Saturday, 05 November 2022 12:01

ኢትዮጵያ የነገሰችበት የሰላም ስምምነት!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(2 votes)

   - የህወኃት ትጥቅ መፍታት “መለኮታዊ ጣልቃ-ገብነት” ነው!
     - ታጣቂው ቡድን ወደ ድርድሩ የገባው ባዱ እጁን ነው እንዴ?
         
        በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ለሳምንት የዘለቀው የሰላም ንግግር፣ በዚህ ፍጥነት በስምምነት ይቋጫል ብዬ ፈጽሞ አልጠበቅኩም። (እንኳን እኔ እነ አሜሪካም አልጠበቁም!) ያለጦርነት ለአንድ ጀንበር ውሎ ማደር የማይችለው የአማፂው ቡድን፤ ሰበብ እየደረደረ የሰላም ንግግሩን ጊዜ መግዣ ያደርገዋል የሚል ነበር ግምቴ። (እኔ ብቻ ሳልሆን ከሊቅ እስከ ደቂቅ!)
በእርግጥ አማፂ ቡድኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጦርነቱ  ድል እየከዳው መምጣቱን አላጣሁትም። የመከላከያ ሃይልና ጥምር ጦሩ የትግራይን ዋና ዋና ከተሞች መቆጣጠራቸውንና ከመቀሌ በቅርብ ርቀት ላይ በተጠንቀቅ እንደሚገኙም ሳላውቅ ቀርቼ አይደለም። እንዲያም ሆኖ የሕወሓት አመራሮች ድል እንደቀናቸው፣ ብዙ ሺ የመከላከያና የኤርትራ ወታደሮችን እንደማረኩ ከመናገር ተቆጥበው ስለማያውቁ፣ የሰላም ንግግሩ በስምምነት ይቋጫል ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም። ለነገሩ እኔ ብቻ ሳልሆን በርካታ የፖለቲካ ተንታኞችና የወታደራዊ ሳይንስ ጠበብቶችም (ያውም ህወሓትን በቅርበት እናውቀዋለን የሚሉ) የሰላም ንግግሩ እንደማይሳካ ነው ግምታቸውን ሲገልጹ የነበረው- ከህወሓት ያለፈ ተሞክሮ በመነሳት።
በተለይ ደግሞ የሰላም ንግግር ወይም ድርድር ጉዳይ በተነሳ ቁጥር አማፂ ሃይሉ ሲያዥ- ጎደጉድ ከቆያቸው ቅድመ-ሁኔታዎች አንፃር፣ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ከስምምነት ላይ መደረሱ ተአምር ቢሆንብኝ አይፈረድብኝም።
እንደኔ እምነት፣ አስር ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ የሰላም ስምምነቱ ላይ የተደረሰው በ”መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት” ነው። (ፈረንጆቹ Divine Intervention እንዲሉ!) ለ5 ወራት ግድም ለሰብአዊነት ሲባል ተግባራዊ የተደረገው የተኩስ ማቆም ስምምነት፣ ባለፈው ነሃሴ ወር  እንዴት እንደተጣሰ ታስታውሳላችሁ? የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ልኡካን ወደ መቀሌ ተጉዘው ከህወሓት አመራሮች ጋር ተነጋግረው (ተሞዳሙደው ቢባል ይሻላል!) ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ፣ የኢትዮጵያን መንግስት ክፉኛ ያስቆጣ መልዕክት ነበር ይዘው የመጡት። የሄዱት ስለሰላም ንግግሩ ለመምከር ነበር። ሲመለሱ ግን የህወሓት ልዩ አማካሪ ሆነው ተገኙ-እጅ ከፍንጅ! ህወሓት በሰላም ንግግሩ ይስማማ ዘንድ እንደ ባንክ፣ መብራት፣ ቴሌኮምና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች በ10 ቀናት ውስጥ እንዲጀመሩለት ነበር ያሳሰበው፤በልኡካኑ በኩል፡፡ ካልሆነ ግን ወደ ጦርነት እገባለሁ ሲል ዛተ፡፡ (ሙያው ዛቻና ጉልበትም አይደል!) እንደዛተውም አደረገ። ለወራት የዘለቀውን የተኩስ ማቆም በመጣስ ዳግም ቆቦን  ወረረ። በአፋር ክልል ነዋሪዎች ላይ ከባድ መሳሪያ  በመተኮስ ህይወት አጠፋ። ብዙዎችን አፈናቀለ፡፡  ይኼ ነው እኛ የምናውቀው - ህወሓት!
ከዚህ አንፃር ነው የደቡብ አፍሪካውን የሰላም ስምምነት አሁንም ድረስ ሳስበው ተዓምር የሆነብኝ። እስቲ አስቡት… ህወሓት በ30 ቀናት ውስጥ ትጥቅ ሙሉ በሙሉ እንዲፈታ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከባድና ቀላል መሳሪያዎችን ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያስረክባል። የፌደራል መንግስቱ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ይመሰርታል ወዘተ… አጃኢብ ነው!
የሆነ ሆኖ መንግስትና ታጣቂው ቡድን (ትጥቅ እስኪፈታ) ከስምምነት ላይ መድረሳቸው በእጅጉ አስደስቶኛል። ከሁሉም ደግሞ ህወሓት በ30 ቀናት ውስጥ ትጥቅ እንዲፈታ ከስምምነት ላይ መደረሱ ትልቅ ድል ነው።( እኔማ በ24 ሰዓት ውስጥ ቢፈታ ሁሉ ደስ ይለኝ ነበር!) አይቻልም እንጂ፡፡ ህወሓት ትጥቅ እንዲፈታ ለምን እንደምፈልግ ልንገራችሁ፡፡
 ህወሓት ትጥቅ ፈታ ማለት እኮ…የትግራይ ወጣት ለማያውቀው ዓላማ ከመሞት ይድናል ማለት ነው። የትግራይ እናት ልጆቿን ለጦርነት ከመገበር ትገላገላለች ማለትም ነው። የአማራና አፋር ክልል ህዝቦች ከስጋት ወጥተው በሰላም ተኝተው ማደር ይጀምራሉ ማለት ነው።
ህወሓት ትጥቅ ፈታ ማለት የግፍ ግድያና ሰቆቃ እንዲሁም የሃብትና ንብረት ውድመት ይቆማል ማለት ነው። የህወሓት ትጥቅ መፍታት ብዙ ብዙ በጎ ውጤቶችን ያመጣል።
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሰብአዊ ጉዳዮች ሰበብ እነ አሜሪካንን የመሰሉ ሃያላን መንግስታት ሲያደርጉብን ከከረሙት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ጫናም እንገላገላለን ማለት ነው። ከማስፈራራትና ከዛቻም እንድናለን። በአጭሩ የህወሓት ቡድን ትጥቅ ፈታ ማለት ኢትዮጵያ እፎይታ አገኘች ማለት ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ በምዕራባውያን ክንደ ብርቱዎች የተዋከበችውና የተሸማቀቀችው በማን ሆነና?! በታጣቂው የህወሓት ቡድንም አይደለ?! ቡድኑ ትጥቁን ሲፈታ ኢትዮጵያ ከዚህ ሁሉ ተጽዕኖ ነፃ ትሆናለች- ካቀረቀረችበት ቀና ትላለች። ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉትም፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ፈርጥ ትሆናለች።
በዚህም የተነሳ ከሰሞኑ ከደቡብ አፍሪካ በታወጀው የሰላም ስምምነት የተሰማኝ ደስታ ወደር የለሽ ነው። መለኮታዊ ጣልቃገብነትን ያስተዋልኩበትም ክስተት ነው።  ያለምንም ጥርጥር “የኢትዮጵያ አምላክ ስራውን ሰርቷል” ብዬ አምናለሁ። (ማመን ህገ-መንግስታዊ መብቴ መሰለኝ!) ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የገጠሟትን ቋጥኝ የሚያካክሉ መከራዎችና ተግዳሮቶችን ተቋቁማ ለዚህ ድል  የበቃችው በፈጣሪ ድጋፍና እገዛ ነው። ከፈጣሪ ቀጥሎ የኢትዮጵያ መከላከያና ጥምር ሃይሉ የከፈሉት የደምና የአጥንት መስዋዕትነት በዓለም መድረክ አሸናፊ አድርጓታል። ክብርና ምስጋና ለኢትዮጵያ ጀግኖች ወታደሮች!!
በተለያዩ ጊዜያት ከወዳጆቼ ጋር ስለሰሜኑ ጦርነት ስናወጋ፣ እኔ በተደጋጋሚ የማቀነቅነው አንድ ሃሳብ ነበረኝ- “ታጣቂው የሕወሓት ቡድን ለአንድ ጀንበር ዕድሜው በተራዘመ ቁጥር፣ የአያሌ ኢትዮጵያውያን (ትግራዋይን ጨምሮ!) ዕልቂት፣ ሰቆቃና መከራ  በእጥፍ ያሻቅባል” የሚል። አልተሳሳትኩም። የህወሃትን ቀንደኛ አመራሮች (ቢያንስ ጦርነቱን የሚመሩትና የሚቀይሱትን) ከመቀሌ በጀት ጠልፎ (አፍኖ) የሚወስድ ዓለማቀፍ የደህንነትና ስለላ ቡድን ቢፈጠር ብዬ ተመኝቼም አውቃለሁ (የሞኝ ሃሳብ ቢመስልም ጭንቀት የወለደው ነው!)  ኢትዮጵያውያን ወገኖቼን ከሰቆቃ ለመገላገል ሳወጣ ሳወርድ የመጣልኝ ሃሳብ ይኼ ነው- ከመብሰልሰል ብዛት!
በተደጋጋሚ ብዙዎች እንዳሉት፣ በዚህ የሰላም ስምምነት አሸናፊና ተሸናፊ ወገን እንደሌለ ከልቤ አምናለሁ፤ አሸናፊዋ ኢትዮጵያ ብቻ ናት!! ሁሉም ወገን የሰላም ሂደቱን የሚያደናቅፍ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ከማራገብ መታቀብ እንዳለበትም አምናለሁ። በተለይ የመከራው ገፈት ቀማሽ ያልሆኑና ፈረንጅ አገር ተቀምጠው በሚልኩት ዶላር ጦርነቱን ሲዘውሩ የነበሩ ዳያስፖራዎች “No more” ሊባሉ ይገባል፤ “በቃችሁ- እጃችሁን አንሱ”፡፡
“በኢትዮጵያ ጥገኝነት ሥር ማደርን አንፈቅድም፤ ትግራይ ነጻ አገር መሆን አለባት” የሚሉ አንዳንድ ጽንፈኛ ትግራዋይ ዳያስፖራዎች፤ ለምን የሰላም ስምምነት ላይ ተደረሰ?  ጦርነቱ ለምን ይቆማል? እያሉ ነው - አለማፈራቸው! አንድ ጥያቄ ግን አለኝ። ለመሆኑ ህወሓት ወደ ድርድሩ የገባው ምን ይዞ ነበር? ባዶ እጁን ነው እንዴ? ለነገሩ ቡድኑ ሁሉን ነገር አጥቶ ሙልጩን የወጣው በጦርነት አፍቃሪነቱ ነው፡፡ እናም በጥላቻ ፕሮፓጋንዳው፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ አጥቷል። የትግራዋይን ድጋፍና- እምነት ተነጥቋል፡፡ ህሊናውንና ማሰቢያ አዕምሮውንም አጥቷል። ወደ ድርድሩ ባዶ እጁን ቢገባ የማይገርመው ለዚህ ነው፡፡
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ታሪካዊ በተባለው (ለእኔ ተዓምረኛ!) የሰላም ስምምነት የተሰማኝን መደነቅና መደመም  በመግለጽ፤ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ማወጅ ነው- ማብሰር!!
በመጨረሻም፣ በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሊሤጉን ኦባሳንጆ ድንቅ አባባል ጽሁፌን (መብሰልሰሌን) ልቋጭ፡- “ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፤ ትልቅ እንደሆነች መቀጠል ይኖርባታል” (ጎምቱው አፍሪካዊ አንጀቴን አራሱኝ!!)
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ይባርክ!

Read 804 times