Saturday, 14 January 2023 10:32

ጎንደር ለጥምቀት እስከ 1ሚ. እንግዶችን ለመቀበል ዝግጁ ናት ተባለ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(3 votes)

  በፀጥታ በኩል አንዳችም የሚያሰጋ ነገር የለም ተብሏል
                        
        የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል በተለየ መልኩ ለማክበር ዘርፈ ብዙ ዝግጅት መጠናቀቁን ያስታወቀው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን፤ ጎንደር ለጥምቀት በዓል የሚመጡ ከ750 ሺህ እስከ 1ሚሊዮን እንግዶችን ለመቀበል ዝግጁ ናት ተብሏል። ለዚህም አስፈላጊው የመሰረተ ልማት፤ የፀጥታና የመስተንግዶ ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሀላፊ ወይዘሮ ጥሩዬ አትክልት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ከዛሬ ጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ከተራው የተለያዩ የጎንደርን ገፅታ ብሎም የክልሉን ባህል፣ ወግ፣ የቱሪዝም ሀብትና ተፈጥሮን ለእንግዶች የሚያስተዋውቁ ከ10 በላይ ኹነቶች መዘጋጀታቸውንም ነው ወይዘሮ ጥሩዬ ጨምረው የገለፁት፡፡
እስከ ጥምቀት መዳረሻ ከሚከናወኑ ኪናዊና ትውፊታዊ ኹነቶች መካከል ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ በአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ የሚካሄደው የአዝማሪ ፌስቲቫል አንዱ ሲሆን የአፄ ቴዎድሮስ ልደትም ይከበራል፡፡ ጥር 7 ቀን በየዓመቱ የሚካሄደው የ5 ኪ.ሜትር የፋሲል ከነማ ሩጫም አንዱ ነው ብለዋል ሀላፊዋ፡፡ በዚሁ እለት ከቀኑ 7፡00 ጀምሮ “ሚስ አማራ” የቁንጅና ውድድር ተካሂዶ አሸናፊዋ የምትለይበት ሥነ ስርዓት እንደሚከናወን ተመልክቷል፡፡ ጥር 8 ቀን ሰኞ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ “ጎንደር ታመሰግናለች” በሚል መሪ ቃል ከአመራር አካላትም ሆነ ከሌሎች ዘርፎች ለጎንደር ተግተው የሰሩና ውለታ የዋሉ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅናና ምስጋና የሚያገኙበት መርሃ ግብር ይካሄዳል ተብሏል፡፡ ከጥር 5-8 የተከፈተውም የባህል ፌስቲቫልና ባዛር አንዱ ሁነት ሲሆን ጥር 9 ቀን ማክሰኞ ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ “ግጥም በመሰንቆ” የተሰኘ ደማቅ የግጥም ምሽት በባህላዊ ሙዚቃ ታጅቦ ለዘጠነኛ ጊዜ በአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ እንደሚቀርብ የገለፁት የኮሙኒኬሽን ሀላፊዋ፤በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ የአምባሰሏን ንግስት ማሪቱ ለገሰን ጨምሮ በሀገሪቱ አሉ የተባሉ ገጣሚያንና የኪነ ጥበብ ሰዎች እንደሚሳተፉበት ተናግረዋል፡፡
የጥምቀት እለት ጥር 11 ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ በፋሲል ቤተ መንግስት የሚካሄደውና የንጉሳውያን የአመጋገብ ሥርዓት የሚያሳይ “የንጉስ ዕራት” መርሃ ግብር ለእንግዶች እራት በማብላት እንደሚከናወንም ተገልጿል፡፡
የሆቴልና የመስተንግዶን ጉዳይ በተመለከተ ሀላፊዋ ሲያብራሩ፤ ከባለ ኮከብ ሆቴል እስከ ዝቅተኛ ሆቴሎችና የመኝታ አገልግሎት ሰጪዎች የእድሳትና የማስተካከል ሥራ ሰርተው እንግዶቻቸውን በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን ጠቁመው፤ የአልጋ እጥረት ቢያጋጥም እንኳን ሆቴሎች ዘመናዊ ድንኳኖችን እንዲያዘጋጁ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የፀጥታን ጉዳይ በተመለከተ ጎንደር በአሁኑ ወቅት ፍፁም ሰላም ብትሆንም እንግዳ ጠርቶ ችላ ማለት ስለማይገባ ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጓል ያሉት ወይዘሮ ጥሩዬ፤ ከፀጥታ አካላት በተጨማሪ በየቀበሌውና በየመንደሩ ኗሪውን በማደራጀት ከፍተኛ የክትትልና የፀጥታ ቁጥጥር ሥራ እንዲሰራ የተሰጠ መመሪያ ከመኖሩም በላይ የጎንደር ከተማ ወጣቶች እንደከዚህ ቀደሙ በቅንጅት የፀጥታውን ሁኔታ ከማስከበር ረገድ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረጋቸው በፀጥታ በኩል አንዳችም የሚያሰጋ ነገር እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡
የመኝታ ዋጋን በተመለከተ በእያንዳንዱ ሆቴል ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊዋ፤ አጋጣሚውን በመጠቀም ያልተገባ ጥቅም ለመሰብሰብ በሚሞክሩት ላይ እርምጃ በመውሰድ የማስተካከል እርምጃ መውሰዱን ገልፀው፤ ሁሉም ሰው ደማቁን የጥምቀት በዓል በውቢቷና ታሪካዊቷ ጎንደር እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

Read 2592 times