Saturday, 05 November 2022 11:03

እነ አምነስቲ የሰላም ድርድሩ ወንጀለኞችን ተጠያቂ አያደርግም አሉ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(4 votes)

  “የሰላም ስምምነቱን የአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል”
                  
          በፌደራል መንግስትና በህውሃት ታጣቂ ቡድን መካከል ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካው ፕሪቶርያ፣ የተፈፀመው የሰላም ስምምነት፣ ድጋፍና ተቃውሞ ማስተናገዱን ቀጥሏል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ፤ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገራት የሰላም ስምምነቱን እንደሚደግፉና ለተግባራዊነቱም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ሲገልፁ፤ ከአገር ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትን ጨምሮ በርካታ ተቋማት ስምምነቱን ደግፈው መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል ዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምኒስቲ ኢንተርናሽናል፣ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ጠቅሶ፤ የወንጀል ተጠያቂዎችን በተመለከተ ምንም ያለው ነገር ባለመኖሩ ግን ጎደሎ ነው ብሏል፡፡ ይህንን ጎደሎ ለመሙላትም ተጨማሪ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በሰላም ጉዳዩን መፈታት የሚቻልበትን መንገድ ለመፈለግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሶ፤ አሁን የተደረገው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ በሚሆንበት መንገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ የአሸናፊና ተሸናፊ ሳይሆን ሁሉም አሸናፊ የሆነበት መሆኑ ታውቆ፤ ስምምነቱን የአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩ ወገኖች ሁሉ ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብሏል- በመግለጫው። በተመሳሳይ ሁኔታ፤ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ትናንትና ይፋ ባደረገው መግለጫው፤ ሁለቱ ወገኖች ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሳቸው እንዳስደሰተው ጠቁሞ፤ ምክር ቤቱ የሰላም ስምምነት አፈጻጸሙን በተመለከተ በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት፣ በመልሶ ማቋቋም ላይና አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ አዎንታዊ ሚናውን ለመጫወት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሁለቱ ወገኖች በኩል ሰሞኑን የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ጠቁሞ፤ ሆኖም ስምምነቱ ተጠያቂነትን በተመለከተ ያለበትን ጉድለት ለመሙላት ተጨማሪ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል ብሏል።  በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት በጅምላና ከፍርድ ውጪ በሆነ ግድያ ውስጥ የተሳተፉ እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃትን የፈጸሙ ሆነው ሳለ ይህንን በቀላሉ የማይታለፍ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ስለሚጠየቁበት ሁኔታ በስምምነቱ ውስጥ የተገለጸ ነገር የለም ብሏል።
ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጸሙ አሰቃቂ ድርጊቶች ሰለባ ለሆኑና ለተጎጂዎች ፍትህን ለማረጋገጥ፤  መንግስት ያልተገደበ ፈቃድ ሊሰጥ ይገባል ብሏል- አምነስቲ በመግለጫው።
ሂዩማን ራይትስዎች በበኩሉ፤ የፌደራል መንግስቱ ከህወሓት ታጣቂ ቡድን ጋር  የተፈራረመው የግጭት ማቆም ስምምነት በጦርነቱ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ህጋዊ ተጠያቂነት እንደሚኖር አይገልጽም ብሏል፤ በወንጀል የሚጠረጠሩ አካላት ላይ ምርመራ ማድረግና ተገቢ ሆኖ ሲገኝም፣ ለፍርድ ማቅረብ እንደሚገባ ያመለከተው ተቋሙ፤ ያለ ፍትህ እውነተኛ ሰላም አይመጣም ሲል ሞግቷል።



Read 11628 times