አስተማማኝ በሆነ የክላውድ መረጃ ቋት በማስቀመጥ በፈለጉ ጊዜ ሁሉ ማግኘትና መጠቀም የሚችሉበት መፍትሄ ነው ተብሏል፡፡
የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የሞባይል ስልኮቻቸው ቢጠፋ ወይም ቢበላሽ ፋይሎቻቸውን ያለ ሃሳብ መልሰው ማግኘት እንደሚያስችላቸው ተነግሯል፡፡
ሌላው ይፋ የተደረገው አገልግሎት ከኩሉ ኔትወርክ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ጋር የተፈፀመው ስምምነት ሲሆን ይህም የእልፍ ሙዚቃ መተግበሪያ ነው፡፡ ይኸው አገልግሎትም ሙዚቃዎችን በመተግበሪያው በመግዛት የሞባይል ዳታ ሳይጠቀሙ በፈለጉ ጊዜ ማዳመጥ እንዲችሉ እንዲሁም በአምስት ቋንቋዎች የሚተላለፍ የቀጥታ ሥርጭት ሬዲዮ ፕሮግራም ያለውና አገልግሎቱ በተመጣጣኝ ዋጋ የቀረበበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የግልና የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ የመረጃ ክምችትና አጠቃቀም እንዲሁም ተዛማች የክላውድ አገልግሎት ፍላጎትን መሰረት በማድረግ፣ እጅግ አስተማማኝ የክላውድ ማዕከላት መሰረተ ልማትንና አስፈላጊ ግብአቶችን ሁሉ በማሟላት ቴሌክላውድ አገልግሎትን በይፋ ለደንበኞቹ ማቅረቡን ያስታወሰው ኢትዮቴሌኮም፣ ከዚህ በተጨማሪም ከዘረጋው የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ጋር በመተባበር የክላውድ ሶሉሽን አገልግሎቶችን በተለያዩ አማራጮች ማቅረቡን ይፋ አድርጓል፡፡  

Read 1481 times