Saturday, 31 December 2022 12:04

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 (በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ውዝግብና ተያያዥ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችን በተመለከተ)


           በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በአፋን ኦሮሞ ትምህርት በሚሰጥባቸው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማን መስቀልና የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እንዲዘመር ከመደረጉ ጋር ተያይዞ ውሳኔውን በሚቃወሙና በሚደግፉ ተማሪዎች መካከል በተከሰተው ውዝግብና ግጭት ምክንያት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ያስከተለውን የሰብአዊ መብቶች እንድምታ በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ምንም እንኳን የጸጥታው ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በተወሰነ ደረጃ ጋብ ያለ ቢሆንም፤ ለወደፊቱም ይህን መሰል ሁኔታዎችንና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በዘላቂነት ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፤ ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትልና ምርመራ የተረጋገጡ ግኝቶችን፣ ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው የሕግ ማዕቀፎች አንጻር በመተንተን ጭምር ይህን ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ ይወዳል፡፡
ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራና ክትትል፣ የጸጥታ መደፍረስ የተከሰተባቸውን ሁሉንም ትምህርት ቤቶች የሚሸፍን ምርመራ ለማካሄድ ባይቻልም፤ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን፣ መምህራንና ኃላፊዎችን፣ በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የነበሩ ተማሪዎችንና ሌሎች ተጠርጣሪዎችንም በማነጋገር፣ የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች የነበሩ ምስክሮችንና የተማሪዎች ወላጆችን እንዲሁም የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሌሎች ኃላፊዎችን በማነጋገርና መረጃዎችና ማስረጃዎች በማሰባሰብ ስለ ጠቅላላ ጉዳዩ ተገቢውን ግንዛቤ ለማግኘት ተችሏል፡፡
ዋና ዋና ግኝቶችና የሰብአዊ መብቶች እንድምታዎች
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ በአፋን ኦሮሞ ትምህርት በሚሰጥባቸው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ መነሻው፣ በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማን መስቀልና የክልሉ መዝሙር እንዲዘመር ማድረግን በሚመለከት የተለያየ ሃሳብና ፍላጎት ባላቸው ተማሪዎችን ጨምሮ የትምህርት ቤቶቹ ማኅበረሰብ አባላት መካከል የተፈጠረ አለመግባባትና ግጭት ነው፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በአፋን ኦሮሞ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ የመስቀልና የክልሉን መዝሙር የመዘመር መብት አላቸው በሚል መነሻ በትምህርት ቤቶቹ ግቢ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ ከፌዴራሉ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ጎን በመስቀልና ጠቅላላው ተማሪዎች የክልሉን መዝሙር በመዘመር የሰንደቅ ዓላማ ሥርዓቱን እንዲያከብሩ በመደረጉ በየትምህርት ቤቶቹ በሚገኙ ከፊል የትምህርት ቤቶቹ ማኅበረሰብ አባሎች እርምጃው ሕጋዊ መሠረት የለውም በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
በአብዛኛው ቦታዎች የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ መሰቀልና የክልሉ መዝሙር መዘመርን በሚደግፉና በሚቃወሙ ተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ሁከት፣ ረብሻና ግጭት፤ እንዲሁም የፖሊስ አባላት ሁኔታውን ለመቆጣጠር በወሰዱት የእስር እርምጃ የሰብአዊ መብቶች አሉታዊ እንድምታ ያስከተለ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
የትምህርት ሂደት በመስተጓጎሉ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ከባድና ቀላል የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሷል፣ የተማሪዎችና የትምህርት ቤቶች ንብረት ወድሟል፣ ሕፃናት ተማሪዎች ለአካላዊ እንግልትና ከሕግ ውጭ ተገቢ ላልሆነ እስር ተዳርገዋል፡፡
ይሁንና በማኅበራዊ ሚዲያና በአንዳንድ ተቋሞችም የተዘገበውና ጉራራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ከፍተኛ 12 ትምህርት ቤት ውስጥ የነበረ ተማሪ ሕይወት ጠፍቷል የተባለው ትክክለኛ መረጃ አለመሆኑንና በዚህ ክስተት የደረሰ የሕይወት መጥፋት አለመኖሩን ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡
በንብረት ላይ የደረሰው ውድመትና በረብሻው ወቅት በተማሪዎች ላይ የደረሰው ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት በተማሪዎቹ የእርስ በእርስ ግጭት የተከሰተ ሲሆን በአካባቢው የነበሩ በርካታ ምስክሮች ለኮሚሽኑ እንዳስረዱት፤ ፖሊስ ብዙ ተማሪዎችን ከማሰሩ በስተቀር፤ አብዛኛዎቹ የፖሊስ አባላት በጥንቃቄና ተመጣጣኝ በሆነ እርምጃ ሁከቱን ለማረጋጋት ይጥሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ፖሊስ አብዛኛዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ተጠርጣሪ ተማሪዎች በፍጥነት ወደ የሕፃናት ልጆች ችሎትና መደበኛ ፍርድ ቤት እያቀረበ ከፍርድ ቤት በተሰጠ የዋስትና መብት በተለያየ ጊዜ ከእስር ተለቀዋል። በተለይም ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ፖሊስ በፍጥነት ወደ ሕፃናት ችሎቶች እንዲቀርቡ እያደረገ ወዲያውኑ ተለቀዋል፡፡
በአንጻሩ እጅግ ብዙ ዕድሜያቸው በአብዛኛው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ተማሪዎች ከመነሻውም ቢሆን ለእስር መዳረጋቸውና ለተለያየ ጊዜ መጠን በእስር መቆየታቸው ተገቢ ያልሆነና ለነገሩ ሁኔታም ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ነው፡፡
የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ በሆነ እርምጃ ሁከቱን በመቆጣጠር፣ እጅግ ቢበዛ ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ ተማሪዎቹን በየትምህርት ቤታቸው ግቢ ወይም ባሉበት ቦታ እንዲቆዩ አድርገው፣ በቀጥታ በወንጀል ተግባር ላይ የነበሩ ተማሪዎች ካሉም እንደአስፈላጊነቱ እጅግ አጭር ለሆነ ጊዜ ብቻ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቆይተው ሳይውል ሳያድርና እንደ አግባብነቱ በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 28(1) መሰረት በፖሊስ ጣቢያ በሚሰጥ ዋስትና መልቀቅ ሲገባቸው፤ ከዚህ ውጪ ብዙ ሕፃናት ተማሪዎችን የተሟላ አገልግሎት በሌላቸውና ለአካለ መጠን የደረሱ ተጠርጣሪዎች በሚታሰሩባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች አስረው ማቆየታቸው የአስፈላጊነት፣ የሕጋዊነትና የተመጣጣኝነት መርሆችን ያልተከተለ የሕፃናትን መብቶች የሚጥስ ተግባር ነው፡፡
በተማሪዎች ተፈጽሟል የሚባል ጥፋት ቢኖርም እንኳን ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በሚመለከተው የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችና አግባብነት በአላቸው የኢትዮጵያ ሕጎች መሠረት ለሕፃናት ልጆች የሚገባው የሕግ ከለላ እንደተጠበቀ ሆኖ የማጣራት ሥራ ከማከናወን በስተቀር፤ ሕፃናት ተማሪዎችን ሊያውም በጅምላ ለእስር መዳረግ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ በመሆኑ ለወደፊቱ ሊደገም የማይገባ ነው፡፡
2. የሰንደቅ ዓላማውና የብሔራዊ መዝሙር ውዝግብና አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች እንድምታው
ለዚህ ሁከትና ለደረሰው የሰብአዊ መብቶች ጉዳት መነሻ ምክንያት የሆነውን የሰንደቅ ዓላማ እና የብሔራዊ መዝሙር አጠቃቀም ሕጋዊ መሠረት እና ምክንያት መፈተሽም ለወደፊቱ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን ለመከላከል አስፈላጊ ነው፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 እንደተደነገገው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ያለው፣ ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ መንግሥት የሆነ እና የከተማው ነዋሪዎችም በፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወከሉ ሲሆኑ፤ የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም የሚጠበቅለት መሆኑና ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰን የተገለጸ ቢሆንም፣ እስከአሁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዝርዝር ሕጉን ያላወጣ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥት የግዛት ወሰን ውስጥ እና የክልልና የከተማ መስተዳድሮችን ጨምሮ በውጭ ሀገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች፣ ንግድ መርከቦችና አውሮፕላኖች ላይ ተፈጻሚ በሚሆነው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ በየቀኑ ወይም ቢያንስ በብሔራዊ በዓል ቀን የሚሰቀልባቸው ቦታዎችና የሰንደቅ ዓላማ አሰቃቀልና አጠቃቀም ሥነ ሥርዓት በዝርዝር ተደንግጓል፡፡ 
በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 3 (3) መሠረት፤ ክልሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና አርማ ሊኖራቸው እንደሚችል በደነገገው መሠረትና በየክልሎቹ በጸደቁ የክልል ሕገ መንግሥትና የክልል ሰንደቅ ዓላማ አዋጆች መሠረትም የየክልሉ የሰንደቅ ዓላማ አሰቃቀልና አጠቃቀም ሥነ ሥርዓት የሚደነግጉ ሲሆን ሁሉም የክልል ሰንደቅ ዓላማ አዋጆች በየክልሉ ከፌዴራሉ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ጋር በአንድነት ተፈጻሚ የሚሆኑ ናቸው ፡፡
ከዚህ ውጪ የአንድ ክልል ሰንደቅ ዓላማ በሌላ ክልል ወይም ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ወይም የግል ተቋሞች ውስጥ እንዲሰቀል የሚያስችል የሕግ መሠረት የለም፡፡
በአንጻሩ በየትኛውም ክልል ወይም የከተማ አስተዳደር የአንድ የሌላ ክልል መለያ በሆነ ተቋም ሕንጻ ላይ ወይም ግቢ ውስጥ (ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሕንጻዎች ላይ) በክልሉ ወይም በከተማው መስተዳድር ዕውቅና የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ ከፌዴራሉ ሰንደቅ ዓላማ ጋር በአዋጅ ቁጥር 654/2001 በተመለከተው መሠረት መስቀል የሚከለክል የሕግ ምክንያትም የለም፡፡
ከዚህ በላይ ከተገለጹት ሕጋዊና ምክንያታዊ የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ውጪ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ውስጥ የሚገኙ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ወይም የሕዝብ አገልግሎት ተቋሞች የሌላ ክልል ሰንደቅ ዓላማን በአስገዳጅነት ለመስቀል መጣር ሕጋዊ መሠረት የሌለው ከመሆኑም በላይ አላስፈላጊ ውዝግብና ሁከት በመፍጠር ለሰብአዊ መብቶች መጣስ ሥጋት የሚፈጥር ድርጊት በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡
በሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት ወቅት የሚዘመረውን ብሔራዊ መዝሙር በተመለከተ በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 4 በግልፅ እንደተመለከተው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር አንድ ብሔራዊ መዝሙር ሲሆን፤ በአዋጅ ቁጥር 673/2002 አንቀጽ 5 እንደተመለከተው ክልሎች በሕግ በወሰኑት የሥራ ቋንቋ የብሔራዊ መዝሙሩ የግጥም ይዘትና ዜማ እንደተጠበቀ ሆኖ በክልሉ የሥራ ቋንቋ በማስተርጎምና በየክልሎቹ ምክር ቤቶች በማስፀደቅ ብሔራዊ መዝሙሩ እንዲዘመር ማድረግ አለባቸው፡፡
ከዚህ ሕጋዊና ምክንያታዊ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር አጠቃቀም ውጪ አላስፈላጊ ውዝግብና ሁከት መፍጠር ለሰብአዊ መብቶች መጣስ ሥጋት የሚፈጥር ድርጊት በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡
በተጨማሪም መንግሥት በሰብአዊ መብቶች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ውሳኔዎች፣ ደንቦች፣ ፕሮግራሞች፣ መርኃ ግብሮች ወይም አሠራሮች ሲዘጋጁ ወይም ከመተግበራቸው በፊት በሰብአዊ መብቶች ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አሉታዊ ውጤቶች አስቀድሞ መለየት፣ ማጤንና መከላከል ወይም መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል። ይህም የመንግሥት ደንቦች፣ ፕሮግራሞች፣ መርኃ ግብር ወይም አሠራሮች መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን ከማክበር፣ ከማስከበር እና ከማሟላት አኳያ ካሉት ግዴታዎች ጋር እንዳይቃረን  ለማድረግ ያስችላል።
3. ስለ ሕፃናት ተማሪዎች ልዩ ጥበቃ
በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችና በኢትዮጵያም ሕጎች መሠረት የሕፃናት ልዩ ልዩ መብቶች የተጠበቁ ሲሆን፤ በተለይ የሕፃናት ልጆች በትምህርት ቤትና አካባቢ የሚደረግ ልዩ ትኩረትና ጥበቃን በሚመለከትም ዓለም አቀፍ ግዴታዎችና መርሆች አሉ፡፡
ከእነዚህም ውስጥ፡-
በትምህርት ቤቶች ውስጥ አመጽ፣ ማስፈራራትና የኃይል እርምጃ የሕፃናት ልጆችን በምቹ ሁኔታ የመማርና የማደግ መብት የሚጎዳ፣ ለሥነ ልቦና ጉዳት የሚያጋልጥና አጠቃላይ የሆነ ፍርሀት፣ ሥጋትና ጭንቀት በማሳደር ትምህርትን፣ ዕውቀትንና ዕድገትን የሚጎዳ በመሆኑ ይህን መሰል ሥጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን በሙሉ ማስወገድ አስፈላጊ ነው፣ 
በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሕፃናት ልጆች የሰው ልጆች ክቡርነትና እኩልነትን፣ የሃሳብ ልዩነትና መቻቻልን እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ሙሉ እሴቶችን በሰላማዊ መንገድ የሚማሩበት የሚለማመዱበትና የሚያጎለብቱበት ስፍራ ስለሆነ፤ ሕፃናት ልጆችን እና ተማሪዎችን በሚመለከታቸው ጉዳይ በማማከር፣ በማሳተፍና በማድመጥ የትምህርት ቤታቸው ሕይወት ውስጥ ፈቃደኛ ተሳታፊዎች ማድረግ እንጂ በኃይል፣ በዛቻ፣ በማስፈራራት፣ በማስጨነቅና በሥጋት ማስተማርና ማስተዳደር ተገቢ አይሆንም፡፡ 
ልጆች በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ፣ ሃሳባቸውንና ተቃውሟቸውን የመግለጽ ነጻነት ያላቸው እንደመሆኑ መጠን አስፈላጊ ክህሎቶችን የሚያጎለብቱበትን መብታቸውን በአግባቡ የሚጠቀሙበትን ምቹ ሁኔታ እና ድጋፍ በትምህርት ቤቶች ውስጥም ማመቻቸት ተገቢ ነው።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን:-
ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወደፊትም እንዳያጋጥሙ ለችግሩ መንስኤ ለሆነው የሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ውዝግብ ሕፃናትን ጨምሮ ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ግልጽ የሆነ የሕግ እና ፖሊሲ መፍትሔ በማበጀት ዘላቂ እልባት በመስጠት፣ እንዲሁም አሁን በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎችና የሰብአዊ መብቶች መርሆችን በማክበርና በማስከበር የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በጋራ እንዲከላከሉ፤ በተጨማሪም የየትምህርት ቤቶቹና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በሰላም፣ በመቻቻል እና የሃሳብ ልዩነትን በመቀበልና በሰላማዊ መንገድ ብቻ በመፍታት ላይ ተመሥርቶ የመፍትሔ አካል እንዲሆን አበክሮ ያሳስባል፡፡


Read 4653 times