Saturday, 27 October 2012 10:20

ቅድመ ማረጥ ... (periomenopause)

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(7 votes)

‹‹...የአንዲት ሴት እድሜ በአርባዎቹ ወይንም በሀምሳዎቹ አመታት መጀመሪያ ከሆነ ምናልባትም በተወሰነ ደረጃ ቅድመ ማረጥ (periomenopause) የሚባለው ደረጃ እየደረሰች በመሆኑ አንዳንድ ምልክቶችን ልታይ ትችላለች፡፡ በቅድመ ማረጥ ወቅት አንዳንድ የጤና ምልክቶችን በመመልከት ላይ ከሆነች ወደ menopause ወይንም የወር አበባ መቋረጥ (ማረጥ) እየደረሰች መሆኑን ልብ ልትል ይገባታል፡፡››
ምንጭ/ perimenopause symptoms.org
ቅድመ ማረጥ ወይንም (periomenopause) ማለት ምን ማለት ነው?

ቅድመ ማረጥ ለምን ያህል ጊዜ ሊቆይ ይችላል?
ቅድመ ማረጥ ከጤና ጋር በተያያዘ ምን ምልክት ያሳያል?
የሚሉትንና ሌሎች ተያየዥ ጥያቄዎችን ያነሳነው ለጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ ሲሆን ለጥያቄዎች መነሻ የሆነንም ከላይ በምንጭነት የተጠቆመው ገጽ ነው፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን በለጠ በካዲስኮ አጠቃላይ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሐኪም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ኢሶግ/ በቅድመ ማረጥ (periomenopause) ዙሪያ ያለው ግንዛቤ ምን ይመስላል;
ዶ/ር የወር አበባ ለመቋረጥ በሚያስብበት ወቅት ወይንም ሴቶች ለዚህ እድሜ በሚደርሱበት ወቅት ያለው የጤናና ሌሎች ተያያዥ ሁኔታዎች በሌላው አለም ትኩረት ተሰጥቶት ብዙ ስራ የሚሰራበት ነው፡፡ በእኛ ሀገር ግን ስለሁኔታው ትኩረት ሊሰጥና የተለየ የስራ እንቅስቃሴ ሊደረግ ቀርቶ... ሴቶቹ እራሳቸው ጭምር ማረጥ ወይንም የወር አበባ መቆምን በሚመለከት ያላቸው እውቀት የተወሰነ ነው፡፡ እንዲያውም የወር አበባ ሲቋረጥ የእድሜ መግፋት የመሳሰለውን ነገር ከማሰብ ባሻገር ስለጤና ሁኔታ መለወጥ ምንም የሚያስቡት ነገር የለም ፡፡ በጤና ባለሙያውም በኩል በአብዛኛው ደንበኞች መጥተው ሲያማክሩ ካልሆነ በስተቀር እንደ አንድ የጤና ጉዳይ ተነስቶ ለውይይት እንኩዋን የሚቀርብበት ጊዜ ባለመኖሩ ጥያቄው መነሳቱ ግንዛቤን ስለሚያሳድግ ጥሩ ነው፡፡
ኢሶግ/ ቅድመ ማረጥ (periomenopause) በየትኛው እድሜ የሚከሰት ነው?
ዶ/ር የወር አበባ ከመቆም በፊት ያለው ጊዜ ቅድመ ማረጥ (periomenopause) ይባላል፡፡ ይህም ወቅት በአንዲት ሴት ተፈጥሮአዊ የሆነ ሂደት የሚካሄድበት ነው፡፡ አንዲት ሴት በእናትዋ ሆድ ውስጥ በእርግዝና ላይ እያለች ወደ ሰባት ሚሊዮን ያህል እንቁላል አላት፡፡ ሴት ልጅ ስትወለድ የነበራት ሰባት ሚሊዮን እንቁላል ወደ ሁለት ሚሊዮን ዝቅ ይላል፡፡ ይህም በተፈጥሮ ቀስ በቀስ እንቁላሎቹ እየከሰሙ ስለሚሄዱ ነው፡፡ በመጀመሪያው አምስት ወር ገደማ እንቁላሎች የመራባት ሁኔታ ያላቸው ሲሆን እስከሰባት ወር ድረስ የደረሰው ቁጥራቸው ከዚያ በሁዋላ ደግሞ እየከሰሙ በመሄድ ይቀንሳሉ ማለት ነው፡፡ ከዚያ በሁዋላ ደግሞ አንዲት ሴት የመጁመሪያውን የወር አበባ ስታይ ማለትም እስከ አስራ ሶስት አመት እድሜ ድረስ እንደገና እንቁላሉ ከ2 ሚሊዮን ወደ አራት መቶ ሺህ ዝቅ ይላል፡፡ ሴቶች የወር አበባቸው ከመጣ ወይንም መውለድ ከጀመሩ በሁዋላ እና ወደማረጥ እስከሚደርሱበት ድረስ እስከነጭርሱንም ይጠፋሉ ባይባልም በየጊዜው ቁጥራቸውን መቀነሳቸውን ግን አያቆሙም፡፡ ይህ የእንቁላል ቁጥር ከተወሰነ በታች ሲደርስ ግን ሴቶችን ሴቶች የሚያሰኘው ከዘር ማፍሪያ አካባቢ የሚመነጨው ኢስትሮጂን የሚባለው ሆርሞን እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ኢስትሮጂን በደም ውስጥ ያለው መጠን እየወረደ ሲሄድ እነዚህ የቅድመ ማረጥ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ እድሜውም ከአርባ አምስት እስከ ሀምሳ አመት ገደማ ነው፡፡
ኢሶግ/ ሴቶች ለቅድመ ማረጥ የሚደርሱበት እድሜ ከአርባው ዝቅ ሊል አይችልምን?
ዶ/ር የቅድመ ማረጥ እድሜ ከ 45 አመት ጀምሮ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን ወደሰላሳውም ዝቅ ብሎ የሚጀምርበት ወቅት እንዳለ ይታያል፡፡ ወደ ሰላሳው አመት ዝቅ የሚለው ግን በአብዛኛው ከጤና ጋር በተያያዘ በሚሰጥ ሕክምና ...ለምሳሌ ሁለቱም የዘር ማፍሪያ እና ማህጸን በኦፕራሲዮን የሚወጣ ከሆነ...በመሳሰሉት ምክንያቶች የሚከሰት ነው፡፡ በእርግጥ ከአርባ አመት በታች የወር አበባ መቋረጥን ምክንያት በአብዛኛው ማወቅ የማይቻልበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ይህ ግን የሚገለጸው እንደህመም እንጂ እንደጤናማ ሁኔታ ስለአይደለ ጥብቅ የሆነ የህክምና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከአርባ አመት በሁዋላ የሚከሰተው ግን ሴት ልጅ በእድሜ እርከንዋ የእንቁላል ቁጥር ቀስ በቀስ እየወረደ በመምጣቱ ምክንያት የሚከሰት ስለሆነ የህመም ሳይሆን ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው፡፡
ኢሶግ /ምልክቶቹ ምንድናቸው? ደረጃስ አላቸው?
ዶ/ር ዋናው እስከ 75ኀ በላይ ባሉት ሴቶች ላይ የሚታየው ሙቀትና ላብ የማላብ ስሜት ሲሆን በተለይም በለሊት ወቅት ከፍተኛ የሆነ ላብ ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ይህንን ሙቀት ብዙዎች ሊቋቋሙት ስለማይችሉ ሲበሳጩ ይታያል፡፡
ይህም በአብዛኛው የኢስትሮጂን ማነስና በዚያም ምክንያት የሚከሰተው ከፒቱታሪና ከአንጎል ስር በሚመነጨው ንጥረ ነገር መጨመር ምክንያት ሙቀትን ያለመቋቋም ሁኔታ ይከሰታል፡፡
ይህም መጠኑ የሚለያይ ሲሆን አንዳንድ ሴቶች በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ምልክቱን ሲያዩ አንዳንዶች ደግሞ በየአንዳንድ ሰአቱ ልዩነት ይህንን ምልክት እያዩ ከሁለት እስከአራት ደቂቃ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡
የላይኛው የደረት ክፍል ወይንም ከፊት ላይ የማቃጠል ...ላብ የማመንጨት...ልብ የመምታት ስሜት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በተለይም ምልክቱ ማታ የሚከሰት ከሆነ የእንቅልፍ መዛባት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል፡፡
ኢሶግ/ ቅድመ ማረጥ (periomenopause) ምልክቶች ከሚባሉት መካከል የልብ ምት እንዴት ይገለጻል?
ዶ/ር FSH(follicle Stimulating Hotmone) መጠኑ ከፍ ሲል የሙቀት መጠን መጨመርን ከደምስርና ከነርቭ ሲስተም ጋር በተያያዘ መልኩ የሚመጣ ለውጥ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ በዚህም ምክንያት የደም ስሮች መስፋት ይከተላል፡፡ በጭንቅላት ውስጥ የሰውነትን ሙቀት የመቆጣጠር የስራ ድርሻ ያለው ቅመም የኢስትሮጂን መጠኑ ሲያንስ አብሮ ስለሚያንስ መደበኛ ስራው ይዛባል፡፡ ስለዚህ ይህ ሁኔታ ልብ ላይም የራሱ የሆነ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ልብ ከትክክለኛው የምት መጠኑዋ ከፍ ባለ ማለትም ወደ 80 እና 90 እንድትመታ ይሆናል፡፡ ይህ የልብ ምት በትክክል በዚህ ጊዜ ተብሎ የሚገለጽ ሳይሆን ባሰኘው ሰአት የሚከሰት እና ለተወሰነ ጊዜ በጥድፊያ ከመታ በሁዋላ ሊመለስ የሚችል ግን አስደንጋጭ ስሜትን የሚፈጥር ነው፡፡
ኢሶግ/ ቅድመ ማረጥ ከጡት ጋር በተያያዘ የሚያሳየው ምልክት አለውን?
ዶ/ር ጡትም እንደማህጸን ለሆርሞኖች የራሱ የሆነ ምላሽ አለው፡፡ ኢስትሮጂን የሚባለው ለሴት ልጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ሆርሞን በከፍተኛ ሁኔታ ዝቅ የሚለው በትክክለኛው የማረጥ ወቅት ነው፡፡ በሽግግሩ ወይንም በቅድመ ማረጥ ጊዜ ግን በተወሰነ ደረጃ የሚኖር ስለሆነ ባለው ተፈጥሮአዊ ሁኔታ አንዳንዴ መጠኑ ከፍ የሚልበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ኢስትሮጂን መጠኑ ከፍ ብሎ በሚመረትበት ወቅት ደግሞ የጡት መጠኑ ከፍ የሚልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በዚህ ጊዜ ልክ በእርግዝና ወቅት እንደሚኖረው ስሜት ሁሉ የህመም ስሜት እና እብጠት ይኖራል፡፡ ነገር ግን ይህ ከወር አበባ መቋረጥ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው? ወይንስ በሌላ ሕመም ምክንያት ነው? የሚለውን ወደሐኪም በመሄድ ሳይዘናጉ ማጣራት ተገቢ ነው፡፡ በእንደዚህ ያለው አጋጣሚም ሆነ በማንኛውም ጊዜ የጡት ካንሰር የሚያጋጥምበት ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል የራስን ምክንያት እየፈጠሩ ወይንም እየተጠራጠሩ ችላ ማለት አይገባም፡፡
ኢሶግ/ ቅድመ ማረጥ (periomenopause) ከወሲባዊ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ምን ስሜት ይፈጥራል?
ዶ/ር ወሲብን በመፈጸም ረገድ አስፈላጊ የሆኑ ተፈጥሮአዊ ሂደቶች አሉ፡፡ በግንኙነት ጊዜ ስሜትን እንደነበረ ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችለው ሁኔታ ይለወጣል፡፡በቅድመ ማረጥ ጊዜ እንቁላል መውጣቱን ስለሚቀንስ እና የወር አበባ ኡደት ስለሚዛባ ወሲብ ለመፈጸም የሚያስችሉት ስሜቶች ይደበዝዛሉ፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ ኢስትሮጂን እያነሰ ሲሄድ ብልት አካባቢ ፈሳሽን የማጣት እና የመድረቅ ሁኔታ ስለሚፈጠር በግንኙነት ጊዜ በሚኖረው መፈጋፈግ ሕመም ሊከሰት ይችላል፡፡ ሴቶች ወደማረጥ እድሜ በሚያመሩበት ጊዜ የሚኖረው የኢስትሮጂን አለመመረት በብልት አካባቢ በግንኙነት ጊዜ ሊኖር የሚገባውን ፈሳሽ ማጣታቸው ይበልጥ ስለሚያስቸግራቸው አሁንም ሐኪማቸውን ማማከር ይጠቅማቸዋል፡፡
-----------------------////-------------------
(ቅድመ ማረጥ (periomenopause) ...በሽንት ፊኛ...በውፍረት እና በመሳሰሉት አካላት ላይ ምን የህመም ስሜት ሊኖረው ይችላል;) ይቀጥላል



 

ዶ/ር ዋናው እስከ 75ኀ በላይ ባሉት ሴቶች ላይ የሚታየው ሙቀትና ላብ የማላብ ስሜት ሲሆን በተለይም በለሊት ወቅት ከፍተኛ የሆነ ላብ ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ይህንን ሙቀት ብዙዎች ሊቋቋሙት ስለማይችሉ ሲበሳጩ ይታያል፡፡

Read 17557 times Last modified on Saturday, 27 October 2012 10:34