Saturday, 14 January 2023 10:53

“ኩኩ መለኮቴ፣ እሷ በበላችው በእኔ ላከከችው!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

  እንኳን ለከተራውና ለብርሀነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው ...መቼም የሆነ በዓል ነገር ሲመጣ ገበያ ላይ ለዛው በዓል ይሆናሉ የተባሉ፤ ምርት ነገሮች ይቀርባሉ አይደል! ለምሳሌ... ‘ክሪስማርስ ትሪ!’ ቂ...ቂ...ቂ...፡፡ የምር ግን እንግዲህ ጨዋታም አይደል.... ‘ክሪስማርስ’ የሚባለው በዓል የትኛው እንደሆነ ግራ እየገባን ስለሆነ ይብራራልንማ! እናማ እንግዲህ የጥምቀት በዓል እየቀረበ አይደል! ለበዓሉ ከሚያስፈልጉት ምርቶች የቀሩ ያሉ እንደሚመስለን ለነጋዴዎች (ወይም ‘ነጋዴ ባይሆኑም መነገድ ለሚችሉት’) ለመጠቆም ያህል ነው፡፡ ለምሳሌ ሀርሞኒካ፡፡ አሀ ልክ ነዋ...ያለ ሀርሞኒካ ጃን ሜዳ ምኑን ጃን ሜዳ ሆነ!
እኔ የምለው... ‘ፋሚሊ ፕላኒንግ’ ምናምን ነገሮችን የሚያጠኑ ክፍሎች የጥምቀት በዓልን የጃን ሜዳ አስተዋጽኦ የማያዩትሳ!
“ከተጋባችሁ ምን ያህል ጊዜ ሆናችሁ?”
“አሁን አርባ ዘጠነኛው ላይ ደርሰናል፡፡”
“የሚገርም ነው፡፡ ለመሆኑ መጀመሪያ የት ነው የተገናኛችሁት?”
“የጥምቀት በዓል ላይ ጃንሜዳ...”
እናላችሁ... ከዛ ዝርዝሩ ላያስፈልግ ይችላል። ልክ ነዋ...ያቺ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የተቀባች ረጅም ዱላና ጫፏ ላይ የሚሰኩት ስፒሎች ምናምን አሉ አይደል...“እና ምን መሰለህ፣ እንግዲህ ዱላዋ ጫፍ ላይ ስፒሏ አለች አይደል...”
“ግዴለም፣ ግዴለም ጌታዬ...የነገሩን በቂ ነው ጌታዬ..” እናላችሁ...የሀርሞኒካው ውለታ አይረሳ ለማለት ነው፡፡
ስሙኝማ... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... አንዲት የድሮ የልጆች ጨዋታ አለች፡፡ የዘንድሮ ልጆች ይወቋት፣ አይወቋት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ (እነ እነትና... ቲክቶክ ላይ ትኖር እንደሁ አጠያይቃችሁ ትነግሩኛላችሁ።) እናላችሁ...“ኩኩ መለኮቴ፣ እሷ በበላችው በእኔ ላከከችው!” የምትል በዜማ አይነት ቅላጼ የምትባል ነገር፡፡ ለዚህ ላለንበት ዘመን በልክ ተለክታ የተሰፋች  አትመስልም? ሁላችንም እኮ በሆነ ባልሆነው አንዳችን በሌላኛችን ላይ፤ ግለሰብ በግለሰብ ላይ፣ ቡድን በቡድን ላይ፣ ሰፋ ሲል ደግሞ ሀገር በሀገር ላይ ማላከክ “ኩኩ መለኮቴ፣” የሚያሰኝ ነው፡፡ 
“ይሄ ነገር እንዴት ነው እንዲህ ሊበላሽ የቻለው?”
“እኔ እንጃ፣ እኔም ግራ ገብቶኛል፡፡”
“እንዴት ነው ግራ የሚገባህ... ዋናው አስተባባሪ አንተ አይደለህ እንዴ!”
“እኔ ምን ላድርግ፣ እነሱ ናቸው ያበላሹት...”
ነገርዬዋ እኮ... አለ አይደል ጥቅም ምናምን የምታስገኝ ነች ተብሎ ሌሎቹን አስወግዶ 
እርስ በእርሳችን እየተላከክን ነን፡፡
ሳት ብሎን፣ ማለትም አዳልጦን እንኳን “የእኔ ስህተት ነው፣” ማለት! ምን ቆርጦን፡፡ ዓይን አፍጥጦ “ወይ በስርአት ሠርቶ አይሠራ! ወይ በደንብ ለሚሠራ ሰው አይለቅ፤ ሁሉ ነገር ውስጥ ዘው እያለ እኮ ነው የሚያበላሸው!  አሁን ይህን አይደለም እሱን የሚያክል ትልቅ ሰው ህጻናቱ እንኳን ያቅታቸዋል! እኮ! አሁን አይደለም ትልቅ ሰው ይህንን እንደው ትንሾቹ ልጆች ያቅታችዋል!” ደግሞ ምን መሰላችሁ... “እከሌ ነው ያበላሸው! እከሊት ነች እንደዚህ ያደረገችው!’ 
ለአፋችን ያህል እንኳን ብለን “ለስህተቱ ሀላፊነቱ የማንም ሳይሆን የእኔ ብቻ ነው!” ብለን ልንናገር! ሞተናላ! አንዳችን...አ.ለ አይደል ወይ ወፍራም ወንበር ወይም ‘ወፍራም ፈረንካ’ ያለን ራሳችንን ተጠያቂ አድርገን፣ “ተጠያቂው እኔ ነኝ፤ ሌሎቹ እዚህ ውስጥ የሉበትም፣” ያልን እለት “ሰበር ዜና” ብቻ አይሆንም፣ “የሰበር ሰበር ዜና” እንጂ! ልክ ነዋ...“የሰበር ሰበር...” የሚል አዘጋገብ ባይኖርስ? እኛ ዘንድ ማንኛውንም ነገር በአስተሳሰባችን አምሳል (ቂ...ቂ...ቂ...) የመፍጠር መብታችንን ስላስከበርን “ሰበር...” የምትለዋን ቃል አይደለም ሁለት ጊዜ አሥራ ምናምን ጊዜ ማባዛት መብታችን ነው፡፡ (አልፎ፣ አልፎ በአንዳንድ የሚዲያ አካላት የምንሰማቸው ነገሮች በባዶ ሜዳ ‘የብዜት ብዜት’ እየመሰሉብን ስለተቸገርን ነው፡፡)
ስሙኝማ...አንድ ሰሞን ማጋለጥ የምትባል ነገር ነበረች፡፡ (ግምገማ ሌላ፣ ማጋለጥ ሌላ!) ነገርዬው ለ‘ቦተሊካ’ የነበረ ቢሆንም የቦለቲካውን አድማስ አሰፋነውና “አቶ እከሌ ስልጣናቸውን በመጠቀም በመሥሪያ ቤታችን የሚገኙ የሥራ ባልደረቦች እህቶቻችን...” ምናምን ይባልና ደረቁ የቦተሊካ ማጋለጡ ‘ሂዩመን ተች’ ይሰጠዋል... (ቂ...ቂ...ቂ...)፡፡ እናላችሁ... ማጋለጥ የሚባለው ነገር አብዛኛውን ጊዜ “ኩኩ መለኮቴ...” አይነት ነገር ነው፡፡ ግምገማ የሚባለው ነገር አብዛኛውን ጊዜ “ኩኩ መለኮቴ...” አይነት ነገር ነው፡፡
ኮሚክ እኮ ነው... ያኛው ወገን የምንለውን በሀሳብ ጥንካሬና በጽንሰ ሀሳብ ጥልቀት ሳይሆን  በማዋረድና በማሳጣት የቦተሊካ ቪክተሪ የሚፈለግበት ዘመን ሆነና ስንቶች ባላጠፉት ጥፋት፣ ባልነቀነቁት አጥር፣ ባልገፉት ግንብ ጣት እየተቀሰረባቸው ሰብአዊ ክብራቸውን ለማዋረድ ሲሞከር፣  እኔነታቸውን ቁልቁል ለመወርወር ሲሞከር መክረሙ አንድ ቀን ታሪክ ዘርዝሮ ለአስተማሪነት ያህል ቁጭ ያደርገው ይሆናል፤ ምንም እንኳን ‘ካለፈው መማር’ በሚሉት ነገር አይደለም “ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ምናምነኛ...” የምንለው አይነት ደረጃ ሊወጣልን ቀርቶ፣ ኳሰኞቹ እንደሚሉት ‘ፎርፌ’ ከሰጠን የከረምን ይመስላል፡፡ አሀ...ልክ ነዋ...ፎርፌ መስጠት እኮ...አለ አይደል... “ካለፈው በመማር ከመቶ ዘጠና ምናምን ሀገራት መቶ ዘጠና ምናምነኛ፣” የሚል (ሴራ ያለበት!) ‘ደረጃ’ እንዳያወጡብን ይከላከልልናላ! እናላችሁ...ነግ በእኔ የተረሳበት ሀገር ሆነችና፣ የዛሬ ገምጋሚ የነገ ተገምጋሚ፣ የዛሬ አንደኛ የነገ መቶ አንደኛ (ያውም ከቀናው) የሚሆንባት ሀገር መሆኗ ተረሳና ነገሮች ሁሉ “ኩኩ መለኮቴ...” ሲሆኑ ማየት አሪፍ አይደለም፡፡ ዛሬ ‘ያኛውን’ ወገን በሀሳብ ለማሸነፍ ሳይሆን በነገር ለማዋረድና ለማሳጣት ስንሞክር፣ ነገ ደግሞ ሌላኛው ወገን እኛ ላይ ይችኑ ጌምፕላን እንደሚጠቀምም ማወቁ አሪፍ ይሆናል፡፡ ባያስተቃቅፈንም ቢያንስ፣ ቢያንስ እርስ በእርስ ከመቦጫጨር ሊያድነን ይችል ይሆናል፡፡ (‘ማስተቃቀፍ’ የሚለው ቃል ጥቅም ላይ የዋለው የሰሞኑን እቅፍቅፎሽና ‘ኪሶሎጂ’ ሳይጠቅሱ ማለፉ በታሪክ ተጠያቂ እንዳያደርግ በማሰብ ነው። “ክሬዚ ፒፕል፣ ክሬዚ ወርልድ” የሚል ዘፈን እስከዛሬ ከሌለ ለመጠቆም ያህል ነው!)
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል...”ለማን ደስ ይበለው ብዬ ነው የእኔ ስህተት ነው የምለው!” የምንላት ነገር አለች አይደል! ደግሞ የሚገርማችሁ እኮ ይቺ አባባል የማትገባበት ቦታ አለመኖሩ ነው...እንደ ካርታዋ ‘ጆከር’ ማለት ነው፡፡ እናላችሁ...“ኩኩ መለኮቴን” ልጆች መጫወታቸው ይኸው ሲኒየር ሲኒየሩ እያጧጧፈው ነው! የምር ግን ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አለ አይደል...”ለማን ደስ ይበለው ብዬ ነው!” የምትለው አባባል የቅሽምናዋን ያህል አንዳንዴ እንደ አሪፍም ነገር ትሆናለች፡፡
“ለማን ደስ ይበለው ብዬ ነው ራሴን የምጥለው!” ብሎ ወላ የሥራ ቀን የለ፣ ወላ የእረፍት ቀን የለ... ስሪ ፒስ ገጭ አድርጎ መሸለል፡፡ “ለማን ደስ ይበለው ብዬ ነው ከእሷ ጋር ተኳርፌ የምቀረው!” ብሎ በማግስቱ “ማሪኝ ብዬሻለሁ እሞትብሻለሁ፣” ብሎ “አይ ጀስት ኮልድ ቱ ሴይ አይ ላቭ ዩ...” ምናምንን ማንጎራጎር፡፡ እኔ የምለው... አንድ ሰሞን “ሁዋትስ ላቭ ጎት ቱ ዱ ዊዝ ኢት!” ምናምን የሚለው ነገር ቦተሊካ መዝገበ ቃላታችን ውስጥ ገብቶ አልነበር! አሁንም አለ ወይስ ‘አፕግሬድድ’ ሆኗል?
እኔ የምለው...እናንተ አትክልት ተራ አካባቢ የነበራችሁትና “ማዳም ጉድ ኦራንጅ...” እያላችሁ የፈረንጅ አፏን የምታቀላጥፏት...ጠፋችሁሳ! እስቲ እንደ መሸለያ፣ ‘እንደ መነስነሻ’ የምትሆን የፈረንጅ አፍ መፈክር ምናምን ነገር ፈልጉልንማ! (አሀ...አንዳንዴ የምንሰማው የፈረንጅ አፍ ‘የየትኛው ፈረንጅ አፍ’ እንደሆነ ግራ እየገባን ስለሆነ ነው! ቂ...ቂ...ቂ...) ለምሳሌ.. “ለማን ደስ ይበለው ብዬ ነው...”  ለምትለዋ እንደው ሙሉ ለሙሉ የፈረንጅ አፍ ባትሆንም ሲናገሯት ወደ ፈረንጅ አፍ የምትቀርብ ነገር ፈልጉልንማ!
እናማ... “ኩኩ መለኮቴ፣ እሷ በበላችው በእኔ ላከከችው!” እየረበሸችን ነው ለማለት ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 758 times