Print this page
Saturday, 26 November 2022 00:00

ስለ ቃለ መጠይቅ አዘገጃጀትና አቀራረብ የሚያስገነዝብ መፅሀፍ ገበያ ላይ ዋለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ስለ ቃለ መጠይቅ አዘገጃጀትና አቀራረብ ግንዛቤን የሚፈጥር “ቃለ መጠይቅ ለጥናትና ምርምር፤ ለስራ ቅጥር ምልመላ፤ ለጋዜጠኝነት” የተሰኘ አዲስ መፅሀፍ ገበያ ላይ ዋለ፡፡ በደራሲ ሲሳይ አሰፌ የተሰናዳው ይሄ ፋይዳ ያለው መፅሀፍ በውስጡ ሰፋ ያሉ ቁምነገሮችን ይዟል ተብሏል፡፡ ከነዚህም ቁምነገሮች መካከል፤ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ግለሰቦች ቃለ መጠይቅ ሲያዘጋጁና ሲያቀርቡ ዕውቀትንና ክህሎትን ባገናዘበ መልኩ እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ያሳያል ተብሏል፡፡ እንደ ደራሲው ሀሳብ ዕውቀትንና ክህሎትን ባላገናዘበ ሁኔታ የሚካሄዱ ቃለ መጠይቆች ምክንያት እስከዛሬ በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎች ተድበሰብሰው መቅረታቸውንና በርካታ ተቋማትም ብቃት ያለው የሰው ሀይል ማጣታቸውን አስታውሰው በርካታ ጋዜጠኞችም ባሰቡት መልክ መረጃ ሳያገኙ ባክነው መቅረታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከላይ ለተዘረዘሩት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሄ ይሆን ዘንደ ይህን መፅሀፍ ማሰናዳታቸውንም ደራሲው ሲሳይ አሰፌ ተናግረዋል፡፡ በ18 ዋና ዋና ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ419 ገፅ የተቀነበበው መፅሀፉ በ400 ብርና በ12 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “ውጤታማ የንግግር ዝግጅትና አቀራረብ” ፤ “ህይወትን በጥራት”፤ “ኮሙኒኬሽን ለቢዝነስና ለአጠቃላይ ህይወት” እና “በክርክርና በውይይት የማሸነፊያ ስልቶች” የተሰኙ መፅሀፍትን ለንባብ ማብቃታቸው አይዘነጋም፡፡

Read 17841 times