Print this page
Monday, 28 November 2022 16:51

ታማሚዎቿን በዳንስ የምታነቃቃዋ ነርስ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በኬንያ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የተኛ ህፃን እየደነሰች ስታነቃቃ የሚያሳይ አጭር ቪዲዮ በቲክቶክ መልቀቋን ተከትሎ፣ በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆናለች፤ የ22 ዓመቷ የነርሲንግ ተማሪ ሉክሬስያ ሮባይ፡፡
ቪዲዮው በኪታሌ ካንቲ ሪፈራል ሆስፒታል በሥራ ላይ ሳለች የተቀረፀ መሆኑን ተናግራለች- ሮባይ። በሆስፒታሉ ውስጥ ህመምተኞችን እየዞረች ስትጎበኝ አንድ የተከፋና የተደበተ ህፃን ማግኘቷን የምታስረዳው ወጣቷ ነርስ፤ በተወዳጅ የህጻናት ዘፈን እየደነሰች  ልታነቃቃውና ልታስደስተው መወሰኗን ትገልጻለች።
“ታማሚው  እግሩ ላይ ስብራት ደርሶበት ወደ ሆስፒታሉ የገባ ሲሆን የፈራ ይመስል ነበር። ወዲያው ሙዚቃውን ከሞባይል ስልኬ ላይ በማጫወት መደነስ ጀመርኩኝ፤በዚህም ህጻኑ ተነቃቃ። እንደ ነርስ ህመምተኞቼ ደህና መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለብኝ ይሰማኛል” ብላለች፤ ሮባይ፡፡
ወጣቷ የጤና ባለሙያ  የዘየደችው መላ ሰርቶላታል። ግትር ብሎ ተቀምጦ የነበረው በሽተኛ ህፃን፤ እጆቹንና እግሮቹን ባለበት ሆኖ ማንቀሳቀስ ችሏል፡፡ ፊቱም በፈገግታ ፈክቷል፤ ዕድሜ ለዳንሰኛዋ ነርስ፡፡  
በዚህም አስደማሚ ተግባሯ የአያሌ ኬንያውያንን ልብ አሙቃለች፡፡ ከሁለት ሳምንታት በፊት በቲክቶክ የለቀቀችው ይኼ አጭር ቪዲዮ፤ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ አንድ ሚሊዮን ገደማ ዕይታዎችንና  በመቶዎች የሚቆጠሩ አስተያየቶችን አግኝቶላታል፡፡
ፎለፎሏ ነርስ፤ ዳንስ በጥልቅ ስሜት የምትወደውና በዙሪያዋ ለሚገኙ ሁሉ የተስፋ መልዕክት ለማስተላለፍ የምትጠቀምበት ጥበብ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡
“ለዳንስ ጥልቅ ፍቅር አለኝ። አብሮኝ የተፈጠረ ነው። በዚህ ህይወታችን  ድንቅ ነገሮችን የሚያበረታታ ህብረተሰብ ወይም ባህል አካል መሆን ጥሩ ስሜት ይፈጥራል።” ብላለች ሉክሬስያ።
የሉክሬስያ አለቃ የሆነችው ቤቲ ናልያካ፣ እቺ ተማሪ ነርስ በልምምድ ጊዜያቶቿ  ላሳየችው ብቃትና ሰብአዊ  ተግባር አወድሳታለች፡፡
“ሮባይ ጎበዝ ተማሪ ናት። አንድ ስራ ስንሰጣት በቅጡ እንደምታጠናቅቀው እርግጠኞች ነን። ምንጊዜም ፈታኝ ጉዳይ ሲገጥማት ጥያቄ የምትጠይቀውና ከሠራተኞቹ ጋር የምትተባበረው እሷ ናት። ለእርሷ የወደፊቱ የነርሲንግ ሙያ ብሩህ ነው።” ስትል ናልያካ መስክራለች፡፡
ነርስነት የዕድሜ ዘመኗ ጥልቅ ፍላጎት እንደነበር የምትገልጸው ሉክሬስያ፤ ሁልጊዜም ሰዎችን መርዳትና ከስቃያቸው መገላገል ትሻ  እንደነበር ጠቁማለች፡፡
“ሁልጊዜም መስራት የምፈልገው ነገር ነው። ከውስጤ ነው ፈንቅሎ የወጣው፡፡  ከልጅነቴ ጀምሮ የህክምና ባለሙያ ለመሆን እፈልግ ነበር። የታመሙትን መንከባከብ እሻ ነበር። ሌላ ሙያ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም…አብሮኝ የተፈጠረ ነው የሚመስለኝ” ብላለች።
ያለ ወላጅ ያደገችው ሉክሬስያ፤የትምህርት ጉዞዋ በብዙ ውጣውረዶች የተሞላ እንደነበር ትገልጻለች፡፡ እዚህ ደረጃም የደረሰችው በነፃ የትምህርት ዕድልና በስፖንሰርሺፕ ነው፡፡
የትራንስ ንዞያ ካንቲ አስተዳደር የቀራትን የአምስት ወር የነርሲንግ ኮርስ ክፍያ ለመሸፈን ቃል የገባላት ሲሆን፤ ትምህርቷን ስታጠናቅቅም ለህመምተኞቿ በፍቅር በደነሰችበት ሆስፒታል ውስጥ እንደሚመድባትም አረጋግጦላታል። በዚህም የ22 ዓመቷ ወጣት ህልም እውን ይሆናል ብሏል፤የኬንያው ሲቲዝን ቴሌቪዥን።

Read 1495 times
Administrator

Latest from Administrator