Saturday, 03 December 2022 12:30

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


                         ልጆችን እንጂ ልጅነትን ማስቆም አይቻልም!
                            አሌክስ አብርሃም

         ወላጆች  ልጅ ሲወልዱ ድካምና ውጣውረዱን የሚችሉበት ፍቅር አብሮ ባይሰጣቸው ኖሮ … ገና በዓመታቸው ዳይፐራቸውን እያስያዙ ከቤት ያባርሯቸው ነበር፡፡ ልጅ ማሳደግ አዲስ ከዚህ በፊት ያልነበረ ሰው መስራት ሊባል ይችላል፡፡ልጅ ማሳደግ  የራስን ፍላጎት  አምሮትና ማንነት ጭምር መተው የሚጠይቅ ከባድ ኃላፊነት ነው። ያስደስታል፣ ያበሳጫል፣ አንዳንዴም ፀጉር ሊያስነጭና ሊያስለቅስ ይችላል!  ለዛም ነው ከመውለድ በፊት ደግሞ ደጋግሞ ማሰብ ወሳኝ ነው የሚባለው፡፡ እሽ አስበንም ይሁን ሳናስብ ልጅ ተወለደ ከዛስ? የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ይሄ ነው …
አንዳንድ ወላጆች ህፃናት ልጆችን ወደቤታቸው  የመጡ ተጨማሪ ፍጥረቶች እንጅ ልክ እንደነሱ ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ የቤቱ ባለቤት መሆናቸውን አያስቡትም፡፡ በህፃናትና ወላጆች መካከል የሚፈጠረው ‹‹ጦርነት››  ሁሉ፣ ልጆች የባለቤትነት መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት የህፃን ጥረትና ወላጆች የልጆቹን ባለቤትነት ለመንፈግ የሚያደርጉት የአዋቂ ክልከላ ውጤት ነው፡፡
ምሳሌ:-  ልጆች የፈለጉት የቤቱ ክፍል ላይ መጫወቻቸውን ማስቀመጥ (መዝረክረክ)፣ እቃዎችን መገለባበጥ፣ መንጠላጠል፣ ማቆሸሽ፣ የሚሰበር ዕቃ ካገኙ መስበር ፣እጃቸው ላይ ባገኙት እርሳስ፣  ከለር  ከሰል ሊፕስቲክ ኩል ወዘተ ያገኙት ነገር ላይ መፃፍ  መሳል ይፈልጋሉ! ወላጆች ደግሞ እነሱ የወሰኑላቸው ቦታ ላይ ብቻ እንዲጫወቱ ፣የፈቀዱላቸውን ዕቃ ብቻ እንዲነኩ ይፈልጋሉ …በዚህ ትግል መሃል ለቅሶው፣ ቁጣው፣ ማስፈራሪያው፣ ማስጠንቀቂያው ገፋ ካለም ቁንጥጫው ነጠላ ጫማው … ዓለም የማይዘግበው ጦርነት ሁሉ በየቤቱ ይኖራል! የወላጆችን ክልከላ ከልጆች ደህንነት እንዲሁም ከቤት ውበት አንፃር ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የሆነ ሆኖ ክልከላ የት ድረስ?
በተለይም በአበሻ ወላጆች ዘንድ በስፋት የተለመደ አንድ ጉዳይ አለ …ይሉኝታ ! እንግዳ ወደ ቤት ከመጣ ልጆች ቤት እንዳያዝረከርኩ፣ እንዳይንቀዠቀዡ ከባድ ማዕቀብ ነው የሚጣልባቸው! ይህም ከጨዋነት ይቆጠራል፡፡ እንግዳ የቤቱን ውበት፣ የልጆቹን ባህሪ መበላሸት ታዝቦን እንዳይሄድ እንፈራለን! አንዳንድ እንግዳ እንደውም አስተያየት ሁሉ ይሰጣል ‹‹አይ እነዚህን ልጆች አቅበጣችኋቸዋል፤ አሁን የእንትና ልጅ  ገና እናቱ በዓይኗ ስትገለምጠው ነው እጅ በደረት አርጎ የሚቀመጠው....!›› ስለዚህ በእንግዶች ፊት ክብራችን ከፍ እንዲል፣ ከእንትናም እናት ላለማነስ፣ ልጆቹን በምንም ይሁን በምን ለጊዜው የእስር ቤት አይነት ክልከላ እንጥልባቸዋለን! የልጆች ተፈጥሮ ደግሞ አሳሽነት  ነው፣ መፈለግ ነው መንካት ነው፣ መሞከር ነው! በደመነፍስ መንቀሳቀስ ነው  ማዝረክረክ ነው …የፈለጉትን በፈለጉበት ጊዜ እንጅ በኋላ እንግዳ ሲሄድ የሚል ነገር አይገባቸውም! ይሄን ተፈጥሯቸውን ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸውም መቋቋም አይችሉም! ልጆች ልጅነትን አይቋቋሙም!
እንግዳም ባይኖር ብዙ  ወላጆች  ቤታቸውን የሚያደራጁበት መንገድ ፈፅሞ ለልጆች የማይመች ነው! (የቤት ችግር እንዳለ ሆኖ) ገና ሲያረግዙ ለአራስ ጥየቃ የሚመጣውን ወዳጅ ዘመድ ታሳቢ በማድረግ፣ አልያም ራሳቸውን ስለሚያስደስታቸው፣ ወይም የሆነ ሰው ቤት ስላዩት  ቆንጆ የቲቪ ማስቀመጫ ጠርዙ ከመሳሉ የተነሳ ዶሮ የሚያርድ … ጫፍና ጫፉ እንደጦር የሾለ በውድ  ዋጋ ይገዛሉ፣ ትልቅ ፍላት ስክሪን ቲቪ ያስቀምጡበታል፣ ልጆች ቶሎ ያድጋሉ፣ ብዙዎቻችን እቃ የመቀየር አቅሙም ባህሉም የለንምና ቦታ እንኳን ሳይቀያየር ይደርሳሉ! በቀላሉ ስለሚደርሱበት ቲቪ ማስቀመጫው ላይ መንጠላጠል፣ ቲቪውን መንካት አስፈላጊ ከሆነም ባገኙት እቃ መኮርኮም ይፈልጋሉ!  ከፈለጉ ደግሞ ያደርጉታል! ወላጅ የዕቃዎቹን ውድነት ከልጆቹ ነፃነት ያስቀድማል! በውድ ዋጋ የገዛው ሶፋ ላይ ሽንታቸውን ሊሸኑ ምግብ ሊያንጠባጥቡ …ወተት ሊደፉ ይችላሉ …ወላጅ በብስጭት ድፍት ሊል ምንም አይቀረውም! ችግሩ ከየት መጣ?
ቤታችሁ ውስጥ  ከጥግ እስከ ጥግ ኤንትሬ ከነተሳቢው የሚያክል ሶፋ ትገጠግጣላችሁ፣ በዛ በኩል ብሔራዊ ሙዚየም የሚቀናበት ቡፌ በብርጭቆና ምናምን አጭቃችሁ  ታቆማላችሁ... አየር አያሳልፍም እንኳን ሰው! …በዛ ላይ የአንዳንዶቻችን  የቀለም ምርጫ እንኳን ልጆችን አዋቂ በድብርት የሚገድል ነው! ከዛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በልጆቻችሁ ላይ ታውጁና ሚስት ወጥ ማማሳያ፣ ባል ቀበቶ ይዛችሁ ትቆማላችሁ! የቤተሰብ “ኮማንድ ፖስት”!
ልጆች ላይ መጮህ፣ መምታት፣ ማስፈራራትን እንደ መከላከያ ይወሰዳል! የዚህ ሁሉ ችግር መነሻው ገና ከጅምሩ ልጆችን የቤቱ ባለቤት ሳይሆን ተጨማሪ እንደ ወላጆቻቸው ፍላጎት ብቻ የታዘዙትን እያደረጉ የሚኖሩ ፍጥረቶች አድርጎ ማሰብ ነው፡፡ ልክ ባል ወይም ሚስት ለእነሱ የሚመቻቸውን የእቃ አቀማመጥ እንደሚወስኑ ሁሉ ለልጆቹንም ታሳቢ ያደረገ  የእቃ፣ የከለር የአቀማመጥ ሁኔታዎችን አቅም በሚፈቅደው ማመቻቸት ግድ ይላል! ምክንያቱም …ልጆችን ማስቆም ይቻል ይሆናል፣ ልጅነትን ማስቆም ግን አይቻልም:: …ልጆች ፊታችሁ የቆሙ ትንንሽ ፍጥረቶች ሲሆኑ ልጅነት እነዚህን ትንሽ ፍጥረቶች ጦር ሰራዊት የሚያደርግ ውስጣዊ ባህሪ ነው! ዋናው ነጥብ  (እንግዶች ሌላ እንግዳ ሆነው የሚሄዱበት ብዙ ቤት አላቸው…ልጆች ግን ልጅ ሆነው መኖር የሚችሉበት ብቸኛ ቤት ቤታቸው ብቻ ነው!)  ያዝረክርኩ፣ ግን እንዴት እንደሚያስተካክሉ ሳትታክቱ አስተምሯቸው፣ ልጆች  ዕቃዎቻችሁን እንዳያበላሹ ከምትጠነቀቁት በላይ ዕቃዎች ልጆቻችሁን እንዳይጎዱ ቀድማችሁ አስቡ ተጠንቀቁ! አመቻቹ! ሶፋ ያረጃል ይጣላል፣ ቲቪ ነገ ከጥቅም ውጭ ይሆናል፤ ልጆች ግን በምንም የማይተኩ  አስቸጋሪ፣ ‹ስማርት›  እና  ውብ ፍጥረቶች ናቸው!  
ዛሬ ቀላል የሚመስላችሁ የልጆች ጨዋታ፣ ነገሮችን ለማወቅ መጓጓት፣  የነገ ማንነታቸው ላይ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አለው! መሳቢያችሁን ከፍቶ እንዳያይ፣ ቡፊያችሁን ከፍቶ የሸክላ ሰሐንና ብርጭቆ እንዳይሰብር በቁንጥጫና በጩኸት፣ በነጠላ ጫማና ቁንጥጫ እያሸማቀቃችሁ  ያሳደጋችሁትን ልጅ፤ ‹‹ልጄ ሲያድግ ናሳ ነው የሚሰራው፣ ጨረቃን ነው  የሚያስሰው…›› ትላላችሁ … ልጆች ማሰስን የሚጀምሩት ከጨረቃ አይደለም፤  ከቤት ነው! ዓለምም ህዋም ለልጆች ቤታቸው ነው፡፡ አዲስ ነገር መሞከርን የሚፈራ፣ ስህተትን የሚፈራ ይሄንና ያን ብነካ ጩኸትና ቅጣት ይከተለኛል በሚል ተሸማቆ ያደገ ህፃን፣ መፈለግ፣ ማሰስ፣ መሞከር ሳይሆን መደበቅ ነው የሚቀናው፡፡ ለዛ ነው  አብዛኞቻችን  ድብቆች ደንጋጭና ግልፅነት የሚያስፈራን፣ አዲስ ነገር ‹ነርቨስ› የሚያደርገን  ሰዎች የሆነው! ሩቅ ሳትሄዱ አስተዳደጋችሁን ዙሩና አስታውሱ! አስተዳደግ!
ሳጠቃልለው (ጨዋታ ለልጆች ቀልድ አይደለም፣ ቤታችሁ መጥቶ ለሚሄድ እንግዳ ሳይሆን፣ ለልጆቻችሁ እንዲመች አድርጋችሁ አመቻቹ! ቤታችሁ  የልጆቻችሁ ዓለም ነው! ዓለማቸውን ነገ ለማያስታውሳችሁ እንግዳ ይሁን ጎረቤት አትቀሟቸው!)  ልጆች ያዝረከረኩትን ቤት ማየት የማይፈልግ እንግዳ ፣እዛ ፓርክ፣ ቤተ መንግስት፣ ሙዚየም ምናምን ሂዶ ይጎብኝ! አንዴ ልድገመው …ቤታችሁን ንፁህ ግን ልጆች  እንዳሻቸው የሚያዝረከርኩት ይሆን ዘንድ መልካም ፈቃዳችሁ ይሁን! እናንተም እንግዳ ሆናችሁ ሰዎች ቤት ስትሄዱ ከወላጆቹ የበለጠ ለልጆች ምቹ እና ቀላል ለመሆን ሞክሩ …በሰው ዓለም አትኮፈሱ!


___________________________________________________
=================================================



                  ስለ “ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” (Settler Colonialism) ማን ምን አለ?
                     ጌታሁን ሔራሞ


        የሀገራችንን የኋላ ታሪክ በተመለከተ ስለ “ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” የሚቃረኑ እሳቤዎች ከዚህኛውም ከዚያኛውም ጎራ ሲሰነዘር እንሰማለን። ለምሣሌ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና ፕሮፈሰር አሰፋ ጃለታ፡፡ (የምኒልክን ወደ ደቡብ አቅጣጫ መዝመትን ከ”ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” አገናኝተው ይተነትናሉ። በተቃራኒው ፕሮፈሰር መሳይ ከበደ፤ (በ”Survival and Modernization” መፅሐፋቸው) እና ዶ/ር ሀብታሙ መንግሥቴ ተገኘ (የ”በራራ-ቀዳሚት አዲስ አበባ” መፅሐፍ ደራሲ) የምኒልክ ዘመቻ በ”ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ”ነት ከተፈረጀ የኦሮሞው የሞገሳ፣ የገዳ እና የፍልሰት ታሪኮችም የ”ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” ይዘቶችን እንዳቀፉ ይሞግታሉ። በተለይም ሀብታሙ መንግስቴ በመፅሐፋቸው፤ (በራራ-ቀዳሚት አዲስ አበባ) ምዕራፍ ሰባት “የሰፈራ ቅኝ ግዛት፣ የባህል ድምሰሳና የዘር መሳሳት በዓለም ታሪክና በኢትዮጵያ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ስለ “ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” ያነሱት፣ እነ ፕሮፈሰር አሰፋ ጃለታ ከሚያነሱት በተቃራኒው ነው።
በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ሌሎች የሀገር ውስጥም የውጭም ፀሐፍት ብዙ ብለዋል። በእኔ ዕይታ በሁለቱም ጎራ ያሉ ዕሳቤዎች ለውይይት መቅረብ አለባቸው የሚል እምነቱ አለኝ። ምክንያቱም በአካዳሚክም ሆነ በፖለቲካ ሊሂቃን የሚነገሩ ሐቲቶች ወደ ሕዝቡ ሲደርሱ፣ ትርጉማቸው እየተዛባ፣ ግጭቶችን የመቀስቀስ ዕምቅ አቅም አላቸው። እይታዎቹ ታች ወርደው ወደ ጠብ-ጫሪነት ከመቀየራቸው በፊት፣ (ተቀይረዋልም) ሚዛናዊነትን በተላበሰ መልኩ መነጋገር ወደ መፍትሔው አቅጣጫ ይወስደናል የሚል እምነቱ አለኝ።
ስለዚህም በቅርቡ “ስለ ‘ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ’ ማን ምን ብሎ ነበር?” በሚል ርዕስ፣ ከፅንሰ ሐሳቡም በመነሳት በሁለቱም ጎራዎች የተንፀባረቁ ሐሳቦችን ላስቃኛችሁ እሞክራለሁ። በነገራችን ላይ የ”ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” ፅንሰ ሐሳብ ከመደበኛው ቅኝ አገዛዝ ፅንሰ ሐሳብ እንደሚለይ ታምኖበት፣ በጥልቀት ጥናት መደረግ የጀመረው ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ ነው።

=========================================================

                     ሙሰኞች፤ ”60 ለመንግስት፣ 40 ለእኛ” እያሉ ነው
                        ሙሼ ሰሙ


        ሙስናና ሙሰኞች የመንግስትን መዋቅር መሳ ለመሳ ገጥመው፣ የራሳቸውን የአሰራር ስርዓት ዘርግተውና “ኮሚሽን” አደላድለው፣ ኪሳቸውን እያደለቡና ሀገር እያፈረሱ እንደሆነ በስፋት እየተነገረ ነው።
መፈክራቸውም  60 ለመንግስት፣ 40 ለእኛ (ሙሰኞች) እንደሆነም እየሰማን ነው። ሙስና ስጋ ለብሶ ነፍስ ገዝቶ በሕዝብና በመንግስት መሃል  በኩራት መንጎማለሉ ሳያንሰው፣ የሚያከብረውና የሚፈራው ሕግ፣ የሚያሸማቅቀውና የሚያፍረው የሞራል መዳድል እንደጠፋም እየተገለጸ ነው።
ይህ እንግዲህ ቱባ ቱባ ሙሰኞች ሲዘከሩ የምንሰማው ወቅታዊ ትርክት ነው። በሙስና ከተጨማለቁትና በሕገ ወጥ መንገድ ሀብት ጠግበው ከሚተፉት ባለሃብቶችና አስፈጻሚ የመንግስት ጋሻ ጃግሬዎች የጥጋብና የፈንጠዝያ ዓለም ወረድ ሲባል፣ በአስተዳደራዊ በደልና በአገልግሎት እጦት በየእለቱ እየተንከራተቱና ደም እንባ እያለቀሱ ያሉ ዜጎች መኖራቸው ፈጽሞ የተረሳ ይመስላል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ሰዓት የማይፈጅ አንድ ተራ አስተዳደራዊ ጉዳይ ለማስፈጸምና አገልግሎት ለማግኘት ከቢሮ ቢሮ፣ ከአስፈጻሚ  አስፈጻሚ መንከራተት፣ መረጃህ የለም፣ ሰነድህ ጠፍቷል፣ ነገ ተመለስ፣ አይመለከተኝም፣ የራስ ጉዳይ፣ ምን ታመጣለህ መባል፣ መንጓጠጥ፣ መገላመጥና የፈለክበት ሂድና ክሰስ  መባል የእለት ከእለት ኑሯችን ሆኗል።
ሙስና በስልጣን ከመባለግና ስልጣንን ተገን አድርጎ ያልተገባ ጥቅም ከማግኘት ባሻገር ሰፊ የበደልና የግፍ ጉሮኖ መሆኑም ተዘንግቷል። የአሰራር ብልሹነት፣ አስተዳደራዊ በደል፣ ተገልጋይ ማጉላላትና ማንገላታት፣ በስራ ሰዓት አለመገኘት፣ የስራ መደብን ጥሎ መጥፋት የመሳሰሉት ኑሮህን እንድታማርርና እራስህንና ሀገርህን እንድትጠላ የሚያደርጉህ ግፎችና በደሎች የሙስና ዓይነተኛ መገለጫ መሆናቸው ከመዝገብ ተፍቋል። አስዳደራዊ በደሎችና ግፎች አብዛኛውን ሕዝብ የሚመለከቱና ከቱባ ሙሰኞችና አቀናባሪዎቻቸው ዘረፋ በላይ እጅግ የላቁ ጉዳት አድራሽና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ተረስቷል ።
የሙስና ትግሉ ግብ ለቱባ ሙሰኞች አዳዲስ ኮሚቴ ከማቋቋምና መረጃ ከማሰብሰብ ባሻገር፣ ሰፋ አድርጎ ሊፈትሸውና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ  አስቻይ (Enabling) ሁኔታዎቹ መታገል መሆኑ፣ ሰሚ ጆሮ ያጣ ጩኽት ነው።
ትኩረትና ትግል የሚሹ አስቻይ ( Enabling) ሁኔታዎች በጥቂቱ እንቃኝ፡
አንደኛው ለሙስና አስቻይ ሁኔታ ሳይሰሩ፣ ሳይለፉና ሳይደክሙ በዘረፋና በንጥቂያ መክበር የማያስጠይቅ መብት መሆኑ ነው። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ ስር እየሰደደና ባህል እየሆነ የመጣው ሳይሰሩ፣ ሳይለፉና ሳይደክሙ ሆኖና መስሎ በመገኘት ብቻ  ያዩትንና የሰሙትን ሀገራዊና ግለሰባዊ ሀብት፣ የኔ ነው በማለት መቀራመትን የሚያበረታታ አስተዳደራዊና ስነ ልቦናዊ አስቻይ ሁኔታ ስር እንዲሰድ መፈቀዱ ነው ።   
ሁለተኛው አስቻይ ሁኔታ ጦርነቱ ነው። ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጠረው ውጥረትና ቀውስ ምክንያት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መዛበት፣  ጥቂት ስርዓት አልበኞች አጋጣሚውን ተጠቅመው በዘረፋና በሙስ እንዲሰማሩ፣ እንደፈለጉ እንዲፈነጩና እንዲከብሩ እድል መፍጠሩ ነው።
ሶስተኛው አስቻይ ሁኔታ የክልከላ፣ የእገዳ፣ የስርዓት መፋለስና  የአሰራር መጨማለቅ የማን አለብኝነትና የቸልተኝነት ስር መስደድ ነው። ቤት መሸጥ፣ መሬት መሸጥ፣ መታወቂያና መንጃ ፈቃድ ማደስና ማውጣት፣ ንብረት ማዛወር የመሳሰሉት መሰረታዊ መብቶች መታገዳቸው በሕገ ወጥ መንገድ መታወቂያ በገፍ መታደሉ ወዘተ መገለጫዎቹ ናቸው። ይህ ተግባር ዜጎች መብታቸውን ለማስከበር አቋራጭ እንዲፈልጉና መብታቸውን በጉቦ እንዲገዙ አድርጓል።
አራተኛው አስቻይ ሁኔታ :- የስልጣን ምንጭ ችሎታና ብቃት, ከመሆን ይልቅ ታማኝነት መሆኑ ነው። በታማኝነት የተገኘ ስልጣን አስተማማኝ አይደለም። የተሻለ ታማኝ እስኪመጣ ድረስ ካልሆነ  በስተቀረ የስራ ዋስትናና በስልጣን ላይ መቆየት አስተማማኝ አይደለም። ለዚህ ደግሞ በተገኘው አጋጣሚ ሁላ በሙስና ተዘፍቆ፣ ዘርፎና አተራምሶ ነገን አስተማማኝ ማድረግ የአሽከሮች ምንዳ መሆኑ ነው።
የሙስና ትግል የትልልቆቹ አሳዎች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሕዝብ የሚያስመርሩና ደም የሚያስለቅሱ የትንንሾቹም ሙሰኞች ጉዳይ መሆን አለበት። የግል ዘርፉ፣ የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት የተዘፈቁበት የሙስና ስፋትና ጥልቀት እንደ ሀገር የሰመጥንበትን የመበስበሰሰ ደረጃ የሚጠቁም ነው። የሙስና ትግሉ መጀመር ያለበት የትናንት ሙሰኞችን በማሳደድ ላይጨብቻ አተኩሮ ሳይሆን የነገ ሙሰኞችን ከወዲሁ ለመመከት በሚረዳ መልክ ለሙስናና ዘረፋ  መንስኤ የሆነ ስነ ልቦናዊ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ አስቻይ ሁኔታዎችን በመታገል ጭምር መሆን አለበት።


Read 1592 times