Tuesday, 29 November 2022 00:00

“ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ተምሮ ችግር የሚያወራና የሚያቃስት ሰው አይገኝም”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ህልምን እውን አድርጎ የማለፍን ያህል ስኬት የለም

      የዛሬው እንግዳችን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ አብራሪ ነበሩ-ፓይለት። በኬንያ፣ በታንዛንያና አውስትራልያ በዚሁ ሙያ  ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል። ባጠቃላይ በዚህ ሙያ ውስጥ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ አሳልፈዋል። ካፒቴን አበራ ለሚ ይባላሉ። ካፒቴኑ ከተቀጣሪነት ወጥተው የራሳቸውን ኩባንያ ከመሰረቱ ከአስር ዓመት በላይ ሆኗቸዋል።
“ናሽናል ኤርዌይስ” የተሰኘ የግል አየር መንገድ በመመስረት የጀመሩት ካፒቴን አበራ፤ በመቀጠልም “ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ”ን መክፈታቸውን ይናገራሉ። “ህልምን እውን አድርጎ የማለፍን ያል ስኬት የለም” የሚሉት እኚህ ባለ ብዙ ዘርፍ  ኢንቨስተር፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በፖሊሲ በተተበተበ አገር ውስጥ ህልምን መኖር ከባድ መሆኑን ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የፖሊሲ ችግሮች ናቸው ይላሉ። እንዲያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ከ10 የማያንሱ ኩባንያዎችን አቋቁመው በስኬት እየመሩ ይገኛሉ። ህልሜን እየኖርኩ ነው ብለው እንደሚያምኑ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። ለመሆኑ ካፒቴኑ የማይደፈረውን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ እንዴት ሊገቡበት ቻሉ? የፖሊሲ ተግዳሮቶችን በምን ሁኔታ አልፈው በኢንዱስትሪው ስኬት እየተቀዳጁ ዘለቁ? ሌሎች ኩባንያዎቻቸው በምን ዘርፍ ላይ ነው የተሰማሩት? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ ከካፒቴን አበራ ለሚ ጋር በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች። እንዲህ ቀርቧል፡ አንብቡት። ትነቃቁበታላችሁ።



         በግሉ ዘርፍ ብዙም ዘው ተብሎ የማይገባበትን የአቪዬሽን ሥራ እንዴት ደፍረው ገቡበት? ያውም ሥራዎን ለቀው… ነው? እንዴትስ “ሪስክ” ወሰዱ?
እውነት ነው፡፡ ሪስክ መውሰድ ከመንግስት ሥራ ወጥቶ የራስን ስራ መጀመር ብቻ አይደለም። ከህልም አለመገናኘትም ሪስክ ነው ለእኔ፡፡ ያለምሽውን በውስጥሽ ያለውን ዓላማ እውን አለማድረግ በራሱ ሪስክ ነው፡፡ “The Power Of Will” የሚባል ነገር አለ፤ የፈቃደኝነታችን ሀይል ምን ያህል እንደሆነ የምናውቅበት፡፡ የመረጥሽውን ትምህርት ስትማሪና በተማርሽው ሙያ ስትሰማሪ፤ ማንም አስገድዶሽ ሳይሆን ፍላጎትሽ ነው  በዚህ መሰመር የሚወስድሽ፡፡ ውስጣችን ያለው ፍላጎት ትልቅ ሀይል አለው፡፡
እኔ አንዳንዴ እንዲህ ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ህዝብ እንዳለ አሜሪካ ብንወስደውና አሜሪካ ያለውን ህዝብ በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ብናመጣው፤ ይህቺ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ አሁን ባላት ሀብትና ተፈጥሮ ሌላ አሜሪካ ልትሆን ትችላለች። በኢትዮጵያ የተሞላው አሜሪካ ደግሞ ወይ ሌላ ኢትዮጵያ ይሆናል ወይ በአሜሪካነቱ ይቀጥላል። የምናውቀው ነገር የለም። እና ሪስክ መውሰድ፤ ከመንግስት ሥራ ለቅቆ የራሱን ስራ መጀመር ብቻ ሳይሆን ድህነትን ተቀብሎ መኖር፣ የፍላጎትን ሀይል አለመረዳት፤ ሽንፈትን ተቀብሎ መኖር በራሱ ትልቅ ሪስክ ነው፡፡ ማንም ሰው ኑሮን ለማሸነፍ ብቻ መስራትና በዚያ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ መኖር የለበትም። እቅዳችንና ዋና ጉዳያችን በቃ ኑሮን አሸንፎ መሞት ነው? በጭራሽ መሆን የለበትም። ይሄ ከሚሆን አለመወለድ ይመረጣል።
በውስጥዎ ይህ ቁጭት ነበር ማለት ነው?
አዎ! በሚገባ ቁጭት ነበረኝ። ኑሮን አሸንፎ መኖር ብቻ የህይወት ግብ ሊሆን አይችልም። በእኔ እምነት፤ ሰው በውስጡ ያለውን ህልም ኖሮ ነው ማለፍ ያለበት። ባያሸንፍ እንኳን ለማሸነፍ እየታገለ መሞት አለበት። በዚህ አይነት እልህና አልሸነፍ ባይነት ከተሄደ ህልምን ማሳካት ይቻላል። እርግጥ በእንደኛ አይነት ሁሉም ነገር በፖሊሲ በተተበተበበት አገር እየኖሩ፤ በቀላሉ ህልምን ማሳካት ይከብዳል። ይህን መስራት አትችልም፤ ፖሊሲው አይፈቅድም፤ ይህን ማድረግ አይቻልም፤ በፖሊሲው አልታቀፈም በሚል በተተበተበ አገር፤ ሰው ፍላጎቱንና ህልሙን እውን ለማድረግ አይችልም። ሌላው ቀርቶ ተማሪዎች እንኳን የሚፈልጉትን ትምህርት መማር አይችሉም። አንቺም ጋዜጠኝነትን መርጠሸ ሳይሆን በወቅቱ የተገኘው ፊልድ ስለሆነ ይሆናል የገባሽው፤ አይታወቅም። ይህ በራሱ ሰው ህልሙን አሳክቶ እንዳያልፍ ትልቅ ማነቆ ነው። ደሀ አገር ነን፤ በደሀ አገር ብዙ መስራት አንችልም እንላለን። ኢትዮጵያ ደሀ አይደለችም፤ ድህነታችን ያለው አዕምሯችን ላይ ነው። በእርግጠኝነት የምነግርሽ ሰው አስተሳሰቡ ሲቀየር ከድህነት ይወጣል። ከድህነት መውጣት ማለት ገንዘብ ማካበት ማለት አይደለም!  በሙያሽ አንድ ነገር ላይ መድረስ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው። ለምሳሌ ዶክተር ሆነው ሰው የሚያክሙ ሰዎች በሀገሪቱ ትልቅ ባለሀብት ላይሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ሰው እያከሙ ነው፤ ህልማቸውን እየኖሩ ነው። ሱቅ በደረቴ የሚሰሩ ሰዎች ከአንድ ፕሮፌሰር የበለጠ ገንዘብ ሊያኙ ይችላሉ። ፕሮፌሰሩ ግን ሀብት ስላላከማቸ ህልሙን አልኖረም፤ ስኬታማ አልሆነም ልንል አንችልም። ሌላ ትውልድ እየቀረጸ ነዋ! ህልምን እውን አድርጎ የማለፍን ያህል ስኬት የለም። ስኬት ማለት በዋሉበት በተሰማሩበት ሁሉ ፍሬ ማፍራት ነው።
አሁን እርስዎ ህልሜን እየኖርኩ  ነው ብለው ያስባሉ?
በደንብ አስባለሁ፤ በዚህ ደግሞ ኩራት ይሰማኛል። ይሄ መታበይ አይደለም፤ የምሬን ነው የምነግርሽ።
አንደኛ አሁን እርስዎ የተሰማሩበት  ዘርፍ በግሉ ባለሀብት ብዙ ያልተደፈረ ዘርፍ ነው። ሁለተኛ ቅድም ነካክተውት ያለፉት የፖሊሲ፣ የደንብና የመመሪያ ተግዳሮት አለ? ይህን ሁሉ እንዴት ተቋቁመው አለፉት?
እውነት ነው፤ እኛ የተሰማራንበትን ዘርፍ ስንከፍት ብዙ ተግዳሮቶችን ነው ያለፍነው። በምሳሌ አስደግፌ ልንገርሽ። ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅን ስንከፍት የሲቪል አቪዬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆኖ የሚሰራ ሰው ነበር። አንድ ደብዳቤ ጻፈልን። ደብዳቤው ምን ይላል መሰለሽ? “በ24 ሰዓት ውስጥ ይህን ት/ቤት ዝጉ” ይላል። ለምን አልንና ጠየቅን፡፡ “አይ ይሄ ለመንግስት ብቻ የተፈቀደ እንጂ ለግል አልተሰጠም” አለን። ያንን ደብዳቤ ይዤ ወደ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሄድኩኝ። በወቅቱ አቶ ጌታቸው መንግስቴ የተባለ ሚኒስትር ዴኤታ ነበር- ያን ጊዜ። ደብዳቤውን አነበበና ስልክ ደውሎ፤ “ይህንን ደብዳቤ ለምን ጻፍክ”? ብሎ ጠየቀው። ያ የሲቪል አቪዬሽን ም/ዋና ዳይሬክተር፤ “አይ ጌታዬ፤ እኛ ይህንን የምንቆጣጠርበት ፖሊሲ የለንም” አለ። “እንግዲያውስ አንተ ፖሊሲ እስክታረቅቅ ድረስ ስራው ይሰራ” አለው።
እኛ ደግሞ መጀመሪያውንም ፖሊሲ የለንም ስላሉ ከካናዳ አገር ኢንተርናሽናል ኤርላየንስ አሶሴሽን (አያታ ከሚባለው) ማዕቀፍን አምጥተን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አስተካክለን ነበር ት/ቤቱን የመሰረትነው።
መቼ ነበር ይሄ የሆነው?
ከ10 ዓመት በፊት። ከዚያ ት/ቤቱ ሥራ ጀመረ፤ ሲቪል አቪዬሽኑም አረጋገጠልን። ባለፉት 10 ዓመታትም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሙያተኛ ልጆች ከእኛ ት/ቤት ወጥተዋል፡፡ እኛ ስፖንሰር አድርገን በነፃ ያስተማርናቸው በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ልጆች፤ አሁን ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ያንቀሳቅሳሉ፤ ብዙ ሰውም ቀጥረዋል፡፡ በውጭም ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ምን ለማለት ነው? ያን ጊዜ የሲቪል አቪዬሽኑን ሰው ሃሳብ አልቀበልም ፤ ይሄ የሰውየው ሀሳብ እንጂ የመንግስት አይደለም ብዬ  ወደ ላይ ሄጄ ዳንኩ እንጂ ሊያዘጋኝ ይችል ነበር፡፡ እንደዚህ አይነት ችግሮች ደግሞ በበርካታ ዘርፎች አሉ፡፡ ይህን አገር ወደ ኋላ ያስቀረው የፖሊሲ ችግር ነው፡፡ ፖሊሲያቸው ነው ድህነታችን፡፡ ስራው ራሱ ይገዳደረን እንጂ እንዴት ፖሊሲ ይገዳደረናል፡፡ ከችግር ለመውጣትና ለመለወጥ የሚፍጨረጨርን ሰው፤ “ይህን ማድረግ አትችልም፤ ይህን መስራት አትችልም” እያሉ በፖሊሲ ማነቅ ምን የሚሉት ፈሊጥ እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ለምሳሌ እኛን በፊት  ከ20 መቀመጫ በላይ ያለው አውሮፕላን ማብረር አትችሉም ይሉን ነበር። ለምን ስንል ”በቃ አትችሉም” ነው መልሳቸው። ሌላ አሳማኝ ምክንያት የላቸውም፤ ግን ኢትዮጵያ አየር መንገድን እንዳትቀናቀን ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይነት አምስትስ አስርስ ቢቋቋም ምንድን ነው ችግሩ?! ከዚያ ወደ 50 መቀመጫ ከፍ አደረጉና ከዚያ በላይ አትችሉም አሉ፡፡ የሆነ ጊዜ ደግሞ ከየመን ወደ አዲስ አበባ ኮንትራት ሥራ አገኘን፡፡ ይህ ሥራ በአንድ በረራ 60 ሺህ ዶላር የምናገኝበት ነው። ለዚህ ሥራ ተለቅ ያለ አውሮፕላን አምጥቼ ሳቆም አይቻልም አሉ፡፡ ለምን ስንል፤ ለግለሰቦች ከአገር ውስጥ መብረር አልተፈቀደላቸውም አሉ፡፡ በጣም ነው እኮ የሚገርምሽ፡፡ እኔማ ሳስበው፤ እኛን እያሰቡ ነው እንዴ ህግ የሚያወጡት እላለሁ፡፡ ይህን ሁሉ የምነግርሽ በእኛ የስራ ዘርፍ ነው፡፡ ነገር ግን በሁሉም ዘርፍ በርካታ አስቸጋሪ ነገሮች አሉ-ሰውን ከህልሙና ከአላማው የሚያጨናግፉ። ይሄ የሚያሳየው ፖሊሲዎቻችን ምን ያህል እያቆረቆዙን እንደሆነ ነው፡፡ ሰው የሰው መብትና መንግስት ያስቀመጠውን ህግ ተላልፎ ህገ ወጥ ሥራ እስካልሰራ ድረስ መስራት አለበት እኮ!
ያው በአንድ ሀገር ውስጥ ፖሊሲ ሲወጣ ለሀገር ልማት፤ ለለውጥ እንዲመች ተደርጎ መሆን አለበት። ሰዎችን የማያሰራ ከሆነ፤ ለስራ እንቅፋት ከሆነ የመፅሀፍ ቅዱስ ቃል አይደለም ፤ለምን አይቀየርም ወይም ለምን አይሻሻልም?
በትክክል! በጣም ነው የሚያበሳጨው። አንዱ ከጀርመን ኢንቨስት ለማድረግ አራት ጊዜ ተመላለስኩ አለ፡፡ ከዚያ ገፍቼ ለመሄድ አቅቶኝ ተመለስኩ ነው ያለኝ፡፡ ከዚያ ይህ ሰው ሌላ አገር ሄደና የሚመለከተውን ሰው አገኘ፡፡ ያ ጉዳዩ የሚመለከተው ሰው ለዚህ ወንድማችን ወረቀት ሰጠውና “የምትፈልገውን እዚህ ላይ ፃፍ፤ በአጭር ጊዜ አስፈፅምልሃለሁ” አለው፡፡ ይህ ሰው “የምሰራው ይህንን ነው፤ የምፈልገው መሬት ይህን ያህል ነው። ለስራው ይህን ያህል ዶላር ኢንቨስት አደርጋለሁ፤ ይህን አሟሉልኝ፤ ይሄ ያስፈልገኛል” ብሎ መፃፍ ብቻ ነው የሚጠበቅበት እንጂ ሌላ ውጣውረድ የለም- በሌላው አገር፡፡ ያውም ኢንቨስት ላድርግ ብለሽ ሄደሽ! ከዚያ ወዲያው የዛ አገር መንግስት “ያልከውን እናቀርባለን” ነው ያለው። በቀላሉ ነው የምልሽ፡፡ እዚህስ? ቀላሉን ነገር እያወሳሰቡ ሰውን ለህገ-ወጥ ድርጊት ያነሳሳሉ። በህጉና በመብትሽ መሰረት የምትፈልጊውን ለመስራት ሞክረሽ ሞክረሽ ሲያቅትሽ፤ ወደ ህገ-ወጥ መንገድ ልትገቢ ትችያለሽ። ለዚህ ተጠያቂው ማነው ታዲያ? አሁን አሁን ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል እየታየ ነው፡፡ ለእኛም አሁን ትልልቅ አውሮፕላኖችን መጠቀም ትችላላችሁ እና የመሳሰሉትን ነገሮች ተስፋ እየሰጡ ነው። ቢያንስ እየተከፋፈቱ ያሉ ተስፋ ሰጪ ነገሮች አሉ፡፡
በአሁኑ ሰዓት እናንተ ምን አይነት አውሮፕላኖችን ነው የምትጠቀሙት? ከሀገር ውጪስ እየበረራችሁ ነው?
ከአገር ውጪ መብረርን እስካሁን መንግስት በህግ አላፀደቀም፡፡ ቀደም ሲል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ውስጥ የነበሩ ሰው ናቸው፤ አሁን የሲቪል አቪዬሽን ዳይሬክተር የሆኑትና፤ እሳቸው እየፈቀዱልን ስራዎች ሲመጡ ከሀገር ውጪ እንበራለን እንጂ በህግ ተቀምጦ ከሀገር ውጪ ትበራላችሁ የሚል የለም፡፡ የሚገርምሽ አትችሉም የሚል ነገርም አልተቀመጠም። ዝም ብለው ነው ሲከለክሉን የነበረው፡፡ አሁን ግን እንሰራለን፡፡ በአሁኑ ወቅት የራሳችንን ቦይንግ 737 አውሮፕላን ኦፕሬት እያደረግን ነው፡፡ ትልልቅ አውሮፕላኖችን ማብረር እንችላለን። በአጠቃላይ በዚህ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ላይ የፖሊሲ ማነቆዎች ቢወገዱና ለስራ አመቺ ሆነው ቢቀረፁ፤ እንደ ሀገር እናድጋለን እንለወጣለን፤ ሰዎች ህልማቸውን አሳክተው ያልፋሉ፡፡ ሰው ከችግሩ ለመውጣት በሚያደርገው መፍጨርጨር ላይ የፖሊሲ ጫና በጭራሽ መኖር የለበትም ባይ ነኝ፡፡
ነፃ መሆን ማለት ህገ ወጥ መሆን ማለትኮ አይደለም፡፡ አሜሪካ ብትሄጂ ሰው ስራውን  በነፃነት ይሰራል፡፡ ግን በእጅጉ ህግ ያከብራል፡፡ ይሄ መለመድ አለበት፡፡
በውጭ ከሚገኙ የግል አቪዬሽኖች ጋር ትስስር አላችሁ? ለምሳሌ በልምድ ልውውጥና በስልጠና የመገናኘት ዕድል አላችሁ?
ምን መሰለሽ? የአቪዬሽን ኢንዱስትሪን ስትመለከቺ፤ አንድ አካል ነው የሚቆጣጠረው። ለምሳሌ አንድ የግል አቪዬሽን ኬኒያ ቢሆን ወይም ደቡብ አፍሪካ፤ ሬጉሌት የሚያደርገው ኢንተርናሽናል አቪዬሽን ባለስልጣን ስለሆነ ስታንደርድ አለ፡፡ በዚያ ስታንዳርድ መሰረት ነው ሁሉም የሚጓዘው። በአሰራር ጥራቱና በደረጃው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ትልቅ ቦታና ደረጃ ነው ያለው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ አየር መንገድ ነው፡፡ በመላው አለም ይሰራል፡፡ በመላው ዓለም እንዲሰራና ተቀባይነት እንዲኖረው በር የሚከፍትለት የሲቪል አቪዬሽኑ ጥንካሬ ነው። ጠንካራ ሲቪል አቪዬሽን ያላቸው አገሮች ላይ የእነሱ አየር መንገድ ቁጥጥር ደረጃቸው ከፍተኛ ደረጃ አለው ስለሚባል በእኛ ኤር ስፔስ ላይ መብረር ትችላላችሁ ብለው ይፈቅዱላቸዋል። እኛም ይህን ፕሪቪሌጅ እነጠቀምበታለን፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ጠንካራ ስለሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያንን ፕሪቪሌጅ ይጠቀማል፡፡ እኛም የግል ብንሆንም የኢትዮጵያ ስለሆንን አቪዬሽናችን የግል የመንግስት ሳይል ፕሪቪሌጁን እንድንጠቀም ይረዳናል፡፡ አቪዬሽን ሲነሳ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን አለ፡፡ እሱ ደግሞ ጠንካራ ነው፡፡
ናሽናል አቪዬሽን ምን ያህል አውሮፕላኖች አሉት?
ሰባት አውሮፕላኖች አሉን፡፡ በዚያ ላይ ትልልቅ አውሮፕላኖች ናቸው፡፡ 50 መቀመጫ ያላቸው ሪጅናል ጀቶች አሉን፤ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሀገር ውስጥ የሚጠቀምበት “k400” አለን፤ ቦይንግ 737 አለን፤ በቅርቡ ደግሞ ሌሎች ኤር ክራፍቶችን እንጨምራለን፡፡
በግል ኩባንያ ደረጃ ብዙ አውሮፕላኖች ነው ያላችሁ …
በሌላው ዓለምኮ ኢትዮጵያ አየር መንገድን የሚያክል በግል ኩባንያ ነው የሚመራው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ 150 አካባቢ አውሮፕላን ያላቸው ይመስለኛል፡፡ እንግሊዝ ያለው ራያን ኤይር ከ480 በላይ አውሮፕላኖች አሉት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ህዝብ ነን፡፡ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ነን፡፡ እኔ ሁሌም ለሰዎች የምለው ዱባይን አታዩም ወይ ዩናይትድ አረብ ኤምሬት ትንሽ አገር ናት፤ አንድ ክፍለ ሀገር ነው የምታክለው ጃይንት አየር መንገድ አላቸው፡፡ በምሳሌነት ፍላይ ዱባይን መጥቀስ እንችላለን። እነ ኤይር አረቢያ፤ኢታድ ኤርዌይስ የሚባል አለ፤ ትልቅ አየር መንገድ ነው። ፍላይ ዱባይ ከመቶ በላይ አውሮፕላኖች አሉት። ጄትዌይስ የሚባልም አለ፡፡ ይሄ ሁሉ እንግዲህ በትንሿ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ብቻ ነው የሚገኘው። እነሱ የሚያደርጉት ዓለምን ወደነሱ ነው የሚሰበስቡት፡፡ ዱባይ የአገር ውስጥ በረራ እንኳን አይሰሩምኮ፡፡ ከዱባይ ተነስተው የት ነው የሚያርፉት? ትንሽ አገር ናትኮ፡፡ እኛ ግን ሰፊ አገር አለን፡፡ የአገር ውስጥ በረራ በብዛት እንሰራለን፡፡ እነ ኤምሬትስ ራሳቸውን አሳድገው የአለምን ገበያ ሰብስበው ነው የሚሰሩት፡፡
እውነት ነው፡፡ ዱባይም ከኒውዮርክ ቀጥሎ ትልቅ የዓለም ቱሪስቶች መዳረሻ ናት። የተፈጥሮ የቱሪዝም መዳረሻ የሌላት በረሃማ አገር ብትሆንም በአርቴፊሻል ቱሪዝም አለምን መሳብ ችላለች፡፡ እኛ ግን ተፈጥሮ ያደለንን መስህብ በአግባቡ መሸጥ አልቻልንም… ምን ይሻላል ይላሉ?
እሱን ነው የምልሽ፡፡ በጣም መስራት አለብን። ለአሰራር ምቹ ሁኔታዎችን መቀየስ አለብን፣ የስራ ባህል መዳበር አለበት። የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልገናል ነው የምለው።
እናንተ ከናሽናል ኤርዌይስ ተነስታችሁ ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅን ከፈታችሁ፡፡ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥም ድርጅቶቻችሁን ወደ ዘጠኝ አሳድጋችሁ “ናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕን”አቋቁማችኋል፡፡ እስኪ በዚህ ላይ ቆይታ እናድርግ?
እሺ! እኛ የተለያዩ ኩባንያዎችን ስንከፍት እዚያም፣ እዚህም የመርገጥ አባዜ ወይም ስስታምነት ተጠናውቶን አይደለም። ስንመለከተው ስራው አለ። ከፍተኛ ክፍተት ያላቸው ዘርፎች አሉ። ለምሳሌ “ናሽናል ሪሰርች ኤንድ ኮንሰልትስ” የሚል ድርጅት ከፍተን በአገር አቀፍ ደረጃ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሆቴል ባለሙያዎችን እያሰለጠንን እንገኛለን። በጣም ብዙ ሺህ ነው የምልሽ። በዚህ ዘርፍ ፍላጎት አለ፤ እያሰለጠንን ነው። በዚህ ሪሰርች ግሩፕ ውስጥ ከኬንያም ከሌሎች ሀገራትም ከዚሁ ከሀገራችንም ብዙ ፕሮፌሰሮች አሉ። እንደዚህ አይነት መንግስት ሊያያቸው ያልቻሉ ነገር ግን ሀገር የሚለውጡ ሥራዎች አሉ። እነዚህ ጥናቶችንና ምርምሮችን እየሰራን ለፖሊሲ አውጪዎች የማቅረብና ትኩረት እንዲያኙ የማድረግ ሥራም እየሰራን ነው።
ሌላው “ዋሊያ ቱር ኤንድ ትራቭል” የሚባለው ድርጅታችን ነው። ይህ የመጀመሪያና ከናሽናል ኤርዌይስም በፊት የነበረ ነው። ሌላው “ናሽናል ቴሌኮም” ይባላል። ከሳፋሪኮም ጋር ተፈራርመን የታወርና ሌሎች የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን እየሰራን ነው። ሳፋሪኮም እንግዲህ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት 28 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት አደርጋለሁ ብሏል። በነገራችን ላይ ሳፋሪኮም ወደዚህ አገር መግባቱ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል። እኛ እንኳን ከእነሱ ጋር ለምንሰራው ስራ በመቶ የሚቆጠሩ ኢንጂነሮችን እየቀጠርን ነው። ሌላው “ቶሎ ካሽ” የተሰኘው ድርጅታችን ነው። ይህም ከሳፋሪኮም ጋር የምንሰራው ነው። ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርሽፕ  የሚባል አለ ፤ሳፋሪኮም የሚሰራውን ስራ ሁሉ ይሰራል።
የክፍያ ስርዓት ነው?
አዎ፤ ከክፍያና መሰል ስራዎች ጋር የተያያዙ ስራዎችን ይሰራል። “ናሽናል አግሮ ሶሉሽን” የሚባልም ሌላ ኩባንያ አቋቁመናል። በግብርና ላይ አተኩሮ የሚሰራ ነው። ለምሳሌ ባለፈው በሀገራችን የበረሃ አንበጣ በተከሰተ ጊዜ ትልቅ ጉዳት ደርሶ ነበር፡፡ የመድሃኒት ርጭት ስራ ለመስራት እንኳን አውሮፕላኖችን ከውጭ በኪራይ እናመጣ ነበር። አሁን ግብርና ሚኒስቴር ለዚሁ ስራ አምስት አውሮፕላኖችን ገዝቷል፡፡ ያን ጊዜ አንበጣውን ለመዋጋት በአጭር ጊዜ ወደ 250 ሚሊዮን ብር እንዳወጣ አንብበናል፡፡ ከኬንያ ከደቡብ አፍሪካና ከሌሎችም አገራት አውሮፕላን ተከራይተናል፡፡ ያንን ችግር ካየ በኋላ ሚኒስቴሩ በሀገራችን ይህ አቅም መጠናከር አለበት በሚል አውሮፕላን ገዝቷል፡፡ እኛ ነን እሱን ማኔጅ የምናደርገው። ግብርናን የሚጠቅሙ ሌሎች ነገሮችንም ወደፊት እንሰራለን፡፡ ይህንን ሁሉ ስታይው በሀገራችን ሊሰሩ የሚችሉ፤ ለሀገርና ለህዝብ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጡ ስራዎች አሉ፡፡
በነዚህ በጠቀሱልኝ ኩባንያዎች ምን ያህል ሰራተኛ ተቀጥሯል?
ብዙ ናቸው፡፡ በድምሩ ከ500 ሰው በላይ በነዚህ ኩባንያዎች ሥር ተቀጥሮ እየሰራ ነው። እኔ ሰራተኞቼን እንደ ልጆቼ ነው የማያቸው። ወላጆች ለልጆቻቸው እንደሚጠነቀቁትና እንደሚንከባከቡት ሁሉ እኔም በዚህ መልኩ ነው የማያቸው፡፡ ሰዎች ክብራቸው ተጠብቆ በአግባቡ ሰርተው ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት የስራ ከባቢ በመፍጠር በኩል ጥሩ ነን ብዬ አስባለሁ፡፡ የሚገርምሽ እኛ ጋር ያሉት አብዛኛዎቹ ሰራተኞች ወጣቶች ናቸው። እዚሁ የትምህርት ዕድል ተመቻችቶላቸው ይማራሉ፡፡ በናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡
ኮሌጁ ምን ምን የትምህርት አይነቶችን ይሰጣል?
በአቪዬሽን ማኔጅመንት፤ በማርኬቲንግ፤ ባንክ ኤንድ ፋይናንስ፤ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ኤንድ ኢኮኖሚክስ፤ ቱሪዝም፤እና ሆቴል ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ ያሰለጥናል። አሁን ደግሞ በዚህ ዓመት የቴሌኮም ኢንጅነሪንግ፤ ኤሮስፔስ ኢንጅነሪንግ፤ ኤርክራፍት ቴክኒሺያን ስልጠናዎች መስጠት ይጀምራል፡፡ የሆስተስ ሙያ፤ ትኬት ላይ ኤርላይን ከስተመር ሰርቪስ አሁንም በኮሌጁ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሌሎች አጫጭር ኮርሶችም አሉ፡፡ እኛ ከሁሉም በላይ የምንኮራበትና ልጆች እየተለወጡበት ያየነው ነገር፤ ሳይኮሎጂና ኮሙኒኬሽን ለየብቻ ነው የምናሰተምረው፡፡ እኛ አገር “ጨዋ ልጅ ማሳደግ” በሚል ልጆችን እየቀጠቀጡ እያሸማቀቁ ስለሚያሳድጓቸው፤ ልጆቹ ራሳቸውን መግለፅና መናገር ይፈራሉ፡፡ በራስ መተማመናቸውን ያጣሉ፡፡ እንግሊዝኛ በአግባቡ መናገር አለመቻላቸው ጥሩ ስሜት አይፈጥርባቸውም፡፡ እኛ ግን “ግዴለም የራሳችን ሌላ ቋንቋ ስላለን ነው፤ እንግሊዝኛ አለመቻል የብቃት ማነስ አይደለም፤ የእውቀት አልባነት መገለጫ አይደለም፤ ልምምድ ነው የሚያስፈልጋችሁ፤ ለብቻ ትማራላችሁ፤ ብለን በደንብ እናስተምራቸዋለን፡፡ ሳይኮሎጂም በደንብ ይማራሉ። እነዚህ ሁለቱን ነገሮች ሲያሟሉ ልጆቹ ቦምብ ነው የሚሆኑት፡፡ እነዚህ ልጆች የማይፈሩ ፤የማያፍሩ፤ ራሳቸውን የሚረዱ፤ ሰውን የሚያከብሩና ችግር ፈቺ የሆኑ ዜጎች ሆነው ይወጣሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ሰርተው ደመወዝ ከመቀበል ያለፉና ህልማቸውን የሚኖሩ ዜጎች ነው እየሆኑ ያሉት፡፡ በዚህ በእጅጉ ኩራት ይሰማናል፡፡ ማሰብ የሚችል ዜጋ መፍጠር ቀላል እንዳይመስልሽ፡፡ ሰው ማሰብ ከቻለ አገሩን ይወዳል፤ ችግር ፈቺ ይሆናል እንጂ እንደ ሮቦት በፎርሙላ የተሞላና ፕሮግራም የተደረገውን ብቻ የሚከውን አይሆንም፡፡ በዚህ አሁንም በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ናሽናል አቪዬሽን ተምሮ ችግር የሚያወራና የሚያቃስት ሰው አታገኚም፡፡
ኮሌጁ የኤርክራፍት ቴክኒሽያን ትምህርት ሊሰጥ እየተዘጋጀ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ የራሳችሁ የጥገና ማዕከል አላችሁ እንዴ? ናሽናል ኤርዌስ ስንት አብራሪዎችስ አሉት?
ወደ 20 የሚጠጉ አብራሪዎችና ረዳት አብራሪዎች አሉት፡፡ በቀጣይ እንደ ቦይንግ 737 ያሉ አውሮፕላኖችን ስንጨምር የአብራሪዎቹ ቁጥር ይጨምራል፡፡ ምክንያቱም አንዱ አውሮፕላን ብቻ አምስትና ስድስት አብራሪዎች ሊያስፈልጉት ይችላል። የጥገና ማዕከልን በተመለከተ ላነሳሽው በአሁኑ ወቅት የለንም፡፡ ከዚህ ደቡብ አፍሪካ እየሄድን ነበር የምናሰጠግነው ለወደፊት እዚህ የምናስጠግንበትን መንገድ እንፈጥራለን፡፡ በነገራችን ላይ ይሄም የፖሊሲ ጉዳይ ነው፡፡
የአውሮፕላን ጥገና ለመማር ከሌሎች ሀገራት በተለይ ከአፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ተማሪዎች አሉ፡፡ ይሄ ማለት የተደራጀ የጥገና ማዕከል ኢትዮጵያ አላት ማለት ነው። ደቡብ አፍሪካ ለጥገና ስትሄዱ የውጭ ምንዛሬ ታወጣላችሁ፡፡ ይህንን ለማስቀረት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እየከፈላችሁ እዚሁ ለማስጠገን አልቻላችሁም? መቼም አውሮፕላን ለማስነሳትና ለማሳረፍ የአየር መንገዱን ቦታ ነው የምትጠቀሙት ብዬ ነው…
በቅርቡ ምናልባትም ገና አንድ ወር ቢሆን ነው “እኛ ልንጠግን የምንችለውን አውሮፕላን እንጠግንላችኋለን” የሚል በጎ ነገር መጥቷል፡፡ ገና በቅርቡ ማለቴ ነው፡፡ ይሄ ጥሩ ነገር ነው፡፡ በፊት የነበረው የተሳሳተ አስተሳሰብ ለብዙዎች የሀገር ሀብት አንመስላቸውም፤ ዝም ብለን ውርውር የምንል ጥቃቅንና አነስተኛ አድርገው ነው የሚያስቡን፡፡ በአየር መንገዱ አይን እያዩን። ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረት እያገኘን ነው። ከትላልቅ ባለስልጣኖች ጭምር ለወደፊቱ የተሻለ ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ አለኝ፡፡ ተስፋ ብቻ ሳይሆን በተግባርም እናያለን፡፡ እንዳልኩሽ የአስተሳሰብ ብልሹነት ስላለ፤ “እነዚህ ኖሩ አልኖሩ ለውጥ የለውም” የሚል ነገር ነበር። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባለ ወደብ አልባ አገር ትላልቅ አየር መንገዶች ብንፈጥር ለሀገር ጥቅም ነው የሚሆነው። ኢትዮጵያን የሚያህል ትልቅ አየር መንገድ እያለ ሌላ ምን ያስፈልጋል የሚል አስተሳሰብ ፍፁም የተሳሳተ ነው፡፡ እኛ ከብዙ ዓለማት ጋር በብዛት የምንገናኘው በአየር ትራንስፖርት ነው ስለዚህ ብዙ አየር መንገድ ያስፈልገናል፡፡ ፖሊሲ አውጭዎችም እይታቸውን ማስፋት አለባቸው፡፡ እንዳልሽው እኛ ለማኮብኮቢያ ለማሳረፊያ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ሜዳ እንጠቀማለን፡፡ ለአገልግሎቱ ክፍያ እንፈፅማለን፡፡ እንደምታውቂው ሶስት ነው፡- ሲቪል አቪዬሽን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኤርፖርቶች ድርጅት፡፡ አቪዬሽኑ ሁሉን የሚቆጣጠር ባለስልጣን ነው፡፡ አየር መንገድ ኦፕሬተር ነው፤ ነጋዴ ነው፡፡ ኤርፖርቶች ድርጅት ደግሞ ኤርፖርቱን አዘጋጅቶ ያከራያል። እሱም የንግድ ድርጅት ነው። ኤርፖርቱን በሙሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለወሰደው እኛ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ክፍያ እንፈፅማለን ማለት ነው፡፡ አቪዬሽኑ አየር መንገዱ በትክክል እየሰራ ነው ወይ? የግልም የመንግስት አየር መንገድ ያሏቸው አብራሪዎች ብቁ ናቸው ወይ የሚሉትንና መሰል ነገሮችን ያለ አድልኦ መቆጣጠር ነው ስራው። ያለድልኦ ይቆጣጠራል ወይ? ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ለምሳሌ ጠዋት ጠዋት እኛ መብረርም ሆነ ማረፍ አይፈቀድልንም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጡት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው ግን ለምንነሳበትም ለምናሳርፍበትም እንከፍላለንኮ፡፡ ኤርፖርቱ ቢዚ ስለሆነ ለእኛ ትኩረት አይሰጠንም፤ አሁንም ያሉት የተስፋ ጭላንጭሎች ወደፊት ሁሉንም እኩል ወደ ማገልገል ያመጡታል ብለን ነው ተስፋችን፡፡
ምን የህል የግል አየር መንገዶች አሉ በአሁኑ ወቅት?
ባለፈው ሲቪል አቪዬሽን እንዳስታወቀው 13 ደርሳችኋል ብሏል፡፡
ማህበር አላችሁ?   
አዎ ማህበርም አለን፡፡
በጋራ ሆናችሁ ድምፃችሁን ለማሰማት አትችሉም?
ምን መሰለሽ? ጉዳዩ አሁንም የአስተሳሰብ ችግር ነው እኛ የግል አየር መንገዶች እንዲህ አድርጉልን ስንል፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዱልን የምንል ነው የሚመስላቸው እንጂ ችግሮቻችን በቀላሉ የሚፈቱ ነበሩ፡፡ ለእኔ አገር ለመለወጥ ቅንነት፤ ቀና አስተሳሰብ፤ ፖሊሲን ለአገር ልማት እንዲውል አድርጎ መቅረፅና የተበላሸ አስተሳሰብን መቀየር ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ይህ ካልሆነ በማህበር መደራጀቱም ምኑም ለውጥ አያመጣም ነው የምለው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

Read 8315 times