Saturday, 24 December 2022 15:23

አራት ወደፊት፣ ሦስት ወደ ኋላ!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን፣ የዱር አራዊቶች ተሰብስበው መሪያቸውን ለመምረጥ ይወያያሉ።
አንበሳ፡-
“እኔ ምን ሆኜ ነው አዲስ መሪ የፈለጋችሁት?” ሲል ጠየቃቸው።
ተኩላ፡- ሲፈራ ሲቸር፤
“እያረጁ ስለመጡ ፈርተን ነው ጌታዬ”
አንበሳ፡-
“እሱ የእናንተ ጭንቀት ሊሆን አይገባውም። ምክንያቱም እኔ አላረጀሁም”
ዝንጀሮ፡-
“ማርጀትስ አላረጁም ግን ደክመዋል”
አንበሳ፡-
“ታዲያ ምን ብመገብ ነው የሚሻለኝ በርታ እንድል?
ድኩላ ልብላ?
ሰስ ልብላ?
ግስላ ልብላ?
አሳማ ልብላ?
ወይስ ከሁለት አንዳችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
እጅግ አሳሳቢ ምርጫና ጸጥታ ሆነ።
ጦጢት ይህን ሁሉ ንግግር ተሸሽጋ ስታዳምጥ ቆይታ ኖሯል።
“የለም አያ አንበሶ፤ እኛ እንስሳ መርጠን፣ አርደን፣ጠብሰን እናዘጋጅልዎታለን። በኔ ምርጫ ከሆነ ግን እንደ ዝሆን ስጋ ለእርስዎ የሚስማማ የለም። ስለዚህ አፈላልገን እናምጣልዎት።”
አያ አንበሶ ተስማማ። ስለዚህም የተጠበሰ ዝሆን ይጠባበቅ ጀመር። የጦጢቷ ዝሆን ግን ሳይመጣ ቀረ። አንበሳ አንድ ጊዜ አገሳና ጫካውን የሚነቀንቅ ጩኸት አሰማ።
 ጦጢት ከች አለች፡፡
“አያ አንበሶ ይቅርታ፤ ዝሆኖች  እኛ እራሳችን ለአያ አንበሶ የሚመቻቸውን መርጠን ብናዘጋጅላቸው ይሻላል፤ ስላሉ እሺ እንታገሳለን ብያቸው ነው” አለች።
አያ አንበሶ፡-
“መልካም፤ ጥቂት ልታገሳችሁ።”
ዝሆኖች ተሰብስበው ለአያ አንበሶ ማን ይሂድላቸው? በመባባል ስብሰባቸውን ቀጠሉ። ተበጣበጡ፤ ተፋለሙ ተፋለሙና እየደከሙ ሲመጡ፤
“በቃ ጦጢት ራሷ ትገላግለን” የሚለው ሃሳብ ላይ ረጉ።
ጦጢት “ሃሳብሽን ግለጪ” ተባለች።
ጦጢትም፡-
“እኔ እናንተን ብሆን እርስ በርስ መናቆሬን ትቼ
አንድ ራስ በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ
እንደምን ለብልቦ አቃጥሎ ይፍጃችሁ?
የሚለውን አገርኛ ግጥም አስተውልና አስብበት ነበር” ስትል ፈረደችላቸው ይባላል።
ከዚያን ቀን ወዲያ አያ አንበሶ፣ በዚያ ጫካ ውስጥ ታይቶ አያውቅም።
***
ፈረንጆች Unity is strength ይላሉ። አንድነት ሃይል ነው እንደማለት ነው። ከላይ በጠቀስነው ተረት አኳያ ደግሞ
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለው የበለጠ ጉልበት ያለው ይሆናል።
ከኢትዮጵያ ቀንደኛ ችግሮቻችን ዋነኞቹ መከፋፈል፣ አድር ባይነትና አምባገነንነት ናቸው።
ማለትም አምባገነንነት ከሁሉም ግልጹና በተደጋጋሚ ያየነው ነው።
መከፋፈል በተለይ በፓርቲዎችና በድርጅቶች ውስጥ ክሱት የሆነ ነው! ከፋም ለማም እናውቀዋለን። እጅግ አደገኛው፣ ከጣሊያን ዘመን እድሜ እኩል የኖረና ያሰቃየን ነው። ስልት የሚቀያይር፣ እንደ እስስት በርካታ ቀለማት ያሉት ሲሆን የብዙ ፖለቲከኞችን ራስ ያዞረና አቋም ያናጋ አብሾ-አከል በሽታ ነው። ሲሻው የሚጥል በሽታ የመሆን አቅም አለው። ሲሻው አሳሪና ታሳሪ ቦታ እንዲቀያየሩ የሚያስችል በሽታ ይሆናል፤ ሲሻው ደግሞ በማያልቅ የስብሰባ ልክፍት ያማርረንና አያሌ መፍትሄ አልባ ምሽቶችን ያስመሸናል። በዚህ መሃል አገር ልጆቿን፣ጊዜዋንና ውድድ የልግስና የለውጥ ሰዓቷን ትሰዋለች።
ሌላው የአገራችን አባዜ ሁሌም የጀመርነውንና የደከምንበትን ነገር ሁሉ በዜሮ አባዝተን ወደ መጀመሪያው ሰንጠረዥ መመለሳችን ነው። ይህ የመርገምት ሁሉ እርግማን ነው! ወደ ኋላ በተመለስን ቁጥር ምን ያህል ኢኮኖሚያችንን እንደምናላሽቅ አልገባንም። የድሮዎቹ የፖለቲካ- ኢኮኖሚ ሊቃውንት፤ “አራት ወደፊት ሶስት ወደ ኋላ” የሚሉት ይህንኑ ነው።
ከዚህ ይሰውረን!!

Read 11179 times