Saturday, 05 November 2022 11:08

ዓለም የሰላም ስምምነቱን አወድሶታል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 “አስከፊውን ጦርነት ለማስቆም ወሳኝ የሆነ የመጀመሪያ እርምጃ ነው”


        የኢትዮጵያ መንግስትና ህውሃት በደቡብ አፍሪካ፤ ፕሪቶርያ ለሳምንት ያህል በአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር ከተካሄደ የሰላም ንግግር በኋላ ባለፈው ረቡዕ ምሽት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣በርካታ መንግስታትና ዓለማቀፍ ተቋማት ስምምነቱን በተመለከተ መግለጫ በማውጣት አቋማቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
የመንግስታቱ  ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ “በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው ስምምነት፣ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ህይወት የቀጠፈውንና ሁለት ዓመት ያስቆጠረውን አስከፊ ጦርነት ለማስቆም ወሳኝ የሆነ የመጀመሪያ እርምጃ ነው” ሲሉ በደስታ ተቀብለውታል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያውያንና  ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ  መንግስትና የህወሓት አመራሮች ሰላም ለማምጣት  የወሰዱትን እርምጃ እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፤ ጉቴሬዝ።  የተመድ ቃል አቀባይ ስቲፋን ዱጃሪክ በበኩላቸው፤“ስምምነቱ፤ለሁለት ዓመት በዘለቀው በዚህ ጦርነት በእጅጉ ለተሰቃዩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ኢትዮጵያውያን ጥቂት እፎይታ ሊያመጣ ይችላል ብለን ተስፋ የምናደርግበት በእጅጉ የሚደገፍ የመጀመሪያ እርምጃ ነው፡፡” ሲሉ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ፕሬዚዳንትና የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል፤ “ግሩም ዜና” ነው ብለውታል- በሁለቱ ወገኖች የተደረሰውን የደቡብ አፍሪካ ስምምነት፡፡
“ተደራዳሪዎቹን እንኳን ደስ አላችሁ” ያሉት ሳል፤ “ሁለቱም ወገኖች ለዘላቂ ሰላም በፅናት እንዲታትሩ አጥብቄ እገፋፋለሁ”  ብለዋል፡፡
የጎረቤት አገር ኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ባወጡት መግለጫ፤ሁለቱ ወገኖች በአፍሪካ ህብረት በተመራው የሰላም ንግግር ሂደት ውስጥ ያሳዩት ቁርጠኝነት፤ በቀጠናችን ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን ካለን የጋራ ፍላጎት ጋር ይጣጣማል ብለዋል፡፡
ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ኢትዮጵያውያን ይህ ስምምነት የሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው ለአገራቸው አዲስ የሰላምና የብልፅግና ምዕራፍ እንዲፈጥሩ መክረዋል፡፡  
ሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች ለሰላም ያሳዩትን ቁርጠኝነትና ፅናት ያደነቀው የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ፤ “ዘላቂ የተኩስ ማቆም ስምምነት” ላይ ለመድረስ ግን ተጨማሪ ንግግር እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡
“ስምምነቱን በፍጥነት መተግበር ያስፈልጋል ያለው ህብረቱ፤በጦርነቱ በተጎዱ ሁሉም  አካባቢዎች በተለይ ደግሞ በትግራይ የሰብአዊ እርዳታ ማድረስና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ  ነው” ብሏል፡፡
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባርቦክ፤ “ይህን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ላሳዩት ፈቃደኝነት” ሁሉንም ወገኖች አድንቀው፤እውነተኛው የሰላም ሂደት መከተል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
“ይህ ተስፋ ሰጪ እርምጃ ነው፤ አሁን እውነተኛው የሰላም ሂደት መከተል አለበት። ኤርትራም ውጊያውን ማቆምና ከኢትዮጵያ መውጣት ይኖርባታል፡፡” ሲሉም ሚኒስትሯ፣ በትዊተር ላይ ፅፈዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ፀሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፤ የኢትዮጵያ መንግስትና ህውሓት በፕሪቶርያ የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ በመድረሳቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
“የጥይት ድምፅ እንዳይሰማና የትጥቅ ግጭትን ለማስቆም ይህ ስምምነት በመፈረሙ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ዕድል አለው” ብለዋል፤ ዋና ፀሀፊው ባለፈው ረቡዕ በፕሪቶሪያ በተካሄደው የፊርማ ሥነ ስርዓት፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና መንግስታቸው ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሄ በመፈለግ ረገድ ላሳዩት አመራርና ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን የገለጹት ዶ/ር ወርቅነህ፤ የአፍሪካ ህብረትና የአደራዳሪ ቡድኑ በሰላም ንግግሩ የተጫወቱትን ጉልህ ሚናም አወድሰዋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት በበኩሉ፤በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር የተደረሰውን ስምምነት እንደሚደግፍ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትና ህውሓት ሁለት ዓመት ያስቆጠረውን ጦርነት ለማስቆም በመስማማታቸውና የተጀመረውን የሰላም ሂደት ለማጠናከር ንግግራቸውን ለመቀጠል እንዲሁም ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስና ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ለማድረግ በመወሰናቸው አሜሪካ  አድናቆቷን ገልፃለች፡፡
በተጨማሪም አሜሪካ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለአፍሪካ ህብረት ያቀረቡትን ምስጋና አድንቃ፤ ጠ/ሚኒስትሩ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባትና ለልማት ያላቸውን ፍላጎት  እንደምትደግፍ አስታውቃለች፡፡

Read 11868 times