Saturday, 17 December 2022 14:07

“እነሱን እያየሁ ለምን ቆሽቴን አበግናለሁ...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው... ሁላችንም እኩል ግራ ገብቶናል ወይስ ለእሱም “በአንደኛ ደረጃ ግራ የተጋባ፤ በሁለተኛ ደረጃ ግራ የተጋባ...” የሚል መስፈርት አለ?! ግርም የሚል ዘመን ነው እኮ! በዚህ በኩል ደህና ሊሆን ነው ማለት ሲጀመር በዛ በኩል ደግሞ የሆንን ሸንቋሪዎች አፈር ምሰን ብቅ! በወዲያ በኩል “አቧራው ሊጠፋ ሳይሆን አይቀርም!” ማለት ሲጀመር በዚህ በኩል ደግሞ የሰሃራ በረሀን አውሎ ነፋስ ካላስነሳን የምንል አፈር ምሰን ብቅ! መከራዋ የበዛባት ሀገር!
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...እኔ የምለው በዚህ ሀገር ቦተሊካ ውስጥ እየከረምን፣ እየከራረምን ብቅ የምንል፤ ከአፈር ውስጥ ሳይሆን ከጮማና ከቅቤ ውስጥ ብቅ ያልን የምንመስል ‘ነምበራችን’ በየጊዜው እየጨመረ አይመስላችሁም! ...ደግሞ...አለ አይደል... ዘዴዋ የየትኛው ‘ሪቮሊሲዮን ዘመን’ ወይም የትኛው ‘ሪቮ  ፈላስማ’ ዘዴ ነች! አሀ ልክ ነዋ...ዘዴው ይታወቅና ሁሉም ተጠቃሚ ይሁና! አሀ...ህዝብ እኛ ‘ከርሞ ብቅ ባለች ‘መፈላሰሚያ’ ሆኖ የሚኖረው እዳ አለበት!
እንዲህ፣  እንዲሀ እያልን፤ እንዲህ፣ እንዲህ አያደረገን ስንቱን ዘመን ቆጠርነው፡፡  ቆጠርነው! ልጆቼ ነች የምትላቸው መከራዋን ያበዙባት ሀገር!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡- ማነህ እንቅልፌን ሳልጨርስ በጠዋት የምትጮኸው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣እኔ ነኝ እኮ!
አንድዬ፡- አሀ... ምስኪኑ ሀበሻ ፣ አንተው ነህ! ለመሆኑ ደህና ከረምክ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እኔ ደህና ነኝ አንድዬ! አንተ እያለህ እኮ ተመስገን ማለት ነው እንጂ ምን እንሆናለን ብለህ ነው፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ አንተ ቆዳህ  የሞኝ ይመስላል እንጂ  አንዳንዴ የወጣልህ ብልጥ ነህ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ አጠፋሁ እንዴ!
አንድዬ፡- እየው አንግዲህ! እየው እንግዲህ የምጠላባችሁ ባህሪይ ሊጀምርህ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እ...
አንድዬ፡- ቆይ፣ ደግሞ ይሄ ገና የሚባለውን በደንብ ሳታዳምጡና ነገሩ ሳይገባችሁ ዘላችሁ ጥልቅ የምትሉትን ነገር መተው አቃታችሁ ማለት ነው! እኔ መች ተናግሬ ጨረስኩና ነው እሽቅድድሙ! የወጣልሀ ብልጥ ነህ ማለት አጠፋህ ማለት ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አይደለም አንድዬ፣ አይደለም፡፡ ልማድ ሆኖብን እኮ ነው፡፡
አንድዬ፡- ገና ማንም ሰው ጣቱን ሳይቀስርባችሁ፣ ቀድማችሁ ራሳችሁ “አጠፋሁ እንዴ!” እያላችሁ በራሳችሁ ላይ ትቀስራላችሁ። ለዚህ እኮ ነው አንዳንዴ  ሞኞች ልበላችሁ፣ ብልጦች ልበላችሁ ግራ የምታጋቡኝ!...ምነው ዝም አልክ ምስኪኑ ሀበሻ!?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ዝም ማለቴ ሳይሆን አንድዬ ምን መሰለህ እኛው ራሳችን ለራሳችን ግራ የገባን ሆነናል፡፡ እንደ እኛ በራሱ ግራ የተጋባ ያለ አይመስለኝም፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ ፖለቲካ አታነካካኛ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ ፖለቲካ አይደለም አንድዬ!
አንድዬ፡- ነው ምስኪኑ ሀበሻ፣ ነው፡፡ ራሳችሁን አታታሉ፡፡ “እኔ ፖለቲካ የሚባል ነገር አልፈልግም፣”  ትሉና “ዋጋውን ሁሉ አስወድደው በረሃብ ሊገድሉን ነው፣” ትላላችሁ።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ይሄማ ምን ፖለቲካ አለበት!
አንድዬ፡- ተው እንጂ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ተው አንጂ! በረሃብ ሊገድሉን ነው የምትሉት ታዲያ ሰሜን ኮሪያ የምትሏቸውን ነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እውነት ለመናገር እኮ ብዙዎቻችን በአፋችን የምንናገረውና  በሆዳችን ያለው የተለያየ ነገር ነው፡፡ አንድዬ፣ በከንፈራችን ስመን በሆዳችን የምንነክስ ነን እኮ!
አንድዬ፡- ጎሽ! ጎሽ! እሱን ማወቅም አንድ ነገር ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ በፊት ለፊት ጽጌረዳ ይዘን በጀርባ ካራ የምንወዘውዝ ነን እኮ! በአደባባይ ያኑርሽ ብለን በጓዳ ይድፋሽ የምንል ነን እኮ! ደግሞ ደግሞ...
አንድዬ፡- ቆይ ቆይማ፣ እስካሁን የሰጠኸኝ ምሳሌዎች ይበቁኛል፡፡ ምስኪኑ ሀበሻ ይሄን ያህል ሆድ ብሶሀል እንዴ! 
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ብሶኛል አንድዬ፣ በጣም ብሶኛል፡፡
አንድዬ፡- ግዴለም ተረጋጋ፡፡ ስለእሱ አይነት ነገር ሌላ ጊዜ እናወራዋለን፡፡  ግን ምስኪኑ ሀበሻ፤ የእናንተኑ ቋንቋ ልጠቀምና ምነው ጣል፣ ጣል አደረግኸኝ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ እንደሱ አትበል!
አንድዬ፡- ለምን አልልም!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ አንተ እንደእሱ አይነት ነገር ስትል ሁሉ ነገሬ ይረበሽብኛል፡፡
አንድዬ፡- እኔ እኮ የምለው “እንደሱ አትበል” ብለህ ያፈንከኝም አንተ! የመሰለኝን ስናገር የምትረበሸውም አንተ! ዲሞክራሲያዊ መብቴን የሰሞኗን ኳስ አደረግህብኝ እኮ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ተው አንድዬ! ተው እንደሱ...
አንድዬ፡- እሺ አልልም፡፡ ግን ደግሞ ምስኪኑ ሀበሻ ምድር ላይ እርስ በእርሳችሁ ስትተፋፈኑ የማየውን እዚህ ድረስ መጥታችሁ በገዛ ጓዳዬ ልታፍኑኝ ነው ብዬ ሰግቼ...ቆይ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ቆይማ፡፡ እንደሱ አትበል ያልከኝን አልልም፡፡ ይኸው ዝም፣ ጭጭ አልኩ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ...
አንድዬ፡- ስማ ይልቅ የጠፋኸው ምን ያህል ቢደላችሁ ነው! ጤፉ በኩንታል አምስት መቶ ብር ገባ እንዴ?! ስኳሩ ኪሎው ሦስት ብር ሆነ እንዴ!?
ምስኪኑ ሀበሻ፡-  አንድዬ የእኛን ነገር እያወቅኸው! አንዴ ዋጋ ከወጣ መች ወርዶ ያውቃል!
አንድዬ፡- ጥሩ፡፡ መቼም ምስኪኑ ሀበሻን እስካሁን እንደማውቅህ ለሰላምታ ብቻ አትመጣም...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ ለሰላምታ ነው የመጣሁት!
አንድዬ፡- ጎሽ! አሁን ገና አንጀቴን አራስከው። አሁን እንግዲህ ሰላም ተባብለን የለ... በል አንተም ወደ ምድርህ ውረድ፡፡ እኔም ያቋረጥከኝን እንቅልፌን ልለጥጥ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ...እንደሱ ማለቴ ሳይሆን...ግን አንድዬ አንተም እንደ እኛ እንቅልፍ ትተኛለህ እንዴ!
አንድዬ፡- አሳምሬ ነዋ፣ እለጥጠው! እድሜ ለእናንተ፣ እናንተ ናችሁ እንድለምድ ያደረጋችሁኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እንዴት ብለን አንድዬ?
አንድዬ፡- በቃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ነገራችሁ ሁሉ እየተቀለባበሰ፣ ጸባያችሁ ሁሉ ብራ ሲሉት ጨለማ፣ ሰማይ ሲሉት መሬት እየሆነ ምናችሁም አልገባ ሲለኝ፣ እነሱን እያየሁ ለምን ቆሽቴን አበግናለሁ ብዬ ለሽ ነዋ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ አሁን በቃ ረስተኸናል ማለት ነው?
አንድዬ፡- ብዬ ነበር፡፡ ግን ምኑን ረሳኋችሁ... ጭራሽ ወፍ ጭጭ ሳይል በማለዳ በሬን እየደበደባችሁ ምኑን ረሳኋችሁ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ ይህን ያህል አማረንሀል ማለት ነው!
አንድዬ፡-አማረንሀል የሚለው ቃል ስለማይገልጸው የሚቀጥለው ጊዜ ስትመጣ ሌላ የተሻለ ቃል አፈላልገህ ይዘህልኝ ና!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እስከዚህ ድረስ አንድዬ!
አንድዬ፡-አዎ፣ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እስከዚህ ድረስ! ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እስቲ ነገ፣ ተነገወዲያ ብቅ በልና ዛሬ ልታወራኝ የፈለግኸውን ነገር እናወራለን፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሺ አንድዬ፣ እሺ፡፡
አንድዬ፡-ሰላም ግባ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
 ስሙኝማ...ዘንድሮ በዓለም ዋንጫ አንዳንድ “እኛን ይወክላሉ...” እያልን ስንደግፋቸው የሰነበትናቸውን ቡድኖች ስናይ ...አለ አይደል...በእርግጥ ለውጥማ አለ፣ ያሰኛል፡፡ እዛ ማዶ ድረስ ተሻግሮ “ወንድሞቻችን፣” “እኛን የሚወክሉ...”  ማለታችን አሪፍ ነው፡፡ ልክ ነዋ...ይሄ ዝግባ፣ ዝግባውን ሲገነድሱልን ያላጨበጨብን ለማን ልናጨበጭብ ነው!
ነገርዬው ግን ምን መሰላችሁ --- ሺዎች ኪሎሜትሮች አቋርጠን ”ወንድሞቻችን...” ያልነውን ያህል እዛ ማዶ ግቢ ካሉት ጋር “ወንድሞቻችን፣” መባባል አቃተን ነው። አለበለዛ ሁሉ ነገር ‘ቲራቲ’ር ብቻ ሆኖ ነው የሚቀረው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 985 times