Saturday, 04 February 2023 18:17

በ2022 የተጨዋቾች የዝውውር ገበያ 6.5 ቢሊዮን ዶላር ተንቀሳቅሷል

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበር ፊፋ ያዘጋጀው የ2022 ዓለምአቀፍ የተጨዋቾች ዝውውር ሪፖርት በአዳዲስ ክብረወሰኖች የተሞላ ሲሆን አጠቃላይ በገበያው ላይ ከ6.5 ቢሊዮን በላይ ዶላር መንቀሳቀሱን አመልክቷል።
Global Transfer Report 2022 በሚል የወጣው ሪፖርቱ እንደጠቆመው በወንዶች እግርኳስ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓመት ውስጥ  ከ20ሺ በላይ ተጨዋቾች ዝውውር አድርገዋል። በሴቶች እግርኳስ ዝውውሮች  በ15% እድገት እንዳሳዩ የተገለፀ ሲሆን፤ በአማተር ደረጃ የ200 አገራት ዜግነት ያላቸዉ ከ50ሺ በላይ ተጨዋቾችን ያካተቱ ዝውውሮች ተካሂደዋል፡፡  በ2022 በዓለም ዙርያ በእግርኳስ በሁለቱም ፆታዎች 71,002 የተጨዋቾች ዝውውሮች የተከናወኑ ሲሆን፤ 21,764 ያህሉ  በፕሮፌሽናል ደረጃ እንዲሁም 49,238  በአማተር ደረጃ የሚገኙ ተጨዋቾች ናቸው።
በወንዶች እግርኳስ በ2022 ላይ በተከናወኑ የ17291 ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ዝውውሮች 4770 ክለቦች መገበያየታቸውና ከ183 አገራት በላይ መሳተፋቸው ተጠቅሷል። በኮቪድ ሳቢያ ለ2 የውድድር ዘመናት ቀዝቅዞ የነበረው ገበያ በ2022 መልሶ መነቃቃቱን የጠቀሰው ሪፖርት፤ በኮቪድ 19 ተፅእኖ ውስጥ በ2020 እኤአ 5.63 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በ2021 እኤአ ላይ 4.86 ቢሊዮን ዶላር ግብይት የተከናወነ ሲሆን፤ ከኮቪድ 19 በፊት በ2019 7.35 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በ2018 እኤአ ላይ 6.94 ቢሊዮን ዶላር የዝውውር ገበያው ማንቀሳቀሱ ታውቋል።
በዝውውር ገበያው 2061 ተጨዋቾችን በማሳተፍ ቀዳሚ የሆነችው ብራዚል ስትሆን፤ አርጀንቲና 1004፤ ፈረንሳይ 921፤ እንግሊዝ 848፤ ናይጄርያ 725፤ ኮሎምቢያ 711፤ ስፔን 603፤ ጋና 515፤ ኮቲዲቯር 428 እንዲሁም ሰርቢያ 425 ተጨዋቾችን በማስመዝገብ እስከ 10 ኛ ያለውን ደረጃ አግኝተዋል፡፡
የአፍሪካ አገራት በፕሮፌሽናልና አማተር ደረጃ በሁለቱም ፆታዎች በርካታ ተጫዋቾችን ለገበያው በማቅረብ ከ1 እስከ 10 ባለው ደረጃ ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡ ለዝውውር ገበያው ባቀረበቻቸው ተጨዋቾች ብዛት ከዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ናይጄርያ ስትሆን 725 ተጨዋቾችን በማስመዝገብ ነው፡፡ ጋና 515 እንዲሁም ኮትዲቯር 428 ተጨዋቾችን ለገበያው በማውጣት ተከታታይ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡  የአፍሪካ ክለቦች በዝውውር ገበያው ከ71.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማንቀሳቀሳቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ በግዢ ከ14.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ማድረጋቸውንና በሽያጭ ደግሞ 55 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን አመልክቷል፡፡ የደቡብ አፍሪካ፤ ቱኒዚያ፤ ግብፅ፤ ሊቢያና ሞሮኮ ክለቦች በተጨዋቾች ግዢው ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ፤ ኮትዲቯርና ቱኒዚያ ደግሞ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ አገራት ናቸው፡፡ በ2022 ላይ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን እውቅና በማግኘት በዓለም አቀፉ የዝውውር ገበያ የገቡ የአፍሪካ ተጨዋቾች ብዛት በ70 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡
በተጨዋቾች የዝውውር ገበያው ላይ የእንግሊዝ ክለቦች በወጭ ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ የሆኑ ክለቦች ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ አድርገዋል፡፡ በዓለም አቀፍ የዝውውር ሪፖርቱ እስከ 10ኛ ደረጃ ከፍተኛ ወጭ ከወጣባቸው መካከል 6 ተጨዋቾች ወደ እንግሊዝ የተዛወሩ ናቸው፡፡ ከቦርስያ ዶርቱመንድ ወደ ማንችስተር ሲቲ የተዛወረው ሃርቪንግ ሃላንድ፤ ከፖርቶ ወደ ሊቨርፑል የገባው ሊውስ ዲያዝ እንዲሁም ወደ ማንችስተር ዩናይትድ የገቡት ብራዚላዊያኑ አንቶኒና ካስሜሮ ውድ ዋጋ ከወጣባቸው ዝውውሮች ይጠቀሳሉ፡፡
በዓለም አቀፍ የተጨዋቾች ዝውውር ሪፖርቱ ከደቡብ አሜሪካ ወደ አውሮፓ እንዲሁም ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ከፍተኛ ትስስር መኖሩን አረጋግጧል፡፡ በግዢና ሽያጭ ከፍተኛውን ግብይት በመፈፀም ግንባርቀደም የሆነው አምስቱ የዓለማችን ታላቅ ሊጎች የሚገኙበት የአውሮፓ አህጉር ነው፡፡ በግዢ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ለ11880 ተጨዋቾች  5.9 ቢሊዮን ዶላር፤ የሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ የእግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለለ1304 ተጨዋቾች 259.4 ሚሊዮን ዶላር፤ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለ2584 ተጨዋቾች 192.9 ሚሊዮን ዶላር፤ የኤስያ ኮንፌደሬሽን ለ2532 ተጨዋቾች 148.8 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለ1901 ተጨዋቾች 14.5 ሚሊዮን ዶላር ወጭ አውጥተዋል፡፡ በሽያጭ ደግሞ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ለ11454 ተጨዋቾች  5.55 ቢሊዮን ዶላር፤ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለ3003 ተጨዋቾች 621 ሚሊዮን ዶላር፤ የሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ የእግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለ1142 ተጨዋቾች 194.2 ሚሊዮን ዶላር፤ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለ2698 ተጨዋቾች 71.2 ሚሊዮን እንዲሁም  የኤስያ ኮንፌደሬሽን ለ1885 ተጨዋቾች 59.4 ሚሊዮን ዶላር  ዶላር ገቢ አግኝተዋል፡፡


Read 941 times