Saturday, 31 December 2022 13:07

የኢሰመኮ 2ኛው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ተጠናቀቀ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት በአምስት ከተሞች ከታኅሣሥ 1 ቀን 2015 ዓ.ም  ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል የመዝጊያ ሥነሥርዓት ባለፈው ታኅሣሥ 18  በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡  
“ሰብአዊ ክብር፣ ነጻነትና ፍትሕ ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በአዳማ፣ በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በሃዋሳና በጅግጅጋ በተካሄደው የፊልም ፌስቲቫል፤ 15 በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ አዳዲስና ከዚህ በፊት ለዕይታ የቀረቡ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር ተቀባይነትን ያተረፉ የሙሉ ጊዜና አጫጭር ፊልሞች እንዲሁም ዘጋቢ ፊልሞች  ለዕይታ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በፌስቲቫሉ ላይ የፊልምና በሌሎች የኪነጥበብ ዘርፍ ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ተማሪዎችን ጨምሮ በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።  
አዲስ አበባ በተካሄደው የፌስቲቫሉ የመዝጊያ ዝግጅት ላይ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባደረጉት ንግግር፤ “ሰብአዊ ክብር፣ ነጻነትና ፍትሕ ለሁሉም” የሚለው የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን መሪ ቃል ሁላችንንም ወደ ሰብአዊ መብቶች መሰረታዊ ነጥቦች መልሶናል ብለዋል።
አክለውም፤ “የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ከኪነጥበብ ዘርፉ ጋር ግንኙነት በመፍጠር እነዚህን መሰል ፌስቲቫሎች የሚያዘጋጁት በሥነ ጥበብና በኪነ ጥበብ ሥራዎች የሚተላለፉ መልእክቶች እንዲሁም ባለሞያ ያልሆንነው ሌሎች ሰዎች ስለምናስተላልፋቸው መልእክቶች በታሰበበትና በታቀደበት መልኩ እንድንጠነቀቅ ለማስታወስ ነው” በማለት አስረድተዋል።


Read 3261 times