Saturday, 07 January 2023 00:00

የበዓል የሙዚቃ ኮንሰርት እየተነቃቃ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ላለፉት ሁለት ዓመታት በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ተዳክሞ የቆየው የበዓላት የሙዚቃ ኮንሰርት መነቃቃት እያሳየ መሆኑ ተነገረ። ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለፈረንጆች አዲስ ዓመት ዋዜማ፣ በሸራተን አዲስ ደማቅ የሙዚቃ ኮንሰርት የቀረበ ሲሆን በዚህ ኮንሰርት አንጋፋው ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ ፣ ብዙአየሁ ደምሴ፣ ልጅ ሚካኤልና ሄዋን ገብረወልድ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን አቅርበውበታል፡፡ በርካቶች የታደሙበት ይህ የሙዚቃ ኮንሰርት መግቢያው እራትን ጨምሮ 10ሺህ ብር ነበር፡፡ ኮንሰርቱን ከ3ሺ በላይ ሰዎች እንደታደሙት  አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል።
በነገው ዕለት ቅዳሜ የሚከበረውን የገና በዓል አስመልክቶ ዛሬ ምሽት የዋዜማ ኮንሰርት በሚሊኒየም አዳራሽ ተዘጋጅቷል - በጆርካ ኢቨንትስ፡፡ በዚህ የዋዜማ ኮንሰርት ዝነኞቹ ድምፃውያን ሚካኤል በላይነህና ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ እንዲሁም የኦሮምኛ ዘፈን አቀንቃኙና የኦዳ አዋርድ ተሸላሚው ዮሳን ጌታሁንና ታዋቂው የኤርትራ ድምፃዊ ዳዊት                             ተ/ሰንበት (ሽላን) የሙዚቃ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ታዋቂ የከተማዋ ዲጄዎች የሙዚቃ ድግሱን ያደምቁታል ተብሏል፡፡
በዚህ የሙዚቃ ድግስ ላይ ለመታደም መደበኛው የመግቢያ ዋጋ 300 ብር ሲሆን ቪአይፒው 900 ብር መሆኑንና ትኬቶቹንም በቴሌብር መግዛት እንደሚቻል አዘጋጁ ጆርካ ኢቨንትስ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ነገ ቅዳሜ ምሽት ከ12 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ “የኔ ዜማ” በሚል የመጀመሪያ አልበሙ ተወዳጅነትን ያተረፈው ድምጻዊ ዳዊት ጽጌ፣ ሃይሉ አመርጋና ሌሎችም ድምጻዊያን የሚያቀነቅኑበት የሙዚቃ ድግስ ከኤድናሞል ወረድ ብሎ በሚገኘው “ዘ ክለብ” እንደሚቀርብ አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ኮንሰርት ላይ ለመታደም የመግቢያ ዋጋው 2 ሺህ ብር ሲሆን፤ ክፍያው ምግብና መጠጥን ያካትታል ተብሏል። የትኬት ሽያጩ የተጀመረ ሲሆን ትኬቱ የሚገኘው በአዘጋጁ በ “ዘ ክለብ” ውስጥ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የበዓል የሙዚቃ ኮንሰርት መነቃቃት ያሳየው በመዲናዋ ብቻ አይደለም፡፡ ባለፈው ረቡዕ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው አንጋፋዋ ድምፃዊት ማሪቱ ለገሰ፣ ነገ ቅዳሜ የመጀመሪያ የአገር ውስጥ ኮንሰርቷን በደሴ ከተማ እንደምታቀርብ ታውቋል። በመቀጠልም በጎንደር ባህርዳርና አዲስ አበባ ከተሞች የሙዚቃ ሥራዎቿን ለአድናቂዎቿ ታቀርባለች ተብሏል።

Read 1527 times