Saturday, 03 December 2022 12:42

ሆድ እና ህሊና

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(8 votes)

  “--ስወጣ ሁለተኛ ተመልሼ እንደማልመጣ ሁሌ እምላለሁኝ፡፡ መሀላ የሽንፈት ቅድሚያ ቀብድ ነው፡፡ መሆኑ እንደማይቀር የሚያውቅ ነው የሚምለው፡፡ ብር እስካለኝ ይሄ ነገር ነገም ይደገማል፡፡ ምናልባት ከነገ ወዲያም፡፡ ሁሉም ጥሩ ነገሮች እንዲህ እያሉ ይቀጥላሉ፡፡ ገንዘብ እስካለ ድረስ፡፡--”
    

        አዲስ አበባ ውስጥ ጥሩ ምግብ ማግኘት  ጭንቅ ነው፡፡ ጥሩ ምግብ ማለት የተለየ ነገር ያለው ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ በሞያ የተሰራ ከሆነ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ባለሞያ ከጠፋ ሞያ አይኖርም፡፡ ባለሞያ ካልበረከተ ሞያ ውድ ይሆናል፡፡
ይሄ የሚሰራው ለምግብ ብቻ አይደለም፡፡ ለሁሉም ነገር ነው፡፡ ጥሩ ሰዎች የሚገኙት ጥሩ ምግብ ያለበት ቤት ውስጥ ነው፡፡ ጥሩ ሰዎች ማለት ያው ገንዘብ ያላቸው ማለት ነው፡፡ ገንዘቡ ራሱ ሰዎችን ጥሩ ያደርጋል፡፡ ሀይማኖተኛ ይመስላሉ፡፡ ዝግ ብለው ነው የሚያወሩት፤ ጮክ ብለው አይጣሩም፡፡ ጎንበስ ቀና ያበዛሉ። እጅ ለመታጠብ “ቅደም! አንተ ቅደም!” እያሉ ይገባበዛሉ፡፡ ቅደም ተከተላቸውን አያዛቡም፡፡ ቡና የሚያዙት ምግብ በልተው ሲጨርሱ ነው፡፡
ገንዘቡ ነው ሁሉንም ነገር የሚያወራው። ገንዘቡ ደረሰኙ ላይ ተዘርዝሮ የሚቀርበው መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ገንዘብ የሚከፍል አይቸኩልም፡፡ ትልቅ ሰረሞኒ አለው፡፡ የአገባብ፣ የአወጣጥ፣ የአነሳስ፣ አቀማመጥ፡፡ ገንዘብ ያላቸው እማኝ ይሻሉ፡፡ በሚጋብዙት ሰው ይከበባሉ፡፡ መጋበዛቸው እንዲታወቅ ለክፍያ ይጋበዛሉ፡፡ “እኔ ልብስ.. አንተ ትብስ” ወዘተ…
እንዳጋጣሚ እንደዚህ አይነቱ ቤት ውስጥ ነኝ፡፡ እንዳጋጣሚ ሳይሆን የተገኘሁት ሆን ብዬ ነው፡፡ ሰሞኑን ትንሽ ገንዘብ ብጤ ኪሴ ውስጥ “አለች”፤ በአንዴ ተመናምኖ ፆታው ሳይቀይር በፊት “አለ” ነበረ፡፡ ትንሽም ትሁን ትልቅ፣ ሁሉም በትህትና ስም ”አለችኝ” ነው የሚለው፡፡
መመላለሴ እንዳይታወቅ ፈልጌአለሁ፡፡ ደህና ምግብን ተመላልሶ መብላት ያስጠረጥራል፡፡ በደሀ ህዝብ መሃል ድንገት ወፍሮ እንደ መገኘት ያሸማቅቃል፡፡ የምጋብዘው የለኝም፡፡ ግብዣ ወጪውን እጥፍ ያደርገዋል፤ ወይንም እጥፍ ድርብ፡፡ ራሴን ብቻ እየጋበዝኩ ነው ዘወትር የምገኘው፡፡
“ተራ ዱለት ለመብላት ይሄንን ያህል ብር መክፈል ወይንም በሜታል ዲቴክተር መፈተሽ አለብን ወይ?” ስል ራሴን እጠይቃለሁኝ፡፡ ሁለታችንም ጭንቅላታችንን እንነቀንቃለን፡፡ ተራ ዱለት እንኳን አይደለም፡፡ ተራ የማያደርገው ዋጋው ነው፡፡ ለሚፈትሸኝ ዘበኛ እንደሚሰቀል ሰው እጄን አግድም አንቀረፍፋለሁኝ፡፡
መታዘብ ደስ ይለኛል፤ የማዘው ምግብ እስኪቀርብልኝ፡፡ የመፃኢው ክፍያ ቀብድ ገና ከቤቱ ጌጥ ይጀምራል፡፡ በለሰለሰ ቆዳ የተለበጠ ወንበር እና በባህላዊ አግባብ የተፈለፈለ የእንጨት ጠረጴዛ ላይ ተሰየም ገና ስባል… ዶሮ ለቢላዋ እንዲመቻች አንገቱ ወደ ኋላ ተቀልብሶ ሲጠመዘዝ እንደሚሆነው ኪሴ ውስጥ ያለው ብር እየተፍጨረጨረ መፈራገጥ ይጀምራል። ካዘዝኩ በኋላ ራሴን እወቅሳለሁ፡፡ ወቀሳዬ በአጭሩ፤ “ሰው ለሆዱ ብሎ ይሄንን ያህል ብር እንዴት ይከፍላል?” የሚል ነው፡፡
ተራ እንጀራ እና የዱለት ምግብ ነው። አይኔ ግን  ከሆዴ የተሻለ ይመገባል፡፡ ገንዘብ ያለው ሰው ደስ ይላል፡፡ ጥሩ ምግብ ያለበት ቦታ ጥሩ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ ሁሉንም እንደ ቤተሰብ የሚያሰባስባቸው ገንዘብ ነው፡፡ የታሸገው ገንዘብ እና  የታሸገ ውሃ አስፈላጊ ነው፡፡ ሰዎቹ ዘላቂ ይመስላሉ፡፡ ምን ያህል ዘመን እንደኖሩ ሰውነታቸው ይናገራል፡፡ ሰውነታቸውን ተንከባክበው ነው የያዙት፡፡ ጥሩ ምግብ እየተመገቡ፣ የተመገቡትን እያቃጠሉ… መልሰው ለመመገብ ይመጣሉ፡፡ ወጣቶቹ በሙሉ  ጂም የሚሄዱ ናቸው፡፡ ከመመገባቸው በፊት ወይንም በኋላ፡፡ እዛ “ትሬድ ሚል” ላይ ወጥተው እዛው ድክ ድክ  እያሉ ላባቸውን ይጠርጋሉ፡፡ ይሄም በዛው የ”ጥሩነት” ካታጎሪ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ ጥሩ ምግብ የሚበላ ሰው በአርማታ በተሰራ የመርቲ ጣሳ (ዳምፔል) ጡንቻውን አያፈረጥምም፡፡ ሰውነታቸውን አይቶ ምን ሰርተው እንደሚበሉ ማወቅ ይቻላል፡፡ ምን ሊበሉ እንደሚችሉ አስበውበት የሚበሉ የሰው አይነቶች ናቸው፡፡
“ራሳቸውን የሚጠብቁ” በሚል ስያሜ በጥቅሉ ይጠራሉ፡፡ ለራሳቸው የሚሰማቸውን ጥሩ ስሜት ከማህበረሰብ ተቀባይነት በኋላ የሚጨብጡት ነው፡፡ እኔም ገንዘብ በኪሴ ቢከርምልኝ የምፈልገው እነሱን ለመሆን ነው። ራሴን በመጠበቅ ተቀባይነትን ከማህበረሰቡ የምጠባበቅ፣ የራሴ አእምሮ በሚያመነጨው “ኦክሲቶሲን” የሰከርኩ ሰው መሆን ነው የምፈልገው፡፡ መስከር መክሰርን ዞሮ ዞሮ ያመጣል፡፡ ሰውነታቸውን አይቶ ምን ሰርተው እንደሚበሉ ማወቅ ይቻላል፡፡
ተያይዞ እጅ ለእጅ የሚሄድ ነገር ነው፡፡ የእጅ ስልክም አለ፡፡ እሱም እንደሚመገቡት ምግብ ጥሩ አይነቱ መሆን አለበት፡፡ ከእጅ ስልኩ ጋር የሚሄድ የእጅ ሰዐትም ያስፈልጋል፡፡ አንዱ ካለ ሌላው ይከተላል፡፡ ሻሜታ ጠጥቶ ውድ ልብስ የሚለብስ የለም፡፡ የፊቱ ወዝ ወይንም `Was` ድሮ በስቃይ ያደገበት፣ አሁን ወደ ደረሰበት ፈፅሞ ድርሽ እንዳይል በገንዘብ ኃይል ተገዝቷል። ወዝ ስለ ዛሬው እንጂ ስለ ትላንቱ አይናገርም፡፡ `was` ሁሌ `is` ነው፡፡
ይታያሉ እንጂ አይዳሰሱም፡፡ በዐይኔ መዳሰስ የምችለው ሁሉ ላይ የድምዳሜዬን ቀንበር እጭንበታለሁኝ፡፡ ቢያንስ ለዐይን አይከፈልም። ለምን በምታየው ላይ ድምዳሜህን ደፈደፍክ የሚለኝ የለም፡፡ አፌ ቁጥብ ነው፡፡ ምግቡ ሲቀርብ እሱንም አላቅቃለሁ፡፡ በቦታው ላይ የተገኘሁበት ምክኒያት እሱው ስለሆነ፡፡
ድንገት፣ ከጀርባዬ የተቀመጠ የወንድ ድምፅ በዝግታ ስድቡን ሲያዥጎደጉደው ከታለመበት ጠረጴዛ ተርፎ ወደ እኔ ክልልም ደረሰ፡፡
ሚስቱን ነው የሚሰድባት፡፡ እሷም በዝግታ እያነባች ነው፡፡ ቁጥብ ናቸው ግን፡፡ ለቅሶዋን መለፈፍ አትፈልግም፡፡ ድምፅ ማጉያዎቹን ነቅለው ነው በሰፊው የምግብ አዳራሽ ውስጥ በምልክት ቋንቋ የሚወቃቀሱት፡፡ እኔ ያዘዝኩት ልክ ሊመጣ ሲል፣ ከኋላዬ እንስቲቱ ተነሳች። እመር ብላ ወይንም ሂጂ ብረሪ በሚያስብል አኩዋኋን አይደለም፡፡ እጇን ልትታጠብ ነው፡፡ ሜካፑዋን ሳታበላሽ ነው የምታለቅሰው፡፡
የቤታቸው ውስጡ እንዲታየኝ ስትመለስ ወንበሬን አዙሬ ፊቷን ትኩር አድርጌ አጠናሁት፡፡ ፊቷን ከታዘዘው ምግብ ጋር እንዲሄድ ለውጣው ነው የመጣችው፡፡ የወለደች አትመስልም፡፡ ወደ ቤታቸው ውስጥ ለማጮለቅ ስጥር የራሴ እጅ ጠቅልሎ ያመጣው ጉርሻ አናጠበኝ፡፡ ያዘዝኩት ምግብ ልብ ሳልል እፊቴ ቀርቧል ማለት ነው፡፡ አይኔ ያላየውን እጄ ጠቅልሎ አመጣው፡፡ አፍ በሰፊው ለጉርሻ ሲከፈት ለካ አይን ያለፍላጎት ይጨፈናል፡፡ አላውቅም ነበር። አይኔ ብቻ ሳይሆን ቤቱ ውስጥ ተከፍቶ የነበረው ክላሲካል ሙዚቃም ቆሟል፡፡ ልክ ውሃ ውስጥ እንደ መስጠም፡፡ ምግብ ይሄንን ያህል ስልጣን በስሜት ህዋሳቶቼ ላይ እንዳለው አላውቅም ነበር፡፡ አላውቅም ሳይሆን፣ ሁሌ በምበላበት ወቅት የሆነውን በልቼ ጨርሼ ስነቃ ስለማላስታውስ ነው፡፡
ስጎርስ ፊቴ ወደ አንድ ጎን ስለተንሻፈፈ… ወዲያ ማዶ ራቅ ያለ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠችዋ ልጃገረድ፣ የድሮ ፍቅረኛዬን መስላኝ፣ ትን ሊለኝ ነበር፡፡ ስውጥ ፎከሴ ተሻሻለ፡፡
ምግብ እንደ ማደንዘዣ የመሰለ ባህሪ አለው፡፡ በህይወቴ ላይ በሁሉም አቅጣጫ ያለ ውጥረትን አርግቦ ወደሚያመሰኳ “ቦቫይን” ይቀይረኛል፡፡  ስጋውን መጠቅለል፣ በአዋዜ… እና በተጨማሪ ሚጥሚጣ፣ ከዛ አይንን ጨፍኖ መጉረስ፡፡ የከፈልኩት ብር አግባብ ስለመሆኑ ያለ ጥርጣሬ የማምነው፣ የመጀመሪያዎቹ የጉርሻ ዙሮች ላይ ነው፡፡ ጨጓራዬ እንደ አፍ ተከፍቶ ከላይ በጉሮሮ የሚወርድለትን ለመቅለብ አንጋጧል፡፡ ሲገባ የገባውን እንደ ስልኬ ይነግረኛል፡፡
“your stomach had been credited with one hefty morsel…”
ማንንም አላውቅም፤ ማንም አያውቀኝም፡፡ ሳንተዋወቅ ግን እንተዋወቃለን፡፡ ሁላችንም ብዙ ብር ከፍለን ለመመገብ የተኮለኮልን ነን፡፡ ያውም በፆም ቀን፡፡ የፆም ምግብ ያዘዙት እንደ ክርስቶስ ሐዋሪያት መከራን በመቀበላቸው ለፅድቅ የተመረጡ መስለዋል፡፡ ፆም ለምኔ ብለው ጥብስ የሚበሉትን (የእኛ አይነቶቹን) በፃድቅ አይናቸው ተጠይፈው፣ ሰጋቱራ የመሰለውን የስልጆ ፍትፍታቸውን በእንጀራ ይነካካሉ፡፡
ራቅ ብሎ የወይን ጠርሙስ የተደረደረበት ሼልፍ አለ፡፡ ቢናድ የሚፈጠረውን ከስሩ በበርጩማ የተኮለኮሉት አያስቡም። አለማሰባቸው እርግጠኛ አድርጓቸዋል፡፡ በእርግጥም የሚፈርስ አይመስልም፡፡ መታመን ማለት ይሄ ነው፡፡
በሩ ላይ የኤቲኤም ማሽን ተገትሯል። የሚተማመኑበት ነገር፣ ከዚህ በፊት አላሳፈራቸውም፡፡ የተበላሸ ምግብ በከፈሉት ብር ቀርቦላቸው አያውቅም፡፡ መታመን ማለት ይሄ ነው፡፡ የተቀመጡበት ወንበር ክብደታቸውን ሁሌ እንደሚሸከም እንጂ እንደ ቄጤማ ከስራቸው ልምሻ ሆኖ እንደማይከዳቸው እርግጠኛ ናቸው። ስኳር እና ደም ብዛት ለግዜው ትዝ አይሉም፡፡ የሚሞቱ አይመስሉም፡፡ መሞት ቀርቶ ትን እንኳን አይላቸውም፡፡
በልተው ሲጨርሱ የማይቀረው ሂሳብ በማይጠበቅ፣ በቀጭን ደረሰኝ ላይ ተዘርዝሮ እያጓራ ይመጣላቸዋል፡፡ ከኪሳቸው መክፈል ካልቻሉ… በር ላይ በቆመው ማሽን ላይ ቢጠነቁሉ መፍትሄ ያዋልዳል፡፡
ከምግብ በፊትና ልክ ምግቡን ተመግቤ ስጨርስ ፀፀት ተመልሶ ይመጣብኛል፡፡ የምከፍለው ገንዘብ ለተመገብኩት ምግብ እንደማይመጥን የሚገልፅ አመፅ በውስጤ ይቀሰቀሳል፡፡ ሆዳዊ ህሊናዬ ይወቅሰኛል፡፡ ኃጢአት በአንደበት ብቻ ሳይሆን በጨጓራም እንደሚፈፀም ግልፅ ይሆንልኛል፡፡
“መልካም ነበር?” ብሎ አስተኛጋጁ ሲጠይቀኝ ደግሞ የባሰ እበሽቃለሁ፡፡
“አይ በጣም አይደለም!”  ብዬ ለመመለስ እፈልጋለሁኝ፡፡ ቁርሴን በመዝለል አዳብሬ የቆየሁት የፆም ትህትና፣ በጥጋቤ ምክኒያት ብትንትኑ ይወጣል፡፡
“ገበታው ከፍ ይበል” ብሎ አስተናጋጁ በድጋሚ ይጠይቀኛል፡፡ በመሶቡ የምግብ መድረክ ላይ እንደ ፈጣሪ ሲያደርገው አይታወቀውም፡፡ ምድርን ፈጥሮ ሰጥቶኝ በኋላ ተጠቅሜ ስጨርስ  ከእነ ሀጢአቴ ሊሰበስበኝ ይመስላል፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን “ሂሳቡን ላሰራው ወይ?” የሚል ነው፡፡
የጥርስ መጎርጎሪያዬን አነሳለሁኝ፡፡ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ ከኋላዬ ባል እና ሚስቱ አድፍጠዋል። ምግብ አስታርቋቸዋል ማለት ነው፡፡
ሳልጠየቅ በፊት ልጠየቅ የምችለውን ጠንቅቄ አውቀዋለሁኝ፡፡ አስቀድሜ አዘጋጅቼዋለሁኝ። “አራት መቶ ብር ለሶስት ጉርሻ…?!” ብዬ እየተበሳጨሁኝ፣ ከዋለቴ አውጥቼ የእነሱ ውስጥ አስገባዋለሁኝ፡፡
የማይቀርልኝን ከፍዬ እነሳለሁኝ፡፡ ለአስተኛጋጁ ትንሽ ካልወረወርኩለት ነገ ፊቱን ሊያኮፋትርብኝ ይችላል፡፡ ስወጣ ሁለተኛ ተመልሼ እንደማልመጣ ሁሌ እምላለሁኝ፡፡ መሀላ የሽንፈት ቅድሚያ ቀብድ ነው፡፡ መሆኑ እንደማይቀር የሚያውቅ ነው የሚምለው፡፡ ብር እስካለኝ ይሄ ነገር ነገም ይደገማል፡፡ ምናልባት ከነገ ወዲያም፡፡ ሁሉም ጥሩ ነገሮች እንዲህ እያሉ ይቀጥላሉ፡፡ ገንዘብ እስካለ ድረስ፡፡ ጥሩ መስዬ ከጥሩ መሳይ ሰዎች ጋር ትከሻ መተሻሸቴ ይቀጥላል፡፡
ትንሽ አለፍ ብሎ፣ ከምግብ ቤቱ ትንሽ መንገድ ላይ ቡና ደግሞ አለ፡፡ ጥሩ ቡና። ስም እና ሎጎ ያለው ቡና፡፡ ዋጋው ሳይጠየቅ የሚከፈል፡፡ አንደኛው ካለ ሌላኛው ይከተላል፡፡
ሰማዩም ከተንጠለጠለበት አይወድቅም፡፡ የሰው ልጅም ይወጣል ይገባል፡፡ ይሄው እስከ ጊዜው ይደጋገማል፡፡



Read 1155 times