Saturday, 14 January 2023 11:32

ካሊሃም

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(2 votes)

   «አላልኳችሁም! ሞተ። ይሄ ልጅ ቁርጥ ካሊጉላን፥ቁርጥ ሃምሌትን ነው። የሁለቱን ጸባይ አጋጭቶ ነው የሰጠው፤ ስምን መልዓክ ያወጣው የለ? ሆ! ካሊሃም። ገደብ አልባ ፍላጎቱ፣ ደንታ ቢስነቱ፣ ራስ አምላኪነቱ፣ሞትን በሰዎች እጅ የመፈለግ ጉዞው አከተመ። የአባቱን ገዳይ አጎቱን የመበቀል አባዜው፣ ቁጡ ባሕርይው አበቃለት።--”
            ድረስ ጋሹ



       በባሕላዊ መንገድ የተሠራ ቤተ-መንግሥት፣ በባሕላዊ ልብስ የደመቁ አሽከሮች፣ የሸክላ ውጤት የሆኑ ዕቃዎ፣ ከቀንድ የተሠሩ ዋንጫዎች፣ ከፍየል ከበግ የተገፈፉ አጎዛዎች_ይታያሉ።]
ንጉሡ ሃጎስ የሚኖረው እዚህ ነው። የቤተ-ክህነት ሰዎች ወደ እርሱ ይመጣሉ። እርሱ ወደ እነርሱ አይሄድም። ለእምነቱ ቀናኢነት ይጎድለዋል ይሉታል። ቅዳሴው ከቤቴ ይቀደስ እንደሚላቸው በትዝብት የሚጠብቁ ቀሳውስት አሉ።
ቅንጡ መንግሥት ነው። ከቤተ-መንግሥቱ ማር እና ወተት አይጠፋም። ሆዱ ረሃብ አይችልም። ዓርብ እና ረቡዕን ገስግሶ ይበላል። «ማህተብ አስረህ ለምን አትጾምም?» ይሉታል ሽማግሌዎች። «አርፋችሁ አርጁ!” ነበር መልሱ!
ንግሥናውን የሚፈልግ ወንድም አለው። በነጋ በጠባ ጉድጓድ የሚምስለት ነው። ጥርሱን ይነክስበት ከያዘ ሰነባብቷል። ዓይን በአፈር ናቸው ቢባሉ አይገልጻቸውም። ዓለም ለገንዘብ፣ለሥልጣንና ለዝነኝነት የሰጠችውን ቦታ ለማንም ሰጥታ አታውቅም። ከሦስቱ አንዱን ለማሳካት የሰው ልጅ ከሰውነቱ ይሟሟል። ወንድሙ ፊንሃስ ይኼንን ነው የሆነው።
ከዕለታት በአንዱ በለስ ቀናው። ወንድሙን፣ንጉሥ ሃጎስን በስለት ወግቶ ገደለው። መንበረ-ሥልጣኑን በእጁ አስገብቶም ይቀናጣ ጀመር። ፊንሃስ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢካቦድ።
ለሃጎስ አሽከር የነበሩት፣ አማካሪ የነበሩት፣ ውስጠ አዋቂ የሚባሉት፣ ሚስቱ አዜብ ሳትቀር ለፊንሃስ ሆኑ። ለመጣ ለሄደ የሚያጎነብስ ጀርባ ይታየኛል። ከሥርዓቱ ለማፈንገጥ የሚንፈራገጡ እግሮች በዱላ ተኮረኮሙ። በቀዳሚ መንግሥቱ የተነቀፉት ድንጋዮች በአዲሱ ለማዕዘንነት ታጩ። ሁሉም ነገር ከወዙ ሆነ።
ሃጎስ በሕይወት ሳለ የወለደው መልከ ቀና ልጅ ካሊሃም አባት አልባ ሆኗል። ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሯ እንደምትሄደው ሆነ። እናቱን ያገባት አጎቱ፤ አባቱን የገደለው አጎቱ ነው። እህቱ እና ፍቅረኛው ዘቢብን ሳይቀር በሞት ያጣ መንታላ ሆኗል። ግማሽ አገር ይገዛ ዘንድ ከአጎቱ ፈቃድ ቢያገኝም ቅሉ የሚመራቸው ሕዝቦች ደስታ እራቃቸው።
ካሊሃም ቁጡ ነው።
እሱ በሚያስተዳድረው ክፍለ-ሃገር ሞት እርካሽ ነው። ከመስመር ያለፈ እግር፣ ፈር የሳተ ንግግር፣ ከአግባብ የወጣ ተግባር ወደ ሞት ያንደረድራል። ወጣቶች ጉርምስናቸውን፣ አሮጊቶች እርጅናቸውን በፀጋ መቀበል ያልቻሉበት ግዛት ነው። ስለ ልጇ የተጎናበሰች እናት፣ ስለ ሚስቱ የተጎናበሰ ባል የመከራ ቀንበር አያጣውም። አይደለም አፍ እላፊ ተናግሮ ከከንፈር ምላሽ ቢያጉተመትም እንኳ ምህረት የለም። አንገቱ ለሻሞላ፣ ወገቡ ለመጥረቢያ የማይገበርበት ተአምር የለም።
ገሥግሦ አሽከሮቹን ያስነሳል።
ለፈላስፋው ምግብ ሥሩ፤ አንቺም ሸበላ ገረድ ተነሽ ግጥም ጻፊ ይላታል። humor & lyrics ለእሱ ደስታ (esctay) ናቸው። ከሚስቱ ፊት ነውር ለመፈጸም አያፍርም። «በዓለም ላይ ጭካኔን መስማት፣ ጭካኔን ማውራት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጭካኔን እንደመኖር ምን ሕይወት አለ?» ይላል።
[ከቤተ-መንግሥቱ በቅርብ ርቀት ላይ ባለች ውዳቂ ክፍል ውስጥ የሚኖር የዕውቀት መናኔ_ፈላስፋ አለ]
ቀትር ላይ።
ፈላስፋው ከአንገቱ ቀና ብሎ ከካሊሃም አሽከሮች ምግብ ተቀበለ። “እናንተ የንጉሥ እግሮች ድካማችሁን አሰብኩ” አላቸው።
«አታስብ! ሲፈጥረን ለመከራ ነው..» ቀይዋ አሽከር የተጠቀለለች ወረቀት ከኪሱ አወጣ። “እንኪ ይኼንን ደብዳቤ ለንጉሥ ካሊሃም አድርሺ” አላት። ገረዲቱ ወረቀቱን ይዛ ወደ ቤተ-መንግሥት አቀናች።
ካሊሃም ወረቀቱን ገለጠ።
«ፈላስፋው ነኝ። በቅድሚያ ሰላም ይግባህ። ስጽፍልህ ከልቤ ነው። ሐቅ አርግዤ መሞትን አልፈልግም። አካሄድህ ምቾት አልሰጠኝም። በዕውቀት እንደምበልጥህ ስላወቅህ የምታደርግልኝ እንክብካቤ ደስ አላለኝም። በዕውቀት ያንሳሉ ያልካቸውን ተንከባክበህ አይቼ አከብርህ ዘንድ ወደድኩ። ሲቀጥል፣ የተቀመጥክበት ወንበር እንደጎረበጠህ አውቃለሁ። አባትህን የገደለውን ንጉሥ ፊናስን እንደ ዳይኖሰር ከምድረ-ገፅ ካላጠፋህ ሰላም እንደማታገኝ እያሰብክ ነው። አካሄድህ የጥፋት ነው። ጥፋትህ ይዞህ እንደሚጠፋም ታውቃለህ። በቀል እስከ የት ያራምድሃል?»
ወረቀቱን አንብቦ አልጨረሰም። አጣጥፎ ከትከት ብሎ ሣቀ። «በቀልን የናቀች ነፍስ ፍርሃት..» ማለት ጀመረ። አጠገቡ የተቀመጠውን ወይን ደጋግሞ በጉሮሮው አንቆረቆረ። ረጅም ቀሚሱን እየጎተተ ተነሳ። “አባቴን ገድሎ ለክፍለ-ሃገር ንጉሥ አደረገኝ። አባቴን ገድሎ እናቴን አገባ። እህቴ እና ፍቅረኛዬ  ዘቢብን ሞት ነጠቃት። ከዚህ በኋላ ማን አለኝ? ደንታዬስ ለማን ነው?..” እያለ ተቀመጠ፡፡
ፊቱ ላይ የንዴት ሥሮች ተወጣጠሩ። የአጣጠፈውን ወረቀት ድጋሚ ለማንበብ ጊዜ ፈጀበት። በወረቀቱ ግርጌ የተቀመጠችዋን ግን ማለፍ አልቻለም።
የስሙ ትርጓሜ በፈላስፋው ዓይን።
«ካሊሃም ብዬ ያወጣሁልህ እኔ ፈላስፋው ነኝ። አንተ ስትወለድ እናትህ አዜብ መጥታ ነው ያስወጣችልህ ስሙን። የዛን ጊዜ እንደ ነቢይ አድርጎኝ ኖሯል መሰለኝ መጻዒ ዕጣ ፋንታህን ገለጽኩት። የስምህ ትርጓሜ የሁለቱ ትልልቅ ትራጀዲዎች ድቅል ነው (caligula of camus & hamlet of shakespeare).ሁለት ሁለት ፊደል ተውሼ ካሊሃም አልኩህ። ግብራቸውን አዋሕደህ የወረስክ ይመስለኛል። አጀማመርህም እንደዚያው ነው»
ቀባጣሪ! ብሎ ወረቀቱን ቀደደው። አሽከሪቷም ደነገጠች።
 ኅዳር ወር።
ካሊሃም በቅሎውን ጭኖ ከአጎቱ እና ከእንጀራ አባቱ ንጉሥ ፊናስ  ጋር ወደ በረሃ ወረደ። ጎሽ የሚያድኑ አሽከሮችን አስከትለዋል ኹለቱ ንጉሶች (ዓብይ እና ንዑስ ሆነው)። ምግብ በግመል ተጭኗል። ሴቶቹ ላብ እየተንቆረቆራቸው፣ እንቅፋት እየቀወራቸው  ከኋላ ይከተላሉ። ወንዶቹ መሳሪያ ይዘው እየቀደሙ የመንገዱን ደህንነት ያጣራሉ። ካሊሃም ከፍ ወደ አለው ቦታ፣ወደ ተራራው ወጣ። ሳያዩት ድንጋይ ፈንቅሎ ወደ ንጉሥ ፊናስ ናዳ ላከ፤ አልተሳካለትም። በረሃው ውስጥ ለማስቀረት ሞከረ፤ በቀሉ አልተሳካም።
በዚያ ንዴት አሽከሮቹን በተራ ከአራዊት እንዲፋጠጡ አዘዛቸው።
«ለምን የሰውን ልጅ ከአራዊት ጋር ታጋጥማለህ?» ንጉሥ ፊናስ ጠየቀው
«ሞት ብርቅ አይደለም፤ ይሙቱ ተዋቸው» ደንታ ቢስነቱ ይነበባል
ከቤት የቀረችዋ አሽከር ለፈላስፋው ምግብ ቋጥራ ኼደች። ትንሽ ቀለም ስለቆጠረች ይግባባሉ። ስለ ካሊሃም aggressive፣ narcissist & jouissance ባሕርይ አስረዳት። ወደ ሰዎች የሚቃጣው የሞት በትር እራሱን እንዳያገኘው ስጋቱን ገለፀላት። በልቡ ያለው ምኞት ምን እንደሆነ በጠየቀችው ጊዜ (“የሰው ልብ ባይታይም፣ በአካላቱ እና በድርጊቱ የሚንፀባረቀውን ልንገርሽ” ብሎ ጀመረላት።)
«ካሊሃምን የአባቱ የሙት መንፈስ ስለ በቀል መልካምነት ሰብኮታል። ይኼ የምታይው ቆራጥ እና ጠበኛ ባሕርይው ከዛ የመጣ ነው። በአባቱ መገደል እጅጉን አዝኗል። ጉዳቱ ጎነ ሦሥት ነው። የአባቱ ገዳይ አጎቱ ነው፤ እናቱንም ያገባት አጎቱ ነው። መበቀል ይፈልጋል። የበቀል ፍላጎቱ ኃያል ነው። በሌላም መልኩ ፍቅረኛውንና እህቱን በሞት ተነጥቋል። በዚህም ፍቅር ያለቀ መስሎታል። ለአሁኗ ሚስቱ የሚሰጣት ፍቅር ማነስ ሰበቡ የእህቱና ፍቅረኛው ሞት ነው። ሞት ለእሱ ብርቅ አይደለም፤ ከዛስ? ብርቁ በቀል ነው። ደም የተጋራውን ስላጣ፣ በፍቅር ይበጀውን ስላጣ ናርስሲስት ሆኗል። አጎቱ (የእንጀራ አባቱ) ከግዛቱ  ቆርሶ ማንገሡም ሰላም አልሰጠውም። የጠፈር ንጉሥ መሆንን ይፈልጋል። የማትደረሰዋን ጨረቃን መያዝ (the desire to impossibility) ፍላጎት አለው። ከዛም አልፎ አማልክቶችን  ጁፒተርን እና ቬነስን መሆን ይመኛል። “ሰዎች ያለቅሳሉ ምክንያቱም ይህች ዓለም ልክ አይደለችም” እያለ የሚደመጥ ትርጉም አልባነትን ሲሰብክ ነው። ለዛም ነው የካሙ እና የሼክስፒር ድቅል ገፀ-ባሕርይ መሆኑን ቀድሜ አውቄ ካሊሃም ያልኩት።»
«ግን ሰዎች ቢቃወሙትስ?...»
«እሱም  ዓለምን ይቃወማላ። እንደ አቡነ አትናቲዎስ፣ እንደ ዲዮጋንም። ለእራሱ እውነት የመሰለው በቀል ነው። ወደፊት ጠራርጎ ካላጠፋችሁ አይረካም። እሱ በውጪ ተጽዕኖ መሞትን ይፈልጋል፤በእራሱ እጅ እራሱን አያጠፋም። ገፍቶ እንዲገፋ ነው የሚመኘው። ተጠንቀቁ!»
[ከበረሃ መልስ አቀባበል፤ ድግስ፤ ዕልልታ ተደረገለት። ከመሐል ግጥም ብቻ ነበር የሚያደምጠው። አንደኛው አሽከር “ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ” የሚል ጭብጥ ያለው ግጥም በማንበቡ ተቀላገና ከበረሃ ከመመለሱ]
የመጨረሻ ሰዓቱ ላይ ነው።
የሚጎነጨውን ወይን አስቀመጠ። «የመበቀል ቀን አሁን ነው ብሎ ተነሳ» የተሰቀለውን ስለት መጥረቢያ ይዞ ወጣ። ፍቅረኛው ሶፊያ ተጨነቀች። አትሂድ ማለት ባለመቻሏ ታዝንም ገባች።
ጠንቀቅ ያለ ልብስ፣ የበቀል ካባ ደርቦ በምሽት ያለ አሽከር እየተሳበ ወጣ። ወደ አጎቱ ቤት ወደ ንጉሥ ፊናስም አቀና። በንጉሡ ቤት ዳንኪራው ደርቷል። መጥረቢያውን እንዳያዩበት በጉንፉ ደበቀ። በሰው መሐል እየተሽሎከለሸከ ገባ። በክብር የተቀመጡ ሦስት ሰዎች ይታዩታል። ጠጋ ብሎ ሲመለከት ንጉሥ ፊናስ የመሰለውን ቀላው፤ ሞተ። ጭፈራው ወደ ለቅሶ እና ድንብርብር ተቀየረ። ሁሉም ቀልቡ ጭፈራው ላይ ስለነበር ገዳዩን ሳያውቁት ቀሩ።
ቤቱ ተመልሶ ለሚስቱ የድል ዜና አበሰራት። የገደለው ግን የሚስቱን አባት ነው። ንጉሥ ፊናስ አልሞተም። ሌላኛው ኀዘን በካሊሃም ቤት።  ንጉሥ ፊናስ ባደረገው ምርመራ ገዳዩ ካሊሃም ለመሆኑ አውቋልና ይጠነቀቅ ጀመር።
በካሊሃም ቤት።
አሽከሮቹን እና ግዛቱን የማፅዳት ዕቅድ ተውጠነጠነ። እያንዳንዱ ሰራተኛ ማጉተምተም ያዘ። ሊገድላቸው አፉን ሲጠራርግ ሲያዩ ፈሩ። ሚስቱ ሶፊያ ከሌሎች ጋር ሆና መላ ትዘይድ ጀመር።
ሌላ ቀን።
ድጋሚ ወደ ንጉሥ ፊናስ ቤት ለበቀል ሲያቀና አሽከሮቹ ተሽቀዳድመው ኼደው ለንጉሡ ሹክ አሉት። ንጉሡም ተዘጋጅቶ ጠብቆት ኖሮ ገደለው።  ንጉሥ ፊናስ ከእነ ሚስቱ በተወረወረባቸው ቦንብ ከሰሙ። ተያይዘው አለቁ።
ፈላስፋው ደብዳቤ ላከ። የተማረችዋ አሽከር በስስት አነበበችው።
«አላልኳችሁም! ሞተ። ይሄ ልጅ ቁርጥ ካሊጉላን፥ቁርጥ ሃምሌትን ነው። የሁለቱን ጸባይ አጋጭቶ ነው የሰጠው፤ ስምን መልዓክ ያወጣው የለ?_ሆ! ካሊሃም። ገደብ አልባ ፍላጎቱ፣ደንታ ቢስነቱ፣ራስ አምላኪነቱ፣ ሞትን በሰዎች እጅ የመፈለግ ጉዞው አከተመ። የአባቱን ገዳይ አጎቱን የመበቀል አባዜው፣ ቁጡ ባሕርይው አበቃለት። ሁሉም ወደ ሞት ሲነዱት (death drive) ነበር። የሚወደው የአጋታ ክርስቲ the mouse trapን ትቶ ኼደ። የተምታታ እውነት፣ በፍርሃት የተተበተበ ዓለም፣ ትርጉም የለሽ ሕይወት፣ የበቀል እና የማይቻል ፍላጎቱ ተጫኑት። (እናቱ ግን ምን ላይ ነበረች?...)
ሁሉም በልባቸው አዘኑ _ለእናቱ።
እናት መከረኛ ናት። ፍዟ ተዋናይ እናቱ አንጀታቸውን በላቻቸው።
«በተፈጠረው ነገር ተደንቀናል። ለመሆኑ ካሊጉላንና ሃምሌትን በተውኔት ውስጥ ምን ያመሳስላቸው ኖሯል?» የሚል ደብዳቤ ለፈላስፋው ደረሰው
ተደሰተ።
«ካሊጉላ የሚወዳት እና የሚያፈቅራት እህቱን በሞት በማጣቱ ጀመረ። ኀምሌትም አባቱን በማጣቱ ነው የሚነሳው። ካሊጉላ የሞተው በውጫዊ ተጽዕኖ ሲሆን፤ ሃምሌትም እንደዚያው ነው። ሁለቱም ቁጡ፣ መረን የለሽ ፍላጎት (unsatisfied desire) እና የራሳቸው አቋም ያላቸው  ጀግኖች ናቸው። ሁለቱም በተውኔቱ መጨረሻ ሞተዋል። ኹለቱም ራስን የማጥፋት ዜማን በሌሎች ተጽዕኖ አቀንቅነዋል። ካሊጉላ በሚስቱና በአሽከሮቹ ሲገደል ፤ሃምሌት ደግሞ በአጎቱ ተገደለ። ካሊሃም ግን የሁለቱ ውርስ ነው።»
አሽከሮቹ በስስት ወረቀቱን፤ እውነትም ስምን መላዓክ ያወጠዋል! ተባባሉ።
|መነሻ፡- አልጀሪያ ተወልዶ ፣የፈረንሣይ ዜግነት ባለው አልበርት ካሙ የተጻፈው “ካሊጉላ” የተሰኘ ታሪክ ቀመስ ተውኔቱ እና ሃምሌት የተሰኘው የሼክስፒር ረጅም ትራጀዲክ ተውኔት ድምር ነው። የኹለቱ ተውኔቶች የሚያመሳስላቸውን (death drive, aggressivity  & jouissance) ለመጠቆም የተፈጠረ  የምናብ ሙክርታ ገፀ-ባሕርይ ነው፤ ካሊሃም።|


Read 6233 times