Saturday, 21 January 2023 20:29

ኸረ የጭቦ አምላክ ወዴት አለህ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ዘንድሮ ብልጥ ካልሆኑ አስቸጋሪ ነው ይባላል። ችግሩ ምን መሰላችሁ...ብልጥ  የሚለው ቃል ትርጉሙ እንደቀድሞው ነው ወይስ ተለውጧል የሚለው ነው፡፡ አሀ... ልክ ነዋ! ፈረንጅ ‘ወንድ’ እና ‘ሴት’ የሚሉትን ቃላት ፍቺ ለውጦ መዝገበ ቃላት ውስጥ ከቷቸው የለ! የምር ግን... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... መላ ቅጧ የጠፋ ዓለም ሆናላችኋለች፡፡
ስሙኝማ... እስቲ ዛሬ ‘ሲሪየስ፣ ሲሪየስ’ ነገር እንሁንማ! በቀደም ዕለት አንድ የአሜሪካ ፖለቲከኞች የነበሩበት ስብሰባ ነበር፡፡ እናላችሁ... ስብሰባው ሲያልቅም አንድ አፍሪካ አሜሪካዊ ፖለቲከኛ የማጠቃለያ ጸሎት ቢጤ ያደርጋሉ፡፡ ሲጨርሱም “አሜን” አሉና ቀጥሎ ደግሞ ምን ቢሉ ጥሩ ነው... “ዉመን!”አሉ፡፡ ታዲያላችሁ...የዜና ተቋማቱ ሲተነትኑት ለካስ ፖለቲከኛው “አሜን” የሚለው ቃል “ሜን” የሚሉት ፊደላት ስለላበት ወንዶችን ብቻ የሚያመለክት ነው ብለው ነው አሉ፡፡ መከራችንን በላን እኮ!
እዛው አሜሪካ ውስጥ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በኦፊሴል እውቅና ይሰጣቸዋል። ይህ ሁልጊዜም ሲደረግ የቆየ ነው፡፡ ተማሪዎቹ ይህን ማዕረግ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ማመልከቻዎቻቸው ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ዘንድሮ ግን በሆነ የአሜሪካ ግዛት የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውጤቶቹን ከማሳወቅ አዘግይተዋቸዋል፡፡ ለምን ሲባል መጀመሪያ የተማሪዎቹ የጾታ ነገር መስተካከል አለበት በሚል ነው፡፡ ተማሪዎች ጾታቸውን የመምረጥ መብት አላቸው አይነት ነገር ነው፡፡ “ስትሬንጅ!” እንዲል ያልለመደውን ጠጅ አብዝቶ የገለበጠ ፈረንጅ!
ምን አለ መሰላችሁ... ከዚህ በፊት እንዳወራነው በአሁኑ ጊዜ በስነ ፍጥረት መለኪያ “ወንድ ነው፣” የሚባል ሰው ...አለ አይደል... “ወንድ አይደለሁም፣ ሴት ነኝ!” የማለት መብት አለው፡፡ ‘ባዮሎጂ’ ምናምን ነገሯን እርሷት! ፍላጎት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ደግሞላችሁ ብዙ ቦታዎች የትኛውም ‘ወንድ’ ተብሎ የሚታወቅ ሰው “ሴት ነኝ...” ካለ እንደ ሴት አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስገድዱ ህጎች አሉ ነው የሚባለው፡፡ ለምሳሌ ካናዳ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለና በ‘ወንድነቱ’ መዝገብ ላይ ስሙ የሰፈረ ወንጀለኛ፣ “እኔ ሴት ስለሆንኩ በሴቶቹ እስር ቤት ነው መታሰር የምፈልገው ካለ ወደሴቶቹ እስር ቤት ይዘዋወራል፡፡  
ኸረ የጭቦ አምላክ ወዴት አለህ!
ስሙኝማ... ይቺ አሜሪካ የሚሏት ሀገር በቃ አንደኛውን የጭቅጭቅ አገር ሆና ትቅር! ፖለቲከኞቹ አርስ በእርስ ያላቸው መናናቅና የፈለፍሏቸው የሴራ ትርክቶች፣ “እነኚህ ናቸው ዓለምን ካልተቆጣጠርን የሚሉ!” ያሰኛል። አሀ... አንድ አፈ ጉባኤ ለመምረጥ እኮ አስራ አምስት ስብሰባዎች አድርገው በሀሳብ ሲከራከሩ ሳይሆን፤ በነገር ሲወራወሩ የከረሙ ናቸው፡፡
አሁን ደግሞ ባይደን ሆዬ ከፍተኛ ምስጢር የሚል የተጻፈባቸውን ጨምሮ በግል መኖሪያ ቤታቸውና በመኪና ማቆሚያ ጋራዣቸው ውስጥ መውጣት የሌሉባቸው ሰነዶች ተገኙባቸው ተብሎ አማሪካን በአንድ እግሯ ቆማለች! ምን መሰላችሁ... የዛች ሀገር ፖለቲካና ፖለቲከኞች የሚመሩት ከመርሆዎች ይልቅ በግለሰብና በቡድኖች ጥቅሞች  ነው፡፡ ዶናልድ ትረምፕ መኖሪያ መአት የመንግሥት ከፍተኛ ምስጢር ሰነዶች ተገኙ ተብሎ ምድረ የኤፍ.ቢ.አይ ቤታቸውን አመሰቃቀለው፡፡ ‘ሊበራል’ የሚባሉ የሲ.ኤን.ኤን አይነት ሚዲያዎች ሰው ከተፈጠረ ጀምሮ ተደርጎ የማያውቅ ከባድ ወንጀል ሊያስመስሉት ምንም አልቀራቸው፡፡ ትረምፕን ደግሞ እንትን የነካው እንትን አደረጓቸው። አሁን በባይደን ቤትና ጋራዥ ወደ ስድስት ዓመታት ተደብቀው የከረሙ ሰነዶች ሲገኙ ግን ዋነኛ ተከላካያቸው ሆነው ነገሩን መሸፋፈኛ ምክንያቶች እየደረደሩ ነው፡፡ ጭርሱን ነገሩን ወዳዛኛው ወገን ለማላከክ ይሞክራሉ፡፡
በሌላ በኩል ወግ አጥባቂ የሚባሉት እንደፎክስ አይነት ሚዲያዎች ባይደንን የማይሏቸው ነገር፣ የማይወረውሩባቸው ዘለፋ የለም፡፡ መአት የሴራ ፖለቲካ ትርክቶችም እየተዘረዘሩ ነው፡፡ የትረምፕ ጊዜ እኮ በሌላኛው ወገን ላይ ለማላከክ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ የነበሩ እነዚሁ ወግ አጥባቂ ሚዲያዎች፤ አሁን ደግሞ ፕሬዝደንት ባይደንን ብቻ ሳይሆን መላውን የባይደን ቤተሰብ “ወንጀለኛ ቤተሰብ...” እያሏቸው ነው...በልጃቸው በሀንተር ባይደን የተነሳ!
ኸረ የጭቦ አምላክ ወዴት አለህ!
ስሙኝማ...ይቺ በሌላው ላይ የማላከክ ነገር እኮ በማይክሮቺፕ ምናምን የተቀበረችብን ልትመስል ምንም አልቀራት! ...ትናንት ጠብ እርግፍ እያልን “እኔ አፈር ልብላልህ!” ስንል  የነበርን ሰዎች ፍራንካና ወንበር ስናገኝ “አፈርድሜ ብላ!” የምንልበት ፍጥነት በሆነ የክብረ ወሰኖች ሰነድ ላይ ሊካተት ይገባዋል። አሀ... ዝግመተ ለውጥ የሚባለው ነገርስ! (ቂ...ቂ...ቂ...) እናላችሁ በምኑም በምናምኑም ጣት ስንቀሳሰር ስንትና ስንት ባቡር እንዳመለጠን አንድዬ ይወቀው! እርስ በእርሳችን ጣት ተቀሳስረን አለቅን እኮ!
ኸረ የጭቦ አምላክ ወዴት አለህ!
ስሙኛማ መላ ቅጧን እያጣች ስለሆነችው ዓለም ስናወራ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ አንድ አንድሪው ቴት የሚሉት ሀብታም ነውጠኛ ቢጤ አንደልቡ ነገር አለላችሁ፡፡ ኪክ ቦክሲንግ በሚሉት ድብድብ የወጣለት ተደባዳቢ ነው...እፍ ያለ ሀብታም፡፡ እናላችሁ...በሆኑ ቪዲዮዎቹ  ላይ በአሁኑ ጊዜ ወደ ሠላሳ ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ሀብት እንዳከማቸ፤ ውድ የሚባሉ መኪኖች፣ እንዲሁም የግል አውሮፕላን እንዳሉት ሲፎክር ነበር፡፡  
ታዲያላችሁ... ቴት በቪዲዮዎቹ ወጣቶችን በጣም የሚያነሳሱ ትረካዎች ያሰማል፡፡ እነኚህ ትረካዎች በአብዛኛው ነውጥ የሚያስነሱ አይነቶች ሳይሆኑ ወጣቶች በቀላሉ ሀብታም መሆን እንደሚችሉ የሚያበረታቱ ኛቸው። በእርግጥ ሀብታም ሊሆኑ የሚችሉባቸው ከሚላቸው ዘዴዎች አከራካሪ የሆኑ አሉበት፡፡ እንዲህም ሆኖ በዓለም ዙሪያ ብዙ ሚሊዮኖች ወጣቶች ይከታተሉታል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውን ተቆጣጥሮት ነው የከረመው፡፡ እንደውም በ2022 ጉግል ላይ ከነበሩ የፍለጋ ጥያቄዎች በአንደኛ ደረጃ የነበረው የእሱ ስም ነበር፡፡
እናላችሁ... በቀደም እለት የሩማንያ ፖሊሶች እሱንና ወንድሙን እስር ቤት ይከቷቸዋል፡፡ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሴቶችን በሴተኛ አዳሪነት እየመለመሉ በመጠቀምና በመሳሰሉት  ነገሮች ነው የተከሰሱት ይባላል፡፡ ከመታሰሩ በፊት ግን በሀሰት ክሶች ይይዙኛል የሚሉ ነገሮች ሲናገር ነበር፡፡ እና ምን መሰላችሁ... ስብከቱን ሀብታሞቹና ባለስልጣናት አልወደዱለትም ነበር፡፡ ሀብታሞችን አብዛኞቹ ገንዘባቸውን በህገወጥ መንገድ የሰበሰቡ ናቸው ይላቸዋል፡፡ ባለስልጣናቱን ደግሞ የሀብታሞቹ አገልጋዮች ነገር ነው የሚያደርጋቸው፡፡ እሱ እንደሚለው ሀብታሞች እንደፈለጉ ሲሆኑ ምስኪኑ ህዝብ ብቻ ነው የሚሰቃየው ባይ ነው፡፡
የኮቪድ ጊዜ ከቤት ያለመውጣት ፖሊሲን ያነሳል፡፡ እሱና ሀብታሞቹ ግን እንደልባቸው ይሆኑ እንደነበር ነው የሚናገረው፡፡ ሰዉ ሁሉ መንቀሳቀስ ሲከለከል እኛ በግል ጄቶቻችን የፈለግንበት መሄድና እንደፈለግነው መሆን እንችል ነበር ነው ያለው፡፡ ለዚህም ነው ወጣቶቹን “ተሟሙታችሁ ሀብታም ሁኑ” የሚላቸው...እንደልብ ለመሆን፡፡ የእሱ እምነት “ዓለም የሀብታሞች ነች!” የሚል አይነት ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ በኤኮኖሚ አቅም ታች ያሉት በመቶኛ ሲሰላ ከሀብታሞች በላይ ታክስ ይከፍላሉ ይላል፡፡ ለዚህ ምክንያት ሲያስቀምጥ ምን ይላል መሰላችሁ... የታክስ ህጉን የሚያወጡት እነሱ ሀብታሞቹ ስለሆኑ ነው ባይ ነው፡፡ እንዲህ አይነት የድፍረት አነጋገሮች ለሀብታሞቹ ብቻ ሳይሆን ለባለስልጣናቱ የሚመቹ አልሆኑም፡፡
ስሙኝማ... አንዲት የተናገራት አሪፍ ነገር ምን መሰላቻችሁ... “ሀብታሞች ደስተኛ አይደሉም ይሏችኋል፡፡ አትሞኙ ደስተኞች ናቸው፡፡” በነገራችን ላይ ይቺ ነገር እኮ እኛ ዘንድ የተለመደች ነች፡፡
“ስማ እንትና ቅልጥ ያለ ሀብታም ሆኖ የሠራውን ጂ ፕላስ ፎር ቤት ብታየው በቃ አፍህን ከፍተህ ነው የምትቀረው!”
“እባክህ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ያስመስላሉ እንጂ ደስተኞች አይደሉም!”
እንዴት! እንዴት! በየትኛው ‘ካልኩሌሽን!’
ኸረ የጭቦ አምላክ ወዴት አለህ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1515 times