Saturday, 24 December 2022 15:25

የእውቀት ፍለጋ መሠረቱ ተጨባጭ ጥያቄ (ችግር) መለየት መቻል ነው?

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   ስንት መጻሕፍት ስላነበብን ነው አንባቢዎች የምንባለው? ስንትስ ፕሮፖዛል ጽፈን ምርምር ስለሰራን ነው፣ ተማራማሪዎች የምንባለው? እንዴትስ ነው አዋቂዎች የምንሆነው? አንድ በቅርብ የማውቀው የዩኒቨርስቲ መምህር አለ። ሁሌም ያነባል፣ ፕሮፖዛል ይጽፋል። አንድ ቀን ይህን ጥያቄ አቀረብኩለት። ሁሌም ታነባለህ፣ ትጽፋለህ። እራሴን ከአንተ ጋር ሳነጻጽር በጣም ሰነፍ መሆኔን እረዳለሁ፣ የምሰራው ነገር መዳረሻው ካልታየኝ ለመስራት እቸገራለሁና። ግን የምታነበውና የምትጽፈው ነገር የመጨረሻ ግብ ምንድን ነው? አልኩት። መልስ አልነበረውም፣ ፕሮፌሰር ለመሆን ቢለኝ፣ ከዛስ? ብዬ እንደምጠይቀው ያውቃል።
ማንበብ ብቻውን አዋቂ አያደርግም። መሥራት ብቻውን ትርፍ አያመጣም። መጽሓፍት የሚቀመሱ፣ የሚታኘኩ ወይም የሚሰለቀጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ማንበብ ለመዝናናትም ሊሆን ይችላል። በአጠቃላይ ግን ንባብ አስተሳሰብንና ግንዛቤን እንዲያሰፋ ይጠበቃል። እዚህ ላይ ዋናው ቁም-ነገሩ ማንበብ ሳይሆን ከንባባችን ምን ጠቃሚ ቁም-ነገር አገኘን? የሚለው ነው።
ምርምርም ያው ተመሳሳይ ነው። በምርምራችን ምን ውጤት አገኘን? የሚለው ቁልፍ ጉዳይ ነው። ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ ብዙ ማንበብ ሳይሆን ብዙ ማወቅ ወይም በጥልቀት ማወቅ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ዋጋ የሚሰጠው ብዙ መመራመር ሳይሆን ውጤት ያለው ምርምር ማድረግ ነው። ያ ደግሞ ከችግር መረጣ ይጀምራል። ለሁሉም ግን ለዓላማ እናንበብ፣ ለዓላማ እንመራመር።
ይህን እንድጠይቅ ያደረገኝ፣ በዚሁ ፌስቡክ ላይ ማንበብን የአዋቂነት መገለጫ አድርጎ የጻፈ ሰው ስለየሁ ነው። ጋዛኒንጋ የተባለ ኒውሮሳይንቲስት “Who is in Charge?” በሚለው መጽሐፉ ይህን ይላል፣ “የማወቅ አቅም ያለው አእምሮ የሌለው ሰው፣ ስልጠና ስላገኘ ብቻ አዋቂ አይሆንም”። እናም የአነበበ ሁሉ አዋቂ፣ የሰራ ሁሉ አትራፊ ሊሆን አይችልም። የሚሰራውን ለምን እንደሚሰራ፣ የሚያነበውን ነገር ከእውኑ አለም ጋር መለንቀጥ የቻለ ብቻ አዋቂም አትራፊም ይሆናል። ስለዚህም ብዙ ማንበቡ ብቻ ሳይሆን የማወቅ አቅም ያለው አእምሮ አስፈላጊነትን እንዳንረሳ ለማሳሰብ ነው።
(መላኩ አዳል)

Read 11804 times