Print this page
Saturday, 27 October 2012 09:49

“ቦተሊካ”ና ነጻ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ለእስልምና ተከታዮች በሙሉ ኢድ ሙባረክ! ይመቻችሁማ!
እኔ የምለው…የእነኚህ፣ አለ አይደል…”ሪሞት ኮንትሮሉን” ይዘውብናል የሚባሉት አሳዳሪዎቻችን የምርጫ ክርክር አሪፍ አይደል! እንደዛ ልክ ልካቸውን “አጠጥተውና ጠጥተው” ሲተቃቀፉ ማየት መአመት ነገር እንድትናፍቁ አያደርጋችሁም! እኛ አገር እኮ…አለ አይደል…አይደለም “ቦተሊከኞች”፣ ኳስ ተጫዋቾች እንኳን የጨዋታው መጨረሻ ፊሽካ ሲነፋ ጀርባቸውን አዙረው ወደ መልበሻ ቤት አይደል እንዴ የሚሄዱት!እናማ…”ቦተሊከኞች” በሆዳቸው “እንዲህ ብለኸኝማ፣ የተወለድክበትን ቀን ባላስረግምህ…” ምናምን አይነት እየዛቱ የሚሄዱ ነው የሚመስለው፡፡ ድሮም እንዲያው ነን…ዘንድሮ ደግሞ ብሶብናል፡፡ 

ስሙኝማ…የዘንድሮ “ቦተሊከኝነት” ለምን ይናፍቅሃል አትሉኝም…ነፃ “ፉድና ድሪንክ”! ልጄ ቀላል ግብዣ አለ እንዴ! ወላ አሮስቶ ዲቢቴሎ፣ ወላ ስቴክ በያይነቱ፣ ወላ ስቶሊችኒያ…ምን አለፋችሁ የሦስተኛው ዓለም “ቦተሊከኛ” ዝም ብሎ በባዶ ሜዳ ፊቱ የቅቤ ቅል የሚሆን አይምሰላችሁ! በ “ፍሪ ፉድ”ማ እኛም ቅል (የቤውን ለማለት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…) የማንመስልሳ!
ኮሚክ እኮ ነው…ዘንድሮ ነፍስ ያለው ምግብ በመጽሔት ማስታወቂያና በአረብ ሳት ጣቢያዎች ላይ ብቻ እያየን…በ’አቋራጭ የሚበላበትን የማንመኝሳ!
እናማ…አንዳንዴ የግብዣውን ብዛት ስታዩ…አለ አይደል…አንዳንድ ቦሶች “እሺ፣ ጤፍ ለምን፣ ለምን ያገለግላል?” ተብሎ ይጠይቁ፡፡ ምን አለ በሉኝ፣ አንዳንዶቹ…ለአርባ አራት ደቂቃ ካሰቡ በኋላ ትዝ ብሏቸው…”እሱ ነገር አሁንም አለ እንዳትሉኝ!” ባይሉ ምን አለ በሉኝ፡፡ (“ከምላሴ ፀጉር…” መባባል የቀረው ምላሳችን ፀጉር ባይኖረውም “በመኮሰኮሱ” ነው እንዴ!) ኑሮ እንዲህ የሆረር ፊልም በሆነበት ጊዜ…
እናላችሁ…ቄስ ትምህርት ቤት ምናምን “በየኔታ ጉሮሮ ጠጅ ይንቆርቆር፣ በእኛ ጉሮሮ ቀለም ይንቆርቆር…” ሲል የነበረ “የቅቤ ቅል ቦተሊከኛ”…አለ አይደል…”በእኛ ጉሮሮ ውስኪ ይንቆርቆር…” ምናምን ይሆናል፡፡ የውጪ ሽርሽሩስ!...ዲስኩሩስ!...ለትንታኔ መጠየቁስ!
ሀሳብ አለን…”ቦተሊካ” ከኬ.ጂ. ጀምሮ ኮምፐልሰሪ ሆኖ ይሰጥልንማ፡፡ አሀ…ማን “ቦትልኮ” ማን ይቀራል! (ያው እንግዲህ ዘንድሮ ብዙ ነገር የሚሠራው “ማን አድርጐ ማን ይቀራል…” በሚል አይደል!)
እናላችሁ…የ”ቦተሊከኝነት” አሪፍ ነገር መን መሰላችሁ…ከአሥርቱ ትዕዛዛት ተጨማሪ አንድ ሺህ አንድ ያልተጻፉ ትዕዛዛት አፍርሶ ምክንያት መስጠት ይችላል፡፡ “ይህንን እያደረግን ያለነው ለህዝቡ ጥቅም ነው…” ማለት ይችላሉ፡፡
(“ጠቀሙ እንዴ!” ይሉ ነበር የአራዳ ልጆች፣ እንዲህ ቁጥራቸው ባይመናመን ኖሮ)
የምር ግን ዘንድሮ ምን ያስጠላን ነገር አለ አትሉኝም…”ዲስኩር”! “ተናጋሪ በዝቶ አድማጭ የሌለባት ብቸኛዋ አገር” የሚባል መዝገብ ውስጥ ያልገባነው ገና “ስላልተነቃብን አይመስላችሁም!” ቂ…ቂ…ቂ…ሀሳብ አለን…ቴሌቪዥን ስንገዛ አብሮ “ላክሳቲቭ” ምናምን ይሸጥልንማ! አሀ…የማይሆኑ ንግግሮች እየሰማን ሀሳብ አለን…ቴሌቪዥን ስንገዛ አብሮ ‘ላክሳቲቭ’ ምናምን ይሸጥልንማ! አሀ … የማይሆኑ ንግግሮች እየሰማን ‘ሆድ ድርቀቱ’ አበገነና!
አለ አይደል … “ቆሻሻ ለጤና ጠንቅ መሆኑን የወረዳ እንትን የእንትን ቢሮ ሀላፊ አስገነዘቡ …” አይነት ሆድ ያላደረቀ ምን ያደርቃል!
የምር ግን ችግሩ ምን መሰላችሁ … እዚህ አገር ሁሉም ነገር ልክ ያጣል አንድ ነገር ከተጀመረ በኋላ ሁሉም ይቀባበለውና ሌላ የሆድ ድርቀት ሰበብ ይሆናል፡፡ እኔ የምለው … አንድ ነገር ከተደረገ የኤፍ.ኤም. ፕሮግራሞች ሁሉ የግድ መጥቀስ አለባቸው እንዴ!
እናላችሁ … ጩኸቱ ይበዛና፣ ዲስኩሩ ይበዛና … ዘግይቶ የደረሰ ፓትሪዮት ይበዛና … “ኧረ ረጋ በሉ…” ማለት ኃጢአት ይሆንና ሁሉም እረጭ ይላል፡፡ እግረ መንገዴን … የሆነ የህዝብ የሚመስል ነገር በተፈጠረ ቁጥር ‘ለመጠጡ ብቻ ከየቤታችን የምንወጣ ብዛታችን…’ ነገሬ ብላችሁልኛል! በአገር ፍቅር ስሜት እየተንጨረጨረ፣ “እኛ እኮ ድሮም ቢሆን ልዩ ነን…” ምናምን የሚል ‘ትዝ አለኝ አገሬ’ ትንፋሹን የሚቆርጥበት አይበዛባችሁም!
ስሙኝማ … እዚህ አገር ዘንድሮ ከምክንያታዊነት ይልቅ በ “ኢሞሽን” (“አንዳንዴም በቅዠት” የሚል ይካተተልንማ!) እናላችሁ … የአውራጁ ዜማና ግጥም ‘ቅዠት’ መሆኑን እያወቅንማ … መቀላቀል፣ ‘ግንባር ማስመታት’ ስለሚጠበቅብን “አሀ ገዳዎ …” እንላለን፡፡ “አሀ ገዳዎ …” ያለ ሁሉ ከአንጀቱ እየተቀበለ እንዳልሆነ ለሚመለከታቸው ሁሉ በውስጥ ሰርኩላር ይተላለፍንማ!
ሰውየው ንግግር እያደረገ እያለ ተሰብሳቢዎቹ በሚገባ አላዳምጥ ይሉታል፡፡ በዚህ ጊዜ በጣም ይናደድና ምን ይላል መሰላችሁ … “እዚህ አዳራሽ ውስጥ ብዙ ደደቦች ያሉ ይመስላል፡፡ በአንድ ጊዜ አንድ ደደብ ብናዳምጥ አይሻልም …” ይልላችኋል፡፡ ይሄን ጊዜ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ ይነሳና እንዲህ ይላል፡፡ “ያቀረቡት ሀሳብ ጥሩ ነው በእርሶ ይጀመራ!”
እኔ የምለው … እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ … ይቺን ስሙኝማ፡፡ ሰውየው ‘ቦተሊከኛ’ ነው አሉ፡፡ እናላችሁ … ስልችት “የዛሬ ስብሰባችን ልዩ የሚያደርገው …” አይነት ንግግር እያደረገ ተሰብሳቢው ሁሉ ተሰላችቶ የየራሱን ነገር ይንሾካሾካል፡፡ ታዲያላችሁ እሱዬው ሆዬ … “እባካችሁ አንድ ጊዜ ጆሯችሁን አውሱኝ…” ይላል፡፡
ከተሰብሳቢው አንዱ ምን አለ መሰላችሁ … “የእኔን ጆሮ መውሰድ ትችላለህ፡፡ አንተን ከማዳመጥ ግልግል ነው…” አሪፍ አይደል! “የእኔን ጆሮ መውሰድ ትችላለህ…” የሚያስብሉ መአት ነገሮች አሉ፡፡ የሚጠይቀን እየጠበቅን ነው…
ስሙኝማ … የንግግር ነገር ካነሳን አይቀር ብቻውን እያወራ የሚሄድ ሰው አልበዛባችሁም! የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ ኑሮ ቀላል እንዳልሆነ ከዚህ የበለጠ ማሳያ የለም … እንደፈለገ አብረቅርቀን ብንወጣም ‘የሚደለልበት ጎመን’ ያጣ ሆድ … ዝም ብሎ አይቀመጥማ! ስሙኝማ … የምር ግን ይሄ “ለማን ደስ ይበለው…” ብለን ከበሶ ዱቄት ይልቅ … አለ አይደል … ‘ፋውንዴሽን’ የምንገዛ የበዛን አይመስላችሁም! (አንተ እንትና ምነው ቅንድብህ ሳሳብኝ … ማስነቀል ጀመርክ እንዴ! ቅንድብ እያስነቀሉ ባዶ ለመሆን ከመክፈል ባዶ ሆድን ለመሙላት መክፈሉ የሚሻል አይመስልህም፡፡
ስሙኝማ … እግረ መንገዴን፣ የስታሊንን ‘መለስተኛ ጫካ’ የሚያስንቅ ሪዝ ያለው ሁሉ ‘ፔዲኪዩር፣ ማኒኪዩር’ እያለ ነው የሚባለው እውነት ነው እንዴ! እኔ እኮ … የአንዳንድ የ ‘አዳም ዘሮች’ እጅ ከልክ በላይ ሲለሰልስብሽ ሰውየው ተሳስቶ የ ‘ገርሉን’ እጁን ተውሶ ነው የመጣው እንዴ ልል ምንም አይቀረኝ)
ሰውየው ወጪ እየበዛበት በጣም ተቸግሯል፡፡ መንገድ ላይ እያወሩ ከሚሄዱት ሰዎች አንዱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እናላችሁ … ጓደኛ ሆዬ “ገንዘብ እንዴት እንደምትቆጥብ ልንገርህ፡፡ አንተ አንድ ክፍል ተኛ፣ ሚስትህ ሌላ ክፍል ትተኛ፡፡” ሰውየውም …
“ታዲያ ይሄ እንዴት ገንዘብ ይቆጥባል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኝዬው ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ … “ሌሊት በየጊዜው እየነቃች ገንዘብ እያለች አትጨቀጭቅህማ!” አሪፍ አይደል!
እኛም … በየ‘ዲስኩሩ’ መጨቅጨቅ እንደሰለቸን ግንዛቤ ይግባልንማ! ስሙኝማ … እኔ የምለው ብዙዎቹ ቦሶቻችን ዲስኩር ምናምን ላይ ፈገግ የማይሉት ለምንድነው! ልክ ነዋ … ለምን ይመስለኛል መሰላችሁ … እዚህ አገር ሰው ‘ቦተሊከኛ’ ሲሆን አንድዬ ‘የሳቅ ጂኖቹን’ በሙሉ ሙልጭ አድርጎ የሚያጠፋባቸው ይመስለኛል … ወይስ ፈገግ ማለት ለእኛ ‘ፊት ማሳየት’ ይመስላቸዋል!
እናላችሁ … እንግዲህ ጨዋታም አይደል … ከ‘ቦተሊከኝነት’ ነጻ ጥራት ያለው ‘ፉድና ድሪንክ’፣ ነጻ የሆኑ በፊት “በነጣ …” የማይገኙ ነገሮች ሁሉ፣ የውጪ ጉዞው ምናምን ቢናፍቀን የሪቮሉሺነሪ ምናምንና የኔኦ ምናምን ጉዳይ ሳይሆን የ‘ሰርቫይቫል’ ጉዳይ ነው፡፡ ኧረ እባካችሁ የ ‘ቦተሊካው’ የ‘ተቀያሪዎች ቤንች’ ላይ እንኳን ቦታ ልቀቁልን! አሀ … በጆሮ የሚገባ ነጻ ‘ዲስኩር’ ሳይሆን የናፈቀን በአፍ የሚገባ ‘ነጻ ፉድ’ ናፍቆናላ! ሀሳብ አለን … “ዳስ ካፒታል” ምናምን የሚለው መጽሐፍ እህት መጽሐፍ የሆነ “ዳስ ነጻ ፉድና ድሪንክ” የሚል መጽሐፍ ይዘጋጅልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4316 times