Saturday, 26 November 2022 00:00

“ኧረ ተመስገን ነው!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)


        “--የእውነት ግርም የሚል ነው... እነሱ ሀገር የሄደ የሌላ ሀገር ሰው አይደለም ህጋቸውን ጥሶ በሆነ ባልሆነው በተለይ ጥቁሮችንና “እኛን አይመስልም፣” የሚሏቸውን እያነቁ እስር ቤት የሚከቱና ከሀገር የሚያባርሩ ‘ፈረንጆች’፤ የኳታርን ህግ የማያከብሩት እብሪት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል፡፡--”
    
       እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ውሀው በየሦስት ቀኑ አንድና ሁለት ቀን ይጠፋል፡፡ እናም በማንኛውም ሰዓት ይመጣል እያልን ባሊያችንን ደቅነን እንጠብቃለን፡፡ ከፈለገ ይመጣል፣ ካልፈለገ አይመጣም፡፡ (ውሀውን ራሱን ሰው አደረግነው እኮ!) ያው እንግዲህ የሚታወቁና የማይታወቁ እርግማኖቻችንን እናወርዳለን፡፡  ከዕታት አንድ ቀን... አለ አይደል... የሆነ ሰው “የማይታወቁ እርግማኖች” በሚል 'ሰበር መጽሐፍ' ያወጣ ጊዜ ጉድ ባይባል ነው!
“ስሚ፣ ልብሶቹን አጠብሽልኝ?”
“ኸረ ገና አላጠብኳቸውም፡፡”
“ሥራ በዛብሽ?”
“ሥራ በዝቶብኝ ሳይሆን ይሄ የተረገመ ውሀ እኮ መጣ ስንለው እየሄደ  ጨጓራችንን ልጦ ጨረሰው እኮ!”
ከዛ ትንሽ ቆይቶ ውሀው በየሁለት ቀኑ መሆኑ ይቀርና በየሳምንቱ አንድና ሁለት ቀን መጥፋት ይጀምራል፡፡
“ስሚ፣ ልብሶቹን አጠብሽልኝ?”
“ሁሉንም ባይሆን ትንሽ ነው የሚቀረኝ፡፡”
“ውሀው ተስተካክሏላ፡፡”
“ባይስተካከልም ተመስጌን ነው፡፡ በየሳምንቱ ብቻ ነው የሚጠፋው፡፡”
እና ተመስገን የምንለው መብታችን ስለተከበረልን ሳይሆን በመብት ጥሰቱ ትንሽነትና ግዙፍነት እየሆነ ነው፡፡ ውሀው በየሁለት ቀኑ በመጥፋቱ እናማርርና በየሳምንቱ በመጥፋቱ “ተመስገን!” እንላለን፡፡
መብራት አይደለም በየአራትና በአምስት ቀን፣ በቀን አራትና አምስት ጊዜ መጥፋቱ እየተለመደ ነው፡፡
“ኸረ እባክህ ያንን ነገር ቶሎ ጨርሰህ ፕሪንት አድርገህ ስጠኝ! “
“እኔ ምን ላድርግ! መብራቱ እኮ አላሠራ አለኝ፡፡ በቀን አራት፣ አምስቴ እየጠፋ እንዴት ተረጋግቼ ልሥራ!”
ከዛ ትንሽ ይቆይና መብራቱ በቀን አራቴ መጥፋቱ ቀርቶ በአራት ቀን ምናምን መጥፋት ይጀምራል፡፡
“ስማ ሥራህን ጨርሼልሀለሁ፤ ኢሜይል አድርጌልሀለሁ”
“እንዴት አለቀልህ! መብራቱ ተስተካከለልህ እንዴ!”
“ባይስተካከልም ተመስገን ነው፡፡ ቢጠፋም በየሦስትና በየአራት ቀን ነው፡፡”
እና ተመስገን የምንለው መብታችን ስለተከበርልን ሳይሆን በመብት ጥሰቱ ትንሽነትና ግዙፍነት እየሆነ ነው፡፡
ቅልጥ ያለ ሠርግ ተደርጎ ሰርገኛ ሁሉ በአደባባይ እስኪሳከር ድረስ ሲጠጣ ያመሸበት፣ ጡንቻው እስኪዝል የጨፈረበት፣ መኪኖች ለተሠሩበት ብቻ ሳይሆን ላልተሠሩበትም ዓላማ አገልግሎት ሲሰጡ የነበረበት ሰርግ፡፡ ልክ ነዋ! አሀ...ይሄ ምንም ሹክ ማለት ምናምን አይደለም። ደግሞ ለዚች የሚሰማባት ጉድ ቀሺም ልብ ወለድ ለመሰለባት ከተማ! መኪና 'ሳይሽከረከር' በቆመበት አገልግሎት መስጠቱ ምን ይገርማል!
እናላችሁ... “ሰርግ ማለት እንዲህ ነው!” ሲባል ይከርማል፡፡ “ሙሽሮቹም ሲወዳዱ እኮ ለጉድ ነው አሉ፡፡”
ከዛ ከተወሰኑ ወራት በኋላ እዚህም እዛም ወሬ ሹክ ሹክ ማለት ይጀመራል፡፡ ያንን የመሰለ ሰርግ ደግሰው አሁን ተተራምሰዋል አሉ!”
“ምን ሆነው? ገንዘቡ የተትረፈረፈላቸው ናቸው ይባል የለም እንዴ!”
“ሞልቶ ቢፈስ  ምን ያደርጋል! ገንዘብ እንደሁ ጠባይ አያርቅ!”
“እኮ ምን ሆኑ ነው የምትሉት?”
“ሰውየው ጥምብዝ እያለ ሌሊት ስድስትና ሰባት ሰዓት ነው አሉ ቤቱ የሚገባው፡፡ ሚስትየዋ መከራዋን እየበላች ነው አሉ፡፡”
እናላችሁ... ወሬው እንደ 'ምንጮቹ' ማንነት እየተለዋወጠ አንዱ “ወደቀ” ያለውን ሌላኛው “ተሰበረ” እያለ  ይከርማል፡፡ ከዛ ደግሞ ይሰነብትና ምን ቢባል ጥሩ ነው...
“በፊት ሳምንቱን ሙሉ ነበር እየሰከረ የሚገባው፡፡ አሁን በሳምንት አምስት ቀን ብቻ ነው አሉ፡፡”
“ተመስገን ነዋ!”  (ሰባት ቀን ጥምብዝ ከማለት አምስት ቀን ጥምብዝ ማለቱ ለመሻሉ በጥናት የተደገፈ አለመሆኑን ማሳወቅ እንፈልጋለን! ቂ...ቂ....ቂ...)
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...በዚች ከተማ ላይ የሚሰሙት የየስርቻና የየምናምን ጉዶች እኮ “ወቸ ጉድ!” ከማሰኘት አልፈው አስደንጋጭም፣ አሳሳቢም እየሆኑ ነው። እናላችሁ... ቀደም ሲል ከእነ ስማቸው “ጉድ!” እንባልባቸው የነበሩ ነገሮች፣ ከአሁኑ የባህሪ አርማጌዶን ጋር ይነጻጸሩና ምን ሊባል ይችላል መሰላችሁ... “ኸረ ያኔ ተመስገን ነበር! እዚሀ ደረጃ አልደረስንም፡፡”
እና በየወሩ የፍጆታ ሂሳቡን 'ሆጭ' የምናደርግበት አገልግሎት  መቋረጡ ትክክል አይደለም ከማለት ይልቅ በተነጻጻሪነት ይሻላል ሳይሆን   «ተመስገን ነው!” የምንለው፡፡
ልክ እኮ... አለ አይደል... እንበልና የሆነ ለምድርም ለሰማይም ያስቸገረ ረብሸኛ አለ፡፡ በቃ ደስ ያላለውን ሁሉ በቦክስ የሚነርት፡፡ እናላችሁ በአንድ ዕለት የሆነ ምስኪንን ተተናኮለው የሚል ወሬ ይሰማል፡፡ ታዲያላችሁ...ወሬውን የሰሙ ሰዎች የተባለውን ሰው ይጠይቁታል፡፡
“ያ እርጉም ተተናኮለህ አሉ፡፡ እውነት ነው እንዴ!”
“ሰው በሌለበት አግኝቶኝ እኮ ነው!”
“በጣም ጎዳህ እንዴ?”
“ኸረ  ተመስገን ነው፤ በጥፊ ብቻ ነው የመታኝ” ቂ...ቂ...ቂ...
ጥያቄ አለን...ጥፊ የቡጢን ያህል አይጎዳም የሚል የምርምር ውጤት የትኛው ሳይት ላይ ነው የሚገኘው!?
እናላችሁ....መብት ነጠቃን በጸጋ እየተቀበልን ነው፡፡
“የባሰ አታምጣ!” ተሸማቃቂ አድርጎ አስቀርቶናል፡፡
ከአዲሱ ገበያ ፒያሳ የሚለውን ታክሲ ትሳፈራላችሁ፡፡ ጊዮርጊስ ስትደርሱ ረዳቱ “መጨረሻ ነው፣” ይላል፡፡
“ገና ፒያሳ መች ደረስን?”
“እኛ ከዚህ ነው የምንዞረው”
“በቃ መጫወቻ አደረጋችሁንና አረፋችሁት!”‘
“ኸረ ተመስገን ነው፡፡ ሌሎቹ እኮ ሦስተኛ ጋ ነው የሚጥሉት!” አይነት ነገር፡፡
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ፈረንጆችና ፈረንጅ የሆኑ ባለ ሌላ የቆዳ ቀለሞች ምን እየሆኑ ነው?! እነሱ ማን ሆነው ነው ሰው አገር ሄደው በዛ ሀገር ህግ የማይገዙት! የምር እኮ... አለ አይደል... በቃ ይሄ የቅኝ ግዛት ሜንታሊቲያቸው ላይለቃቸው ነው! ያዙን ልቀቁን አሉ እኮ! የኳታር ህጎች ልክ ናቸው ልክ አይደሉም ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን መወሰን የሚችሉት የአገሪቱ ዜጎች ብቻ ናቸው። አለቀ! አሁን የዓለም ዋንጫ ላይ ለምንድነው የአስተናጋጇ ሀገር ህጎች የማይከበሩት!
የእውነት ግርም የሚል ነው... እነሱ ሀገር የሄደ የሌላ ሀገር ሰው አይደለም ህጋቸውን ጥሶ  በሆነ ባልሆነው በተለይ ጥቁሮችንና “እኛን አይመስልም፣” የሚሏቸውን እያነቁ እስር ቤት የሚከቱና ከሀገር የሚያባርሩ ‘ፈረንጆች’፤ የኳታርን ህግ የማያከብሩት እብሪት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል፡፡
እናላችሁ... አፋቸውን ይዘው ፎቶ የተነሱት ጀርመኖች በጃፓኖች ጉድ ከሆኑ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ አንዱ የውጭ ሰው ምን አለ መሰላችሁ... “እነሱ ኳታር ላይ አፋቸውን ያዙ፡፡ ጃፓኖች ደግሞ አፋቸውን አስያዟቸው!”
እናላችሁ...ይሄ “ኸረ ተመስገን ነው!” ነገር መብት የሚባል ነገር እንዳለን እያስረሳን ይመስላል፡፡ ለዚሀ ነው አዛዥ ጉልበተኛ የበዛብን፣ በካልቾ ካላቀመስኳችሁ የሚል የበዛብን፣ ከበር ላይ ጥበቃ ሠራተኛ በሮቻቸው እስከማይከፈቱ አለቆች ድረስ ጡንቻውን የሚያሳየን የበዛብን፡፡
ደህና ሰንበቱልኝማ!


Read 1218 times