Saturday, 27 October 2012 09:40

ፍቅርና ጉዞው…

Written by  Ks45soliyana@gmail.com ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(9 votes)

ለሁለተኛ ጊዜ ያፈቀርኩት ሀይገር ባስ ውስጥ ነው፡፡ ፍቅርና ጉዞ አንድ ናቸው፤ ሁለቱም ያስከፍላሉ፣ ሁለቱም ያደርሳሉ፡፡
ትላንትና ምሽት ሀይገር ባስ ውስጥ ሳለሁ የጀምስ ጆይስ መፅሀፍ ከሆነው “A portrait of an artist as a young man” ውስጥ በገፅ አርባ አምስት ላይ ያነበብኳትን አንቀፅ በአዕምሮዬ እያውጠነጠንኩ ነበር፡፡ በባሱ ውስጥ የተለያየ ሰው እየገባ ነው፡፡ የሹፌሩና የረዳቱ ምርጫ ቢሆን ካጠገቤ ላለው ወንበር ከፍዬ ብቻዬን ብቀመጥ እወድ ነበር፡፡ አልሆነም …፡፡ ካጠገቤ አንዲት ወጣት መጥታ ተቀመጠች፡፡ እንደተቀመጠች ይዛው የነበረውን መፅሀፍ ገልጣ ማንበብ ጀመረች፤ የአይኖቼ ብሌን ተቅበዘበዙ፡፡ ቃላቶች የጠገቡ ገፅ ሊመለከቱ ከመፅሀፉ ደፍ ስር ደጅ ጠኑ …
“… each man has his own particular paradise. For you, Paradise will be stocked full of books and big demijohns of ink. For someone else it will be full of casks of wine, of rum and brandy … for me paradise is this; a little perfumed room with gray colored dresses on the wall, scented soaps, a big bed with a good springs, and by my side the female of species…”

ከመፅሀፉ ጋር ግጥሚያ የፈጠርኩ መሰለኝ፡፡ የመጀመሪያዋን አንቀፅ አንብቤ እንደጨረስኩ ከመቀፅበት ቀና ብዬ ልጅቷን አየኋት፡፡ እጅግ በረዘሙ የአይን ሽፍሽፍቶች ብሌኖቿን ከአለም ደብቃ በዚህ ረቂቅ መፅሀፍ ውስጥ የተሰደደች ሴት ሆና አየኋት፤ የጉንጮቿ ግለት ከፀሀይ ንዳድ ሳይሆን፣ ከንባብ ጡዘት ያበራዩ የስሜት ቀለም እንደሆኑ አምኜ አየኋት፤ ተጠንቅቄ ቀልቤን ሳልለቅ፡፡ አይኔ ፈጠነብኝ … አምልጦኝ የተፈጥሮን ህግ ጣሰብኝ … አይኔ አፍ ሆነ … አወራ፡፡ 
“ላንቺ ገነት ምንድን ነው?”
መጠየቄን ያወቅሁት ቀና ብላ ከዚህ ቀደም ለሰው ልጅ ፍጥረተ አለም በሙሉ እንግዳ በሆነ አስተያየት ስታየኝ ነው፡፡ እንግዳ የሆነ አይን፤ ልቤ ድረስ ገብቶ ሸረከተኝ፡፡ እይታዋን አመለኩት፡፡
“ለምንድን ነው የጠየከኝ?”
“እኔጃ”
“ምን አልባት ገነት የምትለው የማስገጃ ቃል ባንተ መልስ ውስጥ ቢኖርስ?”
“ያልመለስኩልሽ፤ ቃላቶቼን ፈልጌ እስካገኝ ነው”
“ምን አልባት ቃላቶችህ እኔ ብሆንስ?”
“አንቺ ማነሽ?”
“ማንነቴ እንግዳ ከሆነው ስሜትህ አላቆህ ወደኔ ያመጣህ የራስህ መንፈስ ነው”
“ጥያቄዎቼን እየመለሽልኝ ነው…?”
“መልሶችህን በጥያቄህ እየነገርከኝ ነው”
መልሳ ወደ መፅሀፉ አቀረቀረች፡፡ ከኮተቤ ነበር ሀይገር ባሱ የተነሳው፣ አሁን ላምበረት ደርሷል፤ ልቤ ግን በጊዜ ቀመር ውስጥ ቀጥ ብሎ ከስርቻው ቆሟል፡፡ አሁንም ደግሜ አቀርቅራ ያለችውን ሴት አየኋት፤ ፀጉሯን አየሁባት (ጥቁር ፏፏቴ)፣ ገብቼ እንዳልሰምጥ አይኔን ከጥቁሩ ማዕበል ውስጥ አንቦጫርቄ አወጣሁት፡፡ በልቤ ላይ አይሆኑት መብረቅ ጣለችብኝ … ከየትም ያልተጀመረ ወሬ ትቀጥል ጀመር …
“አሁን ምን አልባት የማንበቢያ ጊዜዬን እየቀማህኝ ነው፣ እየቀማህኝ ያለውን ደግሞ ታውቃለህ፤ ፍቃድህ ከሆነ ሀሳብህን ከላዬ ላይ አንሳልኝ፤ ካልሆነ ዝም ብለህ አውራ፣ እኔም ላንብብ፤ በቃላቶችህ ተደብሬ ቢሆን ከቀደሙት ፌርማታዎች በአንዱ ወርጄ ሌላ መኪና በያዝኩ ነበር፡፡ ሆኖም የተመቸኝ እንግድነትህ ፍፁም በሆኘው ሀሳብህ ስለተመታ በራስህ መራቅህ እየሳበ ያመጣህቀ ከኔ ነው፤ ከኔ ላይ ውረድ፡፡”
“ቀና ብላ አየችኝ፡፡ ምዕራፎቿን በሙሉ ወደድኳቸው፣ ምዕራፎቿ ሁሉም ተሰባስበው የኔን መቅድም አጥፍተው መውጫዬ ላይ ሰቀሉኝ፡፡ የመውጫዬ ቃላት የተገመቱ እንደሆኑ የነገረችኝ እሷው ናት … ባይኖቿ ነው የነገረችኝ፡፡
“ደግሜ ላገኝሽ እፈልጋለሁ?”
“አሁንስ ደግመህ አግኝተህኝ እንዳልሆነ በምን አወቅህ?”
“ልከተልሽ እሻለሁ … የምትሄጂበትን እየረገጥኩ…”
“ታዲያ አንተ ለምን ትቀድመኛለህ”
“ስምሽ ማነው?”
“እመነኝ በዚህ ሰዓትና ቦታ ላይ ባንተ የተፈጠርኩ ሰው ነኝ … ስሜን ልታወጣልኝ የሚገባህ አንተ ነህ”
“ሚስጥረ አልኩሽ”
“እንዳልክ ይሁን”
እስራኤል ኤምባሲ ጋር ደረስን፤ ልቤ ላይ ቀልጣለች ሚስጥረ፣ ልቤን እያደሰችው ነው፡፡
“የት ነው ሰፈርሽ?”
“ወሰን ግሮሰሪ”
“ደግሜ ላገኝሽ እፈልጋለሁ?”
“የምታወራው ማንን እያዳመጥክ ነው?”
“ሁሉንም…”
“ችግሩ ሁሉም ውስጥ ያልሆንኩትን እኔን ማድመጥ ያቃተህ ጊዜ ነው”
ዝም ብላ አየችኝ፡፡ እንዳያት ብቻ የምታወራ እንዳይመስለኝ፣ አተኩሬ የፊቷን ብልቶች በሙሉ አደመጥኳቸው፡፡
“አሁንስ የምልህ ገባህ?”
“ገባኝ”
መገናኛ ስንደርስ ሁለታችንም ወረድን፡፡ ምንም ቃላት ሳንሰጣጥ እስከ ሀያ ሁለት ሰፈር ተጓዝን፡፡ ቃላት! ምንድናቸው ቃላት፣ ምንድናቸው እነዚህ የአንደበት ስዕሎች? ለመግባባት ነው የተፈጠሩት ወይስ ለመራራቅ? ታዲያ ለምን በፀጥታ ይሸነፋሉ፣ ማስረዳታቸው ለምን የዝምታ ዲቃ ድረስ መክተም አይቻለውም? ሄደው እስኪያመልጡን ዝምታዎቻችን ለህይወታችን ህይወቶች ናቸው፡፡
ሚስጥረን በዝምታ አፈቀርኳት፡፡
ሀያ ሁለት ስንደርስ፣ ለአፍታ ቆም ብላ እንደጉድ የሚተራመሰውን ሰው ተመለከተች፤ በስሱ ፈገግ አለች፡፡ ስለ ፈገግታዋ የፈጠራት ይናገር፣ እኔ ግን የፈጠራትን ፈገግታዋ ውስጥ አይቼዋለሁ፡፡ ዞር ብላ በላሙ አይኖቿ ውጥንቅጤን ካወጣችኝ በኋላ ፈጠን ፈጠን እያለች ታወራ ጀመር …
“ፀጥ ያለ ቦታ መሆን እፈልጋለሁ”
“እኔ ያንን ቦታ ልሆንልሽ እወዳለሁ”
“እንግዲያውስ ወደ ቦታህ ጥራኝ”
ሀሳቤን ፈተነችብኝ፡፡ ከፊቴ እንዳለች አንስቻት ወደ ህሊናዬ በመክተት የወደደችውን ብሰጣት ተመኘሁ፡፡ ሆኖም የተፈጥሮን ህግ እንዳትጥስ ተደርጋ የተፈጠረች እሷ ብቻ ነበረች፡፡ ቦታ አፈላለግሁኝ፡፡ አገኘሁ፡፡ የቦሌ መድኃኒያለም ቤተክርስቲያን ጀርባ፡፡
“ተከተይኝ?”
“የቴሌ ብራስን ታክሲ ይዘን ወደ መድሃኒያለም ተጓዝን፡፡ በመሀል በመሀል ቀና እያለች ታየኛለች፡፡ ቀና ስትል ሁለመናዋ ይናገራል፤ ካይኖቿ ላለመሰወር፣ ለመኖር ጥረት ማድረግ ጀመርኩኝ፡፡ ለቅፅበት አለመሞትን መረጥኩ፡፡
ቤተክርስቲያኑ ጋ ስንደርስ ወርደን በዝምታ ተሳለምን፤ በዝምታ ግቢውን አቋረጥን፣ በዝምታ ከጀርባ ያለው አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀመጥን፡፡ መቀመጣችን መሳፈራችን ሆኗል ለካ፡፡ የተሳፈርነው ፍቅር ወደሚባለው የመለኮት መገለጥ ድረስ ነው፤ እስከከፈልነው ድረስ እንጓዛለን፡፡
“ባል አለሽ?”
“እንዳልገምትህ ሆነህ ለእዚህች ቅፅበት መኖር አትችልም?”
“የወሰድሽብኝን መልሽልኝ”
“የወሰድከውን እወቀው”
“ወስጄብሻለሁ እንዴ?”
“አይኖቻችን ናቸው ቃላቶቻችን፤ ወፍ ስትተነፍስ ማድመጥ አይጠበቅብህም፤ በባህሩ ወለል ላይ ያለው የፀሀይ ድርሰትን ለመረዳት ሄደህ የማየት ግዴታ የለብህም፤ የህይወትህን መጀመሪያና መጨረሻ ማየት ቢያሻህ አሁንነትህን ካልረሳህ መልሶ በእጅህ አይደርስም፡፡ መጨረሻ ላይ የሚታይህ ሁሉ መጀመሪያ ነው፣ መጀመሪያውንም ያልተፈጠረ ዘላለም ነው፡፡”
“በህይወት ሳለሁ ቀኖቼን ሁሉ ልሰጥሽ ቃል እገባልሻለሁ፡፡”
“በህይወት ሳለህ ኖሮህ የማያውቀውን ብትሰጠኝ ፍቃዴ ነው፡፡”
“ወዴት እየወሰድሽኝ ነው ያለሽው?”
“አንተ ወደፈቀድከውና እኔ ወደምጠብቅህ፡፡”
“ከዚህ በላይ መፈቀርን ለምን ትፈልጊያለሽ?”
“ፍቅር የሚያዳልጥ የስሜት ሂደት ነው፣ አዳልጦህ የምትከትመው ደግሞ ዘላለም ውስጥ ነው፣ ዘላለም ውስጥ ሆነህ ደግሞ የምትጠይቀው ጥያቄ ካለህ ገና ያልደረስክበት አንተነትህን እንጂ ሌላ ያመለጠህን አታገኘውም፡፡ ልብ ብለህ አስተውል፤ መነጠቃችን የእርቃን ነፍስ ባለቤት አያደርገንም፣ ስጋችን የሚሸነግለን ከመሰለንም በእውነትም ህያው ሆኖ መኖር አይቻለንም፡፡”
“አሁን በስጋዬ የተሸነገልኩ ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡”
ምራቅ የሚያስውጥ ፈገግታ አሳይታኝ ልትናገር ቸኮለች፡፡
“የህሊናህ ጌታ ሁን፣ ፍርድን ከሌላ አትቀበል፣ የራስህ ሁን፣ ዝም ብለህ አትሰቃይ፤ በዚህ ሰዓት ያሻህን ብትዘላብድ የምትጠብቃቸውን ቃላቶች ላልሰጥህ እችላለሁ፣ ነፍስህን ጠለቅ ብለህ ተመልከታት፤ ስትሻው የነበረው ሙሉ ሆኖ ይታይሀል፡፡”
“እወድሻለሁ ሚስጥረ….”
ከት ብላ ሳቀችብኝ፡፡ በጣም የማሳዝን ፍጡር ሆኜ ራሴን ተመለከትኩ፡፡ ከሚስጥረ ጋር ሆነን በራሴ ላይ ሳቅንበት፡፡ ለረዥም ደቂቃ ሳቅን፡፡ በሳቃችን እንጠፍጣፊ መሀል ቀና ብዬ ሳያት መቼምም ልለያት የማልፈልጋት ሴት እንደሆነች አወቅሁ፡፡
በእጇ የያዘችውን በNikos Kazntakis የተፃፈው “Zorba the greek” የተባለ መጽሐፍ ወደኔ አቀረበችው፡፡
“ተቀበለኝ?”
ፈራ ተባ እያልኩ ተቀበልኳት፡፡
“መውረጃህ ደርሷል፡፡ ለእስካሁን ተሳፍረህ ስትሄድ የነበረው በኔ ውስጥ ነው፡፡ እስከከፈልክበት ድረስ ወስጄሀለሁ፡፡ አሁን ብቻዬን መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ይሄው ነው….”
“መጽሐፉን ታዲያ ምን ላድርገው?”
“ዘወትር በዚህ ሰዓት ከዚህ ቦታ እገኛለሁ፡፡ ቦታውን ፍፁም ወድጄዋለሁ፡፡ ብዙ የምሄድባቸው የስሜት ርቀቶች አሉ፤ ልሳፈርህ ፍቃደኛ ብትሆን ከዚህ መጽሐፍ ጋር ተመልሰህ ና፤ ይህ በእጅህ የያዝከው መጽሐፍ መጠበቄን ይናገርልኝ፡፡”
በሀይል አተኩሬ አየኋት፡፡ ሚስጥረ እንደሌሎቹ የከተማውን ቡቲክ በላያቸው ላይ ከምረው እንደሚንጠራወዙት የጨርቅና የኩል ነፍስ ያላቸው ሴት አይደለችም፡፡ ፍትወት ቅርባቸው ሆኖ በቅጽበቶች ልዩነነት ከአንድ ወንድ ገላ ወደሌላው የሚዘሉትን አትመስልም፤ በመቀመጫቸው እና በጡታቸው ትልቅነት ልክ ህይወታቸው የምትጠብባቸው ዓይነት ሆና የምታውቅ አይመስለኝም፤ ሚስጥረ ያልኳት፤ ያልተገለጠች፣ ገና ያልተደረሰበትን የሴት ልጅን ህቡዕ ስብዕና ገላልጣ ለብቻዋ የምትዝናና የተደበቀች ሴት ናት፡፡
ለጉድ የተጐለጐሉት አይኖቼን ድል ነስታ፣ በቀዘዙ ቃላት በችኮላ ተሰናበተቻቸው፡፡
ታዘዝኳት…፡፡
መኖሪያ ቤቴ ጋ ስደርስ መሽቶ ነበር፡፡ ደክሞኛል፡፡
በውስጤ ያቺ ሚስጥረን ምነው በህልሜ በቀጠርኳት ነበር፤ እያልኩ መቆጨት ላይ ነኝ፡፡ በሩን እያንኳኳሁ በድንገት … “መጣሁ” የሚለውን የልጄን የዮሴፍን ድምጽ ሰማሁት፣ እጅግ ደነገጥኩኝ፡፡ እየሄድኩ ነው እየመጣሁ? በሩ ተከፍቶልኝ በዝግታ ወደ ውስጥ ስገባ፣ ባለቤቴ ሩት ከበረንዳ ላይ ተቀምጣ እሳት እያቀጣጠለች አየኋት፡፡ ለምንድን ነው ይህን ሁሉ ውበት እርግፍ አድርጌ የረሳሁት? ለምንድን ነው ይህ አሁን የማየው ቅድም ሆኖ ቅድም ትዝ ያለለኝ?
ምግብ ቀርቦ ልጄና ባለቤቴ በሀይል እየተሳሳቁ ሲፈነጩ፣ እኔ ልቤ ውስጥ ባለች ስርቻ ስር አነባ ነበር፡፡ ለአስር አመታት በፍቅር የኖርኳት ሴት በአስር ደቂቃ ልዩነት አጣኋት፡፡ አሁን በዚህ ሰዓት በዚህች ሴት ውስጥ ሰጥሜ ወደ ፍቅር የሚወስደውን ትራንስፖርት ልይዝ አይቻለኝም፡፡ ምክንያቱም የምከፍላት አንዳችም የለኝም፡፡ ተዘርፌ ነው የመጣሁት፤ እሷ ይህን ብታውቅልኝ ምን ያህል በቀለለኝ፡፡ በዛች ሚስጥረ በለቀቀችብኝ እዚም ፈዝዤ ለባለቤቴ የምሰጣትን ተቀምቻለሁ፡፡
ልጄንም ተመለከትኩት፤ ሁሉም ነገሩ፣ ንብረቱ፣ ፍቅሩ፣ መተሳሰቡ፣ እውቀቱ፣ እውነቱ፣ መጠጡ፣ ምግቡ…ሁሉም ነገሩ ያለው ከኔው ዘንድ እንደሆነ አወቅሁኝ፡፡ ነገር ግን እንዴት አድርጌ ልስጠው፣ ያጠራቀምኩበትን መጋዘን ሚስጥረ በመክፈቻው ላይ ክታቧን አኑራበት በምን ልከፍለው ተቻለኝ፡፡ ያለኝን በሙሉ ቀምታኛለች፡፡
ያፈቀርኳትን ያህል ጠላኋት፡፡ በጃኒኒሻር ድግምት የተሰወሩትን ትውልዶች ጠርቼ፣ እንደዛር ውስጤን እንዳወከችው ውስጧን ቢያውኩባት ምርጫዬ ነበር፡፡
በእፀ - መሰውር ከአይነ ስጋዋ ተለይቼ፣ የደረሰችበት እየደረስኩ ያላትን ብቀማት ብዬ መናፈቅ ጀመርኩ፡፡ ወይ ደግሞ በእጄ ልትገባ የማይቻላትን፣ የህይወቴና የቀናቶቼ እብደቶች ከሆነችብኝ፣ በድግምት ያሻኝ እና የምጠላው ወንድ ስር ትጋደም ዘንድ አደርጋታለሁ፡፡ አዎ…ሚስጥረን ልኬቱ በማይታወቅ ፍቅር ውስጥ ገብቼ ጠላኋት፡፡
በምሽት ላይ ባለቤቴ ከእቅፌ ገብታ ፍፁም በሰላም ስታንቀላፋ ምቾቷን እየፈራሁት ተደሰትኩላት፡፡ መውደዴን ግን መጠራጠሬ የሞት ሽታን እንዳሸት አስገደደኝ፡፡ ከደረቴ ላይ ተኝታ፣ ውበቷ ግን ከህሊናዬ ውስጥ ተሸርሽሮ ጠፋብኝ፡፡ በዚህ ሰዓት የምወድቅለት ውበት የሚስጥረ ብቻ ነው፡፡ ሚስጥረ ደግሞ ባለቤቴ አይደለችም፡፡
በበነጋታው የቦሌ መድሃኒያለም ጀርባ ካለው ስፍራ አገኘኋት፡፡ ተቀምጣ ሩቅ እየተመለከተች ለራሷ ፈገግ ትላለች፡፡ በሀይል እየተራመድኩ ሄጄ ቀረብኳት፡፡ መናደዴን እንድታውቅብኝ ፈልጌያለሁ፡፡ በእጄ የያዝኩትን መጽሐፍ የተቀመጠችበት አግዳሚ ላይ ወረወርኩት፡፡ እሷ ግን የተለየች ነች፤ እንደዚህ አይነት ኮሶ ፊት አይታም ቢሆን ተረጋግታ ነው የምታወራው…
“ባለ ትዳር ነህ?”
“አዎ”
“ልጅ አለህ?”
“አንድ ልጅ አለኝ…”
አይኖቿን ከፍ አድርጋ በተመስጦ ወደ ሰማዩ ተመለከተች፡፡
ከላይ በሰልፍ የሚሄዱ እርግቦች ይታያሉ፡፡ ለሷ ብለው፣ በሷ ጌትነት ስር በትዕዛዝ የሚከንፉ ይመስላሉ፡፡ ዝግ ብላ መናገር ጀመረች…
“ይታይሃል…ከዛ ያለው የእርግቦቹ ሰልፍ? ማንም ጂኦሜትሪ አላስተማራቸውም፣ ነገር ግን የፈጠሩት መስመር ለአይን ትክክል ነው፤ የሚመራው የፊተኛው ወፍ መሪነቱን አያውቅም፤ ነገር ግን ሌሎቹ በሁሉ ነገራቸው እንዳይስቱ አድርጐ ከክንፉ ደርዝ ስር ያበራቸዋል፤ ሰማዩም ሜዳቸው ነው፣ አየሩ መጓጓዣቸው፣ ሀሳባቸው ደግሞ የሚደርሱበት ቦታ ነው…”
እንደህፃን ልጅ ቃላቶቿን የምከተለውን፣ እኔን ትኩር አድርጋ አየችኝ፡፡
“እንግዲያውስ እኔና አንተ በትላንት እና በነገ ባልተገደበ የጊዜ ርቀት ውስጥ እነዚህን እርግቦች መስለን አብረን ኖረን ነበር፡፡”
ፈገግ ብላ ታየኝ ጀመር፡፡ ሌሊቱን ሙሉ የወጠንኩት ውሳኔ ነበረኝ፤ ያንን ልታውቅ ይገባታል፡፡
“አንቺን መግደል አለብኝ፤ ከዛ በኋላ ተመልሼ ወደ ቤተሰቦቼ እቀላቀላለሁ፣ የቀማሁትን የባለቤቴን ውበት አስመልሳለሁ፤ የልጄን ፍቅር የሚስተካከለውንና ሊያሸንፈው የሚታገኝን ከውስጤ እሰርዘዋለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ የሚሆነው አንቺ ስትሞቺ ነው፡፡”
እሷ ግን ልክ ስወለድ ወደነበረኝ ንፅህናዬ በአይኖቿ ትመልሰኛለች፡፡ እጅግ ሃያል የሆነ ሃጥያትን ተሸክሜ ሳለሁ በአንድ እይታ ብቻ ታነፃልኛለች፡፡
“ባትገለኝ ነው የሚሻልህ፡፡ ብትገለኝ እስከዘላለም ድረስ ይዘኸኝ ትኖራለህ፡፡ የምትነካው በሙሉ እኔ እሆናለሁ፤ የምትሻው በሙሉ ከኔ መዓዛ የራቀ አይሆንም፤ ምንም ላልከፈለ ምንም አትስጠው፣ በግድ ከፍለህም በግድ አትንጠቅ፣ አሁን ሂድ ወደቤተሰቦችህ፡፡ ወደ ፍቅር የምታደርገው ጉዞ ክፍያው ብዙ ነው…ከስሜትም ይልጥ የሚያስከፍል፡፡ መስጠት ይኖርብሃል፣ የምትሰጠው ደግሞ ምን እንደሆነ እኔ ልነግርህ አይቻለኝም፡፡ ካንተ ጋር በመተዋወቄ ደስተኛ ነኝ፡፡”
እተቀመጠችበት እንዳዘነች አቀረቀረች፤ እኔም እጅግ ልቆጣጠረው ያቃተኝን እንባዬን ከታፋዋ ስር ተንበርክኬ አዘነብኩት፡፡ እጅግ በጣም እንደማፈቅራት ገባኝ፡፡ እዛው እያለቀስኩ በሀይለኛ ድካም ተጠምጄ እንቅልፍ ወሰደኝ፡፡
ስነቃ ፀጉሬን እያሻሸች፣ አይን አይኔን እያየችኝ አገኘኋት፡፡
“እንዳልቀሰቅስህ ብዬ ነው፡፡”
ሰዓቱ ነጉዷል፡፡ በድንጋጤ ተነሳሁ፣ በቦታው የሚያልፈው ሰው በሞላ እየገላመጠን ነው ሚስጥረ ግን የአይናቸውን ንቀት የሚያጠፋ ስብዕና በውስጧ ስለያዘች ለኔም አበድራኝ፣ በቦታው ምንም የማንፈራ ሁለት የህይወት ልጆች ሆነን ነበር፡፡ ከተቀመጥንበት ተነስተንም ብዙ ተጓዝን፡፡ በስተመጨረሻ አንድ ማሳለጫ ጋር ቆማ ወደኔ በትኩረት ስትመለከት ከቆየች በኋላ ቆጣ ባለ አንደበት ተናገረችኝ… “ካሁን በኋላ መገናኘት ይኖርብናል ብለህ የምታስብ ከሆነ፣ ከህይወት በምታገኘው አሰስ ገሰስ መጠርቃት ያቃተህ ነህና እራስህን ታዘበው፤ ፍፁም ልትሸሸኝ ብትሞክር፣ የፍርሃትህን ጽኑነት ያልተረዳውን ህሊናህን ያልተረዳህ ግራ ገብ የሆንክ እንግዳ ሰው መሆንህን ተረዳ፤ ቤተሰቦቼን ጥዬ ካንቺ ጋር ረዥም መንገድ እጓዛለሁ የምትል ከሆነ፣ የምትለውን የማታየው መደንገጥ ቢሰለችህና ቢቀፍህ ነው ብዬ የምተረጉምብህ አይምሰልህ፡፡” ተንጠራርታ ጉንጬን ሳመችኝ፡፡ ቀልቤን ማዕበል ሆኖ ያናወጠው ፈገግታዋን ከዓይኔ ላይ አትማብኝ ከጨለማው ሰመጠች፡፡ ከመቅጽበት ቦታ መፈለግ ጀመርኩ፤ ይህችን ሴትና ቤተሰቦቼን የማላገኝበት፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህን አሁን የተሸከምኩትን ማንነት የሚነጣጥለኝ ቦታ፣ ቢቻል “እዚህ ጥግ ስር” የማልለው ቦታ፡፡ ያልተፈጠረ ቦታ ፈለግሁ፡፡
በፍጥነት መሳፈር እንዳለብኝ ገባኝ፡፡ ርቄ መጥፋት አለብኝ፤ ስጋለብ ኖሬያለሁ፤ አሁን ጋላቢው እኔ ነኝ፡፡ ዝም ብዬ ረዥም ረዥም፣ ርቆ የሚወስድ፣ በዘላለማዊነት ተምሳሎት በነፃ የተለቀቀ መንገድ ፍለጋ ባይኔ ማሰንኩ፡፡ አንድ ረዥም መንገድ አገኘሁ፡፡ ሮጥኩ፤ ሮጥኩ…የጣልኩትን ላላይ…ፍርሃቴን ልጥስ…ከእስር ቤቱ ላመልጥ…ከስሜት የራቀውን ቅርሴን ሸጬ ወደ ፍቅር ልሳፈር…የጣልኩትን ላላይ…ሮጥኩ…ሮጥኩ….፡፡

Read 16753 times