Saturday, 29 October 2022 12:10

22ኛው የዓለም ዋንጫ በኳታር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በባህረሰላጤዎች የተከከበች
ኳታር ልዩ መልክዓምድር ያላት አገር ናት።  በምዕራብ እስያ የምትገኝ ሲሆን በሰሜን ምስራቅ የኳታር ባህረሰላጤ፤ በደቡብ በኩል የሳውዲ አረቢያ ባህረሰላጤ፤ የተቀረው ግዛቷ በፋርስና በባህሬን ባህረሰላጤዎች  ተከብቧል። የዓለማችንን ረጅሙን የባህር ጠረፍ  በ534 ኪሜትር አስመዝግባለች፡፡ በ338 ጫማ ከፍታዋ ከዓለማችን ረባዳማ ስፍራዎች በሁለተኛ ደረጃ የምትጠቀስ ሲሆን አንደኛውን ደረጃ በ6 ጫማ ከፍታ የያዘችው ማልድቪስ ናት፡፡  ካ ሆር አልአዳይድ  Khor Al Adaid የተባለው ክልል ባህርና በረሐ ከሚገናኝባቸው የዓለማችን አስደናቂ ስፍራዎች አንዱ ሲሆን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
የውጭ አገራት ዜጎች የበዙበት
የኳታር አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ከ2.6 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ የሚገመት ሲሆን የውጭ አገራት ዜጎች አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ። ከህዝቧ 12%  እስከ  315,000 ኳታራዊያን ሲሆኑ 88 በመቶው ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ከተለያዩ አገራት የገቡ ስደተኞች ናቸው። በኳታር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭ ዜጎች ህንዳውያን ሲሆኑ እስከ 700ሺ ይደርሳሉ። 40% ከአረብ፤  36% ከደቡብ ኤስያ፤ 18% ከህንድ፤ 18% ከፓኪስታን፤ 10% ከኢራን እንዲሁም 14% ከተለያዩ የዓለም አገራት የመጡ ዜጎች ይገኙበታል፡፡
የቱሪዝም መስህብነቷ
ኳታር በቱሪዝም መስክ ፈጣን እድገት ካሳዩ አገራት አንዷ ነች። በየዓመቱ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ አለም አቀፍ ቱሪስቶች ይጎበኟታል፡፡  በቅርቡ ባደረገችው የቪዛ ማሻሻያ የ88 ሀገራት ዜጎች ከቪዛ ነፃ እንዲገቡ አድርጋለች፡፡ ይህም በመካከለኛው ምስራቅ ካሉ የአረብ አገራት ተወዳጅ የቱሪስት መናሐርያ ያደረጋት ሆኗል። ከዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችና ቱሪስቶች እንደሚጎበኟትም ይጠበቃል፡፡ ከኳታር የቱሪዝም መስህቦች መካከል የአርኪዮሎጂ ስፍራዎች፤ የባህር ዳርቻዎች፤ ወደቦች፤ ሙዚዬሞች፤ ብሄራዊ ፓርኮችና የገበያ ማዕከሎች ይጠቀሳሉ።
የአልታኒ ቤተሰብ
ከ1868 እኤአ ጀምሮ ኳታርን የሚያስተዳድረው መንግስት በአልታኒ ቤተሰብ የሚመራ ነው፡፡ የቤተሰቡ ልዩ አስተዳደር ስልጣን ላይ የወጣው ከኳታር እና ባህሬን ጦርነት በኋላ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ኢምር ወይም መሪ ታሚም ቢን ሃማድ አልታኒ የሚባሉ ሲሆኑ ከ203 እኤአ ጀምሮ በስልጣን ላይ ናቸው፡፡ የቤተሰቡ የሃብት መጠን ከ335 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ይገመታል፡፡ የአልታኒ ቤተሰብ በዓለም በስነጥበብ ስራዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግና በመግዛት ግንባር ቀደም ናት፡፡
የዓለም ስነጥበብ ዋና ሰብሳቢ
በኳታር የመንግስት አስተዳደር ላይ የሚገኙት የአልታኒ ቤተሰብ በእስልምናና ዘመናዊ ስነጥበብ ፍቅራቸውና አሰባሳቢነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ከ14 ዓመታት በፊት በአረቡ ዓለም ምርጡን የእስልምና ጥበብ ሙዚየም The Museum of Islamic Art  መስርተዋል፡፡  በኳታር ሙዚየሞች ባለስልጣን ስር የሚተዳደሩ ሌሎች በርካታ ሙዚየሞች በዶሃ ከተማ ውስጥ የተገነቡ ሲሆን Arab Museum of Modern Art ይጠቀሳል፡፡ በመላው ዓለም ከ65 በላይ አገራትን የወከሉ ከ300 በላይ አርቲስቶችን የሚያስተናግደው ኳታር ኢንተርናሽናል አርት ፌስቲቫልም QIAF  አገሪቱ ለስነጥበብ የሰጠችውን ትኩረት ያመለክታል፡፡
ሙሉ ከተማ የሆነው ሃማድ
ሃማድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በ2021 እኤአ ላይ ስካይትራክስ በሰጠው የዓለም አየር ማረፊያዎች አዋርድ ላይ የዓለም ምርጥ ተብሏል። ተመሳሳይ ሽልማትን ለ6 ጊዜያት በመውሰድም ከፍተኛውን ስኬት አስመዝግቧል፡፡ የአየር ማረፊያው የአውሮፕላን መንደርደርያ እስከ 4850 ሜትር ርዝማኔ በማስመዝገብ በምዕራብ ኤስያ ቀዳሚው ሲሆን በዓለም በ6ኛ ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ በሰባቱም አህጉራት የበረራ መስመሮችን በመዘርጋትም የሚታወቀው አየር ማረፊያው፤  በዓመት እስከ 50 ሚሊዮን ተጓዦችን ያስተናግዳል፡፡ ተመሳሳይ አቅም ያላቸው የአየር ማረፊያዎች የቶኪዮው ሃኔዳ፤ የሲንጋፑር ቻንጊ፤ ተዱባዩ ዲአየኤ እና የለንደኑ ሂትሮው ናቸው፡፡ የሃማድ ዓለም አቀፍ ማረፊያ 29 ስኩዌር ኪሎሜትር በመሸፈን  በግዝፈቱ ከዓለም በ9ኛ ደረጃ ይቀመጣል፡፡ ቅጥር ጊቢው ከ100 በላይ ህንፃዎች ፤ ከ100 በላይ ሱቆችና ሬስቶራንቶችን ይዟል፡፡
ኳታር ኤር ዌይስ
ኳታር ኤርዌይስ በዓለም ዙርያ ከ45 ሺ በላይ ሰራተኞችን ቀጥሮ የሚያስተዳድር ነው። ከዓለማችን ትልልቅ አየር መንገዶች አንዱ ሲሆን ከዶሃ በመነሳት  ከ150 በላይ ዓለምአቀፍ መዳረሻዎች አሉት፡፡
የአየር ማቀዠቀዣ ያላቸው ስታድዬሞች
22ኛው የዓለም ዋንጫው የሚካሄዱትን 64 ጨዋታዎች የሚያስተናግዱ 8 ስታድዬሞች ልዩ አየር የማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂ  ተገጥሞላቸዋል። በጨዋታ ሜዳ ላይ የሚያስፈለገውን የሙቀት መጠን ለማመጣጠን ተግባራዊ በሆነው ቴክኖሎጂ በየስታድዬሙ ያለውን የሙቀት መጠን  እስከ 26 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል፡፡ የአየር ማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂው ዘላቂ እና ኃይል ቆጣቢ በሆነ መንገድ ከመስራቱም በላይ በየስታዲየሙ የሚገኘውን ተመልካች በመመርኮዝ የሙቀት መጠኑን መቆጣጠር የሚቻልበት ነው፡፡
የኤሌክትሪክ አውቶብሶች
22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ተግባራዊ ከሚሆኑ አስደናቂ ቴክኖሎጂች መካከል በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አውቶብሶች ይገኙበታል። ደጋፊዎችን ወደ ስታዲየሞችና ወደ የተለያዩ የዶሃ ከተማ ስፍራዎች የሚያመላልሱ ናቸው፡፡  በዓለም ዋንጫ ታሪክ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ለትራንስፖርት አገልግሎት ሲውሉ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን በከፍተኛ የቴክኖሎጂ የመረጃ መሳሪያዎች የሚታገዙ የትራንስፖርት አገልግሎት ናቸው።
ከጨዋታ ውጭን የምትቆጣጠረው ኳስ
አል ሪሃላ Al Rihla ለ22ኛው የዓለም ዋንጫ በአዲዳስ የተሰራች ኳስ ናት፡፡ የዓለም ዋንጫዋ ኳስ  እውነተኛ መረጃን ለVAR ባለሙያዎች የምታስተላልፍ፤ ፊፋ ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ ከሚያደርገውና በከፊል አውቶሜትድ ከሆነ የኦፍሳይድ መቆጣጠርያ ቴክኖሎጂ ጋር በመናበብ የምትሰራም ነች፡፡ በሜዳው ዙርያ የሚገጠሙ  12 ካሜራዎችን ከኳሷ እንቅስቃሴ ጋር በማዋሃድ  የሚሰራ ቴክኖሎጂ ተለጥፎባታል፡፡ከጨዋታ ውጭ የሆኑ ኳሶችን ለመቆጣጠር ፊፋ ተግባራዊ የሚሆነው አዲስ ቴክኖሎጂ ዳኞች ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንዲሰጡ ያግዛቸዋል፡፡
ረጅሙ የብስክሌት ጎዳና
ኳታር የዓለማችንን ረጅሙን የብስክሌት ጎዳናም ገንብታለች፡፡ በዶሃ የሚገኘው የኦሎምፒክ ደረጃ ያለው የብስክሌት ጎዳና በ33 ኪሜ ርዝማኔው በጊነስ ሪከርድ ሬከርድ የተመዘገበ ነው፡፡ ከጎዳናው 25.3 ኪሜትር በአስፋልት ኮንክሪት መነጠፉም ክብረወሰን ላይ ሰፍሯል፡፡
ከዓለም ሃብታም አገሮች ተርታ
ኳታር በድፍድፍ ነዳጅ ና ተፈጥሮ ጋዝ በተገነባው ኢኮኖሚዋ ከዓለማችን ሃብታም አገራት ተርታ ትሰለፋለች፡፡    ነዳጅ የኢኮኖሚ ዋልታዋ ሲሆን በጥልቀት ከተቆፈሩ ጉድጓዶች አንዱ 12290 ሜትር ተለክቷል፡፡ ኳታር ከሉክሰምበርግ፣ ስዊዘርላንድና ሲንጋፖር በመቀጠል አራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ የዓለም ሃብታም አገር ናት፡፡  አንድ የኳታር ዜጋ የነፍስ ወከፍ ገቢ እስከ 100ሺ ዶላር ይደርሳል፡፡
አረቢያን አጋዘን
አረቢያን አጋዘን የኳታር ብሄራዊ እንስሳ ሆኖ ይታወቃል፡፡ ይሄው አጋዘን  መሰል እንስሳ የኳታር ኤርዌይስ ሎጎ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በ1972 እኤአ ላይ ከዱር የጠፋው እንስሳ ከ10 ዓመት በኋላ እንደገና ወደ ዱር እንዲመለስ በማድረግ በማድረግ የኳታር መንግስት ከምድር ገጽ እንዳይጠፋ ተረባርቧል፡፡
በዓለም ዋንጫ ታሪክ ከፍተኛው የገንዘብ ሽልማት
በዓለም ዋንጫው ታሪክ ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ የተመደበ ሲሆን አጠቃላይ መጠኑ 440 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከ4 ዓመታት በፊት ራሽያ ካስተናገደችው 19ኛው የዓለም ዋንጫ በ40 ሚሊየን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የዓለም ዋንጫው አሸናፊ 46 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ያገኛል፡፡ በ21ኛው ራሽያ ላይ 38 ሚሊዮን ዶላር፤ በ20ኛው ብራዚል ላይ 35 ፤ በ19ኛው ደቡብ አፍሪካ ላይ 30፤ በ18ኛው ጀርመን ላይ 20  እንዲሁም በ17ኛው በጃፓንና ደቡብ ኮርያ ላይ 8 ሚሊዮን ዶላር ለዋንጫው አሸናፊዎች ተሸልሞ ነበር፡፡
ሌሎች ተሳታፊዎች የሚሸለሙት
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ለሁለተኛ ደረጃ 30 ሚሊዮን ዶላር፤ ለሶስተኛ ደረጃ 27 ሚሊዮን ዶላር፤ ለአራተኛ ደረጃ 25 ሚሊዮን ዶላር፤ ከአምስት እስከ 8ኛ ደረጃ ለሚያገኙት 17 ሚሊዮን ዶላር፤ ከ9 እስከ 16ኛ ደረጃ ለሚያገኙት 13 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከ17 እስከ 32ኛ ደረጃ ለሚኖራቸው 9 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ የሚከፈል ይሆናል፡፡
የጭልፊት አደንና በረራ ስፖርት
በኳታር ጭልፊት ማልመድ፤ ልዩ የአደንና የበራራ ውድድር ማካሄድ የእግር ኳስን ያህል  አድናቂዎች እያፈራ ነው፡፡  የአየር ሙቀቱ ለጭልፊቶቹ ተስማሚ በሚሆንበት ጊዜ  ለአሸናፊዎች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማቶች እየተዘጋጀ ልዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ጭልፊቶች ከኳታራዊያን የእለት ኑሮ  ፈጽሞ የራቁ አይደሉም፡፡ በዶሃ ከተማ ያሉ የጭልፊት መሸጫ ሱቆች የቅንጦት መኪና ከሚሸጥባቸው ማዕከሎች ደረጃቸው ይስተካከላል፡፡ ዋጋቸው ከ2000 ፓውንድ ጀምሮ እስከ 200ሺ ፓውንድ ይደርሳል፡፡
የግምሎች ሽቅድምድም
በኳታር ተወዳጅ ከሆኑ ስፖርቶች የግምሎች ሽቅድምድም ዋንኛው ነው፡፡ ስፖርቱ በዶሃ ከተማ ውስጥ አልሻሃንያ የሚባል ዘመናዊ የመወዳደርያ ትራክ ተሰርቶለት የኳታር ባህል መለያ ሆኗል፡፡  የስፖርት አይነቱ የቱሪስት መስህብ ሆኖ ቆይቷል። ከዶሃ መሃል ከተማ የአንድ ሰአት የመኪና መንገድ ርቆ የሚገኘው አልሻሃኒያ በግመሎች የሚካሄዱ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ውድድሮችን ያስተናግዳል፡፡ በአንድ አመት ውስጥ ከ6000 በላይ ግመሎች በዚህ ውድድር ይሳተፋሉ፡፡ ተወዳዳሪ ግመሎች በሰዓት እስከ 40 ማይል ይሮጣሉ፡፡
ቡርጃ ዶሃ
በዶሃ ከተማ ከሚገኙ አስደናቂ  ህንፃዎች ቡርጃ ዶሃ ታወር አንዱ ሲሆን በፈረንሳዊው አርክቴክት ጂን ኖቭል የተሰራው ባለ 48 ፎቅ ህንፃ ነው፡፡
 ማቻቡስ
ማቻቡስ የኳታር ተወዳጅ ብሄራዊ ምግብ ነው፡፡ ከሩዝ፤ ስጋ፤ ሽንኩርት፤ ቲማቲም እና ከጀተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ጋር ተዋህዶ ይሰራል፡፡
ስፖርት አዘጋጅነት በኳታር
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ ኳታር ከዓለማችን ታላላቅ የስፖርት መድረኮች የመጀመርያውን ማዘጋጀቷ ነው፡፡  በ2006 እኤአ ላይ ያዘጋጀችውን የኤስያ ኦሎምፒክ በ2030 እኤአ ላይም እንድታስተናግድ ተመርጣለች፡፡
አዳዲስ ታሪኮች የበዙበት የዓለም ዋንጫ
22ኛው ዓለም ዋንጫ  በታሪክ ትንሿ አገር የምታዘጋጀው፤ በፈረንጆች አዲስ አመት ዋዜማ ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄድ፤ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ እግር ኳስ አፍቃሪዎችና ቱሪስቶች የሚሳተፉበት፤ በድምሩ እስከ  5 ቢሊዮን ተመልካች እንደሚያገኝም የተገመተ ፤ እስከ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል የተጠበቀ ነው፡፡
የምንግዜም ውዱ የዓለም ዋንጫ
በ220 ቢሊዮን ዶላር ወጭው የምንግዜም ውዱ ዓለም ዋንጫ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከብራዚልና ከራስያ ዓለም ዋንጫዎች በ10 እጥፍ፤ ከደቡብ አፍሪካ ዋንጫ በ64 እጥፍ የሚልቅ በጀት ወጥቶበታል፡፡

Read 1134 times