Saturday, 21 January 2023 20:18

የበላችው አቅሯታል፣ በላይ በላይ ያጎርሳታል!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 ከሥራ መሰናበት ከባድ አይደለም፡፡ ከአንድ ሥራ ወጥቶ ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ይገባላ! ከሰው መሰናበትም አይገድም- ከሌላ ሰው ጋር መገናኘት፣መዋል ማደር ይቻላላ፡፡ ከሰፈር መሰናበትም ቀላል ነው - ሌላ ሰፈር ይኬዳላ፡፡ ችግር የሚመጣው ከሀገር ሲሰናበቱ ነው!
እርግጥ ከሁሉ ክፉ ከህይወት መሰናበት ነው፡፡ “እገሌ ህይወት በቃኝ ብሎ ስንብት ጠየቀ” አይባልማ፡፡ አንዱ ምክንያት ተጠያቂ አለመኖሩ ነው፡፡ ለቃቂው ማንን ነው መልቀቂያ ስጠኝ የሚለው? ሁለተኛ ከህይወት ቀጥሎ ሌላ መስሪያ ቤት የለምና፣ የት ይገባል? አለስ ቢባል እንዴት ነው የሚያመለክተው? በውድድር የምንገባበት እንዳይባል ፈተናው የት ነው የሚሰጠው? ማነው ፈታኙ? ት/ሚኒስቴር እንዳይባል እራሱ መች ተፈትኖ ገባና? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ባለሥልጣኑ ሁሉ ተሹዋሚ ነዋ፡፡ ያውም ሹሙ ሁሉ ባፍ አመሉ፣ ሹመት ሺ-ሞት ነው እያለ እየኮነነ ከሹመት አለመሸሹ እያስገረመን! እንዲያውም ሥነ-ተረቱ የሚለን እነሆ፡- አንድ ልዑል አባቱ፣ ማለትም ንጉሱ፣ሲሞቱ፣ ስለሚያስራቸው ባለሥልጣን  ሰዎች እያዘነና እየተማረረ ፣”ቆዩ ብቻ እኔ በሰዓቴ ልንገስ ብቻ፤ ይሄ ሁሉ ግፍ ያከትማል!” ይላል፡፡ ይዝታል፡፡
ንጉሱ ሞቱ፡፡ ልዑሉ ንጉስ ሆነ፡፡ ህዝቡ “አንድ ልዑል ብቻ ነው እንዴ ያለን? ሌሎቹም ልኡላን ይወዳደሩ እንጂ?” ሲል ጠየቀ፡፡ ይሄኔ ያ ልዑል፣”ይሄም አለ እንዴ?” አለና አንድ አዋጅ አወጣ፡-  
“ከዛሬ ጀምሮ ማናቸውም ዓይነት ብረት ነክ ነገር ይሰብሰብ፡፡ ማረሻ፣ ዶማ፣ አካፋ፣ ድጅኖ፣ ማጭድ፣ የእጅ አምባር፣ የአንገት ሃብል፣ የአጥር ሽቦ፣ የብረት በር፣ የጦር፣ የሻምላና ጎራዴ ዘር… ወዘተ አንድም ሳይቀር ይሰብሰብ!” አለ፡፡
ያለው ሆነ፡፡ በመቀጠልም፤ “አንጥረኛ፣ ቀጥቃጭ፣ብረት አቅላጭ፣ ወዘተ… በሙሉ ተሰባስቦ ብረታ ብረቶቹን በሙሉ ያቅልጡልኝና ሁሉንም ወደ እግረ-ሙቅና ድምድማ እንዲሁም የእጅ ሰንሰለት  ይቀይሩልኝ!” ሲል ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ትዕዛዙ ተፈጸመ፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን ሌሎቹ ሦስት ታናናሽ ልዑላን ወንድሞቹ ለካ አድማ ሲጠነስሱለት ከርመው ኖሮ፣ አንድ አሳቻ ቀን ቤተ-መንግስቱን አስከብበው “እጅህን ስጥ!” አሉት። በእጁ ጦርም ሆነ ሾተል፣ ጩቤ ወይም ሌላ- ስለት የሌለው ልዑል እጁን ከመስጠት ሌላ ምርጫ ጩቤ ወይም የሆነ ሌላ ስለት የሌለው ልዑል፣ እጁን ከመስጠት ሌላ ምርጫ አልነበረውም። ፍፃሜው ይሄ ሆኖ ቀረ፡፡ ከሀገር ቀርቶ ከህይወት ስንብት ለማድረግ ጊዜ ያልነበረው ልዑል አበቃለት፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ይኼው ሥልጣንም፣ ህይወትም ከምንም በላይ አጓጊ መሆናቸውን አየ፡፡ ሁለቱንም ማጣት እርግማን መሆኑን ተገነዘበ፡፡ አንዱንም ማጣት አሰቃቂ መሆኑን ተረዳ፡፡ ያባቱን ዘመን አወደሰ፡፡ ውግዘቱን ሁሉ በፀፀት አነሳ፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊ ገጣሚ እንዳለው፣ “እርግማኔን መልስልኝ!” አለ፡፡
 እስካሁን ያወጋነው በፈቃደኝነት አገርን ስለመልቀቅ ነበር፡፡ ተገድደው ሀገርን መሰናበትስ ምን ይመስላል? የሚከተሉትን ስንኞች እናጢን፡-
“… መሄድ መሄድ አለኝ፤ ጎዳና ጎዳና
አልግደረደርም ዘንድሮስ እንዳምና”
ያሰኘን ይሆን!? ይሄ የምሬት አንድ እጅ ነው እንበል፡፡
“ዝናቡ ዘነበ፤ ደጁ ረሰረሰ
ቤት ያላችሁ ግቡ፤ የኛስ ቤት ፈረሰ”
ይሄ የመረረው ዜጋ ቃል ነው፡፡
“እኔ እዘጋዋለሁ፤ደጄን እንዳመሉ
የት ሄደ ቢሏችሁ፤ ከፍቶት ሄደ በሉ!”
 የተከፋ ዜጋ ፍፃሜ ቃል ነው፡፡
“እሾክ ብቻ ሆነ፣ እግሬን ብዳብሰው
እንዴት መራመጃ ፤መኸጃ ያጣል ሰው!”
 አገሩን  ጥሎ ለመሄድ ልቡ የሸፈተ ሰው ምሬት ነው፡፡
ሰፈራ በተጀመረ ሰሞን ደግሞ ወሎ እንዲህ ሲል ገጥሞ ነበረ፡-
“ቀና ብዬ ባየው፣ ሰማዩም ቀለለኝ
 አንተንም ሰፈራ፣ ወሰዱህ መሰለኝ!”/ እግዜሩን ሰፈራ ወሰዱት መሰለኝ
 አምላኩን ምነው ስቃያችንን አላይ አልከን ለማለት ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልጅ የነበራቸው ባልና ሚስት በአንድ ሰፈር ይኖሩ ነበር። ልጃቸው በየጊዜው እያለቀሰ ያስቸግራቸው ነበረና አባትየው እንደማስፈራራት ብለው፣
“ዋ ለአያ  ጅቦ ነው የምሰጥህ!” ይሉታል።
 ልጅ ፀጥ ይላል። እንዲህ እያሉ እየኖሩ ሳሉ፣ አንድ ቀን ማታ ልጁ እንደተለመደው ሲያለቅስ፣ አባት፤
“ዋ! ለአያ ጅቦ  ነው የምሰጥህ!! አፍህን ብትዘጋ ነው የሚሻልህ!” ይሉታል።
ለካ አያ ጅቦ በሩ ላይ ሆኖ ያዳምጥ ኖሯል። ልጅ ማልቀሱን ይቀጥላል። አባቱም ከቅድሙ በባሰ ሁኔታ፤
“ዋ ዛሬ! ነግሬሃለሁ! ለአያ ጅቦ ነው የምሰጥህ!” ይሉታል፣ ከቅድሙ  በጎላ ድምጽ በጣም ጮክ ብለው።
አሁን ልጁ ፀጥ አለ። ጅብ ቢጠብቅ ቢጠብቅ ፀጥታ ብቻ ሆነ የሚሰማው።
አያ ጅቦ ሲጨንቀው፤
“ኸረ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?” አለ፡፡
ባልና ሚስት ልጃቸውን  አቅፈው ለጥ ብለው ተኙ።
ይሄኔ አያ ጅቦ፤
“ኧረ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?!” አለ፤በድጋሚ።
ድምፅ የለም።
አያ ጅቦም ተስፋ ቆርጦ ወደ ማደሪያው ሄደ! የነጋበት ጅብ ሳይሆን አመለጠ።
***
የምናደርገው ተስፋ ተጨባጭ ካልሆነ ቀቢፀ-ተስፋ ነው። ጥረታችን ሁሉ ንፋስ መዝገን ነው የሚሆነው። በመሪዎቻችን ንግግር ውስጥ የምንሰማው ቃል ሁሉ ጥብቅና የሚታመን ነው ብለን ካመንን የዋሆች ነን። ሥልጣን ላይ መቆየታቸውን እያጠናከርን ነው ማለት ነው! መሪና ተመሪ ሰላማዊ ግንኙነት ቢኖራቸው መልካም ነው ቢባልም፣ ፍትሐዊ ግንኙነት መሆኑን አስተውሎና ልብ- ገዝቶ ማጤንን ይጠይቃል!
የሀገራችንን የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ ምስቅልቅል ሂደት እንዲህ  በዋዛ ፈትተን አንጨርሰውም። በቀላሉም አንገላገለውም።  ምክንያቱም ሰንሰለታዊ ትስስሩ የኖረና ስረ መሰረት ያለው በመሆኑ ነው። እያንዳንዱ ያሳለፍነው ሥርዓት የየራሱን አሻራ አሳርፎበታል። ጠባሳው ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግሯል። ስለሆነም ችግራችንም የቅብብሎሹ አካል ሆኗል። ማናቸውም ታሪካችን የመከራችን መከር ነው የምንለውም ለዚህ ነው። አያሌ ምሁራን እንዳፈራን እናውቃለን። ችግር-ፈቺና ለሀገርና ለህዝብ ተቆርቋሪ ምሁራንን ግን ገና ገና አልጨበጥንም፡፡ አንድ የጥንት ድምጻዊ ከዓመታት በፊት እንዳቀነቀው፡-
“ፈረንጅ አገር ሄዶ ተምሮ ሲመጣ
ትምህርቱን ሳይሰጠን ነቀፌታው ጣጣ
በወላጁ ዛተ
በአገሩ ተረተ
ቢማር ተሳሳተ” ብሎናል።
የመማር ሁነኛ ትርጉሙ አገርን መለወጥ ሊሆን ይገባዋል። ድካማችን ሁሉ የተሻለ ሕይወት ለማምጣት ነው። እንጂ በችግር ላይ ችግር ለመጨመር መሆን የለበትም። ያለፈውን መንግስት ጥፋት ይሄኛው ከደገመ፤ “ትላንትና ማታ ደጃፍህ ላይ እንቅፋት ሆኖ የመታህ ድንጋይ ዛሬም ከደገመህ፣ ድንጋዩ አንተ ነህ።” የተባለው ተረት ዕውን ሆነ ማለት ነው።
በመከራ ላይ መከራ  እየደረትን መኖር የለብንም። ይልቁንም በየዕለቱ አንዳንድ ዕዳ እየቀረፍን ለማደግ መሞከር ያባት ነው። በዕዳ ላይ ዕዳ እየጨመርን ይህቺን መከረኛ አገራችንን ጣሯን ካበዛንባት፣ “የበላችው አቅሯታል፣ በላይ በላይ ያጎርሳታል!” የተባለው ተረት ዓይነት ሆነ ማለት ነው። መንግስታችን ይኼን ያስብ ዘንድ ልብና ልቦና ይስጠው!!

Read 2367 times