Monday, 31 October 2022 00:00

ግርማዊት እቴጌ መነን በራዲዮ ለዓለም የተናገሩት ቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ኢትዮጵያ ምኞቷ ሁሉ ሰላምን ለማግኘት ነው”
በዓለም ለሚገኙ ሴቶች ሁሉ ድምፃችንን ለማሰማት ዛሬ ማታ ምክንያት ስላገኘን እጅግ ደስ ብሎናል፡፡
ባገራችንና በሕዝባችን ላይ የአጥቂነት ሥራ ሊደረግበት በሚዘጋጅበት ጊዜ፣ ሰላምንና ነፃነትን ለማፅናት የቆመው የዓለም ሴቶች ማኀበር ስለ ገለጠልን የጋለ ወዳጅነት አሳብ ጥልቅ የሆነ ምስጋናችንን ስናቀርብላቸው ደስ ይለናል፡፡
አሁን የምናገረውን ቃል ለሚያዳምጡ ሁሉ ትርጉሙ በቶሎ እንዲገባቸውና በመጠባበቅም ጊዜ እንዳይወስድባቸው አስበን እጅግ የተወደደች ልጃችን ፀሐይ በእንግሊዝ ቋንቋ እንድታነበው አድርገናል ብለው ግርማዊ እቴጌ ባማርኛ ቋንቋ ከተናገሩ በኋላ፣ ልዕልት ፀሓይ ቀጥሎ ያለውን ቃል አነበቡ፡፡
በሰውነታችን ላይ እጅግ የሚመዝነውና የሚከብደን ጦርነት እንዲደረግብን በታሰበበት ሰዓት አሁን በምንኖርበት በዚህ እጅግ ብርቱ በሆነውና በሚያሳዝነው ጊዜ በዓለም የሚገኙ ሴቶች ሁሉ በመላ ድምፃቸውን ማሰማትና አሳባቸውን መግለጥ ዋና የተገባቸው ነገር መሆኑን እናሳስባለን፡፡
በዓለም ያሉ ሴቶች ምንም የሚኖሩበት አገር ልዩ ልዩ ቢሆን፣ ነፋሱና አየሩም የተለዋወጠ ቢሆን፣ ሴቶች ሁሉ ስለ ዓለም ሰላምና ፍቅር በተመሳሰለ ፈቃድ ባንድ ዐይነት ፈቃድ የተያያዙ ናቸው፡፡ በማናቸውም ጊዜ ቢሆን ጦርነት የሰውን ልጅ ከሚያስጨንቁ መከራዎች አንደኛው ብርቱ መከራ የሚያመጣ መሆኑ የተገለጠ ነው፡፡
በዓለም የሚገኙ ሴቶች ሁሉ በዘር በሃይማኖት ባገር ልዩ ልዩ ቢሆኑ፣ የኀይል ስራ የሚፈጸምበት ጦርነት የሚያመጣው ፍሬ የሚያሰቅቃቸውና እጅግ የሚወዷቸውን ባሎቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን፣ ልጆቻቸውን የሚጨርስባቸው ቤተሰባቸውን የሚያጠፋባቸውና የሚበትንባቸው ስለ ሆነ ጦርነትን ይጠላሉ፡፡
የኢጣሊያ ሴቶች መካንም የልጆችም እናት ቢሆኑ፣ ማሰሪያ የሌለውና የማይመስል ታላቅ መከራ የሚያመጣው የጦርነት አሳብ እንዲያስጨንቃቸው፤ እናውቃለን ፡፡ ስለዚህ በዓለም የሚገኙ ባል ያገቡ ያላገቡም ቢሆኑ፣ ወላጆች ወይም መካኖች ቢሆኑ፣ የሰው ደም በከንቱ እንዳይፈስ ለሸክም የሚከብድ መከራ በሰው ልጅ ላይ እንዳይደርስ ድምጣቸውን አስተባብረው መጮህና መጠየቅ ይገባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ምንም የኀይል ሥራ ለማድረግ አታስብም፤ ምኞቷ ሁሉ ሰላምን ለማግኘት ነው፡፡ ከብዙ ወራት በፊት ዠምሮ የተፈለገባትን ጥል ለማብረድ በማናቸውም ረገድ ቢሆን የተቻላትን አድርጋለችና ኀሊናዋ ንጹሕ ስለ ሆነ አይወቅሳትም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ በእውነተኛነት ሥራ ሠርተው ለመኖር የሚመጡትን የውጭ አገር ሰዎች ሁሉ በወንድማማች አሳብ በደስታ ሲቀበል የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕርይ ከጥንት ዠምሮ ሲነገርለት የኖረ ታሪክ የሚመሰክርለት ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆነው አንድ መንግስት፣ የኢትዮጵያ መንግስት በሰላም ለመኖር በሚጣጣርበት ጊዜ፣ የራሱን ጥቅም ብቻ በማሰብ ኢትዮጵያን በጦር ኀይል ለመያዝና ለመግዛት ተነሥቷል፡፡
ለየም ወልወል የሚገኘው በኢትዮጵያ ወይም በኢጣልያ ግዛት ውስጥ መሆኑ እንዲመረመርና እንዲቆረጥ ጠየቀ። የኢጣሊያ መንግስት ግን ይህን ነገር የሽምግልና ዳኞች አይመረምሩብኝም ብሎ ተቃወመ፡፡ ወልወል የሚገኘው በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ መሆኑን በኢጣሊያ በቅኝ አገር ሚኒስቴር በኦፌሲዬል የወጣው ካርታ አይበቃም ቢባል እንኳ ይህ የኢጣሊያ መንግስት አደራረግ ለማስረዳት የሚበቃ ነበር፡፡
በመንግስት ማኀበር ብርታትና በሕግ የሚገባና የሰላምን መንገድ ተከትሎ ፍጻሜ እንዲያገኝ መንግሥታችን ጠንክሮ በመያዙ በወልወል የተደረገው ግጭት በሽምግልና ዳኞች ፍርድ ተቆርጦ ስለ ኢጣሊያ ባለፈው ዓመት በነሐሴ ወር የወልወል ግጭት ሳይደረግ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለማድረግ ስላሰበች፣ ይህን ጦርነት ለማድረግ ካ፭ ወር በኋላ በወልወል ላይ የተደረገውን ግጭት ምክንያት አገኘሁ ብላ የያዘችውን አሳብ ዛሬም እያረጋገጠች ትሄዳለች። ከነሐሴ ወር ፲፱፻፳፭ ዓመት ዠምሮ ኢጣሊያ በኤርትራና በሱማሌ ቅኝ አገሯ መሣሪያ መላክ ስለ ዠመረች፣ ወታደር መሣሪያ ልዩ ልዩ የጦር መኪና ጥይት ሳታቋርጥ እየላከች ስታጠነክር ቆየች፡፡ የመንግስታት ማኀበር አማካሪዎችና የሽምግልናም ዳኞች በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል የተነሣውን ነገር በሰላም ለመጨረስ ሲነሡ፣ ኢጣሊያ መሣሪያና ወታደር መላኳን አላቋረጠችም፡፡
ዛሬ የወልወል ነገር ስለ ተጨረሰና ጦርነት ለማድረግ ለኢጣልያ ምክንያት ስላጠረባት ኢትዮጵያ ለመከለከያ የሚያስፈልጋትን መሣሪያ እንዳታገኝ ሌሎቹ መንግስቶች እንዳይሸጡላት ካደረገች በኋላ፣ “የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አውሬ ስለሆነ አሠልጣኝ ያስፈልገዋል” እያለች ለዓለም ሕዝብ ለማሳመንና ኢትዮጵያን ለማስጠላት ትሠራለች፡፡
የኢጣሊያን አኳኋን ታሪክ ይፈርደዋል። ኢጣሊያ ሥልጣኔ የተዋሐደኝ ነኝ እያለች ስትናገር ሰላማዊ በሆነ አስቀድሞ መሣሪያ እንዳያገኝ በተደረገበት በነሐሴ ፳ ቀን ፲፱፻፳ ዓመት ኢጣሊያ በግልጥ ሰላምና ወዳጅነት ጸንቶ እንዲኖር የፈረመችውን ውል ተማምኖ በሚኖር ሕዝብ ላይ በማይገባ ጦርነት ታደርጋለች። ኢጣሊያ ወታደሮቿ ድል እንዲያደርጉላት ብዙም ጉዳት እንዳያገኛቸው ወደ ፊት ጦርነት አነሣበታለሁ ብላ ያሰበችበትና ኢትዮጵያን መሣሪያ እንዳታገኝና እንድትደክም አድርጋ በሕዝባችን ላይ ለመፈፀም የምታዘጋጀውን የማይገባ ሥራ የተገባ አስመስላ ለማስረዳት ትፈልጋለች፡፡
ስለዚህም የኢጣሊያ ወታደሮች በማይገባ ወሰን ተላልፈው አገራችንን ያዙብን ብለን ላቀረብነው በሕግ ለተመሠረተው ማስረጃችን የሮማ መንግስት ምላሽ ሳይሰጥ፣ በእኛ ዘንድ የተሾሙት እንደራሴዎቹ ኢጣሊያ ስለ ኢትዮጵያ ከልብ የሆነና የማይጠፋ ወዳጅነት አላት እያሉ ብዙ ጊዜ በግልጥ እንዲያረጋግጡ አድርጎ በግዛታችን ውስጥ የነዛቸው ቁጥራቸው የበዛ ደመ ወዝ የሚሰጣቸው ሠራተኞቹ የማያመጡለትን ወሬ ከብዙ ጊዜ በፊት ዠምሮ እየሰበሰበ ሲያጠራቅም ኖሮ አሁን በመጨረሻው ሰዓት ለመንግስታት ማኀበር አማካሪዎች አቀረበ፡፡
የኢጣሊያ መንግስት በብልግናና በሐሰት ላቀረበው ክስ ለመንግስታት ማኀበር አማካሪዎች በነሐሴ ፳፱ ቀን ክስ ያቀረበበት ማስታወሻ ገና ስላልቀረበልን ይህንኑ ክስ የምናውቀው ለጊዜው ባጭሩ ነውና አሁን ምላሹን በዝርዝር የምንሰጥበት ጊዜያት አይደለም፡፡ ነገር ግን መንግስታችን ምክንያቱ ለዓለም ሕዝብ የተገለጠ የሆነውን በመጨረሻ ሰዓት የቀረበውን የዚህን ክስ ምላሽ አንድ ባንድ ለመመለስና ማስረጃውን ለመስጠት የተዘጋጀ ነው፡፡ ላሁኑ ግን በዠኔብ ያሉን መላክተኞቻችን ነገሩን የሚመረምር የእንተርናሲዮናል ኮሚሲዮን እንዲቆም ከመንግስታት ማኀበር አማካሪዎች እንዲጠይቁ የተጣራ ትእዛዝ ማሳለፋችንን ብቻ ማስታወቅ ይበቃል፡፡
የኢጣሊያ መንግስት ያቀረበውን ክስ፣ የሁለቱንም ነገር መርምሮ ለመቁረጥ የሚችል ይህ የጠየቅነው የእንተርናሲዮናል ኮሚሲዮን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ አጥብቆ ሰላምን ይፈልጋል፣ ከዚህም በቀር አገሩን በልቡ ይወዳል። ምንም የሚበቃ መሣሪያ ባይኖረውና በኢጣሊያ ፖለቲካ ምክንያት እንዳያገኝም ቢደረግ፣ ባገር ፍቅር የተቃጠለና የኮራ ልብ ያለበት ደረቱን መክቶ ከጠላት በመከላከል ይቃወማል፡፡
በሰላም እርሻቸውን እያረሱ የሚኖሩ፣ ክንዳቸው የጠነከረ ለነጻነታቸው ቀናተኞች የሆኑ ገበሬዎቻችን እርሻቸው በጠላት እጅ  እንዳይገባ ለመከልከል ማረሻቸውንም በቅልጥፍና የሚያገላብጡትን ያኽል ጎራዴና ጦራቸውንም በቅልጥፍና ሊሠሩበት ይዘው ነሳሉ፡፡ ጦርነት አንዲደረግ አንፈቅድም፤ ነገር ግን በጦርነት ስንጠቃ ሳንከላከልና ጠላታችንን ሳንቋቋም አናሳልፍም፡፡ ኢትዮጵያ እምነቷ በእግዚአብሔር ላይ ስለ ሆነ የእግዚአብሔር ፍርድ ከሰው ፍርድ እንዲበልጥ ታውቃለች፡፡ ሰውም ወገኑን ለማጥፋት ያወጣው አዲስ መሣሪያና መድፍ የሥልጣኔ ምልክት አይደለም፡፡ …
ኢጣሊያ ለራሷ በማሰብ ብቻ ሰላምን ለማጥፋት ስለ ተነሣች ሰላም እንዳይጠፋ ለማጠንከር የሚጥሩ የመንግስት ሰዎች ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግስት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ ሕዝቧም የመንግስት ሰዎች የሆኑ ሁሉም ሰላምን ለመጠበቅ የሚደክሙት ድካም መልካም ፍሬ እንዲያፈራ መሪያቸው እንዲሆን ጸሎታቸውን ሳያቋርጡ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባሉ፡፡
ኢትዮጵያ በውል የገባችውን ማናቸውንም የእንተርናሲዮናል ግዴታ ሁሉ አክብራ ዘወትር መፈፀሟን ደግሞ አሁን በርሷና በኢጣሊያ መካከል የተነሣው ግጭት በሰላም እንዲጨረስ ክብሯና ማዕርጓ በሚፈቅድላት መጠን መስማሚያ መንገድ መፈለጓን ታውቃለችና ኀሊናዋ አይወቅሣትም፡፡ ታላቅ መንግስት የተባለችው ኢጣሊያ በማይገባ የምታደርገው ይህ የአጥቂነት ሥራ፣ ለሰው ልጅ ሁሉ ሥልጣኔ የሚሰጥና ኑሮውን የሚያሻሽልለት ሰላም መሆኑን ተረድተው ሐሳባቸውን በዚሁ ላይ ለሚኖሩ ለትልቅም ለትንሽም፣ ለዓለም መንግስታት ሁሉ የሚያሠጋ ስለ ሆነ፣ በመንግስታት ማኀበር አማካሪዎች ርዳታ በሚገባ ፍርድ ከመንግስታት ማኀበር ውል ጋር የተስማማ ሆኖ እንዲጨረስ እየተመኘች ኢትዮጵያ ተስፋ ታደርጋለች፡፡
(መስከረም 13 ቀን 1928 ዓ.ም፤ ከሌሊቱ በ7 ሰዓት ባቃቂ ነፋስ ስልክ ለዓለም የተነገረ)

 

Read 9875 times