Saturday, 17 December 2022 14:07

እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

“ዝም አልኳቸው ዝም ይበሉኝ
ትቻቸዋለሁ ይተዉኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ”
ብለህ፤ተገልለህ ርቀህ
እውነት ይተዉኛል ብለህ
እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?!...
ተስፋ አርገህስ ምን ልትሆን፤ወይስ ተስፋው
ምን ሊሆንህ?
እንቅልፍ እንጂ እሚያስወስድህ፡፡
“አልጠራቸውም አይጥሩኝ
አይንኩኝ ስሜን አያንሱኝ”
ብለህ እንዴት ትመኛለህ፤እንደማይተዉህ
ስታውቀው
የተወጋ በቅቶት ቢተኛ፤ የወጋ መች እንቅልፍ
አለው
የጅምሩን ካልጨረሰው?
የተበደለ ቢችልም
ቢሸሽግም ቢደብቅም
የበደለ ዝም አይልም፡፡
እንዴት አስችሎት ዝም ይበል? ለፍልፎ
ከማስለፍለፉ
አደል እንዴ የሱ ቤዛ፤ የበደሉ ጥቅም የግፉ
ሰላም መንሳት አደል ትርፉ?...
ዝምማ ካለ ጉድ ፈላ
ነገር በጤና ሲብላላ
እያደር ሲጣራ ኋላ
ግፉ ይፋ ይሆናላ!...
ሰላምማ ከለገሰህ
ሕመምህ እየታወሰህ
ትዝታ እየቀሰቀሰህ
የሕሊናህ ሚዛን ረግቶ ፤ ጉዱ ሁሉ ኩልል ሲል
ያደፈረሰው ሲያጠልል
እግዜር ያሳያችሁ ብለህ፤ ፍረዱኝ ዳኙኝ
እንዳትል
ከነአካቴው ሳይጨርስህ
ምን ቢሆን ሰላም አይሰጥህ፡፡
እሱስ ቢሆን ያለትክሉ፤ ያላጥንቱ የሰላም ውርስ
ከቶ የማያውቀውን ቅርስ
ይሰጠኝ ብትል የት ይሆናል
ያልተዘራ መች ይበቅላል?
የጓሮ ጎመን ሲያጠላ
አጥፊ ትሉን እንዲያፈላ
እንዲያው በነገረ ቀደም፤ እንደሱስ ስሙን
ቢለፍፍ
ሰላምን የሰጠህ መስሎህ፤ በጉጉት ስታሰፈስፍ
ተለሳልሰህ እንደቃተትክ፤ ተስፋ አርገህ እንዳትል
እርፍ፡፡
እና ዘበት ነው ጥረትህ
በከንቱ ተስፋ ማድረግህ
ላያዋጣ መመኘትህ
የሰላም ቅዠት ማየትህ
ምን ልትሆን? ምን ሊሆንህ?...
ይቅርብህ፡፡ በኔ ይሁንብህ
እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ፡፡
ለኤድዋርድ ሞንድላን- (1959-ዳሬ ሰላም)

Read 2044 times