Saturday, 21 January 2023 20:23

ለ44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(2 votes)

 በአዳዲስ ፈጠራዎች የተሞላ አጓጊ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና እናካሂዳለን፤ የመወዳሪያው ሜዳ መቼምቢሆን የማይረሳና      አውስትራሊያን በልዩ መንገድ የሚያስተዋወውቅ ይሆናል።"
         ልዩ ቃለ ምልልስ ከአውስትራሊያ (የWXC BATHURST 23 ዋና ስራ አስፈፃሚ ሪቻርድ ዌልሽ)

             • 4 ሳምንታት ቀርተዋል፤ አዲስ አድማስ ተጋብዟል
             • የኬንያው ፖል ቴርጋት የሻምፒዮናው አምባሳደር ሆኗል


     ለ44ኛው የዓለም  አገር አቋራጭ ሻምፒዮና 4 ሳምንታት ቀርተዋል። በተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ላይ በመገኘት ሰፊ ሽፋን የሚሰጠው አዲስ አድማስ የዓለም  አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን ላይ እንዲዘግብ በዓለም አትሌክስ ማህበርና በአዘጋጅ ኮሚቴው ተጋብዟል።
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን የምታስተናግደው በደቡብ ዌልስ አውስትራሊያ፤  የምትገኘው ባቱረስት ከተማ ናት። በኦሺኒያ ክፍለ ዓለም የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ሲካሄድ ከ45 ዓመታት በኋላ  የመጀመሪያው ነው። በ1988 እ.ኤ.አ ላይ በኒውዝላንድ የምትገኘው የደሴት ከተማ ኦክላንድ  የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን አስተናግዳለች።
በ2023 እ.ኤ.አ  ሻምፒዮናውን የምታዘጋጀው ባቱረስት ከአውስትራሊያ ዋና ከተማ ሲዲኒ 120 ማይሎች ርቀት ላይ ትገኛለች። ወርቃማዋ ምድር የምትባለው ባቱረስት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነው  የሞተር ሽቅድምድም መወዳደሪያ “ማወንቴን ፓናሮማ ሰርኪውት” ይገኝባታል። 6178 ኪ.ሜ የሚረዝመው የውድድር ስፍራው ለዓለም ሻምፒዮናው ምቹ እንደሚሆን ተረጋግጧል።
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ከ1 ዓመት በፊት ከአውስትራሊያ በኋላ ቀጣዮቹን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች የሚያዘጋጁ አገራትን አስታውቋል። በ2024 እ.ኤ.አ ላይ 45ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የአውሮፓዋ ክሮሽያ ስታስተናግድ፤ በ2026 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ 46ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን አሜሪካ ታዘጋጃለች።
በተያያዘ ዜና የኬኒያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት የሆነው አንጋፋው አትሌት ፖልቴርጋት የውድድሩ አምባሳደር ሆኖ ተሹሟል። ፖልቴርጋት ከዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የምንጊዜም ምርጥ አትሌቶች አንዱ ሲሆን ከ1995-1999 ድረስ ለ5 ጊዜ በረዥም ርቀት የዓለም ሻምፒዮና ሆኗል። የዓለም አገር አቋራጭ ስኬታማነቱ በኦሎምፒክ፣ የዓለም ሻምፒዮና ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላገኛቸው ውጤቶች መሰረቱን ጥሎበታል። “አገር አቋራጭ ሁልጊዜም በአትሌቲክስ ዘመኔ ልዩ ውድድሬ ነው” በማለት ፖልቴርጋት ይናገራል። በሩጫ ዘመኑ እውቅና ልምድ ያገኘበትና ስለህይወት የተማረበት መሆኑን ገልጿል።
ኢትዮጵያ ባለፉት 43 ዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች  275 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች። በ2019 እ.ኤ.አ ላይ በዴንማርክ አርሁስ የተካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን በ5 የወርቅ በ3 የብርና በ3 ነሐስ በአጠቃላይ በ11 ሜዳልያዎች ከዓለም አንደኛ ደረጃ አግኝቷል።
   ባቱረስት ለዓለም ሻምፒዮና ያደረገችው ዝግጅት ምን ይመስላል?
ፌብሩዋሪ 18 ላይ ዓለም አቀፉን ውድድር ለማዘጋጀት በጉጉት እየጠበቅን ነው። በ2021 እና በ2022 ውድድሩ ለ2 ጊዜያት ተሸጋሽጎብናል። ከዚያም በኋላ በደንብ አቅደንበት እጅግ በጣም አስደናቂ ተሰጥኦ ባላቸው ፕሮፌሽናል ባለሙያዎች በተሰባሰቡበት ቡድን እየሰራን ዝግጅታችንን አጠናቀናል። አውስትራልያ ግዙፍ ዓለም ዓቀፍ ዝግጅቶችን በስኬት የማስተናገድ ባህል አላት። ባቱረስት በምናዘጋጀው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በእርግጠኝነት ይህን ስኬት መቀጠል እንፈልጋለን። ሻምፒዮናው የሚካሄደው በኒው ሳውዝ ዌልስ ተወዳጅ የአገራችን ክፍል ላይ ነው። በሞተር ስፖርት አስደናቂ ታሪክ ያለውና በመላው ዓለም የሚታወቅ ነው። ዋናው ዓላማችን ይህ የአገራችን ክፍል በአገር አቋራጭ ሩጫ አፍቃሪዎች ተመራጭ እንዲሆን ነው።
ሻምፒዮናው የሚካሄድበትን ስፍራ ብትገልጽልን?
ማውንት ፓናሮማ በባቱረስ የሚገኝና እጅግ በጣም ታዋቂ የሞተር ስፖርት መወዳደሪያ ስፍራ ነው። አውስትራልያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያስተዋውቁ አብይ መሰረተ ልማቶች አንዱ ነው። በሞተር ስፖርት መወዳደሪያ ጎዳናውን ለአገር አቋራጭ እንዲመች አድርገን አዘጋጅተነዋል። መልከዓ ምድሩ በተፈጥሮ ዕፀዋት የተሞላ ነው። ከ100 በላይ ካንጋሮዎች ይገኙበታል። አብዛኛው የመሮጫ ሜዳ በሳር የተሸፈነ ነው። አቀበታማና አስቸጋሪ መዞሪያ ስፍራዎችም ተፈጥረውለታል። አውስትራሊያን የሚያስተዋውቁ ነገሮች ከውድድሩ ጋር አብረው እንዲቀርቡ እናደርጋለን። ቢላቦንግና ቡሜራንግ ለዓለም እናሳያቸዋለን። የቦንዲ ባህር ዳርቻ፤ ታዋቂው የአውስትራሊያ ጫካና የወይን እርሻም የውድድሩ አካል ናቸው።
ምን ያህል ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ለሻምፒዮናው ጋብዛችኋል?
በሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ ዓለም አቀፍ ሚዲያው ያሳየው ፍላጎት ከጠበቅነው በላይ ሆኗል። በመላው ዓለም ድንበሮች ሁሉ ክፍት መሆናቸው ምስጋና ይግባውና። ከአውስትራሊያ እንኳን ከ50 በላይ የሚዲያ ተቋማት ሻምፒዮናውን ለመዘገብ አመልክተዋል። የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በሚያገኘው የቴሌቪዥን ስርጭት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚገመት ተመልካች እንደሚያገን ተስፋ አድርገናል።
በአውስትራልያ ያለውን የዓለም አገር አቋራጭ ሩጫ ባህል እንዴት ትመለከተዋለህ?
አውስትራሊያ በአገር አቋራጭ ውጤት ያላትና የምትኮራ ሀገር ናት። በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ከ1970ዎቹ ጀምሮ ተሳት ስናደርግ ቆይተናል። በብዙዎቹ ሻምፒዮናዎች እስከ 10 ባለው ደረጃ እንገባለን። በቡድን ውጤቶችም የሜዳሊያ ሽልማት አግኝተናል። ትልቁ ውጤት ግን በ2004 እ.ኤ.አ ላይ ቤኒታ ዊልያምስ በአዋቂ ሴቶች ውድድር ላይ የወርቅ ሜዳሊያ መጎናጸፏ ነው።
ፖል ቴርጋት የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው አምባሳደር ሆኖ ስለመሾሙ ምን አስተያየት አለህ?
ፖል ቴርጋት  እጅግ ዝነኛ የስፖርቱ ባለታሪክ ነው። አውስትራሊያ ደግሞ እጅግ ይታወቃል። በሲድኒ ኦሎምፒክ በ10,000 ሜትር ላይ በተካሄደው አስደናቂ ውድድር ነው። በዚያን ወቅት እስከመጨረሻው ዙር እየመራ ቆይቶ የእናንተው ኃይሌ ገ/ስላሴ በልዩ ብልሃት ቀድሞት በመግባት አሸንፎታል። ይህን አስደናቂ ውድድር በርካታ አውስትራሊያውያን ተደስተውበታል። ከዚያ ኦሎምፒክ በኋላ የዓለም የማራቶን ሪከርድ ማስመዝገብ ችሏል። በዓለም አገር አቋራጭ ውጤቱም 5 የወርቅ ሜዲያሊያዎችን እዳገኘ ይታወቃል። ከዓለም አትሌቲክስ የምንጊዜም ምርጦች አንዱ ነው። በአዘጋጀነው ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ ወደ አውስትራሊያ ደግሞ በመምጣቱ እጅግ ተደስተናል።
ኢትዮጵያ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ስኬታማ ከሆኑ አገራት ግንባር ቀደሟ ናት። ሻምፒዮናውን የማስተናገድ እድል ግን አላገኘችም። ይህን ለማሳካት ምን መሰራት አለበት?
ለበርካታ አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የረጅም ርቀት ሩጫ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቧ ይታወቃል። በትራክ፣ በጎዳና ላይ ሩጫና በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ታላላቅ ስም ያላቸውን ስኬታማ አትሌቶች አፍርታለች። ዓለም አቀፍ ውድድርን ለማዘጋጀት በትልልቅ የውድድር መስተንግዶዎች ልምድ ያስፈልጋል። ውጤትና ተሳትፎ ያን ያህል የሚያስፈልግ አይሆንም። በእኛ በኩል የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን ያዘጋጀው ቦርድ፤ የአስተዳደር ቡድን፤ የስፖርቱ ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች ባቱረስት 23 WXC BATHURST 23 ለማስተባበር ከፍተኛ ልምድ የያዙ ናቸው። ብዙዎቻችን በ2000 እ.ኤ.አ በሲድኒ ኦሎምፒክ፤ በ2001 በዓለም አትሌቲክስ ፍጻሜ፤ በ2006 በሜልቦርን ኮመንዌልዝ ጌም እንዲሁም በ2018 በጎልድ ኮስት ኮመን ዌልዝ ጌም በመስራት ከፍተኛ ልምድ አካብተናል። በሌሎችም ትልልቅ ውድድሮችና ዝግጅቶች ጥሩ ልምድ አለን። በአጠቃላይ የእኛ አስተዳደር ቡድን የግዙፍ ዓለም አቀፍ ዝግጅት ልምዱ ከ100 ዓመታት በላይ ይሆናል። የኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት አስተዳደር ለሻምፒዮናው በቂ የሚሆነውን በጀት በመስጠት ከፍተኛ እገዛ አድርጎልናል። የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ብቻ ሳይሆን ሌሎች ትልልቅ ውድድሮችንም የማስተናገድ ብቃት አለን።
ኢትዮጵያ ያለጥርጥር በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከፍተኛ ውጤትና እውቀት አላት። ለመሰል ውድድር የሚመች የመወዳደሪያ ስፍራና የተሟላ መሰረተ ልማት አዘጋጅቶ መጠየቁ ግድ ይላል። ከሚመለከታቸው ባድርሻ አካላትና ከመንግስት ኢንቨስትመንት ድጋፍ ያስፈልጋል። ይህን ሁሉ አስተባብሮ በተሟላ እቅድ እና አቅም መስራት ይጠይቃል። በተገቢው ጊዜና አጋጣሚ ከዓለም አትሌቲክስ ማህበር ጋር መስራትና ወደፊት ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት በሚቀርብ እቅድ ላይ ምክክር ማድረግ ይገባል።  በ2017 በኡጋንዳ እንዲሁም በ2007 ኬንያ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን ማዘጋጀታቸው አፍሪካ ያላትን ብቁነት ያመለክታል።
ከ44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ምን ትጠብቃለህ?
በእርግጠኝነት የምንጠብቀው በአዳዲስ ፈጠራዎች የተሞላና አጓጊ  የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ማካሄድ ነው። የመወዳሪያው ሜዳ  መቼም ቢሆን የማይረሳና አውስትራሊያን በልዩ መንገድ የሚያስተዋወውቅ ይሆናል። አውስትራሊያውያን ለአትሌቲክስ ስፖርት ልዩ ፍቅር ስላላቸው ሻምፒዮናውን በሺዎች ሆነው ስፍራው ላይ በመገኘት ደማቅ ድባብ ይፈጥሩለታል።



Read 850 times