Saturday, 31 December 2022 12:22

ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


     ከዕለታት አንድ ቀን፣ እመት ጦጢት፣ ከዛፍ ዛፍ  እየዘለለች ፍሬ ትለቅም ነበር፡፡
አያ ገበሬ ደግሞ ወደ እርሻ ሄዶ ዘር ዘርቶ መመለሱ ነው፡፡
“እመት ጦጢት እንደምንድነሽ?“ አላት፡፡
“ደህና ነኝ፤ አንተስ እንደምንድ ነህ?“ ጦጢት አፀፋውን መለሰች፡፡
“እኔም በጣም ደህና ነኝ፡፡”
“ሥራ እንዴት ነው?” አለችው፡፡
“ምንም አይልም፡፡ ዝናቡ ብቻ ለዘር አልተመቸኝም”
ጦጢት አሁን ወደ ጉዳዩዋ ገባች፡፡
“ለመሆኑ ዘንድሮ ምን ዘራህ?”
ይሄ ገበሬ በትክክል የዘራውን ቢነግራት እርሻው ውስጥ ልትቦጠቡጥበት ነው፡፡ ስለዚህ የዘራውን ትቶ ለጦጢት የማይመቻትን ነው መጥራት ያለበት፡፡
“እመት ጦጢት ዘንድሮስ ተልባ ነው የዘራሁት” አላት፡፡
ጦጢትም፤
“ይሁን እስቲ ወርደን እናየዋለን!” አለችው፡፡
እመት ጦጢት ሌሊቱን ስትቦጠቡጥለት አደረች፡፡
ገበሬ ተናዶ ሲያሳድዳት ከረመ፡፡
ጦጢት ነቅታ ኖሯልና ደብዛዋን አጠፋች፡፡
ብልጥ ለብልጥ ዐይነ-ብልጥጥ ይሏል ይሄው ነው!
***
ነገርን መሬት ወርዶ ማየት ብልህነት ነው!
መሬት ሳይወርዱ ሁሌ ወንበር ላይ  መቀመጥ አያዋጣም፡፡ ምናልባትም አንዳንዴ የማይቻል ነገር ነው!  ሥልጣን ብዙውን ጊዜ ይሞቀናል ተብሎ ቢታሰብም አንዳንዴ ብርድ ብርድ ይላል፡፡ ያንቀጠቅጣል፡፡ አፍና ቅብቅብ ሁልጊዜ አንበላም ይባላል፡፡ አያሌ ሰዎች በንግግር ጥበብ ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ሚዲያን የሙጥኝ ሲሉ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም የምላሥ ወለምታ በቅቤ አይታሽም የሚለውን ተረት ልብ ቢሉ መልካም ነወ፡፡
ለረዥም ዓመታት በመንግስት ዙሪያ የሚሰገሰጉና በሽር-ብር የሚኖሩ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ከትናንትና ፖለቲከኞች አወዳደቅ አይማሩም፡፡ ምክንያቱም አድር-ባይነትን እንደ ሙያ ይዘውታል፡፡ ያለ ፍሬንና ፍሬቻ መጓዝን አደገኛነት አይሰጉበትም፡፡ ቁልቁለትና ዳገት አይመርጡም፡፡ ትላንት የሰራውን ሰው “እሰይ!” ይሉታል እንጂ ነግ በኔ አይሉም፡፡ ምክር አይሰሙም፡፡ ሁሉን እንደ ምቀኛ ይቆጥራሉ፡፡ ሲቀናቸው ለሰርገኛው ሁሉ አንደኛ ሚዜ ናቸው፡፡
ሆኖም ሁኔታዎች ተለዋዋጭ ናቸው፡፡ የዕድገትና የለውጥ ህግ ያለ፣ የነበረ የሚኖር ነው፡፡ መለወጡን ማወቅና ሁሌ ለለውጥ መዘጋጀት ፣ በተለይ በመሪዎች ዘንድ ታላቅ ግዴታ ነው! አመራሮች እንደነበሩ እንደማይቆዩ፣  ሕዝብ ለውጥን መሻቱ አይቀሬ ነው፡፡
ይህን ደጋግመን ብለናል፡፡ ዛሬም እንላለን! በዚህ ረገድ ምሁራን ያላቸው ሚና በርካታ ነው፡፡ በየደረጃው የወረዳው፣ የቀበሌውና የቀጠናው ዘርፎች ሁሉ ዓላማቸውን አውቀውና ተረድተው መጓዝ አለባቸው፡፡ ያልተቀናጀ ትግል የትም አያደርስም፡፡
ከሁሉም በላይ አጥፊያችን መናናቅ ነው! ንቀት አገር ያደቅቃል፡፡ ኢኮኖሚን ይገድላል!
“ባለቤቱን ካልናቁ
አጥሩን አይነቅንቁ”
የምንለው ለዚህ ነው፡፡
ወደ አምባገነንነት ማምራት የሚመጣውም እንዲህ እያለ ነውና - እንጠንቀቅ!



Read 4953 times