Saturday, 12 November 2022 13:13

ኳታር እንገናኝ!

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)

    • ከ26ሺ በላይ ኢትዮጲያውያን በኳታር ይገኛሉ
         • 12 ዓመታት የዘለቁ ትችቶች በከፍተኛ ስራ ድል ተደርገዋል
         • ከ5 ቢሊዮን በላይ ተመልካች፤ እስከ 4.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይጠበቃል
         • ክለቦች ከ306 ሚሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ አላቸው


       በኳታር የሚካሄደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ አንድ ሰሞን ቀርቶታል። ይህን ዓለም ዋንጫ በኳታር መዲና ዶሃና በሌሎች ከተሞች በሚገኙ ስምንት ዘመናዊ ስታድዬሞች በአካል ተገኝቶ ለመዘገብ በስፖርት አድማስ በኩል ዝግጅቱን አጠናቅቀናል።
ከ12 ሺ በላይ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚታደሙበት የዓለም ዋንጫን አዲስ አድማስ ከእግር ኳስ ፌደሬሽንና ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ያገኘውን ግብዣ በመጠቀም የሚሰራበት ይሆናል። 22ኛው የዓለም ዋንጫ በሳምንታዊው የአማርኛ ጋዜጣ አዲስ አድማስ፤ www.addisadmassnews.com ድረገፅ በየቀኑ ፤ በአራዳ ኤፍ ኤም 95.1 ላይ እና በሳምንት ለሁለት ቀናት በሚተላለፈው የጥበብ ሞገድ ሁለገብ የሬጌ መዝናኛ፤ የዓለም ዋንጫ ማስታወሻ በሚለው የፌስቡክ ጦማር እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ሰፊ ሽፋን የሚያገኝ ይሆናል።


ከ4 ዓመት በፊት ራሽያ ካስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ማግስት ነው። በሞስኮው ሉዝንሂኪ ስታድዬም ደጃፍ በሚገኘው ሞስኮባ ወንዝ ዳርቻ ላይ በኳታር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጀበ ልዩ ኤግዚብሽን ቀርቦ ነበር። በርካታ የዓለም ሚዲያዎች በታደሙት ይህ ኤግዚብሽን ላይ የተሳተፍከ ሲሆን በወቅቱ ታዋቂ የኳታር የስነፅሁፍ ሰው ስሜን በአረብኛ በመፃፍ See you in Qatar የሚል ፖስትካርድ ሰጥቶኛል። ረቡዕ ህዳር 7 ላይ በኳታር ለ32 ቀናት ቆይታ ለማድረግ እና ዓለም ዋንጫውን ለመዘገብ እጓዛለሁ።
ከ26ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ
በዓለም ዋንጫው ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ሚዲያዎች ለሚኖራቸው ቆይታ በኳታር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥሩ ዝግጅት ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል። በባህረሰላጤዋ አገር ያሉት የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች በአገራቸው የልማት እንቅስቃሴ በተለይ በህዳሴ ግድብ ላይ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በተለያዩ የዲፕሎማሲ ተግባራት በመንቀሳቀስ የሚታወቁ ናቸው።
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይም ይሄው ማህበረሰብ በልዩ ቀለማትና ድባብ ትኩረት ሊስብ እንደሚችልም ተጠብቋል። በዓለም ዋንጫው በስነጥበብ ዲፕሎማሲ አገሩን በአምባሳደርነት የሚያስተዋውቀው ሰዓሊ ተሰማ ተምትሜ ከስፍራው በላከልን መረጃ መሰረት በአሁኑ ቅት በኳታር የሚኖሩና የሚሰሩ ኢትዮጵያውን ብዛታቸው ከ26ሺ በላይ ይሆናል።
ኢትዮጵያውያኑ ከ3 ዓመት በፊት በተካሄደው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወቅት፤ እንዲሁም በየዓመቱ በዶሃ በሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ስታድዬሞችን በደማቅ ድጋፋቸው በማስዋብ የዓለም ሚዲያዎችን ያስደናቁ ናቸው። በዓለም ሻምፒዮናው እና በዳይመንድ ሊግ ለሚሳተፉ የአትሌቲክስ ቡድኖቻችን ድጋፍ በመስጠት አንፀባራቂ ውጤቶችን ያጣጣመ ማህበረሰብም ነው። በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይም በስፖርት መሰረተልማቶችና ስታድዬም ግንባታዎች፤ በሬስቶራንት እና በትራንስፖርት መስኮች ላይ ኢትዮጲያውያኑ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በስፖርት መሰረትለማቶች ግንባታ ከሲቭል ምህንድስና እስከ ጉልበት ስራ ያገለገሉ እንዲሁም በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰማሩ ኢትዮጵያውን በርካታ ናቸው።
ለ12 ዓመታት የቆየን ውዝግብ በድል የሚቋጭ መስተንግዶ
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ኳታርን ለዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት የመረጣት ከ12 ዓመታት በፊት ነው። ይህን ውሳኔውን ግን መላው ዓለም በፀጋ የተቀበለው አልነበረም። በተለያዩ መንገዶች የኳታርን መስተንግዶ የሚያጣጥሉና የሚያወግዙ ትችቶች ሲሰራጩ ቆይተዋል። የመጀመርያው ንትርከ የፊፋ አስተዳደርና አባል አገራቱ አዘጋጅነቱን ለኳታር ለመስጠት ሲወስኑ በሙስና ተደልለዋል የሚለው ነው። የኳታር ንጉሳዊ መንግስት ለአዘጋጅነት በተካሄደው ምርጫ የድጋፍ ድምፆችን ለማግኘት እስከ 6 ሚሊዮን ዶላር በተለይ ለአፍሪካ አገራት ፌደሬሽኖች ማከፋፈሉን ያወሱ ዘገባዎች ነበሩ። ይሁንና ሁሉም አሉባልታዎች በትክክለኛ መረጃዎች ዛሬም ድረስ አልተረጋገጡም። አንዳንድ የኤስያ አገራትና በተለይ ደግሞ አሜሪካ የዓለም ዋንጫውን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው መሰል ዘገባዎች ተሰራጭተዋል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በ2010 እኤአ ላይ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሂድ በ2018 እኤአ ላይ ራሽያ 21ኛውን የዓለም ዋንጫ እንድታስተናግድ ከመረጠ በኋላ በ2022 እኤአ ላይ ደግሞ ኳታር 22ኛውን ዓለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ ወስኗል። አሜሪካ፤ አውስትራሊያ፤ ጃፓንና ደቡብ ኮርያ ለመስተንግዶው ፉክክር አድርገው አልተሳካላቸውም። ፊፋና የዓለም ዋንጫው አዘጋጅ ኳታር በውድድሩ ታሪክ ዘላቂ የስፖርት ልማቶች በመገንባት፤ ከካርቦን ልቀት የነፃ መስተንግዶ በማካሄድ፤ በዘመናዊ ዝግጅት የተሟላ እንደሚሆን እምነት ማሳደራቸው የሙስናውን ወሬ አደብዝዞታል። በሌላ በኩል የዓለም ዋንጫው የሚካሄድበት ወቅት ከተለመደው መርሃ ግብር እንዲቀየር መደረጉንም ያማረሩ አልጠፉም። ኳታር በሙቀታማ አየር ንብረቷ ሳቢያ ዓለም ዋንጫው የፈረንጆች አዲስ አመት ዋዜማ ባለው ወር እንዲካሄድ አድርጋለች። በመደበኛው የዓለም ዋንጫ ወቅት የአየሩ ሙቀት ከ50 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ ይሆናል። አዲስ በታቀደው የዓለም ዋንጫ ወር ግን የኳታር አየር ንብረት እስከ 29 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መውረዱ ውሳኔውን አፅንቶታል። ኳታር የዓለም ዋንጫን የሚያስተናግዱ ስምንት ስታድዬሞች ከሙቀቱ ጋር ለማመጣጠን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመስራት ከአየቅጣጫው የመጡትን ትችቶች አብርዳለች። የኳታር ዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰፋ ያለ ጥናትና ምርምር ካደረገ በኋላ በተጨዋቾች፤ በደጋፊዎች እና በአጠቃላይ በስታድዬም ውስጥ ቀዝቃዛ አየር የሚያነፍስ ዘመናዊ የማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂ በመፍጠር ተግባራዊነቱን አረጋግጧል። አስደናቂዎቹ የዓለም ዋንጫ ስምንት ስታድዬሞች በዚህ ረገድ ስኬታማ ውድድር ለማስተናገድ እስከ 7 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖባቸዋል። ሌላው ትችት ኳታር የዓለም ዋንጫን የመስተንግዶ ደረጃ በታሪክ ከፍተኛውን በጀት በማውጣት ሰቅለዋለች በሚል የተናፈሰው ነው። በአረቡ ዓለም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ዋንጫውን ለማዘጋጀት ከ229 ቢሊዮን ዶላር በኳታር መንግስት መውጣቱ በቀጣይ ዓለም ዋንጫዎች በብቸኝነት ውድድሩን ለማስተናገድ የሚችል አገር ማሳጣቱ ነው የተሰጋው። ከኳታር በፊት ራሽያ ለ21ኛው የዓለም ዋን 14.6 ቢሊዮን ዶላር ብራዚል ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ 11 ቢሊዮን ዶላር እንዳወጡ የሚታወስ ሲሆን የኳታር በጀት ከ10 እጥፍ በላይ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል። በ2026 እኤአ ላይ 23ኛውን የዓለም ዋንጫ አሜሪካ፤ ካናዳና ሜክሲኮል ለሶስትዮሽ ለማስተናገድ ያቀዱት በነፍስ ወከፍ እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ለማውጣት በማቀድ ነው።


ከትችቶቹ ሁሉ የከፋው ኳታር በዓለም ዋንጫ ዝግጅቷ ባከናወናቸው የስፖርት መሰረትልማት ግንባታዎች ላይ ከውጭ አገር የመጡ ዜጎችን ጉልበት በዝብዛለች፤ ለከፋ አደጋ እንዲጋለጡ አድርጋለችና ባልተመጣጠነ ክፍያ ስትጎዳ ቆይታለች የሚሉትም ይገኙበታል። በዓለም ዋንጫ ዝግጅት ላይ ባለፉት 12 ዓመታት ከግንባታዎች ጋር በተያያዘ ከ6500 በላይ የግንባታ ሰራተኞች ለሞት ፤ ለከፋ አደጋ እና ሌሎች ጉዳቶች መጋለጣቸውን ትልልቅ የዓለም ሚዲያዎች አውስተዋል። አንዳንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከኳታር ዓለም ዋንጫ ዝግጅት በተገናኘ ጉዳት ለደረሰባቸው ፊፋ እና የኳታር መንግስት እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር የካሳ ክፍያ እንዲያቀርቡ በይፋ ጠይቀዋል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበርና የኳታር መንግስት በዚህ ረገድ የቀረቡ ትችቶች መግነናቻውን በመግለፅ ተሟግተዋል።
በዓለም ዋንጫው ዝግጅት ጉዳት ለደረሰባቸው ሁሉ የሚያስፈልገው የካሳ ክፍያ እና ፈጣን ምላሽ በመስጠት የቀረቡ ማመልከቻዎች ሁሉ ምላሽ ማግኘታቸውንም ይገልፃሉ። አብዛኛዎቹ ትችቶች የኳታርን መስተንግዶ ከማብጠልጠልና በሚዲያ የዘገባ ቱማታዎች ለመፍጠር የሚሰሩ መሆናቸውንም አውግዘዋል።
ባለፉት አምስት አመታት ኳታር ከጎረቤቶቿ ሳውዲ አረቢያ፤ ባህሬንና ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ጋር ገብታበት የነበረው ውጥረትም ተፅእኖ መፍጠሩም አልቀረም። ጎረቤት አገሮቹ በኳታር ላይ ድንበራቸውን በመዝጋት፤ ማዕቀቦችን በመጣል እና ለዓለም ዋንጫው መስተንግዶ ትኩረት በምነፈግ ቢቆዩም ይህ ሁኔታ የታር መንግስትን ጠንክሮ እንዲሰራ አድርጎታል። ባለፈው አንድ አመት ደግሞ ጎረበተ አገራቱ በመካከለኛው ምስራቅ ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ ለማገዝ ጥረት ማድረግ ጀምረዋል። ሳውዲ አረቢያና ናይትድ አረብ ኢምሬትስ ለዓለም ዋንጫ ተራዳሚዎች ማረፊያነት መልካም ፈቃደኛ መሆናቸን አሳውቀዋል። በትንሿ አገር የዓለም ዋንጫውን ለመታደም ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የእግር ኳስ አፍቃሪና ቱሪስት ተጠብቋል።
የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች ከ90 በመቶ በላይ ተሸጠው ማለቃቸው የመስተንግዶውን ሁኔታውን ያከብደዋል በሚል ተነግሯል። የኳታር መንግስት፤ ኳታራውያን፤ ከ10 አገራት በላይን የወከሉ የውጭ አገር ዜጎች በማረፊያ እና በዓለም ዋንጫ ታዳሚዎች ቆይታ እንግዳ ተቀባይ ሆነው እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቦላቸው ሙሉ ዝግጅት አድርገዋል። የዓለማችን ግዙፍ የአየር መንገድ ኳታር ኤርዌይስ የዓለም ዋንጫው በሚካሄድባቸው 28 ቀናት በቀን ከ1300 በላይ በረራዎችን በማስተናገድ ከፍተኛ ስራ ይጠበቅበታል።
ከ5 ቢሊዮን በላይ ተመልካች፤ ከ4.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ
ከ4 ዓመታት በፊት ራሽያ ባስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫን በቲቪ ስርጭት ከ3.5 ቢሊዮን በላይ ተመልካች ማግኘቱ እና በፈረንሳይና ብክሮሽያ መካከል የተካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ ከ1 ቢሊዮን በላይ የቲቪ ተመልካች ማግኘቱ ይታወሳል። በኳታር 22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የተጠበቀው የቲቪ ተመልካች ከ5 ቢሊዮን በላይ እንደሚሆን ነው። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ በ23 የብሮድካስት ቀጠናዎች ከ100 አገራትን በላይ በሚያካልለው የዓለም ዋንጫው ከስርጭት መብት የሚያገኘው ገቢ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ተገምቷል። 22ኛው የዓለም ዋንጫ በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች በሚያገኘው ትኩረትም የላቁ ክብረወሰኖች እንደሚመዘገቡበትም ተጠብቋል። ስለ ዓለም ዋንጫው የተለያዩ ቪድዮ ምስሎችን በመጠየቅ በቀን ከ300 ሚሊዮን በላይ ፈላጊዎች ተሰማርተዋል። ዓለም ዋንጫው እስኪጠናቀቅ በቪድዮ ላይ ከዓለም ዋንጫው ጋር ተያይዘው የሚለጠፉ ይዘቶች እስከ 3 ቢሊዮን ድምር ተመልካች እንደሚያስመዘግቡም ተጠብቋል።
የክለቦች ክፍያ ከ306 ሚሊዮን ዶላር በላይ
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ከዚህ ወጭ ለኳታር ድጋፍ ያደረገው 1.7 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህ በጀት ከ440 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነውን የሽልማት ገንዘብ ይጨምራል። ፊፋ እና የኳታር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ የሚጠብቁት ገቢ ከ4.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው። የዓለም ዋንጫውን በ32 ብሄራዊ ቡድኖችና በ64 ጨዋታዎች ለ28 ቀናት ለማካሄድ ፊፋ እና የኳታር ዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ የመስተንግዶ ወጭያቸው ከ1.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው። ከ247 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለቴሌቭዠን የስርጭት ኦፕሬሽን፤ ለዓለም ዋንጫው የስራ ግብረሃይል ከ207 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም በዓለም ዋንጫው ተጨዋቾቻቸን ለሚያሰልፉ ክለቦች የሚከፋፈል 326 ሚሊዮን ዶላር ወጭ እንደሚሆን ታውቋል። በዓለም ዋንጫው በተጨዋቾቻቸው ተሳትፎ ያገኙ ክለቦች በአንድ ተጨዋች በቀን 10ሺ ዶላር ይታሰብላቸዋል። ከ4 ዓመት በፊት በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ 736 ተጨዋቾች በ24500 የአበል ቀናት ከ208 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተከፈላቸው ሲሆን፤ በ2014 ብራዚል ላይ 70 ሚሊዮን ዶላር በ2010 ደቡብ አፍሪካ ላይ 40 ሚሊዮን ዶላር ነበር ክለቦች የተከፋፈሉት።





Read 11803 times