Saturday, 19 November 2022 19:40

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት እውቅ ሀብታም ገበሬዎች በአንድ መንደር ይኖራሉ። ሁለቱም ራሳቸው ላይ ምናምኒት ፀጉር አልነበራቸውም። በዚህም ምክንያት “ሁለቱ እንቁላሎች” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷቸው ነበር። በጣም የሚዋደዱ ባልንጀሮች ናቸው። አንድ ቀን  አብረው በመንገድ እየሄዱ ሳሉ፣ ከሩቅ አንድ የሚያብረቀርቅ ነገር አዩ። በሩጫ እኔ እቀድም እኔ እቀድም እያሉ እየተገፋፉ፣ እየተናነቁ ወደቁ።
ይሄ ሁሉ ሲሆን ትግላቸውን በቅርብ ሆነው ያስተውሉ የነበሩ አዛውንት ሰው፣ ያንን የሚያብረቀርቅ ነገር አነሱና እንዲህ አሏቸው፡-
“እንደምታዩት ይህ እቃ ማበጠሪያ ነው፤ ለመሆኑ በዚህ ማበጠሪያ አስቀድሞ ጸጉሩን የሚያበጥር ከሁለታችሁ ማን ነው” አሉ።
ሁለቱ ጓደኛሞች ተያይዘው በሀፍረት ተሳሳቁ። ሰው ሁሉ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ሳያውቅ እርስ በእርስ መባላቱ  እጅግ ያስገርማል።
“ምን ፍላጎት ቢኖር ቢፈልግ ቢቃጣ
ምን ያደርግለታል ሚዶ ለመላጣ!”
               (ከበደ ሚካኤል)
***
የምንሻውን ነገር ጥቅሙን ሳናስተውል ፈጥነን ጠብ ውስጥ አንግባ። ረጅም ጊዜ ያኖርነውን ማንነት በአፍታ ፍላጎት አናበላሸው!
ሰሞኑን  በመንግስትና በተቃዋሚዎች መካከል እየተካሄደ የሰነበተው ፍሬ ጉዳይ  ጦርነት ሁሉ እርቅና ድርድርን፣ የተኩስ አቁም ስምምነትን፣ የሰላም ቅድመ ሁኔታን ግድ ያለ፣ የመሳሪያ ክምችትን ያዘለ፣ የአስታራቂና አደራዳሪዎችን ራስ ያዞረ፣ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ ሁኔታን የቀፈቀፈ፣ ጎረቤት አገሮችን ያነቃቃ፣ የመሸምገልንም መንገድንም፣ የመሸንገልንም ጥበብ ያካተተ ከባድና ውስብስብ ሂደት እንደነበረ አሳይቶናል።
በየወገኑና በየጎራው፤
“ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም
አንዴ ከገባህበት ግን እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም”
እየተባባሉ የሄዱበት አይነት መሆኑንም  ያረጋግጣል።
ናፖሊዮን ቦናፓርት እንዳለው፤
“Place, you can recapture,
Time, you can not!”
“ቦታን መልሰህ መቆጣጠር ትችላለህ
ጊዜን ግን በጭራሽ!”
ጊዜ እየገፋ ይሄዳል። መንግስት መለዋወጡ ያለና የነበረ ነው። ለውጥ አይቀሬ ነው። ዛሬ ያሸነፈ ነገ ሊሸነፍ ይችላል። በደምና በኢኮኖሚ ረገድ የሚከፈለው መስዋዕትነት የትየለሌ ነው። የአያሌ አምራች ወጣት ኃይል ይጠፋል። ብዙ ተስፋና ምኞት ይቀጫል።
የየጦርነቱ መላ ይሄው ነው! መንግሥት ሊያስብበት ይገባል። ኢትዮጵያና ጦርነት መቼም ተለያይተው አያውቁም። በየጦርነቱ ዋዜማና ማግስት “እገሌ ይውደም! እገሌ ይለምልም!” ሲባልባት ነው የኖረችው። እየተካሄደ ያለው የሰላም ስምምነትና ድርድር የተሻለ አቅጣጫ ይመስላል- በቅን ልቦና ከሆነ! አለበለዚያ ጊዜ መግዣ ብቻ ነው የሚሆነው- ሂሳዊ ግብብነት (Pseudo deal እንዲሉ) ፤ ሌላ አዙሪት ውስጥ ነው የሚከትተን።
ከላይ ከተረቱ ያገኘነው ትምህርት:-
አንደኛ፡- “የሚያብረቀርቅ ሁሉ ወርቅ አለመሆኑን
ሁለተኛ፡ “ከጥሩ ወዳጅነት የሚበልጥ ነገር አለመኖሩንና
ሦስተኛ፡- ስስት ለሀዘን እንደሚዳርግ ነው!”
እነኚህን ሶስት ትምህርቶች ወደ ሀገር ጉዳይ መንዝሮ ማጤን ነው። ብዙ አስመሳዮች (አብረቅራቂዎች) አሉና፤ እንጠንቀቅ!
ወዳጅነት ስንመሰርት ከልብ ይሁን!
አድርባዮችን እንዋጋ!
የመሳሪያ ጋጋታ የጦርነት ሱሳችንን የማርካት አባዜን ያጠነክራል እንጂ ከውድቀት አያድንም! ባለብን የኢኮኖሚ ድቀት ላይ፣ ጦርነት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ነው የምንለው ለዚህ ነው! ጦርነት ስካር ነው፡- It is like chamagne. It goes to the head of fools, as well as brave men at the same speed. (ጅሉም ጀግናውም አንዴ ጦርነት ውስጥ ከገቡ እኩል ይሰክራሉ) እንዳሉት ነው ጸሐፍት። ስለዚህ ከጦርነት አባዜ እንላቀቅ። ክብ ጠጴዛው ላይ እናተኩር። የመከርንበት ነገር በጎ ነው። ቢያንስ አድረን ከመጸጸት ያድነናል?
በአራቱም ማእዘናት ጦር የሚሰብቅባትና ሻቦል የሚመዘዝባት አገር ከደም በላ ለመውጣት ብዙ ጊዜ ይፈጅባታል። ልበ-ንፁሕ ሆነን ካላገዝናት መከራ እንዳባዘተች ትኖራለች። ፈጣሪ በቃሽ ይበላት!

Read 21995 times