Wednesday, 16 November 2022 10:23

የእሾክ ላይ ሶረኔ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

የእሾክ ላይ ሶረኔ

አንድ የአፈ ታሪክ ወፍ
አሳረኛ ፍጡር
የእሾክ ላይ ሶረኔ
ሽቅብ መጥቃ በራ
ካጋም ዛፍ ጫፍ ሰፍራ
ገላዋን በእሾኩ
ጠቅጥቃ እያደማች
ሥቃይ ሲያጣድፋት
ግቢ ነብስ
ውጪ ነብስ
የሞት ጣር ሲይዛት
ከጣሩ ማህፀን ከሰቆቃ ላንቃ
ስልቱ የረቀቀ ድንቅ የተሰኘ ድምፅ
ልዕለ ሙዚቃ…….
የዘመነ-ብሉይ ከያኒ ያላየው
የዘመነ- ሐዲሰ ጠቢብ ያልቀሰመው
የተቃኘ ቃና፤
በህይወቷ ዋዜማ
ፈጥራ ታላቅ ዜማ
ህላዌ ሙዚቃ ፤
ወዲያው ትሞታለች ከህይወት ተላቃ፤
የአንድ አፈ-ታሪክ ወፍ
የአፈ-ታሪክ ወግ ነው
የጥበብን ልደት….
የአጉል ዘመን ጠቢብ
ምጧን ያስረዝማል
ሥቃይዋን ያበዛል
ድልድይ ሥራም “እምቢ”
ድልድይ ሁንም “እንቢ”
አሳልፍ “እምቢየው”
እለፍ “አሻፈረኝ”
ተወለድ “በጭራሽ”
ሙት ሲሉት “ሞቴ ነው”
ልጅ የለ፤ አባት የለ፤ ሁለተዜ በደል
ግራ- ገብ ጥበብ የህይወት እርግማን
ባንድ-ፊት የሙት ልጅ ባንድ- ፊቱ መካን!
*****
የጥበብ አበሣ የእሾክ ላይ ሶረኔ
የዘመኔ ስዕል የዘመኔ ቅኔ
ዜማና ሙዚቃው ስልትና ምጣኔ
በአበባ ዕድሜ ሙሾ
በእርጅናዬ ዘፈን፤
ጥበብ ያልወጣለት ግራ-ገብ ዘመን
ከእንግዲህ ለእንግዲህ
የጥበብ ፈተና….
ፀሐይ ለመጨበጥ
ብርሃን ለማየት
ከየግል ጓዳ ከራስ ዓለም መውጣት
ከህብረ-ሰው መኖር
በሀሳብ መጋጨት መላተም መካረር
ህብረ -ጥበብ መፍጠር
በምጥ የመለምለም
በሞት የመወለድ
አዲስ ዓለም ማለም
የስሜት ረሀብ
የጥበብ ሰው ጩኸት
የውብ ህይወት ጠኔ
የጥበብ አሻራ
ለስላሳ ሻካራ
እንደሶረኔ እሾክ ወግ ምጡ መከራ
አዲስ ህይወት ማለም…..
አስፋልቱን ሜዳውን ካንቫስ ሸራ ማድረግ
ሰው እንዲሄድበት ቀለም ላዩ ማፍረጥ
አሻራና ዱካው ውበትን እንዲገልጥ
መንገድ ላይ መዘመር
ብርሃን ላይ መጫር
ብርሃን ላይ መፃፍ
….. ፀሐይን መሻማት
ያኔ ነው ዝግ- ባህል በራፉ እሚከፈት
ስዕል ፈገግ ሲል
ሳቅ ሲል ሙዚቃ
ዕውነት ሲሆን ትያትር
ደፈር ሲል ቅኔ
የእሾክ ላይ ሶረኔ ወልዳ
አትሞትም ያኔ
ወልዳ አትሞትም ያኔ
የእሾክ ላይ ሶረኔ!
(ለአዲስ የኪነ-ጥበብ ሳምንት)
ነቢይ መኮንን



Read 1440 times