Saturday, 10 December 2022 13:29

ወሎ የትምህርት የሳይንስና የባህል ጉባኤና ኤግዚቢሽን ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  በወሎ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የሚካሄደው “ወሎ የትምህርት የሳይንስና የባህል ጉባኤና ፌስቲቫል” በአዲስ አበባና በደሴ ከተማ ይካሄዳል፡፡
በአዲስ አበባ የሚካሄደው ፌስቲቫል “ጉዞ ወደ ወሎ” በሚል መሪ ቃል ከታህሳስ 19-23 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮ ኩባ የወዳጅነት ሀውልት በሚገኝበት ቦታ ላይ የሚከበር ሲሆን በርካታ ሁነቶች፤ ጥናታዊ ፅሁፎች፤ የሙዚቃና የባህል ሁነቶች ይቀርቡበታል ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ትላንት ረፋድ ላይ በጁፒተር ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡  
በደሴ ከተማ ከታህሳስ 29 እስከ ጥር 6 በሚካሄደው አለም አቀፍ ፌስቲቫል ላይ በርካታ ወሎን ሊገልፁ የሚችሉ ሁነቶች እንደሚካሄዱ የገለፁት ምሁራኑ ፌስቲቫሉ በእውቋ የሙዚቃ ንግስት የክብር ዶ/ር ማሪቱ ለገሰ የሙዚቃ ኮንሰርት ይጀምራል የተባለ ሲሆን፤ አውደ ጥናት፤ የማቲማቲክስ ኦሎምፒያድ የጎዳና ላይ ትርኢቶች የባህል አልባሳት ትርኢት፤ የቱሪስት መስህብ ጉብኝቶች፤ የፈጠራ ሥራ ውድድሮችና በርካታ ወሎን ለዓለም ሊያስተዋውቅ የሚችል ሁነት እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡ ፌስቲቫሉ ከዚህም በላይ በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ የነበረውን የአካባቢውን ህዝብ በመጠኑም ከዚያ የስነ-ልቦና ጫና በማውጣት በኩል እገዛ ያደርጋል የተባለ ሲሆን፤ በጦርነቱ ተቀዛቅዞ የነበረውን የንግድ እንቅስቃሴም ያነቃቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዩኒቨርሲቲው ሀላፊዎች ገልፀዋል፡፡

Read 31370 times