Saturday, 31 December 2022 13:13

ብላክ ሌብል፤ ወይም ብላክ ፎረስት!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው...የስጦታ ነገር እንዴት ነው! ማለቴ እሺ ግዴለም ‘እነሱ’ ቪ ኤይት ምናምን ይሸላለሙ፡፡ ቪ ኤይት ስጦታ! (አይ. ኤም. ኤፎች ይሄን ነገር የሰሙ ጊዜ ብቻ...አለ አይደል... “እነሱ እንዲህ ተርፏቸው እኛ በምን እዳችን ነው አንዲት ዶላርስ የምንሰጠው!” አይሉም እንጂ ቢሉን “አቤት የፈረንጅ ክፋት! እነኚህ ሰዎች ነክሰው አልለቅ አሉን እኮ!” ልንል ነው! የምር እኮ አንዳንዴ ኮሚክ ዘመንና ኮሚኮች እኛ የገጠምን ነው የሚመስለው፡፡)
“ስማ ይቺ ኮሮላ ምን የሚሏት መኪና ስንት ነው የምትሸጠው?!”
“መቶ ሀያም፣ መቶ ሀምሳም ትባላለች አሉ፡፡ ምነው አሰብክ እንዴ?!”
“ማን እኔ! ቢኖረኝ እንኳን መቶ ሀምሳ ሺህ ለመኪና ላወጣ! ሀምሳ ጨምሬበት ባለ ሁለት መኝታ ጎጆ አልሠራበትም!”
እንዲህ የሚባልበት ዘመን ነበር፡፡ ሁለት መቶዋ ሁለት መኝታ መሥራቷ በጽሁፍ የሰፈረ መረጃ ባናገኝም (ቂ...ቂ...ቂ...) የእኛዪቱ በመረጃ የሚወራባት ሀገር ስላልሆነች ወሬ እስካሳመረ ድረስ ልክ ያልሆነ ነገር የለም!
 (እኔ የምለው... የቀለም አብዮት ምናምን ሲሉ የነበሩት ሀሳቡን ያገኙት ‘ጎልድ፣’ ‘ብሉ፣ ‘ብላክ፣’ ‘ሬድ፣’ ምናምን ከሚሏቸው የ‘ሲፕ’ ምርቶች ነው እንዴ! አሀ...ልከ ነዋ! አብዮት መለያ ስንት ነገር እያለ ቀለም ላይ ምን አስኬዳቸው ብለን ነው፡፡  በነገራችን ላይ አንድ ሰሞን የከተማው ህንጻዎች ሁሉ ግራጫ እንዲቀቡ ምናምን የሚል ውሳኔ ተላለፈ ተብሎ እኛም “ጉድ” ብለን ነበር። አሀ... እኛ ግራጫ መሆናችን አንሶ ጭራሽ ህንጻው ሁሉ ግራጫ በግራጫ ሊሆን!
ለምልክትም ያስቸግራላ! “ቢጫው ህንጻ አካባቢ ስትደርስ ወደ ቀኝ ታጥፈህ ቀይ መስኮት ያለው ሱቅ አለ፣ ከእሱ ፊትለፊት በሩ ቡኒ የሆነ ግቢ አለ፣ በቃ እሱ ነው ቤቱ፡፡” ልጄ ቀለም እኮ ለስንትና ስንት ነገር ምልክትነት አግዞን ነበር፡፡ “እሱዋ ሴትዮ ግን ሁልጊዜ ቀይ በቀይ የምትሆነው የእሷ ቫለንታይንስ ዴይ ምናምን አያልቅም እንዴ!”
ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ምን መሰላችሁ... ስለ ሀያና ሀያ አራት ሚሊዮን ብር መኪኖች እየሰማን ነው፡፡ “ያ ጥቁር መኪና ይታይሀል! ሀያ አምስት ሚሊዮን ነው፡፡” ‘በሰው ፍራንክ’ ምቁነት እንዳይመስልብንማ። ወዳጆቻችን እንደሚነግሩን ከሆነ ዘንድሮ እነኚህ የጂ ፕላስ ምናምን ቤቶች ምረቃ ውስኪ ምናምን ለደስ፣ ደስ ብሎ ነገር የለም አሉ፡፡ በስጦታ ብልጭልጭ ወረቀት ሳይጠቀለል በሩ ላይ የሚደረገው የምናምን ሚሊየን ብር መኪና ነው አሉ...እንደ ቪ ኤይት ማለት ነው፡፡  የምር እኮ አንዳንዴ ነገራችንን ስታዩት ልክ ለዓለም እይታ የቀረብን የስታንድአፕ ኮሜዲ ትርኢት ልንሆን ምንም የቀረን አንመስልም፡፡ ደጎቹም፣ ክፉዎቹም ነገሮች ከትናንት ዛሬ ተስፈንጥረው የሚሄዱበት ፍጥነትና የሚስፈነጥሩበት እርቀት ግርም የሚል ነው፡፡
ከውጭ ለሚመጡ ወዳጆቻችን ማስረዳት እንኳን እያቃተን ነው፡፡ አሀ...ልክ ነዋ... እኛ ግራ ገብቶን! ግራ ገብቶን! ግራ....የበቃን ምኑን እናስረዳቸዋለን!
“ስማኝ ትናንት ማታ የሆነ ቦታ ወጥተን ነበር፡፡ ምን አየን መሰለህ... እንትን.. (በአርትኦት የቀረ!)...እንዴት ነው ነገሮች ሁሉ እዚህ ደረጃ የደረሱት?” እናንተም እኮ ብትጠይቁ፣ ብትጠይቁ “አውቃለሁ...” የሚል ሰው ያጣችሁለት ነው እኮ!
“እባክህ እሱ እኛንም ግራ የገባን ነገር ነው!”
ለምን ይዋሻል፣ አንዳንድ ከውጭ የመጡ ወዳጆቻችን እንዲህ አይነት መልስ ስንሰጣቸው ምን ይሉን መሰላችሁ... “እንዴት እዚህ ዓይናችሁ ሥር የሚደረገውን አታውቁም!” በዚህ ቢተዉን ጥሩ፤ ግን ይጨምሩልናል... “የኢንፎርሜሽን ዘመን መሆኑን አታውቁም እንዴ!” በዚሁ እኛ ላይ ቢቆሙ ሸጋ፣ ሌላም ይጨምሩልናል... “በቃ ይህ ህዝብ ዘለዓለሙን ከኢንፎርሜሽን ወደ ኋላ እንደቀረ ሊኖር ነው!”  አይ ምነው! እንዴ...ተቀብለን ባስተናገድን (‘ወጪው’ ከእነሱ ቢሆንም) የእኛ ሳያንስ ህዝብን ቀላቀሎ አንድ ሙቀጫ ውስጥ መክተት ምን  የሚሉት ‘የኢንፎርሜሽን ዘመን’ ነው!
እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...ኸረ እባካችሁ ቦተሊከኞች ሀገርና ህዝብ ላይ በፊት ለፊትና በ’ሾርኒ’ የምትወረውሯቸውን “ምን እንዳታመጡ!” እሚመስሉ ነገሮች ተዉን! አንዳንድ ጊዜ ዘላለምዓለም በገዛ ልጆቿ (ወይም ልጆቿ ናቸው ብለን በምንታሰብ) ስትብጠለጠል የምትኖር ሀገር የእኛይቱ ብቻ ሳትሆን አትቀርም! በገዛ ወገኖቹ (ወይም ወገኖቹ ናቸው ተብለን በምንታሰብ) ሲብጠለጠል የሚኖር ህዝብ የእኛ ብቻ ሳይሆን አይቀርም! 
እና ነገሮች ሁሉ ‘ፋስት’ እና ‘ሱፐር ፋስት’ እየሆኑብን ግራ ተጋብተናል ለማለት ያህል ነው፡፡ ስማኝማ ወዳጄ በቀደም የሰማነው ነገር ሲገርመን ሰነበተ ነው የምልህ! አንተስ? እቤት የነበረው የአዲስ ዓመት ጠጅ አልቋል አይደል! ቂ...ቂ...ቂ... የምር ግን ድሮ በ’ቴን’ ብሯ ከበዛም ድግሞ በፊፍቲና በሀንድረድ ብሯ ያለድርድር ‘ይሆንልን የነበረው ነገር’ (ቂ...ቂ...ቂ...) ትዌንቲና ሰርቲ ታውዘንድ የደረሰባቸው ቦታዎች አሉ የተባለውን አጣራህ እንዴ! (ደግሞ ‘ፐር ናይት’ የሚለውን የፈረንጅ አፍ ትርጉም አጣርተህ ላክልኝማ!)
ስማኝማ...ደግሞ እሱ ሲገርመን ያኛው የስሪ ሀንድረድ ፊፍቲና የፎር ሀንድረድ ታውዘንድ ወሬ በድንጋጤ እስካሁን ያጎደለብኝን ኦክሲጅን ማንን ጠይቄ እንደማስተካ ግራ ገብቶኛል፡፡ እሱ ወሬ እውነት ከሆነማ የራሳችንን “ናይንቲን ኤይቲ ፎር” ምናምን የማንጽፍሳ! ስማኝማ...የትም፣ የትም ነው የምልህ እንዲህ አይነት ወሬ ቢሰማ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ ባይታወጅ ነው! አሀ...ብሪቱ የፈለገውን ያህል አቅም ትጣ እንጂ እስከዚህ ድረስ! ወዳጄ፣ እሱን ነገርማ በ’ምግብ ለሥራ’ አይነት የሚያገለግል ኢንቬስቲጌቲቭ ሪፖርተር ፈልገን ጎረቤት እየሰበሰብን ቀለቡን መቻል አያቅተንም፡፡ (ብሪቱን ምዘዙ አይበሉን እንጂ!) በራሳችን እኮ ስለጉዳዩ  ተጓዳኝ ጥያቄዎች እንዳንደረድር ችግሩን ታውቀዋለህ፡፡
ሰሞኑን እንግዲህ ለተረፈን፣ ባይተርፈንም እንደተረፈው ለሚያደርገን የ’ሲፕ’ ሰሞን ነው። (ደግነቱ ከዓለም ‘ዩኒክ’ ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ ነው ተብሎ የሚጠረጠረው የፈለገ ኑሮ ቢደቁሰን ‘ሲፕ’ ማድረጊያ አለማጣታችን ነው! እንደውም የሦስት ብሩ ዳቦ ስምንት ብር ሲደርስ በየ’ሲፕ’ ቤቱ ‘ቀምቃሚዎች’ የምንቀመጥበት ወንበር እያነሰ የሚሄድበት ኬሚስትሪ ሊገባን አልቻለም፡፡ ወገኖች በልክ ‘ሲፕ’ እናድርግማ! (“በልክ ተዝናኑ” ማለቱ የቃላት ብክነት ስለሚሆንብን ነው፡፡ ስለዚህ እቅጭ እቅጯን ነው፡፡)
የእኛ ሀገር ኢቭና ዋና በዓል በአብዛኛው ‘ፉድና ድሪንክ’ አይደል! እናማ ‘ሲፕ’ ስናደርግ ታዲያ እባካችሁ ሌላው ላይ ቴረር ምናምን የሚመስል ነገር የምንለቅ አልፎ፣ አልፎ አለን እየተባለ የስሚ ስሚ ይነገራል፡፡ እናማ በመሸተኛ ግጥም ባለው ቡና ቤት ጠረጴዛው ላይ ከቢራ ጠርሙሶቹ ጋር ‘ነገርዬውን’ አብረን ጉብ እናደርጋለን የምንባል ሰዎች እንዴት ነው ነገሩ! አሀ  ‘ሎው ኤንድ ኦርደር’ የሚባለው ነገር ቅልጥ ብሎ የተሰደደባት ከተማ አናስመስላታ! ወይስ ድሮ የ’ቴክስ’ ፊልም ማየት ያበዛን አለን!
እና ይህ የስጦታ ነገር..እኛስ! አትርሱና! እኛ እኮ የምናምን ሚሊየን መኪና አላልን! ሬድ እና ብላክ ሌብል አላልን! (እነ እንትና የብላክ ሌብሉ ጣዕም እንደ ድሮው ነው እንዴ!)  ጂ ፕላስ ምናምን አላልን! የግድ በፈሳሽ መልክ ከተባለ ይቺ የሀገር ውስጧ ምርት...አለ አይደል...ከመውሰዷ በፊት ወዝ በወዝ ታደርጋለች የሚባልላትን ‘ኦሪጅናሌዋን’...እሷኑ የምታደርገንን ማየቱ ይሻላል፡፡ አንድ ጊዜ፣ በሌላኛው ዘመን፣  አንድ ወዳጄ ቤቴ መሶብ መኖሩን ሳያጣራ የመሶብ ክዳን ያመጣልኝን “በአንተ ቤት ስጦታ መስጠትህ ነው!” እያልኩ መከራውን ሳበላው ከርሜ ነበር፡፡ አሁን ሁሉ ነገር ጸጥ፣ ጸጥ ሲል ‘ስዊት ሜሞሪ’ ነገር ሆና ልትመጣ! ወዳጄ ሁሉ ነገርዬው ስለተለወጠ እንጂ ባይለወጥ ኖሮ “ሂሴን ውጫለሁ...” እልህ ነበር! ጠባቂ እንጂ ሰጪ የጠፋበት ዘመን ሆነብን! አይደለም ብላክ ሌብል ሲፑዋን የሚያመጣ፣ ብላክ ፎረስት የሚሉትን ኬክ የሚገዛ ወዳጅ እንኳን ‘ኢንዴንጀርድ ስፒሽስ’ ሆኗል፡፡  እንትና ተቆራጯ አርባና ሀምሳ በገባችበት ጊዜ ብላክ ፎረስቱ ስንት ደረሰ? አይ፣ አንተ ባትበላውም፣ ‘የሚበሉትን’ በሳምንት ሦስቴ አታጣም ብዬ ነው፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1461 times