Saturday, 24 December 2022 15:31

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ፓስተሩ “ፈጣሪን ለማሳየት” 1 ሺ 600 ዶላር ክፍያ ጠይቋል
    የተዓምራት የዋጋ ዝርዝርም በፌስቡክ ገጹ አውጥቷል

        በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአፍሪካ “ተአምራትን እናሳያለን” እያሉ ገንዘብ የሚያጋብሱ “ነብያት” እየተበራከቱ መጥተዋል። ሰሞኑን ከወደ ደቡብ አፍሪካ የተሰማው ዜናም በሃይማኖት ስም የሚነግዱ ሰዎች የደረሱበትን የማጭበርበር ጥግ ያሳያል።
“ፈጣሪን በገነት ለማየት ከፈለጋችሁ 1 ሺ 600 ዶላር መክፈል አለባችሁ” ያለው ፓስተርም፤ የሰሞኑ መነጋገሪያ መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል በድረ ገጹ አስነብቧል።
ኤምኤስ ቡደሊ የተባለው ፓስተር፥ ምዕመናን ክፍያ መፈጸም ከቻሉ የማይታመን የሚመስሉ ተአምራቶችን ማሳየት እችላለሁ ባይ ነው።
ፌስቡክ ላይ ያሰፈረው ለተአምራቱ የሚያስከፍለው የዋጋ ዝርዝርም በማህበራዊ ሚዲያዎች ተቃውሞ አስነስቶበታል። ቡደሊ በስማርት ስልኮች መጻኢ እድላቸውን ማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች መፍትሄው በጄ ነው ብሏል።
“እዳችሁን ማሰረዝ የምትፈልጉም ወደኔ ኑ” የሚል መልዕክቱን አጋርቷል። “ፈጣሪን መመልከት” የሚፈልጉ ምዕመናንም፣ በፈረንጆቹ ታህሳስ 25 ቀን 2022 በሚያደርገው የአምልኮ ጉባኤ ላይ እንዳይቀሩ አሳስቧል፡፡
በባዶ እጅ ወደ አምልኮው ቦታ መሄድ ግን ከተአምራቱ ጋር አያገናኝም።
“በገነት እግዚአብሄርን ለመመልከት” 20 ሺህ ራንድ ወይም 1 ሺህ 600 ዶላር መክፈል ግዴታ ነው። ብድራቸው እንዲሰረዝላቸው የሚፈልጉ ምዕመናን ደግሞ 5 ሺህ ራንድ (290 ዶላር) መክፈል ይኖርባቸዋል ብሏል፤ ፓስተሩ፡፡
በአምልኮው ቀን ማግስት ለመግባት የፈለገ ሰው 10 ሺ ራንድ መክፈል ይኖርበታል ይላል፤ ቡደሊ የለጠፈው የቅሰቀሳ ፖስተር።  በስማርት ስልኮቻቸው መጻኢ እጣ-ፈንታቸውን  መመልከት ያሰኛቸው ወገኖችም 1 ሺ 660 ዶላርን ይከፍሉ ዘንድ ተጠይቀዋል።  የሃይማኖት አባት ነኝ የሚለው ቡደሊ፣ “ፈጣሪን በገነት ከማሳየት” 15 እጥፍ የበለጠ ዋጋ የጠየቀው አቬየተር የተሰኘውን ታዋቂ የኦንላይን ጌም ማሸነፍ ለሚፈልጉ ምዕመናን ነው፤ 17 ሺህ 400 ዶላር መክፈል ጌሙን አሸናፊ ያደርጋል ይላል።
ይህ በፖስተር ላይ የተለጠፈ የአምልኮ ጉባኤና የተአምራት ዋጋ ዝርዝር፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወር ከፍተኛ ነቀፌታ ወርዶበታል፡፡
“ይህ የለየለት ቅጥፈት ነው፤ የሚሰረዝ  እዳም ሆነ በስማርት ስልክ የምንመለከተው ነገ አይኖርም” የሚሉና ሌሎች አስተያየቶችም በተለጠፈው ምስል ስር ተሰጥተዋል።
“ነገሩን በየዋህነት የሚያዩ ምስኪን ቤተሰቦቻችን፣ የሚሳካ መስሏቸው ወደ ቡደሊ ሊሄዱ እንደሚችሉ አልጠራጠርም” ያለ አንድ አስተያየት ሰጪም፤ እንዲህ አይነት የእምነት ነጋዴዎችን የልብ ልብ የሚሰጠው ንቃተ ህሊናው ዝቅ ያለ ምዕመን ነው የሚል ሃሳብ አስፍሯል።
በደቡብ አፍሪካ በ2019 “የሞተ ሰው አስነሳለሁ” ያለው ፓስተር ኤልፍ ሉካኦ፤ ያልሞተን ሰው እንደሞተ አድርጎ በማስነሳት ምዕመናንን በመሸወዱ ዘብጥያ መውረዱ ይታወሳል።
በዚምባቡዌም “ከፈጣሪ ጋር በስልክ እናወራለን” ያለው ፓስተር ፖል ሳንያንጎሬ፤ በቴሌቪዥን ጣቢያ “ቀጥታ ከገነት” የሚል ፕሮግራም ሊጀምር እንደሆነ ማስታወቁና  “የፈጣሪን ስልክ ቁጥር ይፋ አደርጋለሁ” ሲል  መደመጡ አይዘነጋም።
ወይ ጉድ! ምን ዓይነት ዘመን ላይ ደረስን!?
(አል አይን)

________________________________________________

                           “ትጾማለህን?”
    በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ (በአማርኛ ወልሳነ እንግልጣር)


          ትጾማለህን? እንግዲያውስ በሥራህ አረጋግጥልኝ!
በምን ዓይነት ሥራ ካልከኝ?
ደሃውን ካየህ እዘንለት (ቸርነትን አድርግለት)!
የተጣላኸውን ካየህ ታረቀው!
ጓደኛህ ክብርን ሲያገኝ ካየህ አትቅናበት!
መልከኛ ሴት ካየህ እለፋት!
አፍህ ብቻ ከምግብ አይከልከል፤ አይንህም፣ ጆሮህም፣ እግርህም፣ እጆችህም፣ ሁሉም የሰውነትህ ክፍሎች ይጹሙ።
እጆችህ ከንጥቂያና ስግብግብነት (ንፉግነት) ይጹሙ። እግሮችህ የማይገቡ ትእይንቶችን ለመመልከት ከመንደርደር ይጹሙ። አይኖችህ ውብ መልኮች ላይ ያልተገቡ እይታዎችን መቼም መች ከማሳረፍ መከልከልን ይማሩ እና ቁንጅና ላይ ከመጠመድ ይጹሙ። ማየት ለዐይን ምግብ ስለሆነ ያልተገባ እና የተከለከለን እይታ ካደረግህ ጾምህን ያፈርሰዋል፣ የነፍስህንም ሙሉ ደህንነት ያነዋውጣል፤ ነገር ግን የተገባና ጥንቁቅ ከሆነ ጾምህን ያስጌጣታል። የተከለከለውን በዓይን እየነካህ ነገር ግን በጾም ምክንያት ከማያረክስ ምግብ መጾሙ ከንቱ ከሆኑ ነገሮች መካከል ይቆጠራል። ሥጋን አትበላም አይደል? ስለዚህ በዐይኖችህ አማካኝነት ፍትወትን አትመገብ። ጆሮህም ይጹም። የጆሮ ጾም ክፉ ወሬን እና ሐሜትን አለመቀበልን ያካትታል። “ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል” እንዲል። (ዘጸ. 23፥1) አፍም እንዲሁ ከመጥፎ እና ከጥላቻ ንግግሮች ይጹም። ከአዕዋፋትና አሳዎች ብንከለከል ነገር ግን ወንድማችንን ብንበላው ምን ይጠቅመናል? ክፉ ተናጋሪ የወንድሙን ሥጋ ይበላል፤ የባልንጀራውንም ሰውነት ይነክሳልና።

_________________________________________________

                       “አሁን ለይቷል ልበል፤ መልሰኝ”
                          ሥምረት አያሌው ታምሩ


         “አንድ ዓይነ ሥውር ይኖር በነበረበት አንድ አገር ከዕለታት በአንዱ ቀን ኡ!ኡ! ተባለ፡፡ ዓይነ ሥውሩም ጩኸቱ ወደ መጣበት አቅጣጫ በደንብ አንቅቶ ሲያዳምጥ ኡ!ኡ! የሰው ያለህ! እየተባለ ሲጮኽ ሰማ፡፡ በዚህን ጊዜ “ልብሴን አቅርቡልኝ፣ ከዘራዮንም ስጡኝ” ብሎ መሪውን ጠርቶ ውሰደኝ ሲል ሚስቱ ሰማች፤ “እርስዎ ደካማ ዓይነ ሥውር ነዎት፤ ወዴት ሊሄዱ ነው? ምንስ ሊያደርጉ ነው? ይልቅ አርፈው ይቀመጡ።” አለችው፡፡
ዓይነ ሥውሩም” “አገሬ እኮ የሰው ያለህ እያለች ነው፡፡ ሞኝ ነሽ እንዴ? እሄዳለሁ!” ብሎ ብዙ ርቀት ከሄደ በኋላ እንደገና “ኡ!ኡ! የጎበዝ ያለህ!” እየተባለ ሲጮህ ሰማ፡፡ በዚህ ጊዜ “አሁን ለይቷል፤ በል መልሰኝ” ብሎ ተመለሰ ይባላል፤ በማለት አገርንና ወገንን ለመመከት የሚችል ጥቂትም ቢሆን አቅም ያላቸው ሁሉ የጉልበታቸውን ማነስና መብዛት ከግምት ሳያስገቡ፤ ለጥሪው ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው በምሳሌ አስተምሯል፡፡
ምንጭ፡- “አባቴና እምነቱ (የአለቃ አያሌው ታምሩ የሕይወት ታሪክ)”

Read 944 times