Saturday, 21 January 2023 20:26

ሰምና ወርቅ “አንቺ እንዴትነሽ” የተሰኘ የጥበብ መሰናዶ በዱባይ ያካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

ሰምና ወርቅ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት የንጋት ለኢትዮጵያ ፕሮጀክት አካል የሆነውን “አንቺ እንዴት ነሽ” የተሰኘ የኪነ ጥበብ መሰናዶ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዋና ከተማ ዱባይ ከየካቲት 11-12 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚያካሂድ ተገለፀ፡፡ የዚህ መሰናዶ አላማ ከኢትዮጵያ ወደ አረብ ሀገራት የሚሄዱ እህቶቻችን ላባቸውን እያፈሰሱ የሚያገኙትን ገንዘብ ለቤተሰብና ለፍቅረኛ በመላክ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ያለ ጥሪት እየቀሩ፣ ወንዶች (ፍቅረኞቻቸው) እነሱ በሚልኩት ገንዘብ፣ ሌላ አግብተው ወልደው እየጠበቋቸው ለስነ ልቦናና ለኢኮኖሚያዊ ጫና ሲዳረጉ መቆየታቸውን መነሻ በማድረግ አሁንስ ሁኔታዎች በዚህ መቀጠል አለባቸው ወይ?
ከዚህ በኋላ ምን ታስቢያለሽ፣ ለቤተሰብሽ ከምትልኪው በትንሹ አንድ አራተኛውን መቆጠብና ወደ ሀገርሽ ስትገቢ የራስሽን ቢዝነስ ለመጀመር የሚያበቃ ሀብት መቆጠብ የለብሽም ወይ? የሚሉና መሰል በአረብ አገራት ላይ ያሉ እህቶችን የማንቃትና የማስገንዘብ ዓላማ የሰነቀ ስለመሆኑ የሰምና ወርቅ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት  ባለቤትና የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው አለሙ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
“ንጋት ለኢትዮጵያ” የተሰኘው የሰምና ወርቅ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ንጋትና ተስፋ እንዲኖር በተለያዩ መድረኮች መፍትሄ አፍላቂ መርሀ ግብሮችን ማዘጋጀት እንደሆነ የገለፀው ጋዜጠኛ ጌታቸው፣ ይህም የዱባይ ፕሮግራም በዱባይ ከኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ስለመሆኑ ገልፆ በቀጣይም በዱባይና በሌሎች አለማት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲዎች ጋር በጋራ እንደሚዘጋጅ አብራርቷል፡፡ የካቲት 11 እና 12 ቀን በዱባይ በሚዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር ላይ ዶ/ር ወዳጂነህ መሃረነ፣ ገጣሚ ተስፋሁን ከበደ (ፍራሽ አዳሽ) ገጣሚ ኤልያስ ሽታሁን፣ ገጣሚ ህሊና ደሳለኝና ተዋናይና ገጣሚ አማኑኤል ሀብታሙ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን በዱባይ ነዋሪ የሆነችውና ከሰምና ወርቅ ጋር በመተባበር መርሃ ግብሩን የምታዘጋጀው ቤተልሄም አሰፋ ስትሆን መድረክ በመምራትም ሚና ይኖራታል ተብሏል፡፡
ሰምና ወርቅ ከዱባይ መልስ የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም በጎንደር ከተማ የኪነ ጥበብ መሰናዶውን እንደሚያካሂድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2189 times