Saturday, 12 November 2022 11:45

ዢ ጂንፒንግ - እንዲህ ይነግሳሉ ብሎ ማን አሰበ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 • ሰባቴ በማመልከቻ መጠየቅ፣ አስር ጊዜም ተስፋ ሳይቆርጡ ደጋግመው መሞከር ለምን? የፓርቲ አባል ለመሆን!
       • ተራ የፖርቲ አባል ለመሆን የተጉላሉት ሰውዬ፣… ዛሬ የፓርቲ አለቃ፣ የአገሪቱም ገዢ ሆነዋል። እንዲያውም፣ በዓለማችንና በዘመናችን፣          እንደ ዢ ጂንፒንግ በሥልጣን የገነነ ሰው የለም ማለት ይቻላል።
      • የቅዱስ ያሬድን ትረካና የአብዱ ኪያርን ዘፈን ሰምተዋል
             ዮሃንስ ሰ        የአገሪቱ ብቸኛ ገዢ ፓርቲ ውስጥ፣ ከወደ አናቱ ደህና ቦታ ለማግኘት የሚፈልግ ሰው፣ ገና በልጅነቱ ወደ መወጣጫው መሰላል መጠጋት አለበት። ታዲያ፣ ወደ ፓርቲው ዘው ብሎ መግባት አይቻልም። በቅድሚያ “በወጣቶች ሊግ ለመታቀፍ” ማመልከቻ መጻፍ ያስፈልጋል። የወጣቶች ማህበር አባል ለመሆን ነው ማመልከቻው።
በለጋ እድሜ የወጣቶች ሊግ ውስጥ በአባልነት የተመዘገበ ሰው፣ በኮሙኒስት ፓርቲው ውስጥ ቦታ ለማግኘት መንገዱን ይጠርጋል። ከሥልጣን ሽሚያውና ከሽኩቻው ጋር ቀስ በቀስ ይተዋወቃል፤ በቅርበት ይላመዳል።
ብዙዎቹ ረዥም ርቀት አይጓዙም። ገሚሶቹ ከቀበሌና ከወረዳ አይወጡም። ጥቂቶቹ በስንት መከራ ወደ ትልልቆቹ ከተሞች ይደርሳሉ። በጣም ጥቂቶቹ ግን፣ ከበርካታ ዓመታት ድካም በኋላ ወደ መናገሻው ከተማ ገብተው፣ ወደ ዋናው የሥልጣን መነሃሪያ የመድረስ፣ ወደ ገናናው የሥልጣን ተራራ የመረማመድ ተስፋ ይኖራቸዋል።
ወደ ፓርቲ የሚገቡ ሰዎች፣ ምክንያታቸው ይለያያል። ፖለቲካ እንደ ትልቅ ሙያ የሚማርከው ሰው አለ። ሁሉንም መሞከር የሚያምረው፣ ሁለገብ ለመሆን የሚመኝ ብኩን ሰውም ሞልቷል። አዛዥ አናዛዥ ለመሆን የሚያጓጓ፣ የሥልጣን ጥም የሚያንገበግበውም አይጠፋም።
ተወደደም ተጠላም፣ ፓርቲ ውስጥ መግባት፣ እንደ ግዴታ መስሎ የሚታየውም ይኖራል። በተለይ፣ አንድ ፓርቲ ብቻ በሚገዛት አገር፣ ኮሙኒስት ስርዓት በሰፈነበት ዘመን፣… ሌላ አማራጭ ላይታየው ይችላል። ወይ የፓርቲ አባል ይሆናል፤ ወይ የፓርቲ ጠላት ተብሎ ይፈረጃል። ወይ የባለሥልጣን መጫወቻ ይሆናል፤ ወይም የሥልጣን ጨዋታው ተሳታፊ ይሆናል።
ከሥልጣን ቅርጫው እንደ አቅሚቲ በቀበሌና በወረዳ እየተሻማና እየተቃመሰ፣ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ መናገሻው ከተማ መድረስ ቀላል ባይሆንም፣… ስራው አለቀ ማለት አይደለም። አገር አቀፉ የሥልጣን ቅርጫ፣ ተራራ የሚክል ክምር ነው። ተዝቆ አያልቅም። ሽቅብ ለመግነንም ይመቻል።
አደጋውም፣ ግን የዚያኑ ያህል ነው። ከግራና ከቀኝ በየጊዜው፣ በከፊል የሚደመረመስ፣ ከወዲያ ግድም ቁልቁል የሚንሸራተት ናዳ ይኖራል።
ናዳ የወረደበት፣ ከላይ የተደረመሰበት የሥልጣን ተቀናቃኝ፣… እንጦርጦስ ይወርዳል። ተቀብሮ ይቀራል። የሥልጣን ቅርጫው እንደ ተራራ ሲቆለል፤ በማንኪያም በአካፋም ለመዛቅ የሚቀራመት፣ ወደ ከፍታ ለመረማመድ የሚሽቀዳደም ይበዛል። ተቀናቃኙን ከተራራ ስር ጨፍልቆ ለማጥፋት የሚያሴርና የሚዘምትም ሁልጊዜ ይኖራል። አለምክንያት አይደለም። የተራራው አናት፣ ከአንድ ሰው በላይ አያስተናግድም።
በእርግጥ፣ የሥልጣን ቅርጫ እንደተራራ ያልገዘፈበት፣ “በብዙ ተራራ የተባረከ አገር” መፍጠር ይቻላል። ታዲያ፣ “ባለብዙ ተራራ” መሆን ማለት ግን፣ እልፍ የሰፈር ንጉሦችን ለመፈልፈል አይደለም። በዘርና በሃይማኖት ሰበብ ጥቃቅን የመንደር አውራዎች የሚርመሰመሱበት ረግረግ ለመፍጠርም መሆን የለበትም። ብዙ ተራራ ማለት፣ አገሪቱን ተቀራምቶ መተራመስ ማለት ከሆነ፣ ቢቀር ይሻላል። መርህን የሚያጠፋ “ብዝሐነት” ለአገርም ለሕይወትም ጥፋት ነውና።
ይልቅስ ባለ ብዙ ተራራ መሆን ማለት፣ በነፃነት እያንዳንዱ ሰው የየራሱን ሕይወት እንዲመራ፣ የገዛ ራሱ ንጉሥ እንዲሆን፣ በአጠቃላይ አገሬው ብዙ ሚሊዮን አምባ መስራት እንዲችል ነው። ግን፣ የነፃነት ሕይወትን ማስፈን ቀላል አይደለም። ረዥም ጊዜ፣ ከፍተኛ ብቃትና አድካሚ ጥረትን ይጠይቃል።
ሌላው አማራጭ፤ አንድ አገር፣ አንድ ተራራ፣ አንድ ገናና፣ አንድ አውራ፣… በሚሉ ስሜቶች የተቃኘ ነው። ይህን እውነታ መካድ ይቻላል። ለማስካድ የሚያገለግሉ አባባሎችም ሞልተዋል። “የሕዝብ ሥልጣን”፣ “የብዙሃን ተሳትፎ”፣ “የተቋማት ሃላፊነትና የሥልጣን ክፍፍል”፣ “የምክር ቤትና የፓርቲ ወሳኝነት”፣ “የጋራ አመራርና የኮሚቴ አሰራር”፣… እያሉ ይናገራሉ። “ባለ ብዙ ተራራ ነን” ለማለት ነው። ግን ለማስመሰል ነው።
በኮሙኒስት ፓርቲ ስር፤ ሁሉም ጉብታዎች የአንድ ተራራ እርከኖች ናቸው። ኮሚቴው፣ ምክርቤቱ፣ ተቋማቱ፣… ከወረዳ እስከ ማእከላዊ አስተዳደር፣ ከዘርፍ እስከ ክንፍ ሁሉ፣… የመሰላል መረማመጃ ናቸው - ወደ ተራራው አናት።
ወደ ኮሙኒስት ፓርቲው አናት ለመጠጋት፣… ማለትም ወደ አገሪቱ የሥልጣን ቅርጫ፣ ለዚያውም ወደ ከፍተኛው ጫፍ ለመቅረብ፣… በ50 ወይም በ60 ዓመት እድሜ ላይ ይህን እድል ለማግኘት፣… የታችኛውን የመሰላል መረማመጃ ገና በለጋ እድሜ መጀመር ያስፈልጋል። በቅድሚያ የወጣቶች ሊግ አባል መሆን የግድ ነው።
ዢ ጂንፒንግ፣ ገና በታዳጊ እድሜያቸው ነበር የአባልነት ማመልከቻ ያስገቡት። ተቀባይነት አላገኙም። አንዴ ብቻ አይደለም። ተስፋ ሳይቆርጡ ለሰባት ጊዜ ሞክረዋል። ከሰባት የአባልነት ማመልከቻዎች በኋላ ነው ተቀባይነት ያገኙት ሲል ዘግቧል ታይም መፅሔት። የሕይወት ታሪካቸውን በሰፊው የሚተርክ መፅሐፍ ደግሞ፣ በ8ኛ ሙከራ እንደተሳካላቸው ይገልጻል።
ዢጂንፒንግ የኮሙኒስት ፓርቲ አባል እንዲሆኑ የተፈቀደላቸውና የተመዘገቡትም፣ በአስረኛ ሙከራ ነውይላል- ዘገባው። መከራ ነው። ግን አይገርምም።
የሥልጣን ቅርጫው ውስጥ መግባት የሚፈልግ ሰው፤ የወጣቶች ሊግና የኮሙኒስትፓርቲ አባል ለመሆን፣ ሰባቴ ወይም አስሬ ብቻ ሳይሆን፣ ሰባት ጊዜ ሰባ መሞከር አለበት።
የሥልጣን ቅርጫ ባይማርከው ወይም ቢያስጠላውም እንኳ፤ ሌላ የሙያ ፍቅርና የኑሮ መተዳደሪያ ቢኖረውም እንኳ፣ ዝም ማለት የለበትም። አባል የመሆን ጉጉት ካላሳየ፣ ጥያቄ ካላቀረበና ማመልከቻ ካላስገባ፣ በጥቁር መዝገብ ውስጥ ጥቁር ነጥብ ይያዝበታል።
ወደደም ጠላም፣ ከልብ ይሁን ለይምሰል፣ የጉጉት ስሜት ማሳየት ይጠበቅበታል። አንዴ ማመልከቻ አስገብቻለሁ ብሎ መቀመጥ የለም። እየደጋገመ ማመልከቻ ይጽፋል። እንደገናም ይሞክራል።
 እንደ ሙዚቀኛው እንደ ያሬድ ትረካ ቢመስልም፣ ይለያያል።
ስድስቴ ወይስ ሰባቴ?
ግንድ ላይ ወደ ላይ ለመውጣት የምትታትር አንዲት ጉንዳን፣… ትንሽ እንደሄደች ትወድቃለች። አሁንም ትሞክራለች። ስንዝር ሳትርቅ ተደናቅፋ ትወርዳለች። እንደገና እየተውተረተረች የግንዱን አቀበት መቆናጠጥ ትጀምራለች። መሃል ላይ አባጣ ጎርባጣ አይጠፋም፤ አወላክፎ ይጥላታል። ተስፋ ሳትቆርጥ እንደገና ከወደቀችበት ተነስታ፣ ወደ ከፍታ የግንዱን ዳገት ለመውጣት ትያያዘዋለች።
በጉንዳን አቅም የግንዱ ርዝመት፣ የኤቨረስት ተራራ ሳይሆንባት አይቀርም። ከሰባተኛው ዙር ሙከራ በኋላ ነው የሚሳካላት።
ስድስት ጊዜ ወድቃ በሰባተኛው ነው ወይስ? ሰባቴ ወድቃ ሰባቴ ተነስታ ስትሞክር?
ደግነቱ ስድስቴም ቢሆን ሰባቴ፣ በቁምነገሩ ላይ ለውጥ አያመጣም።
ብዙ ጊዜ ተደናቅፋም፣ ብዙ ጊዜ ችግር ገጥሟትና ወድቃም፣ የከፍታ ጉዞዋን በጽናት ቀጠለች እንጂ፤ ሰንፋ ወይም ተስፋ ቆርጣ አልተወችውም።
በጥቅሉ ተስፋ አለመቁረጥና በፅናት መትጋት የሚል ነው መልዕክቱ።
ጥቅል ሃሳብን ተጨባጭ ምስል አላብሶ መቅረጽና ማሳየት ነው- የትረካው ፋይዳ። ጥልቅ ሃሳብን በእውን ሊታይ በሚችል ምናባዊ ድርጊት መግለጽ ነው- የትረካው ፋይዳ…። selection, concretization, projection “ከተሰኙ መሰረታዊ የኪነጥበብ ባሕሪያት ጋር ይዛመዳል። የኪነጥበብ ዝምድናውን ለዛሬ እንተወውና ፖለቲካውን ወደ እልባት እናድርሰው።
ለማንኛውም ሃሳብንና ስሜትን በቀጥታ ቃል በቃል አይናገርም ኪነጥበብ። “ከመናገር ይልቅ በተጨባጭ ያሳያል” እንዲሉ ነው።
የከፍታ ጉዞ የሚል ሃሳብ አለ።
ትረካው ውስጥ ግን ምስልና ድርጊትን ነው የምናየው፣ የግንዱ ርዝመትና የጉንዳንዋ ጉዞ።
ለችግር ሳይበገሩ በፅናት ደጋግሞ መጣርና በብርቱ መትጋት የሚለው ሃሳብ ደግሞ፣… በሚታይ በሚጨበጥ ድርጊት ነፍስ ዘርቶ ህይወት ተላብሷል። ወድቃ ተነስታለች አይበገሬዋ ጉንዳን። ስንቴ ወድቃ ስንቴ እንደገና እየተነሳች እንደሞከረች ይተርካል። ስድስቴ ብንል፣ ወይም ሰባቴ ብንል፣… ያስኬዳል።
ይሄ ሁሉ ጽናትና ጥረት፣ በቅዱስ ያሬድ ትረካ ላይ እንደተጠቆመው፣… ከሙዚቃ ፍቅር የመነጨ ለሙያ ፍቅር የዋለ፣ “መልካም ፍልሚያ” ሊሆን ይችላል።
ከውስጣዊ ሃሳብና መንፈስ የፈለቀ ነው፤ ፅናቱ።
ውበትን የተጎናፀፉ ጥዑም የሙዚቃ ፈጠራዎች ደግሞ ከዚሁ የሙያ ፅናት ይፈልቃሉ። ተስፋ ሳይቆርጥ በፅናት መትጋት ማለት፤… በያሬድ እንደምናየው ለኪነጥበብ ፍቅርና ለሙዚቃ ፈጠራ የተከፈለ ዋጋ ነው።
ግን ደግሞ፤ የጉንዳንዋ ትረካ፤ የእለት ለእለት የኑሮ ብርቱ ትግልም ነው።
ሰርቶ የመኖር፣ ሕይወትን የማሻሻል፤ ቤተሰብን የማደላደል ጉዳይ፤… ያላሰለሰ የዘወትር ውጣውረድን፣ ፅናትንና ትጋትን ይጠይቃል። የጉንዳንዋ ተረት፣ የጥበበኛው የያሬድ ትረካ፣ በእለታዊ የኑሮ ጥረትና ግረት ሊተረጎም ይችላል- አብዱ ኪያር እንደዘፈነው።
ወድቆ አይቀርም የመርካቶ አካባቢ የታታሪዎች መንፈስ።… ለወከባና ለውጣ ውረድ ያልተሸነፈ የሰባተኛ ሰፈር የኑሮ ሩጫ ውስጥ፤… ተስፋ መቁረጥ የለም እያለ አብዱ ኪያር ይደነቃል። ሰባቴ ቢወድቅ፣ ሰባቴ ይነሳል። ለዚያውም፣ ከችግሩ እየተማረ፣ የተሻለ አቅም ይዞ እየጠነከረ ነው የሚነሳው- ካወቀበት።
እናም ጽናቱና ብርታቱ የሚመነጨው፣ ከኑሮ ነው።  ተመልሶም ለኑሮ ነው። ማለትም የኑሮ ሃላፊነት፣… የራሴ ሃላፊነት ነው ብሎ በመቀበል ይጀምራል። በዚህ ላይ ሲታከልበት ነው ከቤተሰብና ከጓደኛ ጋር መደጋገፍ የሚያምረው። ከኑሮ ሃላፊነት የሚፈልቅ መንፈስ፤ ተመልሶ ኑሮን ያገለግላል። የኑሮ የገቢ ምንጭ ይሆንለታል። እያንዳንዷ የህልውና ቀን የዚህ የፅናት መንፈስ ምንጭ ናት። እንዲሁም የፅናት ውጤት ናት። “ሰርቶ መብላት” ወይም “በልቶ መስራት” እንደማለት ነው።
ያው፣… ሰባቴ ቢወድቁ ሰባቴ እየተነሱ።
በአጭሩ ጽናትና ትጋት፣ ለቅዱስ ያሬድና ለሙዚቃ ጥበብ፣ እንዲሁም ለመርካቶ የስራ ወከባና ለእንጀራ ሩጫ፣… ለሰው ሕይወት ሁሉ ያገለግላል። የጉንዳንዋ ተረት፣…
ለእለት ተእለት ኑሮ ሊሆን ይችላል።
በአምስት በአስር ዓመት ወደተሻለ ሙያና ኑሮ ለመሸጋገርም ይሆናል።
በአርአያነት የሚጠቀስ የሕይወት ዘመን ፍሬማነትን፣ በታሪክ የሚደነቅ ስኬትን ለመቀዳጀትም፣… ተመሳሳይ ጽናትና ትጋት ያስፈልጋል።
ታሪክን የሚቀይርና ዘመናትን የሚሻገር፣ በልዩ የብቃት ልህቀትና በተዓምረኛ ጥበብ፣ እጅግ የተትረፈረፈና ያማረ የፍሬ በረከት እውን የሚሆነውም፣ በዚሁ በጽናትና በትጋት መንገድ ነው- በያሬድ መንገድ።
የዢ ጂንፒንግ ታሪክ ደግሞ አለ። የወጣቶች ሊግ አባል ለመሆን ሰባቴ ወድቆ ሰምንቴ ሞክሯል - ታዳጊው ጂንፒንግ። የኮሙኒስት ፓርቲ አባል ለመሆን ደግሞ 10 ጊዜ ደጋግሞ መሞከር ነበረበት?
ይሄስ ምን የሚሉት “ጽናት” ይሆን? ፓርቲውንና የወጣቶች ማህበርን ከመውደድ ነው? ከኮሙኒዝም ጋር ፍቅር ይዞት ነው? ፍቅር ከሆነ አይጣል ነው። ወይስ በደህና ለመሰንበት? አቋራጭ የኑሮ ማሳመሪያ፣ የወረፋ ቅድያ፣ አጥፍ ራሽን፣ የመንግስት የውጭ አገር ስኮላርሽፕ ለማግኘት?
ኮሙኒስት ፓርቲ በብቸኝነት በሚገዛት አገር፣ ለዚያውም የዛሬ 50 ዓመት ገደማ፣… ጂንፒንግ እና ሌሎቹ ወጣቶች፣ የፓርቲ አባል ለመሆን ቢሽቀዳደሙ አይገርምም።
ኑሯቸውን ለማሻሻል ሳይሆን፣… ሥልጣን ለመሻማት የሚቀራመቱም ሞልተዋል። የሥልጣን ጥም፣ በሌጣው… የራስን ሕይወት ለማሳመርና ኑሮን ለማሻሻል የመጓጓት ጉዳይ አይደለም። በሌሎች ሰዎች ሕይወትና ኑሮ ላይ ፈቃጅና ከልካይ፣ አዛዥ እና አናዛዥ የመሆን ክፉ ረሃብ ነው - የሥልጣን ጥም።
የሥልጣን ጥምን የማርካት እድል የሚያገኙት፣ ፓርቲው ውስጥ ከገቡና በሥልጣን መሰላል ላይ፣ አንዱ ሌላኛው ጫንቃ ላይ ለመረማመድ ተሸቀዳድመው ከቀደሙ፣ የቅርጫ ተራራውን እየቧጠጡ ለመቀራመት ከተሻሙ ብቻ ነው። ከፓርቲው ውጭ ሌላ አማራጭ የለም።
በእርግጥ፣ ከሥልጣን ጅራፍ ለመትረፍም በፓርቲው መታቀፍ ያስፈልጋል። ከፓርቲው ርቆ በደህና መሰንበት አይቻልም። በሩቁ ከዳር ከቆመ፣ በቀላሉ ይታያል። ለጅራፍ ይመቻቻል። የፓርቲ አባል መሆን ነው የሚያዋጣው።
አባል የመሆን ጉጉት ያላሳየና የአባልነት ማመልከቻ ያላስገባ ወጣት፣… የፓርቲውና የመንግስት አይን ውስጥ ይገባል። ሚጢጢ ባለሥልጣናትና የመንደር ካድሬዎች ይጠምዱታል፤ ያጠምዱታል። ከሥልጣን ጣጣና ሽሚያ፣ ከሥልጣን ሽኩቻና ፍዳ እርቃሁ ብሎ ይባስኑ ወደሚንቀለቀለው እቶን ተጎትተው ማገዶ ያደርጉታል።
ከሥልጣን አይንና ጆሮ እጅግ መራቅ የፈለገ፣ እዚያው የሥልጣን አምባ ስር የፓርቲው ጉያ ውስጥ መግባት ይኖርበታል።
ለመግባት ሞክሮ ሰባቴ ቢወድቅ፣ ሰባቴም አስሬም ተነስቶ ይሞክራል።
በእርግጥ ወጣቱ ጂንፒንግ፤… እንደሌሎቹ ተራ ወጣቶች የዚህን ያህል መጉላላት አልነበረበትም።  በወቅቱ ትልቅ ባለሥልጣን ናቸው አባቱ።
ከፓርቲው መሪ ከአገሪቱ ገዢ ከማኦ ዜዱንግ ጋር በቅርብ የሚተዋወቁ አንጋፋ ባለሥልጣን ነበሩ በጊዜው። የፓርቲው የፕሮፓጋንዳ ሚኒስትር፣ የአገሪቱ ምክር ቤት ሰብሳቢ ነበሩ-የጂንፒንግ አባት።
የኮሙኒስት አገር ባለሥልጣናት፤… በተለይ በአውራ የሥልጣን ቅርጫ አጠገብ፤ ከተራራው አናት አቅራቢያ የደረሱ ጥቂት ባለሥልጣናት፤… ከሰው ክምር ላይ የተቀመጡ ያህል ናቸው። ከነሱ ስር ብዙ ሚሊዮን ዜጎችን እንዳሻቸው የማዘዝና የማናዘዝ ሃይል ይኖራቸዋል። ሥልጣናቸው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለልጆቻቸውም ይተርፋል።
ጣጣውም ግን፣ የዚያኑ ያህል ከተራራ የገዘፈና የከበደ ነው። በሥልጣን ሽምያው መሀል ተጠልፎ የወደቀ፤ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ ላይ ለአፍታ የተዘናጋ፤ ከጎን በኩል በአፈንጋጭነት የተፈረጀ፣ በተቀናቃኝነት የተጠረጠረ፣ ወይም ያልጥፋቱ ጭዳ እንዲሆን የተዶለተበት ባለሥልጣን፤… ወዮለት!
ስሙ የማይታወቅ ተራ ዜጋ ቢሆን ይሻለው ነበር።
ትልቅ ባለስልጣን፣… አንዴ እግሩ ከከዳው፣…በሌሎች ባለሥልጣናት ጥርስ ውስጥ ከገባ፤… አንዴ ከተጠቆረ፤ መከራው ማለቂያ የለውም። ጦሱ፤ ለልጆቹም ይተርፋል።
ትልቁ ባለሥልጣን፤ ድንገት የፓርቲ ጠላት ተብሎ ከተወነጀለና ከተዋረደ በኋላ፤… ልጆቹን በመጥመድና በማስቃየት ተወዳጅነትን ለማግኘት የሚሸቀዳደሙ የበታች ባለሥልጣናትና ጀማሪ ካድሬዎች ከየአቅጣጫው ይረባረባሉ። ልጆቹ ጭምር የወንጀል ተካፋይ ሆነው ይታያሉ።
ዢ ጂንፒንግ እንዲህ አይነት እጣ ነው የደረሰባቸው። አባትዬው በፓርቲው ውስጥ የነበራቸው ቦታ ተንዶ ከሥልጣናቸው ሲባረሩ፣ ወደ ገጠር ተባረሩ። ወደ ገበሬ ማህበር እንዲገቡ ተነገራቸው። ከመናገሻ ከተማዋ ተሰናበቱ። ምንም ማድረግ አይችሉም።
ከእንግዲህ ሁሉንም ነገር ትቼ ገበሬ ሆኜ ለመኖር ወስኛሁ ብለው ለፓርቲያቸው በደብዳቤ ሲያሳውቁስ? መብትህ ነው አልተባሉም። የአንድ ፋብሪካ ሰራተኛ እንዲሆኑ ተወሰነባቸው። ከዚያም ፀረ አብዮተኛ ተብለው በየጎዳናው ለተመልካች መቀጣጫ እንዲሆኑ ተደርገዋል።  አንዴ ብቻ አይደለም። የውግዘት ስብሰባና ሰልፍ እየተደጋገመ ይካሄዳል። በጠላትነት ተፈርጀው ሲዋረዱ፤ ፍርጃው ልጆቸውም ላይ ወርዶባቸዋል።
ችግሩ ደግሞ፤… የመከራከርና የመቃወም ሙከራ ይቅርና ማኩረፍም አይቻልም። ፖለቲካን በሩቁ የመተውና አርፎ የመቀመጥ እድልም የለም። እንዲያውም፣ ከሌሎች ዜጎች በላቀ ስሜት የፓርቲ ታማኝነቱን ለማስመስከር፣ የፓርቲ ፍቅሩን ለማሳየት መሯሯጥ አለበት።
ፓርቲው የአባልነት ማመልከቻህን ካልተቀበለ፤ እንደገና በሃይለኛ የጉጉት ስሜት ለአባልነት ማመልከት ይኖርብሃል።
“ችግር አለብህ፤ ፓርቲው አልወደደህም። ጥፋት አለብህ፤ ፓርቲው ይጠረጥርሃል” ተብሎ እንደተነገረህ ቁጠረው። ታማኝነትህንና አገልጋይነትህን ለማስመስከር ካልፈጠንክ ጉድህ ይፈላል።
ፓርቲው ወይም መንግስት ያለ ጥፋትሽ በጠላትነት ቢፈርጅሽና ቢቀጣሽ፤ ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ፓርቲውን እንደምታፈቅሪ፣ የመንግስት ባለሥልጣናትም ዋና ተቆርቋሪ እንደሆንሽ ማሳየት ይኖርብሻል። ቢያንስ ቢያንስ መስለሽ ለመታየት መፍጨርጨር ይኖርብሻል።
ሰባቴ ወይም አስሬ አይደለም፤ ሰባ ሰባት ጊዜ የፓርቲ አባል ለመሆን መምከር፤ በደህና ለመሰንበት የግድ ከሆነ፣መቼስ ምን ይደረግ?


Read 7169 times