Saturday, 24 December 2022 15:44

ኢትዮጵያ ወዴት ወዴት--?

Written by  በአክሊሉ ገብረ መድህን
Rate this item
(3 votes)

  አድማስ ትውስታ

                          ኢትዮጵያ ወዴት ወዴት--?

           “--አረቄ ጠጥቶ የማይሰክር ሰው ተየት ይገኛል? ዘውድ ዙፋን፣ ከአረቄ አስር እጅ የባሱ አስካሪዎች ናቸው። አስካሪነታቸው ንጉስ ለተባለው ሰው ብቻ አይደለም። ለባለሟሎቹም፥ ለዘመናዮቹም ነው። ሕዝቡንም ጭምር ለማስከር እንዲችሉ ተደርገው ተሰናድተዋል። የአረቄ ስካር በቶሎ ይበርዳል። የዙፋንና የዘውድ ስካር ለመቼም አይበርድ።--”
      
           ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ መልካም መሪ ገጥሟታል ብለው ደረታቸውን ነፍተው ለሙግት የወጡ ደጋፊዎቻቸው፣ በተለያዩ ጊዜያትና ሁኔታ እየተዘረሩ አቅጣጫ ሲቀይሩና አንገት ሲሰብሩ ደጋግምን አይተናል፤ በተቃራኒውም እንደዛው። የእኔ አይነቱ አንገት መስበር ብርቁ ያልሆነ “ጨበሬ” ደግሞ ግራ ተጋብቶ መሃል መንገድ ላይ ብቻ አይቆምም። ዙሪያ ገባውን ይመረምር ዘንድ ግድ ይለዋል። የኢትዮጵያችን ዕድል ፈንታ ከአረማመዷ አቅጣጫዋን አይቶ “ወዴት ወዴት?” ያሰኛል:: ይህን ጊዜ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) እየከፈለ በመንግስት ጉያ የሰበሰባቸው ባለስልጣናትና አማካሪዎቻቸው ሚና ምን እንደሆነ ይገለፅለታል።
በዚህ ሙስናውን እንዳላየ፣ በዚህ ቢሮክራሲውን እንዳልሰማ፣ በዚህ መፈናቀሉ እንዳልገባው፣ በዚህ ዝርፊያና ሞቱ እንዳላመመው መስሎ ዛሬን ቢደርስም፣ ሳይጠራ አቤት እንዳላለ ተፈልጎ የማይገኝበት ደረጃ መድረሱ ግን ሆድን ይቆርጣል። “ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው?” ይሉት አባባል;፤ የአፍ ማሟሻና የማህበራዊ ሚዲያ ማሟሟቂያ  መሆኑን እያየ ባላየ አልፏል።  ቢብስበት እሱም “ወዴት ወዴት” ማለት ግድ ሆኖበታል።
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በአስፈላጊው ሁኔታ አላካሄደችም በሚል የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የነበረውን የሁለት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አዘግይቷል። እነዚህ በመንግስት በኩል እንዲደረጉ የሚጠበቁ ማሻሻያዎች ምንድን ናቸው? ከተባለ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን [እንደነ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ] ወደ ግል ማዞር። የፋይናንስ ዘርፉን ለገበያ ክፍት ማድረግ [የብር የመግዛት አቅምን ማዳከምን ጨምሮ] በፋይናንስ ዘርፉ ቁልፍ ተዋናዮች የሆኑትን የመንግስት ባንኮች ድርሻ በግል ባንኮች እንዲተካ ማድረግና ሌሎች መሰል ሁኔታዎች ይጠቀሳሉ። ስለነዚህ ጉዳዮች ጉዳት አቶ ክቡር ገናና ዋዜማ ሬዲዮ በተለያዩ መድረኮች በጣም በስፋት የፃፉበትና ውይይት ያቀረቡበት ስለሆነ ፅሁፎቹን ፈልጎ ማንበብ አይን ከመግለጥ ባለፈ ቀጣይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕጣ ፋንታን ለመገመት ይረዳል።
ይባስ ብሎ የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ዙሪያ በወሰደችው አቋም ምክኒያት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር እርዳታ እንዳይሰጥ አግዷል። ይህም የመንግስትን እጅ ለመጠምዘዝ በተሰናሰለ መልኩ እየተሰራ ለመሆኑ አብይ ማሳያ ነው። እጅ ጥምዘዛው ግን በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይመስልም፡፡ ተቃዋሚ ማስነሳት ህዝብን ማወክ፣ በሂደትም ስልጣኑ እጁ የገባ ወገን አለቅም የሚልበትንና ድጋፉ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ማለትም ጫናውን ከሚያሳድሩት ሃይላትና ከትሮይ ፈረሶቻቸው የሚመጣ በማስመሰል ኢትዮጵያን በእጅ አዙር የመግዛት እንቅስቃሴ ነው፡፡
የእንጨት ፈረስ!
የትሮይ ፈረስ በትሮይ ጦርነት ወቅት ግሪኮች የትሮይን ቅጥር አልፈው ለመግባት የተጠቀሙበት ብልሃት ነው። ከአስር አመት አሰልቺ ውጊያ በኋላ ግሪኮች ትልቅ የእንጨት ፈረስ ገንብተው ምርጥ ምርጥ ጦረኞቻቸውን በውስጡ በመደበቅ የትሮይ ቅጥር ጋር ትተውት ይደበቃሉ። ትሮያውያኑ በራቸውን ወለል አድርገው ይህን ግዙፍ ፈረስ ወደ ቅጥራቸው ያስገባሉ። በዚህ የግሪካኑ ብልሃት ነው ትሮይ ልትወድምና  ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታሪክ ሆና ልትቀር የቻለችው።
ይህን ታሪክ እንዳስታውስ ያደረገኝ ከጥቂት ወራት በፊት ያየሁት በእስራኤላዊው ጊድዮን ራፍ’ እና ማክስ ፒሪ የተሰራው ዘ ስፓይ የተሰኘ ተከታታይ ፊልም ነው። ፊልሙ በእስራኤላዊው የሞሳድ ሰላይ ኢሊ ኮሆን ህይወት ላይ ተመስርቶ የተስራ ነው። ኢሊ ኮሆን እ.ኤ.አ ከ1961 እስከ 1965 [ከ1967ቱ የስድስት ቀን ጦርነት ጥቂት ቀድም ብሎ] በሶሪያ ስላደረገው የስለላ ተግባርና የሶሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር አማካሪ ለመሆን ስለበቃበት ሂደት የሚተርክ ነው። የሞሳዱ ኢሊ ኮሆን ሶሪያ ቅጥር ውስጥ እስራኤልን ይዞ መግባት የቻለ ሰው ነው። በሌላ አነጋገር፤ እንደ  እንጨት ፈረስነት [የትሮይ ፈረስነት] አገልግሏል።
ግሪኮች ትሮይን ለማጥቃት የተጠቀሙበትን ብልሃት፣ ሃገራት ሌላን ሀገር ለማጥቃት መልኩን እየቀየሩ ለግልጋሎት እንደሚያውሉት ዘ ስፓይ ሁነኛ ምሳሌ ነው። ኢሊ ኮሆን እንደ ሀገሬው ሰዎች እየበላ፣ እንደ ሀገሬው ሰዎች እያወራ፣ እንደ ሀገሬው ልማድ እየኖረ፣ ሀገሬውን ያለ ርህራሄ ማስጠቃት ችሏል። አሁን በኢትዮጵያም እየታየ ያለው ልክ እንደዚህ ይመስላል። ሲታዩ ኢትዮጵያዊ ሲያወሩ ኢትዮጵያዊ፣ ሲለብሱ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ብዙ የሌላ ሀገር ጉዳይ አስፈፃሚ “የእንጨት ፈረሶች” በብዛት ማየት ጀምረናል። ይህም ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው? ባሉን ቁጥር አይን እንድናፈጥ ምክኒያት ሆኖናል።
የስልጣን ስካር!
ወጣትነት ብዙ ውሳኔዎች በችኩልነት ሊፈፀምበት የሚችልበት ወቅት ነው። ትምህርትና ዕውቀት ቢኖርም ማስተዋልን ጋርዶ፣ በቸልተኝነት በንዴትና በበቀል ብዙ ጥፋት ውስጥ ሊያስገባ ይችላል። ፊታውራሪ ተክለ ሃዋሪያት “ኦቶባዮግራፊ” በተሰኘ የግለ-ታሪክ መፅሐፋቸው፤ “ሰው መማሩ ስህተቱ ያነሰ እንዲሆን ነበር። ነገር ግን ስህተት እንዲያንስ መማር ብቻ አይበቃም። መሸምገልም ያስፈልጋል።” ያሉት ለዚህ ነው። [ሽማግሌን፦ የሸመገለ ያረጀ ፤ አሮጌ፤ ወግ ታሪክ አዋቂ፤ ጨዋ፤ ገላጋይ አስታራቂ በሚል ነው የደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላት የሚፈታው።] እንግዲህ እዚህ ወጣትነት ላይ ስካር ሲጨመርበት ምን እንደሚፈጠር መገመት ነው።
መንግሥት በአንድ አገር ውስጥ ሕጎችን ለማውጣትና ለማስፈጸም ስልጣን ያለው አካል መሆኑ ብዙ አያከራክርም። አንድ ሃገር የሚተዳደርበት ሥርዓት ያቆመው [ያበጀው] ሃይል [አቅም] በአደራ መልክ የሚገኘውም በመንግስት እጅ ነው።
የባለስልጣን ሚናው ይህን “ሃይል” በአስፈላጊው ጊዜና ቦታ ለተገቢዎቹ ሰዎች ማከፋፈል ነው። በአደራ የተሰጠው ሃይል [አቅም] የህዝብ የላብና የደም ውጤት በመሆኑ ብዙ ነገርን የመግዛት ጉልበትና ብቃት ስላለው፣ ዘላለም ከሃይሉ ጋር አብሮ የመቆራኘትን ምኞት ሊፈጥር ይችላል። የዚህ ምኞት ጫፍ መድረስ ነው ሰውን ለስካር የሚዳርገው።
ፊታውራሪ ተክለ ሃዋሪያት “ኦቶባዮግራፊ” በተሰኘው ግለ ታሪካቸው ስለ ስልጣን እንዲህ ይላሉ፦ “አረቄ ጠጥቶ የማይሰክር ሰው ተየት ይገኛል? ዘውድ ዙፋን፣ ከአረቄ አስር እጅ የባሱ አስካሪዎች ናቸው። አስካሪነታቸው ንጉስ ለተባለው ሰው ብቻ አይደለም። ለባለሟሎቹም፥ ለዘመናዮቹም ነው። ሕዝቡንም ጭምር ለማስከር እንዲችሉ ተደርገው ተሰናድተዋል። የአረቄ ስካር በቶሎ ይበርዳል። የዙፋንና የዘውድ ስካር ለመቼም አይበርድ።”
መንግስት ትምህርትና ዕውቀትን እንደ መመዘኛ መውሰዱ ተገቢ ቢሆንም እንደ ብቸኛ መስፈርት ለማፅናት መሞከሩ ግን ተገቢ አይሆንም። በአገር ጉዳይ አንድ ብቸኛ መስፈርት ሊኖር አይገባም። ብቸኛ መስፈርት የግድ ከሆነ ግን አገርን ከመውደድ የተሻለ አይኖርም። በኢትዮጵያ ጉዳይ ከግብፅ ጋር እያሴሩ፣ ከአለም ባንክና የጤና ድርጅት ጋር እየዶለቱ ባሉ ባለስልጣንና አማካሪዎች መከበብ በራሱ መንግስት ላይ ብዙ ጥያቄ ያስነሳል። እነዚህ ወጣት “ሰካራሞች” በምግባራቸው ሳይሆን በስልጣናቸው መከበር የሚፈልጉና የሰከኑ ባለመሆናቸው፣ አገራቸው ላይ እያመጡ ያሉትን በደል ማስተዋል እስከማይችሉ ድረስ ታውረው ስልጣንን “የኔ ዕፁብ [ማይ ፕሪሸስ]” እያሉ በኩራት ሲንጎማለሉ እየታዘብን ነው።
የጎረቤት በ-”ሽታ”
ሃዝራት ሃሰን አልበስሪ የተባሉ የእስልምና ሊቅ፣ አንድ ቀን በጣም ይታመሙና ከአልጋ ይውላሉ። ከአልጋ መዋላቸውን የሰማ ጎረቤታቸው ሊጠይቃቸው ይመጣል። ትንሽ ይጨዋወቱና፦ “ኢማም ሆይ!” ይላቸዋል። “ኢማም ሆይ፤ በጣም የሚሰነፍጥ ጠረን ይሸተኛል። ምንድን ነው?” ኢማሙ በሽታው ያመጣባቸው መሆኑን ይነግሩታል። ጎረቤታቸው አላመነም። “ይህማ የህመም ሽታ አይደለም። ከቆሻሻ ማስወገጃ የሚመጣ አይነት እኮ ነው። በፈጣሪ ስም ይዤዎታለሁ ይንገሩኝ ምንድን ነው?” ብሎ አለቅም አላቸው። ይሄን ኢማሙ እንዲህ አሉት፤ “ለወራት የቆሻሻ ፍሳሽ ከአንተ ቤት በኩል ወደ እኔ መምጣት ጀምሮ ልደፍነው የቻልኩትን ሞከርኩ። አልሆነልኝም። ይበልጥ እየባሰ መጣና ጭራሽ ይሄው ከአልጋ ጣለኝ።” ጎረቤታቸውም፤ “ምነው ታዲያ አልነገሩኝ?” ቢላቸው፤ “እንዳላስከፋህ ብዬ ነው” ሲሉ መለሱለት።
መንግስታችንን እንዳናስከፋ ብለን ስንቱን ነገር እኛው ልንደፍን እየሞከርን ነው፤ ጉቦው  ቢሮክራሲው ስርዓት አልበኝነቱ ሳያንሰን፣ የእንጨት ፈረሶቹ ሰካራምና ወጣት ባለስልጣንነቱ ኢትዮጵያን ለሌላ ገዥ አሳልፎ ለመስጠት በብርቱ እየታገሉ እንደሆነ በግልፅ እያየን ነው። ነቅቶ ዙሪያውን ማየትና ቤቱን ማፅዳት የራሱ የመንግሥት ሃላፊነት ነው። በእጅ አዙር ህዝቡን ለባዕድ ገባር ለማድረግ የሚሻ መንግስት እንዳለን ባናምንም፣ ከቤቱ የሚወጣው በ-ሽታ ግን አልጋ ላይ ሊጥለን እንደሆነ ነጋሪ አያሻውም።
ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች እንደሆነ አጢኖ በሸመገሉት [በሰከኑት] ታግዞ፣ ቅጥሩ የተሰገሰጉትን የእንጨት ፈረሶችና ወጣት ሰካራሞች፣ ጊዜው ሳይረፍድ ያጸዳ ዘንድ እንማፀናለን። ክብር የሚሰማው ማንም ኢትዮጵያዊ፤ ሎሌ ከመሆን ሞቱን ይመርጣልና።
(ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ድረገጽ፤ 19 ሴፕቴምበር 2020)


Read 3385 times