Tuesday, 10 January 2023 00:00

“አገሬ በልጽጋ ከውጭ ልመና ወጥተን ማየት እሻለሁ”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

• መንግስትና ህዝብን ማጭበርበር እግዚአብሔርን ማጭበርበር ነው

 • ለህዝቡ መንገድ ለመሥራት ከቀበሌ አመራሮች ጉቦ ተጠይቀናል

ባለፈው ሳምንት በልጅነታቸው ከሸንኮራ አገዳ ንግድ ጀምረው ዛሬ የቢሊዮኖች ዶላር ኢንቨስትመንት ባለቤት የሆኑትን የአቶ አቶ መኩሪያ ባሳዬ ቃለምልልስ የመጀመሪያ ክፍል አቅርበናል፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከታሪኩ ባለቤት ጋር ያደረገችውን
ሁለተኛ ክፍል አስደማሚ ቃለምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡ ታሪኩ በራስ ጥረትና ልፋት የሚገኝ ስኬትን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነውና ትወዱታላችሁ፤ ትማሩበታላችሁ ብለን እናምናለን፡፡ የመጀመሪያውን ቃለምልልስ ያላነበባችሁ በአዲስ አድማስ ዌብሳይት
ህብረተሰብ አምድ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡


  አሁን ላይ ከትዳር አጋርዎ ዶ/ር ማርጋሬት መኩሪያ እና ናኦል መኩሪያ የተባሉ ልጆችን ማፍራት ችለዋል ---
አዎ! እውነት ነው፡፡ እውነት ለመናገር በወቅቱ አባትየው እውነት ነበራቸው፡፡ እኔ እንኳን የእሳቸው ልጅ ማግባት ቀርቶ የቤት ሰራተኛቸው መሆን አይገባኝም፡፡ አንደኛ አልተማርኩም፣ ሁለተኛ የገጠር ልጅ ነኝ፤ ሶስተኛ የገበሬ ልጅ ነኝ፡፡ እሳቸው  በቦሬ በጉጂና በአዲስ አበባ በጣም የታወቁ ብዙ ሀብትና መኪኖች የነበሯቸው የተከበሩ ሰው ናቸው። በሰው አይንና ሚዛን የሚሆን አልነበረም፤ እግዚአብሔር ስለፈቀደ ነው ሁሉም የሆነው። እንዳልሽው በ1987 ዓ.ም የመጀመሪያ ልጄ ማርጋሬት ተወለደችልኝ፡፡
ስሟን ግን እንዴት ማርጋሬት ብላችሁ ሰየማችኋት?
በ1987 ቦንኬ የሚባል ሰባኪ ከውጪ መጥቶ ሀዋሳ ስታዲየም ላይ እየሰበከ ነበር፡፡ በዚያን ዕለት ሰባኪው ስለ አንድ የራሽያ ወታደር ታሪክ ይነግረናል። ወታደሩ በዓለም ጦርነት ጊዜ ማርጋሬት የተባለች የሚወዳትን ሚስቱን ጥሎ ነው የሄደው፡፡ ከጦርነቱ ሲመለስ ከተማው በሙሉ ወድሞ የእሱ ቤት ብቻ ቀርቷል፡፡ “በቃ ሚስቴ አለች እድለኛ ነኝ” ብሎ በሩን አንኳኳ። በሩን ስትከፍትለት እሱ መሆኑንም ስታይ ደንግጣ በሩን ዘጋችበት። እሷ ሞቷል ብላ ሌላ አግብታለች፡፡ ይህ ሰው “ማርጋሬት ማርጋሬት” እያለ እየጮኸ፣ በሌላ አቅጣጫ ከባሏ ጋር ጠፍታ ሄደች” እያለ ታሪክ እየነገረን ባለለቤቴ ምጥ ያዛትና በ30 ደቂቃ ውስጥ ወለደች፡፡ ከዚህ ታሪክ ጋር ተያይዞ ነው ማርጋሬት ያልናት። አያቷ (የእናቷ እናት) ፋዮ ካልቻ ይባላሉ። እሳቸው ናቸው እንዲያውም ማርጋሬት ትባል ያሉት። ሁለተኛው ልጄ ናኦል ይባላል፡፡ አሜሪካ እየተማረ ይገኛል፡፡ ከዚያ ልጅ የመውለድ ፕሮግራም አቆምንና ባለቤቴን ወደ ት/ቤት መለስኳት፡፡ እንደነገርኩሽ ጎበዝ ተማሪ ነበረች። ከ9ኛ ክፍል ነው ጠልፌ ያገባኋትና ሀዋሳ ታቦር ሀይስኩል ጨርሳ፣3 ነጥብ 8 አምጥታ፣ አዳማ ዩኒቨርሲቲ ገባች፡፡ በጥሩ ነጥብ ተመርቃ ወጣች። እሷ አራት ዓመት ተምራ እስክትጨርስ ልጆቼን ያሳደግኩት እኔ ነኝ፡፡ እኔ ባልማርም የሚማር ሰው እወዳለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች እንዲማሩ ደግፌያለሁ፡፡ ከዜሮ ጀምረው እስከ ከፍተኛ ትምህርት አጠናቅቀው ውጪ የሄዱም አሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በሀላፊነት የሚሰሩም አሉ፡፡ በዚህ ደስ ይለኛል፡፡ ባለቤቴ ተመርቃ ከወጣች በኋላ በሀዋሳ ማዘጋጃ ቤት እንድትቀጠር አደረግሁ፡፡  ወይዘሮ ውቤ ዮሐንስ ትባላለች፡፡ እሷ ማዘጋጃቤት መስራት ስትጀምር እኔ የኮንስትራክሽን እቃ አስመጪነት ጀመርኩኝ፡፡ እሱን አንድ አመት እንደሰራሁ ወደ ኮንስትራክሽን ገባሁ፡፡ ደረጃ አራት ተቋራጭ ድርጅት መሰረትኩ፡፡ ያን ጊዜ ሼህ አላሙዲን በጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ላይ የቴክኒክና ሙያ ተቋም እየሰሩ ነበርና እሱን በግብዣ መልክ እኔ እንድገነባ ሰጡኝ፡፡ እሱን በአንድ ዓመት አጠናቅቄ ሀዋሳ መጣሁ፡፡ ሀዋሳዎች  አራት የክፍለ ከተማ ፅ/ቤቶች ግንባታ ሰጡኝ፡፡ እነሱ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር እንዳስረክብ ነበር የፈለጉት፡፡  እኔ በ6 ወር ጨርሼ አስረከብኩ፡፡
በጣም አስገራሚ ነው! እስኪ በሀዋሳ ስላፈሯቸው ሀብቶች ያጫውቱኝ?
በሀዋሳ ከሰዎች የግል ይዞታ  መሬት እየገዛሁ፣ ቤት እየሰራሁ እሸጣለሁ፡፡ ሀዋሳ አደባባይ ላይ በርካታ ግንባታዎች አሉ፤ ነገር ግን ከግለሰቦች መሬት እየገዛሁ እንጂ ከመንግስት ጠይቄ አይደለም የምሰራው፡፡ እኔ ከመንግስት ለመኖሪያ ቤት እንኳን መሬት  ጠይቄ አላውቅም። አሁን በቅርቡ ትልቅ ሆቴል ለመገንባት አዲስ አበባ መሬት ጠይቄ ተሰጥቶኛል፡፡ ከዚያ ውጪ መሬት እየገዛሁ ነው የምገነባው፡፡
ሀዋሳ ላይ መሃል ፒያሳ “ታይም ካፌ” ፣ “ታይም የገበያ ማዕከል”፣ “ታይም የገበያ አዳራሽ”፣ “ታይም የመኝታ አገልግሎት” የተሰኙ ተቋማት ከፍተዋል፡፡ አሁንም ሀዋሳ ላይ ነው ኑሮዎን ያደረጉት ወይስ ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል?
እኔ አዲስ አበባ መኖሪያ ቤት የለኝም፤ አሁንም የምኖረው ሀዋሳ ነው፡፡ ምን መሰለሽ -- የሰሜኑ ጦርነት ሲቀሰቀስ በጣም ነበር ያዘንኩት። በዚህ በኩልም ከትግራይ በኩልም የሚሞቱት ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ በዚህ ጦርነት ዱባይ ቤት ያልገዛ፣ ሀብት ያላሸሸ ባለ ሀብት የለም፡፡ አብዛኛው ማለት ይቻላል እንደዛ አድርጓል፡፡ እኔ እንኳን ዱባይ ሄጄ ቤት ልገዛ አዲስ አበባ እንኳን ቤት የለኝም። አልፈልግም። ከደሀ ማህበረሰብ መሃል ወጥተን አድገን የት ነው ጥለን የምንሄደው፡፡ ይቺ አገር እኮ እኔ አንቺ ሌሎች ወንድሞቻችን እህቶች እንጂ ሌላ የላትም’ኮ፡፡ ከዚህ ደሀ ህዝብ ጉሮሮ ነጥቄ ዱባይ ቤት የምገዛበት ምክንያት የለም፡፡ ዱባይም  አሜሪካም የሚኖር ሁሉም ይሞታል። ወደ መሬት ይገባል፡፡ ስለዚህ እኔ የቅንጦት ህይወት አልፈልግም፤ መኖሪያዬ ሀዋሳ ነው። ቅድም የጠቀስሽው ታይም ካፌ ሀዋሳ ላይ በጣም ብራንድ ነው፡፡ ሻይ፣ ቡና ማኪያቶና ጭማቂ ነው የምንሸጠው፡፡ ዓመታዊ ሽያጫችን 32 ሚሊዮን ብር ገብቷል፡፡ መንግስት ከዚያ ብዙ ታክስ ያገኛል፡፡  አንዲት ሽራፊ ሳንቲም አናጭበረብርም፡፡ መንግስትና ህዝብን ማጭበርበር እግዚአብሄርን ማጭበርበር ነው፡፡ ደረሰኝ ሳንቆርጥ አንድ ውሃ አንሸጥም፡፡ በዚህ የመንፈስ እርካታ ይሰማኛል። እንዳልኩሽ ሀዋሳ ላይ ከ10 በላይ ግንባታዎች እየተገነቡ ነው፡፡ ሁሉንም መሬት ገዝቼ ነው እየገነባሁ ያለሁት። መንግስት መሬት አመቻችቶ ሰጥቶኝ ቢሆን ለመሬት ግዢ የሚወጣው ብር ይተርፍና ሌላ ይሰራ ነበር ፤ነገር ግን ከመንፈስ እርካታዬ አይበልጥም፡፡
ኢንዱስትሪም ገንብተዋል  ልበል?
አዎ ሀዋሳ ላይ የገዛሁት የዱቄት ፋብሪካ አለ፤ በዘመናዊ መንገድ አደራጅቼ አልሚ ምግብ ማምረት እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ለህፃናት አልሚ ምግብ በጣም ያስፈልጋል። በእኔ አቅም ጥቂት ልጆች ከአልሚ ምግብ እጥረት ከተላቀቁና ጤናማና ብሩህ ሆነው ካደጉ ለእኔ እርካታ ነው። ሌላው ላለፉት 12 ዓመታት ስጠይቅና ስጠብቅ ቆይቼ፣ ገና አምና ነው ቦታውን የሰጡኝ፤ የኦሮሚያ ክልል መንግስትን አመሰግናለሁ፡፡ አዲስ አበባ ላይ ግዙፍ የማዕድናት ማቀነባበሪያ ልገነባ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ ግንባታውን ለውጪ ተቋራጮች ነው የምንሰጠው፤ በጣም ግዙፍ ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ አፍሪካ ህብረት አካባቢም የህንፃ ግንባታ ጀምረናል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ወረዳ ጫንጮ ከተማ ላይ ትልቅ የወተት ማቀነባበሪያ ልናቋቁም ከግለሰብ ኩባንያ  ገዝተን  ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ልናደራጅ በሂደት ላይ ነን፡፡  እዚያ አካባቢ ያለው ጥሩ ያልሆነ ቢሮክራሲ ይዞን እንጂ እስካሁን  ብዙ እርቀት በሄድን ነበር፡፡ እኛ የግንባታ መሳሪያ ሙሉ በሙሉ አስገብተናል፡፡ ችግሩንም ለሚመለከተው የኦሮሚያ መንግስት አቤት ብለን እየተፈታ ነው፡፡ በ2016 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ይጀመራል፤ ኢንቨስትመንቱ 59 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
በአጠቃላይ ስንት ኩባንያዎች ናቸው ያሉዎት?
32 ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በስራቸው ከ3 ሺህ በላይ ሰራተኞች አሉ፡፡ አሁን እዚያም እዚህም ሆነው በዝተው እኔንም እያደከሙኝ ነው፡፡ እስከ ዛሬ በቀን ከ18 ሰዓት በታች ሰርቼ አላውቅም ነበር። አሁን በቅርቡ 17 ሰዓት መስራት ጀምሬያለሁ። እነዚህን ኩባንያዎች ጠቅለል አድርገን በአንድ በሶስቱ ላይ ማተኮር እንፈልጋለን፡፡ ሻኪሶ ውስጥ ለምሳሌ የቡና እርሻ አለኝ፡፡ እኔ 160 ሄክታር የቡና እርሻ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት በ35 ሚሊዮን ብር መሬቱን ገዝቼ፤ መሬቱን የሸጠልኝ ግለሰብ  በ7 ሚሊዮን ብር መፈልፈያ ሸጦልኝ በድምሩ በ42 ሚሊዮን ብር ነው ወደ ቡና እርሻ ስራ የገባሁት፡፡ ነገር ግን መሬት በሊዝ ባገኝ ኖሮ፣ በ2 ሚሊዮን ብር ማለቅ ይችል ነበር፡፡ የሆኖ ሆኖ  የቡና እርሻው ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሷል። አንደኛ ደረጃ ኦርጋኒክ ቡና ነው፡፡ በጉጂ ዞን ኦዳ ሻኪስ ወረዳ ሀንገዲ ቀበሌ ነው የሚገኘው፡፡ እዚህ አካባቢ ደስ የሚለንን ነገር ልንገርሽ፡፡ የቡና እርሻውን እንደገዛሁ መንገድ የለም ነበር፡፡ የአካባቢው ህዝበ በመንገድ እጦት ያለቅስ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ህዝቡ ይሰቃይ ነበር፤ 14 ኪ.ሜትር መንገድ ነው ለህዝቡ የሰራሁት፤ ያንን መንገድ ስሰራው ብዙ ፈተና አይቻለሁ፤ ለህዝቡ እንባ ስል ለቀበሌ አመራሮች እጅ መንሻ ከፍያለሁ። ለምን እከፍላለሁ ባልሰራ ቢቀርስ ማለት እችል ነበር። ግን ደግሞ ህዝቡ ያሳዝናል። ማሽን ጭነን ሄደን፤ ዶዘር ኤክስካቫተር፣ ሩሎ፣ አስራምናምን ዳምፕ ትራክ ይዘን ሄድን አትሰሩም ተባልን፡፡ እኔ ለአንድ እራሴ አይደለም የምሰራው፤ ለሀገር ለወገን ነው፡፡ ላልማ ባልኩ ጉቦ ተጠየኩኝ፤ እጅግ ያሳዝናል፡፡
ስንት ብር ጉቦ ከፈሉ?
እሱን ተይው፡፡ 500 ሺህ ብር ካልሰጣችሁን አሉ፤ የቀበሌ አመራሮች፡፡ ሦስት ቀን አጉላሉን። ትሮ ኡዴሳ የሚባል የኔ ስራ አስኪያጅ ነበር የመንገዱን ሥራ የሚያስተባብር፡፡ እሱ አንከፍልም፤ ማሽኖች ተጭነው ይውጡ አለ፡፡ እግዚአብሄር ያሳይሽ--- ማሽኖቹ ከአዲስ አበባ ተጭነው ነው የገቡት፤ ለሎቤድ ብቻ 700 ሺህ ብር ነው  የከፈልነው፡፡ ጭነን እንውጣ ብንል ሌላ 700 ሺህ ብር ለማሽነሪዎቹ መመለሻ ከምንከፍል 500 ሺህ ብር እንስጣቸውና መንገዱን ለሚያለቅሰው ህዝብ እንስራለት ብለን ተመካከርን፡፡ መንገዱን ሰራን፤ ያንን መንገድ እንደ ሦስተኛ ልጄ ነው የማየው፤ ዋጋ ከፍዬበታለሁ፡፡ በህይወቴ ፈታኝ አጋጣሚ ዎች ከምላቸውም አንዱ ነው፡፡
አሁን  የተበታተኑትን 32 ኩባንያዎች እያጠፍን በሦስቱ ላይ ለማተኮር አቅደናል።  ቡና ኤክስፖርት ማድረግ፣ ወርቅና ማዕድን ማቀነባበርን በተጠናከረ መልኩ አዲስ አበባ ላይ መሥራት ፈልገናል፡፡ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ላይ የከበሩ ማዕድናትን በከፍተኛ ጥረት እያቀነባበርን መላክ እንጀምራለን፡፡ ወርቅ መላክ አይቻልም፤ ብሔራዊ ባንክ ነው የሚገባው፡፡ የሀዋሳዎቹ ካፌዎች ይቀጥላሉ። አንድ ነገር ግን ልንገርሽ፤ ታይም ካፌ ብለን የዛሬ 13 ዓመት የከፈትነው የሙስሊሙም፣ የኦርቶዶክስም የፕሮቴስታንትም ትልልቅ የሀይማኖት መሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሚጠቀሙበት ቀደምት ታዋቂ ካፌ ነበር፡፡ በስሩ 116 ሰዎች ይሰራሉ። አሁን እሱን ልንዘጋው ነው፡፡
ለምንድን ነው የሚዘጋው?
አሁን አዲሱ ትልቁ ታይም ካፌም ሆነ የበፊቱ ላይ ምንም የትራፊክ መጨናነቅ በሌለበት መኪና እንዳይቆም አምጥተው ምልክት አስቀመጡ። ደንበኞቻችን መኪና ማቆሚያ ስላጡ በተለይ የበፊቱን ካፌ መጠቀም አቆሙ፤ ሽያጩ በቀን እስከ 130 ሺህ ብር ነበር፤ አሁን ስላሽቆለቆለ ልንዘጋውና ሰራተኞቹን ልናሰናብት ነው፡፡ ከዘጠኝ ዓመት እስከ አሥራ ሦስት ዓመት  የሰሩ ሰዎች አሉ፤ ግን ምን እናድርግ? የግድ ማሰናበት አለብን፡፡ እኛ ለከንቲባውም ነግረናል፤ መስተካከል አለበት ብለን እናምናለን፡፡
አዲስ አበባ ላይ ጋዜቦ አደባባይ ታይም ኮፊ  ከፍታችኋል አይደል?
አዎ! ታይም ኮፊ  በዚህ ዓመት ብቻ በአዲስ አበባ ውስጥ 15 ይደርሳል ቁጥራቸው፡፡ ለዚህም ቦታዎችን ገዝተን አዘጋጅተናል፡፡ ብሄራዊ አካባቢ ገዝተናል፣ ስቴድየም ሁለት ገዝተናል፣ ገነት ሆቴል አካባቢ ና ሌሎችም ቦታዎች ገዝተን ወደ መክፈቱ ስራ እየገባን ነው፡፡ እቅዳችን አዲስ አበባ ላይ ብቻ 150 የታይም ኮፊ ቅርንጫፍ መክፈት ነው፡፡ ከዚያ ኬኒያ፣ ዱባይ፣ ጀርመንና አሜሪካ ታይም ኮፊ ይከፈታል፡፡ የኬኒያውን ፈቃድ አግኝተን ጨርሰናል። የአዋጭነትና የቦታ ጥናት የሚያደርጉ ከፍተኛ ባለሙያዎች አሉን። በዚህ ረገድ ተግተው እየሰሩ ነው፡፡ ከላይ የገለፅኩልሽ የውጪ ሀገራት በሙሉ የኢትዮጵያ ቡናን የሚወዱ ናቸው፡፡
እስኪ ወደ ወርቅ ማውጣቱ ስራ እንምጣ። በ2 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት “ታይም ማዕድን”ን በይፋ ጀምረዋል፡፡ ወደዚህ ኢንቨስትመንት የገቡት በቁጭት መሆኑን ሰምቻለሁና ስለለሱ ይንገሩኝ..?
ወርቅ በጣም ከባድ ስራ ነው፡፡ በዚያው ልክ ጥሩ ስራም ነው፡፡ እኔ በህይወቴ የሚፈታተነኝ ስራ ከሌለ  ወይም ተግዳሮት ካልገጠመኝ ስራ የሰራሁ አይመስለኝም፡፡ ያንን ተግዳሮት ማለፍ  ማሸነፍ ነው ደስታ የሚሰጠኝ፡፡ ሀገራችን እንዳየሽው በዶላር ችግር እንደተሰቃየች አለች። እኔ ውስጤ ያለቅሳል፡፡ መሪዎቻችን ብድርና ልመና ፍለጋ ወደ ውጪ ይሄዳሉ። በዚህ በጣም ውስጤ ያለቅሳል፡፡ የሀገር መሪ ምልክት ነው፤ መከበር አለበት፡፡ መሪን የሚሾመው እግዚአብሄር ነው፡፡ እሱ አመፀኛ ከሆነ ያምፅ እንጂ የሚሾመው እግዚአብሄር ነው፡፡ መሪዎች ሁሉ ለማኝ ሆነው ውጪ ሲሄዱ ሀዘን ይሰብረኛል። የምሬን ነው የምልሽ፡፡ ዋናው ወደ ማዕድን ዘርፍ እንድገባ ያነሳሳኝ ይሄ ቁጭት ነው፡፡ ለምን በዚህ ዘርፍ ገብቼ የራሴን አስተዋፅኦ አላደርግም የሚል ቁጭት፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ከዚህ በፊት ከዚህ ቦታ አንድ ገበታ አፈር አውጥቼ 22 ሺህ ብር ሸጫለሁ። በዳሰሳ፣ የተማረ የሰው ሀይልና ቴክኖሎጂ በሌለበት ይህን ያህል ካገኘሁ፣ በተማረ የሰው ሃይል በቴክኖሎጂ ተደግፈን ብንሰራ እዚህ ቦታ ላይ ሊሰራ የሚችለውን ታሪክ አስቢው፡፡ እዚህ ያለንበት አርዳጂላ፣ በኃይለስላሴ ዘመን ነው ስራ የተጀመረው። ያኔ በሰው ሀይል እየተቆፈረ ነበር የሚጠናው። በደርግም በሰው ሀይል ነበር የሚቆፈረው። በኢህአዴግም ብዙ ለውጥ የለም። አሁን የብልፅግና መንግስት መጥቷል። በዛው አይነት መቀጠል የለበትም፡፡ የተማረ የሰው ሀይል አለን፡፡
ቴክኖሎጂውን ተጠቅመን ሀገራችንን ከዶላር ቆፈን፣ መሪዎቻችንን በሰው ፊት በልመና ከመገረፍ ለምን አናድንም? ደግሞ እንችላለን፡፡ ይሄ ቁጭት ነው ወደ ዘርፉ  ያስገባኝ። የወርቅ ማውጣት ስራ እንደሚታሰበው አይደለም፡፡ ኢንቨስትመንቱ  2 ቢሊዮን ዶላር ነው  ሲባል የተጋነነ ገንዘብ የሚመስለው አለ። ይሄ ግን ግማሹ ነው፡፡ አይበቃውም፡፡ አንድ የወርቅ ማውጫ ማሽን  በ780 ሚሊዮን ብር ገዝተን ከደቡብ አፍሪካ  እያስመጣ ን ነው፡፡ አንድ ማሽን ብቻ 780 ሚሊዮን ብር ! እሱም ትልቁ አይደለም፤ ዝቅተኛው ነው፡፡ አሁን በሥራ  ላይ ያያችኋቸው ኤክስካቫተሮች ወርቅ አይደሉም፤ የግንባታ ማሽነሪዎች ናቸው፡፡ የማዕድን ብቻ ተብለው የተሰሩ እያንዳንዳቸው 60 እና 70 ሚሊዮን ብር  የሚገዙ ማሽኖች ናቸው፡፡ ስራውን በሙሉ አቅም ስንሰራ 10 ቢሊዮን ዶላር ላይበቃ ይችላል፡፡ በአጠቃላይ የማዕድን ሥራ እጅግ ፈታኝ ነገር ግን ውጤቱ አስደሳች ነው፡፡ ውጤቱ ለሀገር ነው፡፡ ወርቅ አውጥተን ብሄራዊ ባንክ ነው የምናስገባው፤ የሀገር ጥቅም ነው። የእኛ ታይም ማዕድን 25 በመቶውን የወርቅ ፍላጎት ይሸፍናል ብለን እናምናለን፡፡
ሁለተኛው ቁጭቴ አካባቢው ላይ በርካታ ወጣቶች ሥራ የላቸውም፡፡ እነዚህ ልጆች የሚመራቸውና የሚያግዛቸው ነው ያጡት። በሀገራችን ትልቅ ሥራ  ሆኖ የተያዘው ለፎቅ ድንጋይ መቆለል ነው፡፡ ይሄ አያዋጣም፡፡ 90 በመቶው ሳይበላ፣ 10 በመቶው የሚበላ ከሆነ የሚቆለሉ ፎቆች ይፈርሳሉ የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ ኢንዱስትሪ ማብዛትና  ማዕድኖቻችን ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን፡፡ ለዚህ ነው  እኔም ከወሬ ባለፈ እያንዳንዳቸው ከ80 በላይ አባላት ያሏቸው 77 ማህበራትን አደራጅቼና ሥልጠና ወስደው፣ ከታይም ማዕድን ጋር ወርቅ በማውጣት የጥቅም ተካፋይ እንዲሆኑ ያደረግሁት። ይሄው እናንተ ባላችሁበት ከ6 ሺህ 700 በላይ ወጣቶች ስልጠና ወስደው ወደ ስራ እየገቡ ነው፡፡
ሀገራችን ሀብት አላት፤ ወርቅ ላይ ተኝተን ደሀ ነን፡፡  እኛ በዘርና በሀይማኖት ስንናከስ የውጪ ዜጎች በስደተኛ መታወቂያ እየገቡ፣ ወርቅና ማዕድናትን እየተዘረፍን ነው፤  መንቃት አለብን እላለሁ፡፡
የወርቅ ስራ በጀመሩባቸው ቀበሌዎች አራት ቀበሌዎችን የሚያገናኙ 41 ኪ.ሜትር መንገድ ገንብተዋል---
አካባቢው በጣም አስቸጋሪ ነው፤ መንገድ የለም። ህዝቡ ምርቱን ወደ ከተማ አምጥቶ የሚሸጠው በሸክምና በእንስሳት ጉልበት ነው። ድሮ  እህል ስነግድ ከአናሶራ ቦሬ ከተማ ድረስ 54 ኪሎ ሜትር በፈረስ ጭኜ እወስድ እንደነበር ነግሬሻለሁ፡፡ ከዚያ በላይ እናቶች በምጥ፣ በሌሎች ህመሞች ህክምና ሳያገኙ ይሞቱ ነበር፡፡ ይህንን በመመልከት 41 ኪሎ ሜትር መንገድ ሰርተናል፡፡ ለዚህ የመንገድ ሥራ 800 ሚሊዮን ብር አውጥተናል፡፡ ይሄ መንገድ አራት ቀበሌዎችን ከዋና ዋና መንገዶች ጋር የሚያገናኝ   ነው፡፡
ነገር ግን ነዋሪው ውስጥ ለውስጥ  መንገድ ያስፈልገዋል፤ ገና 380 ኪሎ ሜትር መንገድ  የመገንባት እቅድ አለን፡፡ አሁን በተገነባው መንገድ ህዝቡ ያገኘውን እፎይታ ከአንደበቱ  ሰምታችኋል፡፡
በህይወት እያሉ በአገርዎ ላይ ሆኖ ማየት የሚፈልጉት ምንድን ነው?
ሀገሬ ባላት ሀብት በልፅጋ ከድህነት ወጥተን፣ መሪዎቻችን ከውጭ ልመና ወጥተው  ማየት እፈልጋለሁ፡፡ይህንንም ለማየት በቀን 18 ሰዓት እየሰራሁ ነው፡፡ ይህን ሳላይ ፈጣሪ ከዚህ ምድር  እንዳይወስደኝ  ፀሎቴ  ነው፡፡

Read 1223 times