Saturday, 10 December 2022 13:21

“ማገዶ ስላላቀርብክ ነዋ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)


         “--የአየር ለውጥን ለመከላከል፣ ለአካባቢ ጥበቃ ምናምን ተብሎ ኔዘርላንድ ሦስት ሺህ እርሻዎችን ልትዘጋ ነው ተብሎ ይኸው እየታመሱ ነው፡፡ ስሙኝማ...ዘንድሮ እኮ ከአውሮፓ የምንሰማቸው ነገሮች ገራሚዎች ብቻ ሳይሆኑ...አለ አይደል... “እነዚህ ሰዎች ይበልጥ እየተፋቁ ሲሄዱ ገና ብዙ ጉድ የሚያሰኙ ነገሮች እንሰማለን፣” የሚያስብሉ ናቸው፡፡--”
      
      እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እሱዬው ጉዳይ ለማስፈጸም የሆነ ቦታ አመላለሱት፡፡ ቢቸግረው አንደኛውን ሠራተኛ “ጉዳዩ አለቀ ከተባለ ቆየ፡፡ ለምንድነው የምታመላልሱኝ?” ይለዋል፡፡ ሠራተኛው ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው...
“ማገዶ ስላላቀርብክ ነዋ!”
ማገዶ! “ጉድ በይ ዩክሬይን!” ማለት ይሄኔ ነው። ጭራሽ ባለጉዳይ ጉዳዩን ለማስፈጸም ማገዶ አንዲሸከም ይጠየቅ ጀመር! ቂ...ቂ...ቂ...! የምር ግን ባለጉዳዩ በሆዱ...አለ አይደል... “ሰውየዋ በጠዋቱ ነጯን ብቻ ሳይሆን የኮሶዋንና የጥቁር አዝሙዷን ቀላቅላ ነው እንዴ የቀነደበችው!” ቢል አይፈረድበትም፡፡ ልክ ነዋ! እናንተ የሆነ ጉዳይ ለማስፈጸም ነው የሄዳችሁት፡፡ እና ደግሞ ሊገጥሙ ይችላሉ ብላችሁ የምታስቧቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡
“የጎደለ ዶኪዩመንት ስላለ በሦስት ቀን ውስጥ አቅርብ፡፡”
“ማስረጃው የተሟላ ስላልሆነ የጎደሉትን ማስረጃዎች በሳምንት ውስጥ አጠናቀህ አቅርብ፣” ምናምን ይባላል እንጂ  «ማገዶ አቅርብ!” ብሎ አማርኛ ምንድነው! መቼም ዘንድሮ የጠርጥር ዘመን አይደል! “እነኚህ ሰዎች ማገዶ አቅርብ ብለው ዛፍ ስቆርጥ እጅ ከፍንጅ ሊያሲዙኝ ነው እንዴ!” ቢል አይፈረድበትም፡፡ መጠርጠር ደግ ነዋ! (አይደለም እኛ ይቺ ሀገር እኮ መከራዋን እየበላች ያለችው ባልጠረጠረቻቸው ሰዎች ነው!)
“ሰዉ ሁሉ የኤሌትሪክ ምጣድ እያስገባ ባለበት ማገዶ የሚጠይቁኝ የሆነ ስውር ተልዕኮ ቢኖራቸው ነው እንጂ መቼስ ከአፋቸው አምልጧቸው አይደለም!” (‘ስውር ተልዕኮ’ የሚለው ነገር ለፊልምና ለልብወለድ ወይንም  ዩቲዩቡን ቀውጦት ‘ላይክ’እና ‘ቪው’ ለመሰብሰብ ብቻ ሲመስለን የኖርን፣ አሁንም እዛው አስተሳሰብ ላይ ከሆንን ችግር አለ ማለት ነው፡፡ አሀ...ልክ ነዋ! በምንም ነገር አንድ ቦታ ላይ፣ አንድ አስተሳሰብ ላይ ‘ተቸክሎ’ መቅረት አሁን፣ አሁን በብዙ ነገሮች እያየን እንዳለነው ወደ ታች መንሸራተት ያመጣላ!)
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ምን ሆነ መሰላችሁ...ጓደኞቹን “ማገዶ አቅርብ ያሉኝ ምን ማለታቸው ነው?” ብሎ ሲጠይቃቸው፣ አንደኛው መለሰለታ!  “ጉቦ አምጣ ማለታቸው ነው” የእውነት ግርም የሚል ነገር ነው እኮ! ቃላትም ይሁኑ ሌሎች የሚፈጠሩት ነገሮች ሁሉ...አለ አይደል... እንጀራውን ጠረጴዛችን ላይ የሚያስቀምጡ ሳይሆኑ የተቀመጠውን የሚነጥቁ እየሆኑ ተቸገርንሳ!
እናላችሁ...
“በእጅ በለና!”
“ለምንድነው ሸጎጥ የማታደርጋቸው!”
“በእራት ሰዓት እንትን ባህል ምግብ ቤት እንጠብቀሀለን፣” ምናምን በሙሉ በቃ...'ኦልዲስ ስለሆኑ ተጣሉ ማለት ነው! ኮሚክ እኮ ነው... ለ'ማገዶው' የተባለው ዛፍ ያለው ኪሳችን ውስጥ ነው ማለት ነው፣ አይደል! ወይ ታሪክ! ለስንቱ 'ማገዶ' አቅርቦ ይቻላል፡፡ መቼስ ዛፉ ካልተቆረጠ ማገዶ አይሆን! እናላችሁ... ይቺ ሁለት መቶዋ ነገር ዝም ብላ እንደማንኛውም ባህር ዛፍ ሳይሆን ዋርካ ልትሆን ነው ማለት ነው! ቂ...ቂ...ቂ...
እንግዲህ ጨዋታም አይደል ... ምንም ነገር ትንሽዬ እንኳን የማይጠረጥር ሰው አልፎ፣ አልፎ አለ አይደል! ለእሱ አይነት 'ኢኖሰንት' ሰው እንዲህ አይነቱን ነገር ለማስረዳት ያስቸግራል እኮ!
“አንተ በየቀኑ ነው እንዴ እዛ መሥሪያ ቤት የምትመላለሰው!”
“ምን እባክሀ የቸገረ ነገር ሆኖብኝ ነው...”
“ሁሉንም ዶኪዩመንት አሟልቼ ሰጥቻለሁ አላልከንም እንዴ?”
“ያላቀረብከው ነገር አለ ብለውኝ ነው፡፡”
“ምን?”
“ማገዶ፣ ማገዶ አቅርብ አሉኝ!”
አዳማጩ ምን ያደርጋል መሰላችሁ... ጠደፍ ብሎ ሰዓቱን አየት ያደርግና “ሶሪ፣ ረስቼው ነበር። የሆነ ከባድ ቀጠሮ ረፈደብኝ፡፡ እደውላለሁ፣” ብሎ ሽው ነው፡፡ (ያው ደህና ባላችሁት ወሬ መሀል ድንገት “እደውላለሁ...” ብሎ የሚሮጥ ሰው...አይደውልም!) አሀ..ልክ ነዋ! ሰዉ ሁሉ 'ማገዶ! ማገዶ! ማገዶ!' የሚለው ሲደጋገምበት “ሰውየዋ ጢው ብላለች፣” ምናምን ማለት መጀመሩ አይቀርም፡፡ ያን ጊዜ “ይህን የመሰለ ልጅ ምን ቢያስነኩት ነው እንዲህ መዘባረቅ የጀመረው!” ምናምን ይባልና ከዛ የሆነ ሹክ ባይ አይጠፋም አይደል... (በተለይ በዚህ ዘመን!) ይሄድና “መቼ እለት ነው ከእንትና ጋር ሲያወሩ አይቻቸዋለሁ፣” ብሎ ሹክ ይላል፡፡ በቃ... ከዛ ታሪክ ይደረደርላችኋል፡፡
“እሱ አንኳን ጥሩ ሰው ነበር፡፡ አሁን ምን አድርገኝ ብሎ ነው እዚህ ምስኪን ላይ መድሀኒት የሚያደርግበት!”
“ምቀኝነት ነዋ! ገና ለገና ሊበልጠኝ ነው ብሎ፡፡”
“እኔ እኮ እሱ ሰውዬ ዓይነውሀው አይመቸኝም ስላችሁ አልሰማ ብላችሁኝ ነው፡፡”
ምን መሰላችሁ...እንዲህ የሚሉት እኮ እራሳቸው “ለመልካም ባህሪው ለምንድነው የሆነ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት የማይሰጠው'!” ሊሉለት ምንም የማይቀራቸው የነበሩ ናቸው፡፡ እናማ... የዘንድሮ ወዳጅ ሲያወጣ እንደ ሸምበቆ፣ ሲያንከባልል እንደ ሙቀጫ ነው ለማለት ያህል ነው፡፡
የቡድና የቡድን አባቶች ዘመን ሆነና ነው ግራ እየገባን ያለውና ወደፊትም ግራ እየገባን ላለመቀጠላችን ‘አሹራንስ’ ያለን የማይመስለው።
“የቡድንና የቡድን አባቶች...”
“ከምንና ከምን?”
“ከሰማይ በራሪ፣ ከምድር ተሽከርካሪ?”
“የምድር ተሽከርካሪ” ይባል ነበር፡፡ በቃ ጣጣ የለ፣ “የየት ሀገር ሰው ነህ?” ብሎ ነገር የለ፤ “የእነማን አበልጅ ነው!” ብሎ ነገረ የለ፤ “የየትኛው ቡድን ደጋፊ ነህ?” ብሎ ነገር የለ! አሁን በ‘አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ’ ዘመን ብዙዎቻችን ‘አርቲፊሻል ምናምን’ እየሆንን ይመስላል፡፡ ልከ ነዋ...ዘንድሮ በሆነ ባልሆነው  እየተሽከረከርን፣ እየጦዝን አይደል! ከምድር አንድ ኢንች እንኳን ከፍ ማለቱ አዳግቶን እያለ “ማንም የማይደርስብኝ የሰማይ ተሽከርካሪ ነኝ፣” ባዮች በዛንሳ! የምር...ለዚህ ነው እኮ ይሄ ምስኪን ህዝብ ኦፊሴላዊ ያልሆኑ አለቆች የበዙበት!
የአየር ለውጥን ለመከላከል፣ ለአካባቢ ጥበቃ ምናምን ተብሎ ኔዘርላንድ ሦስት ሺህ እርሻዎችን ልትዘጋ ነው ተብሎ ይኸው እየታመሱ ነው፡፡ ስሙኝማ...ዘንድሮ እኮ ከአውሮፓ የምንሰማቸው ነገሮች ገራሚዎች ብቻ ሳይሆኑ...አለ አይደል... “እነዚህ ሰዎች ይበልጥ እየተፋቁ ሲሄዱ ገና ብዙ ጉድ የሚያሰኙ ነገሮች እንሰማለን፣” የሚያስብሉ ናቸው፡፡ እነሱ ይኸው ስንት ነገር ይከለክላሉ፤ እኛን ጭራሽ “ማገዶ አምጣ!” ‘ፌይር’ አይደለም!
ደግሞላችሁ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ጀርመን ውስጥ ሀያ ምናምን ሰዎች መንግሥት ሊገለብጡ ሲዶልቱ ተያዙ የሚለውን ነገር ሰማችሁልኝ? ያውም ጀርመን ውስጥ! እኔ የምለው... “መንግሥት ግልበጣ” የሚባለው ነገር ለእነ አፍሪካና ለእነ ላቲን አሜሪካ ብቻ የተሰጠ አልነበረም እንዴ! ታዲያ...ቀድመው ሳያማክሩን በእኛ ሰፈር ዘው ብለው ይገባሉ እንዴ! ቂ...ቂ...ቂ... 
ስሙኝማ... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...የዘንድሮ መሰዳደቢያዎችና መወነጃጀያዎች ስለሰለቹን የቀድሞዎቹ ይመለሱልን፡፡ ልክ ነዋ...በቃ የዘንድሮዎቹ ቀለማቸው ሲለቅስ!
“ያቺ ሴትዮ ጉዳዩን ጨረሰችልህ እንዴ?”
“ምን ትጨርስልኛለች! የሆነች...”
“እሷ ሴትዮ ግን... ነገርዬው ምንድነው! የሆነ ፕሮሚስ ምናምን የተደረገላት ነገር አለ እንዴ! አሁን፣ አሁን እኮ በየቦታው እንዴት እንደምትሆን ብታያት!”
“ከተማው ውስጥ ሹክ የተባለችው ነገር ሁሉ የማታመልጥህ አጅሬ፣ ስለ እሷ አልሰማሁም እንዳትለኝ!”
“አልሰማሁም፡፡”
“አምስተኛ ረድፈኛ ሆናልሀለች፡፡”
“አምስተኛ ረድፈኛ ማለት ምን ማለት ነው?”
“እኔ ምን አውቅልሀለሁ፡፡ ብቻ የሆነ ፖለቲካ ምናምን ነገር አለበት መሰለኝ፡፡ ‘አምስተኛ ረድፈኛ!’ ከተባልክ ፖለቲካዊ ስድብ ነው አሉ፡፡”
“ልክ ያለፈው ስርአት ናፋቂ እንደሚባለው!”
“እሱ እሱማ ሰለቸን እኮ...”
“ይልቅ አምስተኛ ረድፈኛ ያሏት ምን ለማለት እንደሚመስለኝ ልንገርህ!”
“እባክህ መልካም ፈቃድህ ከሆነ ንገረኝ፡፡”
 “ልክ ድሮ ብይ ጨዋታ ላይ እንደምንለው ‘እሰይ ብል ባንከረባብት’ ብላ አምስቱን በአንዴ ጠብ ታደርጋለች ለማለት ይሆናል፡፡” ቂ...ቂ...ቂ...
“በሰለጠነና ዘመኑን በተከተለ መልኩ የማገዶ አቀራረብ ስልቶች፣” የሚል ወርክሾፕ ይዘጋጅልንማ! “ማገዶ ስላላቀርብክ ነዋ!” እየተባልን ‘እንዳንጉላላ’ ለማለት ያህል ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1493 times