Saturday, 26 November 2022 00:00

“በጋራ ቆስለናልና በጋራ እንታከም!”

Written by  ዘቢብ ሪ.
Rate this item
(0 votes)

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትምህርትና ሥነ-ባህርይ ጥናት ኮሌጅ የሚዘጋጀው ወርሀዊ  ሴሚናር ህዳር 1 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ ገልፆ፤ የሚቀርቡትን ሥራዎችና  አቅራቢዎቹን የሚያስተዋውቅ  መልዕክት ደረሰኝ፡፡ በዕለቱም በሥፍራው ተገኘሁ፡፡ ሁለት ርዕሰ ነገር  ለዕለቱ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
አንደኛው ርዕሰ ነገር  በተባባሪ ፕሮፌሰር አበባየሁ ምናዬ የቀረበ ሲሆን ስለ ፍልሰትና  መፈናቀል ከጽንሰ-ሃሳባዊ ዳራ በመነሳት የፖሊሲ ክፍተትን አሳይቶ የአተገባበር አለመቀናጀት  ተተንትኖ ቀረበ፡፡
ሁለተኛዋ  አቅራቢ ቀልቤን የሚስብ አዲስ ዕይታን አንቆረቆረች፡፡ ዶ/ር ዋጋነሽ ዘለቀ፤ በቨርጂኒያ ኮመንዌልዝ ዩኒቨርሲቲ በአዕምሮ ጤና ማማከር ተባባሪ ፕሮፌሰር ናት፡፡ በዕለቱም፤  “Intergenerational Trauma and Collective Healing in Toxic Culture” በሚል ርዕስ ተተንትነው በቀረቡት ሀሳቦች ታዳሚውን ያነቃቃ ጽሑፍ ለመወያያነት አቀረበች፡፡
“Trauma ይወረሳል”
Intergenerational Trauma ተብራራ:: Trauma -  በአንድ አጋጣሚ የሚፈጠር አደጋ ወይም አንዳች አስደንጋጭ፤ አሳማሚ፤ ለመቀበል የሚያዳግት የህይወት ክስተትና ጥሎት የሚያልፈው ሥነልቡናዊ ጠባሳ ተደርጎ፣ በብዙዎቻችን የሚታሰበውን ዕይታ ያስቀየረ ሃሳብ  በአስረጅ አስውባ  አሳየችን፡፡  
Trauma ይወረሳል አለችን፡፡ እንዴት? አልን:: ክስተቱ በተፈጸመበት ቦታና ጊዜ ያልነበረ የሰው ልጅ እንዴት Traumaን ይወርሳል አልን። በምሳሌ አጀበች፡፡ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጥንስሱ ከ50 ዓመት በላይ  የቆየ እንደሆነና የቅኝ ገዢ ሀገራት አንዱን ብሔር ባንዱ ላይ ለማነሳሳትና የገዢነት ዘመናቸውን ለማርዘም የተጠቀሟቸው የሥነልቡና ጨዋታዎች ትልቅ ሚና እንደነበራቸው  ተብራርቷል። ጥርስ ሲነክሱ የቆዩት የሁቱ ብሔር አባላት ምቹ  ሁኔታና ጊዜ ሲያገኙ በቱትሲ ብሔር አባላት ላይ የማይታመኑና በሰው ልጅ ታሪክ ዘግናኝ ከሚባሉት ጭፍጨፋዎች አንዱን ፈጽመዋል፡፡  ይህንን የፈጸሙት በአብዛኛው ወጣቶች ሲሆኑ ያለፈውን የሩዋንዳን የታሪክ ሁነት ያዩም የተሳተፉም አልነበሩም፡፡ ነገር ግን እየተዋረሰ በመጣ Intergenerational Trauma  ስነልቡናዊ ተጽዕኖ አድሮባቸዋል፡፡ ለዚህም ጊዜያዊ አባባሽ ምክንያት የፕሬዝዳንቱ የሀብያሪማና መገደል ቢመስልም ስር በሰደደ  ስነልቡናዊ ችግር ውስጥ መቆየታቸውን የሚያመላክቱ ብዙ የታሪክ ሁነቶች በ100 ቀናት ውስጥ ተፈጽመዋል፡፡ Trauma ን እንደ አንድ ጊዜ ኹነትና  በአንድ ቁንጽል ዕለታዊ ክስተት ብቻ የሚፈጠር አድርጎ መውሰዱ መፍትሄውንም ያርቀዋል፡፡ Left to Tell በሚለው መጽሐፍ ውስጥ የተተረኩት በሩዋንዳ የነበረውን ሁኔታ እንደ ስዕል የሚያሳዩ ትረካዎች በምሳሌነት ተወስደዋል፡፡ ገዳዮቹ ለምን ግድያውን እንደፈሚጽሙ ሲጠየቁ፣ የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን ስቃይና ኑሮ ይገልጻሉ፡፡ እኛን የበደለንን እናጠፋለን ይላሉ፡፡ ባዮቹ ግን የታሪኩ ተሳታፊም፤ተመልካችም አልነበሩም፡፡                         
Trauma ይዋረሳል፡፡ የባህል Trauma አለ። የታሪክ Trauma አለ፡፡ ግለሰብ ብቻውን የማያዳብራቸው በማህበራዊ መስተጋብርና አካባቢያዊ ሁኔታ እየሰረጹ ሄደው ስነልቡናዊ ምላሽን ያበጃጃሉ፡፡
 በነዚህና መሰል ሁኔታዎች ውስጥ Individual healing ብቻውን  መፍትሔ ላይሆን ይችላል፡፡
 እነሆ መፍትሔ አለች - Collective healing
“Since we are wounded collectively, I invite collective healing…”
በአዕምሮ ጤናና  ማማከር  ላይ ለህትመት  የበቁ ከ30 በላይ የምርምር ጽሁፎች ባለቤት የሆነችው ዶ/ር ዋጋነሽ፤  ከዳበረ ልምዷ  የመፍትሔ ሀሳቦችንም ጀባ ስትል  ቆየች፡፡
በመፍትሔ ሃሳብነት የቀረበው Collective healing ሂደቶቹ ከአፍሪካ ፍልስፍና ኡቡንቱ የሰላም  መሥሪያ ሂደቶች ጋር ተቀራራቢነት አለው፡፡
ሀ. ተነጋገሩ ማለትም የእውነት መነጋገርና ያለፈ የታሪክ ስህተትን ማመን ያስፈልጋል አለች። ይህ ሲሆን ግን ህብረተሰቡ በሂደቱ ዉስጥ ተሳታፊ መሆን አለበት፡፡ ያለፈ ህጸጽን ስናምን  ስንጠቀማቸው የነበሩ ቃላት እንኳ አዎንታዊ በሆኑ ቃላት መተካት አለባቸው አለች፡፡
ለ. ይቅር ተባባሉ፡፡ ያደሩና የተረሱ የሚመስሉ ቂምና ቁርሾዎችን፣ እዚህም እዚያም እያየን ነው፡፡ ታዲያ ለምን ማለባበስ? አድሮ የሚፈነዳ የሚዋረስ Trauma ምንጭ እንዳይሆን ይቅር መባባል የግድ ነዉ፡፡
እንዴት?
ሙዚቃው ፍቅር ይስበክ፡፡ ስዕሉም፣ ስፖርቱም፣ ትያትሩም የሚያመረቅዝ ቁስል ከሚነካካ፤ ፍቅርን የህይወትና የመኖር ትርጉምን ይጥራ - ይህ በርግጥ ብዙ ትግል ይፈልጋል። አንዱን አኮስሶ ሌላውን  ወርቅ ካልቀቡ አይሸጥማ…
ሐ. ማህበራዊ መስተጋብርን  የሚያነቃ Intergenerational Traumaን ለመቀነስ በሚያስችሉ ያልተቋረጡ ጥረቶች  የcollective healingን  መንገድ እንጀምራ …የሷ ጥልቅ እና ብዙ ነው፡፡ እንዲህ አሳጠርኩት፡-
እዚህም እዚያም የምናይ የምንሰማቸው መዘያየሮችና መሰዳደቦች የIntergenerational Trauma ውጤቶች ናቸው ተብለናል፡፡
ስለዚህ  በጋራ ቆስለናልና በጋራ እንታከም!
እርስ በርስ እንተካከም!


Read 1012 times