Print this page
Saturday, 21 January 2023 20:28

የእኛ ሰው በኳታር

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

 የ”ሀበሻዊ ትሬዲንግ” መሥራችና ባለቤት - ዮርዳኖስ ፀጋው
              


       እንደ መግቢያ
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ  ዋዜማ ላይ በኳታር መዲና ዶሃ በሚገኘው ኮሪንሽ ጎዳና ላይ፣ ልዩ የባህልና ኪነጥበብ ፌስቲቫል ተካሂዶ ነበር፡፡ በኳታር የሚገኘውን የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ባሰባሰበው በዚህ ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን በመወከል  ባህልንና አገርን የሚያስተዋውቅ ዝግጅት ያቀረበችው ብርቱ እንስት ዮርዳኖስ ፀጋው ትባላለች፡፡ በኳታር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በይበልጥ የሚታወቀው የ”ሀበሻዊ ትሬዲንግ” መሥራችና ባለቤት ናት። ድርጅቷ የባህል አልባሳትን በትዕዛዝ ሰርቶ በማቅረብ ይታወቃል፡፡ የቆዳ ውጤቶችን፣ የውበት መጠበቂያዎችንና ሌሎች አገር በቀል ምርቶችንም ለኳታር ገበያ ያቀርባል፡፡ ዮርዳኖስ ከቢዝነስ ሥራዋ ባሻገር አገርንና ባህልን ለማስተዋወቅ በምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያውያን  ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታንና አድናቆትን  አትርፋለች፡፡ አንዳንዶች “የባህል አምባሳደር” እያሉም ይጠሯታል።
ዮርዳኖስ ከንግድ ሥራዋ ባሻገር በአሁኑ ወቅት በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ተቋም ውስጥ ተቀጥራ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ወደፊት በአገሯ ላይ ብዙ የመሥራት ሐሳብና እቅድ አላት። በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀች የልብስ ዲዛይነር  መሆን ህልሟ ነው፡፡
ሁለት ልጆች ያሏት ሲሆን የ9  ዓመቱ ኤግላስያስና የ8 ዓመቱ ጆኤል ናቸው። ጆኤል ኳታር ውስጥ የሚገኘው ትልቅ ክለብ አልሳድ አካዳሚ ገብቷል። ወደፊት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ነው ህልሙ።  
ኑሮ በኳታር - አጀማመሬ  
ትውልድና እድገቴ በአዲስ አበባ ቄራ በሚባለው ሰፈር ነው። ወደ ኳታር የገባሁት በ2008 ዓ.ም የዛሬ 15 ዓመት ነው። ኳታር እንደመጣሁ ከዝቅተኛ ሥራ ነው የጀመርኩት። በወቅቱ ብቻዬን ስለነበርኩ ሆድ እየባሰኝ አለቅስ ነበር፤ ወደ አገር ቤት ለመመለስ ሁሉ ሃሳብ ነበረኝ፡፡ ዶሐ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት የተለየች ነበረች፡፡ ከጅምሩ የቋንቋ ችግር ነበር። እንግሊዝኛ የሚያወራ አልነበረም፤ እኛም በደንብ አንችልም ነበር፡፡ በምልክት ቋንቋ ነበር የምንግባባው፡፡ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ በረዳት አገልግሎት ዘርፍ እሰራ ነበር፤ አስተማሪዎችን በማገዝ፡፡ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ እንደምንም አረብኛ ቻልኩ፤ ለመግባቢያ ያህል፡፡ ቋንቋውን ሳዳብር በየሱቁ በትንሽ ደሞዝ እየተቀጠርኩ መሥራት  ጀመርኩ፡፡ በአንድ ወቅት አሰሪዬ ኢራናዊ ነበር፡፡ በሱቁ ውስጥ እየሰራሁ ባሳየሁት ቅልጥፍና፣ በአንድ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ውስጥ የመቀጠር ዕድል አገኘሁ፡፡ ጎን ለጎን በአንድ የስፓኒሽ ኩባንያ ውስጥም እሰራ ነበር፡፡ ለሰባት ዓመታት በስቶር ማናጀርነት ሰርቻለሁ፡፡  
የራስን ህልም እውን የማድረግ ጉዞ
ኮቪድ-19 በተከሰተ ጊዜ ኳታር ውስጥ ሥራ አልነበረም። ከሌሎች ሰራተኞች ጋር ከስራ ተቀነስኩ፡፡ ያን ጊዜ ነው በዶሃ ምን ያልተሰራ ነገር አለ ብዬ ማሰብ የጀመርኩት። ከልጅነቴ አንስቶ ባህሌንና ፋሽን እወድ ነበር። በአዕምሮዬ ይመላለስ የነበረውም ይህን ፍቅሬን ወደ ቢዝነስ መለወጥ የሚል ሃሳብ ነው። ስለዚህም መጀመርያ ያደረግሁት የተለያዩ የባህል አልባሳትን በኦንላይን አስተዋውቄ ከኢትዮጵያ በማስመጣት መሸጥ ነበር። በኮቪድ ሳቢያ ገበያ ወጥቶ መግዛት ስለማይቻል፣ ይህን የግብይት መንገድ ስጀምር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነትን  አገኘልኝ፡፡
በመጀመሪያ “ኢትዮ ኳታር ሀበሻ” የሚል ገፅ በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ከፍቼ  ባህላዊ አልባሳቶቻችንን በስፋት አስተዋወቅሁ። በኮቪድ ምክንያት ገበያ ሁሉ ዝግ ስለነበር፣ ለብዙዎች ጥሩ አማራጭ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ የባህል አልባሳት ከሚሰሩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ፈጥሬ የባህል አልባሳትን በቀጥታ ወደ ኳታር በማስገባትና በትዕዛዝ እያሰራሁ በማስመጣት ማቅረብ ጀመርኩ፡፡ የባህል አልባሳትን በቀጥታ መግዛት የሚፈልጉና በትዕዛዝ የሚያሰሩ ብዙ ደንበኞችን አፈራሁ። በትዕዛዝ ማሰራት የሚፈልጉትን ለማስተናገድ ኳታር ውስጥ በያሉበት እየዞርኩ የልብስ ልኬታቸውን እሰራለሁ። ከዚያም ከአዲስ አበባ አሰርቼ በማስመጣት በያሉበት አደርስላቸዋለሁ።  
 አሁን “ሀበሻዊ ትሬዲንግ” ብዬ የምሰራበትን ሱቅ ከመክፈቴ በፊት ንግዱን የምሰራው በገስት ሀውስ እንደ ሾው ሩም አዘጋጅቼ ነበር፡፡ በአካል መጥተው የሚሆናቸውን የባህል አልባሳት የሚገዙና ትዕዛዝ የሚሰጡን ደንበኞችም ነበሩ፡፡ ከጊዜ በኋላ እዚያው ኳታር ውስጥ የተለያዩ የፋሽን ጨርቆችን እያስመጣሁ በልዩ ፋሽን ዲዛይን እያደረግሁ በመሥራት  መሸጥ ቀጠልኩ፡፡ የፋሽን ጨርቆቹን ከህንድ እያስመጣሁ በሱቃችን የምንሰራቸው አልባሳት  ተወዳጅነትን  አትርፈዋል፡፡ ከኢትዮጵያውያን ባሻገር ኤርትራውያን ፤ኳታራውያን ፤ሱዳኖችና በዶሀ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ደንበኞቻችን ናቸው። የሐበሻ ቀሚሶች ከ300 ሪያል እስከ 1200 ሪያል እንሸጣለን። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢትዮጵያ የምናስገባቸው የቆዳ ጫማዎችና ምርቶች ተፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል፡፡
እህቶቻችንን በባህላቸው ማስዋብ
በአረቡ ዓለምና በኳታር የሚሰሩና የሚኖሩ  እህቶቻችን ማህበራዊ ሚዲያዎችን በእጅጉ ይጠቀማሉ፡፡ እኛ የባህል አልባሳቱን በኦንላይን ስናስተዋውቅ የሚወዱትን የሚፈልጉትን ነገር ይመለከታሉ፡፡ ይሁንና በሥራቸው ፀባይ የተነሳ እንዲሰፋላቸው ለማዘዝ ወይም ከቤት ወጥቶ ለመለካት ወይም ለመግዛት ይቸገራሉ፡፡ ያላቸው ምርጫ በቀጥታ  ከእኔ ጋር ግንኙነት መፍጠር ነው፡፡ ብዙዎቹ የሙሉ ጊዜ ሰራተኞች ስለሆኑ ወደ ገበያ የሚወጡበት እድል የላቸውም፡፡ አሰሪዎቻቸውም አይፈቅዱላቸውም፡፡ ያሉበት ድረስ እየሄድኩ ለልብሳቸው ልኬታቸውን እሰራለሁ፡፡ እኔ ህጋዊ ፈቃድ  ኖሮኝ የምሰራ ቢሆንም የልብስ ልኬቱን የምንሰራበት መንገድ የሚያሰቅቅ ነው፡፡ አሰሪዎቻቸው ሳያውቁትና ሳይፈቅዱት የምናደርገው ስለሆነ መስጋታችን አይቀርም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ልብሱ ተሰፍቶ ከደረሰ በኋላም ያሉበት ድረስ እንወስድላቸዋለን። በዚህ በጣም ይደሰታሉ። በአሁኑ ወቅት  የምንሰራቸው ፋሽን ቀሚሶች ተወዳጅ ሆነዋል፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ያለው የባህል አልባሳትን ብዙዎች ይወዱታል፡፡ የየራሳቸውን ብሔረሰብ አልባሳትም ያሰሩናል። ከኛ የገዟቸውን የባህል አልባሳት በአብዛኛው ከቤት ባይወጡም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ  ይለብሱታል፡፡
የባህል አልባሳቱ ሱቅ በሚዘር
“ኢትዮ ኳታር ሐበሻ” ብዬ ስራውን ስጀምረው በኳታር ግቢ ሀበሻን ይገልጻል በሚል ነው፡፡ ኦንላይን በምንሰራበት ወቅት ብዙዎች “ወደዚህ ነይልኝ፤ ወደዚህ ላኪልኝ” እያሉ ጥያቄ አበዙ፡፡ ለምን ለሁሉም አልቀርብም ብዬ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደሚገኙበት የዶሐ ክፍል ማለትም ሚዘር በመግባት ሱቄን ከፈትኩ፡፡ ይህን ሱቅ ባገኘሁ ሰዓት አዳዲስ ለውጦች ተፈጠሩ፡፡ በኳታር ንግድ ፍቃድ በምታወጣበት ወቅት የአገሪቱ መንግስት ነው ስያሜውን የሚፈቅድልህ፡፡ ሦስት አማራጮችን ይዘህ ታመለክታለህ፡፡ ከዚያም ስያሜውን ይመርጡልሃል፡፡ “ኢትዮ ኳታር ሃበሻ” የሚለው ስያሜ በኢንተርኔት ብዙ ቢታወቅም ኳታር የሚለው ስላለበት ፈቃድ አላገኘም፡፡ ሌሎቹ አማራጭ ስያሜዎች “ሀበሻዊ ትሬዲንግ” እና “ዮርዲ ትሬዲንግ” የሚሉ ነበሩ፡፡ ሃበሻዊ ተመረጠ፡፡ በጣም ነበር ደስ ያለኝ፡፡ በአጠቃላይ ሃበሻን የሚገልፅ ስያሜ ይመስለኛል።  ኢትዮጵያን ኤርትራን ሁሉንም ያዋስናል፡፡  “ኢትዮ ኳታር ሃበሻ” የሚለው ስያሜ ፍቃድ ቢያገኝ ጥሩ ነበር፤ በኦንላይን ብዙ ደንበኞችን ስላፈራንበት፡፡
በሱቃችን  የባህል አልባሳት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተፈላጊ ነገሮችም ይገኛሉ፡፡  በፊት የስፖርት ማልያዎች  ትጥቆች ቤት ለቤት የምናቀርብበት አሰራር ነበረን፡፡ ዛሬ የስፖርት ማልያ በጅምላ አስመጣለሁ፡፡ እዚህ አገር ውስጥ ያሉ ታላላቅ ደጋፊዎች በኢንተርኔት አዘው ይገዙኛል፡፡ የቡናን፣ የጊዮርጊስንና የሌሎችንም ክለቦች ማልያዎች በየቤቱ እናደርሳለን፡፡ የብሔራዊ ቡድንና የአትሌቲክስ ቡድን ማልያዎችም አሉን፡፡ በ22ኛው የዓለም ዋንጫ የብራዚል የአርጀንቲና፣ የቤልጅየም፣ የሴኔጋልና የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ማልያዎችን በደንብ ቸብችበናል፡፡ ከቡና ክለብ ጋር በቀጥታ ጥያቄ አቅርበን ነው ማልያዎችን የምናገኘው፡፡ በደንበኞች ፍላጎት ላይ ተመስርተን ያስፋፋነው ነገር ነው፡፡ ከየደንበኛው ለሚቀርብ ጥያቄ ትኩረት ስለምሰጥ፣ ብዙ ነገር እየጨመርን እየሰፋ ይሄዳል፡፡
“ሀበሻዊ ትሬዲንግ”- ባህልን ማስተዋወቅ
በኳታር ውስጥ በየጊዜው በሚካሄዱ የተለያዩ ባዛሮች እንሳተፋለን፡፡ ለምሳሌ በ2021 ላይ ዶሓ ውስጥ በሚገኘው ካታራ የባህል መንደር ያደረግነውን ተሳትፎ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በባህልና እደጥበብ ፌስቲቫሉ ላይ  ከ36 በላይ  አገራት ተሳትፈዋል፡፡  ኢትዮጵያን ወክለን ባደረግነው ተሳትፎ በምርጥ ስራችን  የስኬት ሰርተፍኬት ተቀብያለሁ። በዓለም አቀፍ ፌስቲቫሉ ላይ የባህል አልባሳቱን ለማስተዋወቅ ጥጥ ፈተላውን፤ መባዘቱን ሁሉን ነገር አያይዘን አሳይተናል፡፡ የቡና ሥነስርዓት በባህላዊ መንገድ አዘጋጅተን ከማጠጣታችንም በላይ ስለ አማርኛ  ፊደሎች  ያስተዋወቅንበትን  ትርኢትም  አቅርበናል።

Read 1476 times